የወልቃይትን ጥያቄ የዳያስፖራ ነው ብሎ ማድበስበስ ከእሳት ጋር መጫወት ነው (ግርማ ካሳ)

ለትግራይ ሕዝብ ጎንደር አገሩ ነው። ለጎንደር ሕዝብ ትግራይ አገሩ ነው። በተለይም ወልቃይት ጠገዴ የፍቅር፣ የአንድነት ተምሳሌት የነበረ አካባቢ ነው። ትግሬ፣ አማራ ሳይባባል ሕዝቡ በሰላምና በፍቅር ነው ለዘመናት የኖረው። ማንኛውም ዜጋ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍል ሄዶ የመኖር መብት ስላለው፣ ትግሪዎችም ከትግራይ ተነስተው በብዛት በወልቃይት ጠገዴ ሰፍረዋል። ያም መብታቸው ነው። በተለያዩ የአገሪቷ ግዛቶች በሰላም በፍቅር ከሌላው ጋር ተዋልደው፣ ተዛምደው ኖረዋል። በወልቃይት ሕዝቡ በብዛት አማርኛ እንደሚናገረው ትግሪኛም ይናገራል። ያም ጸጋ ነው። ሲያሻው ሽሬ፣ ሲያሻው ጎንደር ሄዶ ይነግዳል። ሕዝቡ ለዘመናት ምንም ችግር ሳያጋጥመው በሰላምና በፍቅር ነው የኖረው።

ነገር ግን ሕወሃት ያመጠው የዘር ፖለቲካና በዘር ላይ የተመሰረተ ፌዴራል አወቃቀር ብዙ ጣጣዎችን አመጣ። መርዝ ረጨ። በአገሪቱ ሕገ መንግስት አንቀጽ ስምንት «የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ስልጣን ባለቤቶች ናቸው» ይላል። ይህ ማለት አገሪቷ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ወይም የዜጎቿ ሳትሆን የብሄር ብሄረሰቦች የሚሏቸው እንደሆነች ተደርጎ መደንገጉን የሚያሳይ ነው።አገሪቷ በዘር ተሸነሸነች። ከአማራ ክልል፣ ከድሬዳዋና ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ያለው የኢትዮጵያ ግዛት በዘር ተለየ። ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ናት። የሶማሌ ክልል የሶማሌዎች ናት። የአፋር ክልል የአፋሮች ናት። የሃረር ክልል የኦሮሞዎችና የአደሬዎች ናት። የቤኔሻንጉል ክልል የጉሙዝ፣ የበርታ፣ የሸናሽ፣ የሳሆና የማኦ ብሄረሰቦች ናት። የጋምቤላ ክልል የአኙዋክ፣ የመዠንገርና የንዉር ብሄረሰቦች ናት። የትግራይ ክልል የትግሬዎች ናት። የደቡብ ክልል ደግሞ በዞን ደረጃ ስንወርድ፣ የሃዲያ ዞን የሃዲያዎች፣ የጉራጌ ዞን የጉራጌዎች፣ የሲዳማ ዞን የሲዳማዎች፣ የወላይታ ዞን የወላይታዎች፣ የጌዶ ዞን የጊዶዎች… ሆኑ። ትንሽ በደቡብ ክልል በሰሜንና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ብዙ ብሄረሰቦች ስላሉ በዘር መሸንሸኑ አስቸጋሪ ስለሆነባቸው ዞኖቹን ለአንድ ብሄረሰብ አልመደቡትም። ማንም ይሄ ትክክል አይደለም ብሎ የሚከራከር ካለ የክልሎቹን ሕግ መንግስት አንበቦ መረዳት ይችላል። አንድ ዜጋ ለርሱ ዘር ከተመደበለት ቦታ ውጭ መጤ መጤ ተደረጎ ነው የሚቆጠረው። ባለ አገር አይደለም ነው የሚባለው።

በአማራ ክልል ስንመጣ ግን ለኦሮሞዎች ብቻ ተብሎ ከተሸነሸነው ልዩ ዞን ውጭ በተቀሩት ዞኖች ሁሉ አገዉ፣ ቅማንቱ፣ ኦሮሞው፣ ትግሬው …. መብቱ እኩል ተጠብቆ እየኖረ ነው። የአማራ ክልል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው ማለት ይቻላል። በክልል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በዞን ደረጃም ሳይቀር።

በሶማሊያና በኦሮሚያ ድንበር መካካል ያለው ችግር፣ በአዲስ አበባ ዙሪያና በሸዋ ያለው ችግር፣ መንሴው የዘር ፌዴራሊዝም ነው። ብዙ ሶማሌዎች የሚኖሩባቸው አካባቢዎችን ለኦሮሚያ ብቻ በሆነ ክልል፣ ብዙ ኦሮሞዎች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ለሶማሌዎች ብቻ በሆነ ክልል ውስጥ ተጠቃለዋል። ሶማሌው በኦሮሚያ ኦሮሞው በሶማሌ ሁለተኛ ዜጋ ነው። እንደ ሸዋ፣ ጂማ ባሉ ቦታዎች ብዙ ሕብረ ብሄራዊና አማርኛ ተናጋሪዎች ያሉበት ቦታ ኦሮምኛ ብቻ የስራ ቋንቋ በሆነበትና የኦሮሞዎች ብቻ በሆነች ኦሮሚያ በምትባል ክልል በግድ እንዲጠቃለሉ ተደርጎ መብታቸው ተረግጧል። አሁንም በአቶ እመ መገርሳ አስተዳደርም እንደተረገጠ ነው። እንደ መጤና ሁለተኛ ዜጋ ነው የሚታዩት።

አንድ የነበሩ አዉራጃዎች ሳይቀሩ ነው በዘር የተከፋፈሉት። የሶማሌ ሞያሌ፣ የኦሮሞ ሞያሌ፣ የሶማሌ መኢሲ፣ የኦሮሞ መኢሶ፣ የሶማሌ ጉርሱም የኦሮሞ ጉርሱም የሶማሌ ባቢሌ የኦሮሞ ባቢሌ፣ የትግሬ ጸለመት የአማራ ጠለመት ፣ የትግሬ ጸገዴ የአማራ ጠገዴ፣ የኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ፣ የአማራ ሰሜን ሸዋ…እየተባለ።

ዶር አብይ አህመድ ስለ ወልቃይት ሲናገሩ ዋናው ህዝብ እንደሆነና ትግራይ ሆነ አማራ ሆነ ችግር እንደሌለው፣ የሕዝቡ ጥያቄ መንገድ፣ ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት እንደሆነ ብቻ አድርገው፣ ሕወሃቶችን ለማስደሰት፣ የወልቃይትን ጥያቄ ለመደባበስ ነው የሞከሩት። እንደዉም ብዙዎቻችንን ያስገረመውና ያሳዘነው ጠቅላይ ሚኒስተሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ የሚያነሳዉን ጥያቄ የዳያስፖራ ጥይቄ ነው ብለው ማጣጣላቸው ነው።

የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ የዳያስፖራ ጉዳይ አይደለም። ከተከዜ በስተምእራብ ያለው ግዛት በሙሉ የበጌምድር ግዛት ነበር። በደርግ፣ በአጼ ሃይለስላሴ፣ በአጼ ሚኒሊክ፣ በአጼ ዮሐንስ፣ በአጼ ቴዎድሮስና በዘመነ መሳፍንት ጊዜ ድረስ የትግራይ ግዛት ሆኖ አያውቅም። በዘመነ መሳፍንት ጊዜ የየጁ ኦሮሞ ራስ ማሪዬ የትግሬውን ገዢ ደጃዝማች ሳባጋዲስን ካሸነፉ በኋላ፣ ራስ ዉቤ ሰሜን ተብሎ የሚታወቀዉን ወልቃይት ጠገዴን ጨምረው ትግሬን እንዲገዙ አደረጉ። ያኔ ብቻ ትግራይና ወልቃይት ጠገዴ በራስ ዉቤ ስር፣ አስተዳደራዊ አንድነት ነበራቸው። እንደዚያም ሆኖ ትግራይ በሰሜን ስር እንጂ ሰሜን በትግራይ ስር አልነበረችም።የአክሱም ጊዜን አስታወሰው ከሆነ ደግሞ ወልቃይትን ብቻ ሳይሆን ድፍ ኢትዮጵያን፣ ሱዳንን፣ የመንን ሁሉ ሳይቀር ወደ ትግራይ መጠቅለል ይኖርባቸዋል ማለት ነው።

እንግዲህ ለመጠቅለል መርሳት የሌለብንም ነገር፡

አንደኛ – ሕወሃቶች “የትግራይ ፀገዴ” ፣ “የአማራ ጠገዴ” ብለው ስለ ጠገዴ ሲናገሩ፣ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ጠገዴ የሚባለውን፣ ሕዝቡ በሰላምና በፍቅር ተዋዶ ከዘመናት የኖረበትን አንዱን አውራጃ ሰንጥቀው፣ በ ‹‹ፀ›› እና በ ‹‹ጠ›› ፊደላት ለይተው ፣ ጸገዴን የትግሬዎች ፣ ጠገዴን የአማራዎች ብለው በዘር መሸንሸናቸው አንዱ ትልቁ ነጥብ ነው። አብዛኛውን የጠገዴ መሬትን “ጸገዴ” ብለው፣ ካፍታ/ሁመራ፣ ወልቃይትንና ጠለምትን ሙሉ ለሙሉ ወደ ያለ ሕዝቡ ፍላጎት፣ ሕዝቡ ሳይጠየቅ በሃይልና በጠመንጃ ነው የጠቀለሉት።

ሁለተኛ – ወልቃይት ጠገዴ ወደ ትግራይ ከተጠቀለለ በኋላ ሁሉንም ነገር በትግሪኛ በማድረግ ነዋሪዎችን በግድ «ትግሬ ናችሁ» የሚል ጫና ተደረገባቸው። ብዙዎች ከዚህ ጫና የተነሳ ወደ ጎንደርና ወደ ዉጭ አገር ተሰደዱ። ብዙዎች ታስሩ። በአጭሩ ትግሬ አይደለንም በማለታቸው የዘር ማጽዳት ወንጀል ተፈጸመባቸው።

ሶስተኛ ፣ ከላይ እንደጠቀስኩት ፣ ሕወሃት ከመምጣቱ በፊት ትግሬዎች በወልቃይት ጠገዴ እንዲሁም በጎንደር ያለ ምንም ችግር በሰላም ነበር የሚኖሩት። በወልቃይት ጠገዴ ሕዝቡ አማርኛም ትግሪኛም ይናገራል። ሲያሻው ጎንደር ሲያሻው ሽሬ ሄዶ ይነግድ ነበር። ትግሬ አማራ ተባብሎ እንኳን ሊጣላ፣ የተዋለደ የተደባለቀ የተሳሰረ ሕዝብ ነበር። ለጥቂት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት። ሆኖም ሕወሃቶች ዘረኞች በመሆናቸው ትግሬ ፣ አማራ በማለት ሕዝቡን ከፋፈሉት። የትግሬ መሬት፣ የአማራ መሬት የኦሮሞ መሬት ብለው አገሪቱን ሸነሸኑ። ወልቃይት ጠገዴ ትግሪኛም አማርኛ ይናገራሉ። አማርኛ መናገራቸውን አይተው፣ ወልቃይት ጠገዴን ወደ አማራ ክልል አላካተቱም። ግን ትግሪኛም ስለሚናገሩ «ትግሬ ናችሁ» ብለው ያለ ፍላጎታቸው፣ ሳይጠየቁ የሚኖሩበትን መሬት በግድ ወደ ትግራይ እንዲጠቀለል ተደረገ።

አራተኛ – ሕዝቡ አገሩ የትግሬ ነው ተብሎ በአማርኛ አገልግሎት እንዳያገኝ ተደረገ። በወልቃይት ጠገዴ አማርኛ መናገር ያስቀጣል፤ ያሳስራል።

እንግዲህ እነዚህና ተመሳሳይ ችግሮች ናቸው በወልቃይት ያሉት። ትግራይ እንደ ክልል ሁሉም ነዋሪዎች እኩል የሆኑባት ክልል ብትሆን ኖሮ፣ ምን አልባት በወልቃይት ዙሪያ የተነሱ ጥያቄዎች ላይነሱ ይችሉ ነበር። ሆኖም ግን ትግራይ የትግሪዎች ክልል ናት። የትግሪዎች ክልል በሆነች ክልል፣ ትግሪዎች ልጆች ሌሎች የእንጀራ ልጆች በሆኑበት ክልል፣ ወልቃያት ጠገዴ የትግራይ አካል ሆና ልትቀጥል አትችልም። በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ የግድ የወልቃይት ጥያቄ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ምላሽ ማግኘት አለበት።

ህወሃትን ለማስደሰት ብቻ፣ ጤና ጣቢያ፣ ክሊኒክ፣ ልማት እያሉ ማድበስበስ የሚያዋጣ ፖለቲካ አይደለም። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ «የወልቃይት ጉዳይ ጥያቂያችን ነው» ብለው ድምጻቸውን ያሰሙበትን ትልቅ ጉዳይ፣ የዳያስፖራ ጉዳይ ነው ብለው ዶር አብይ ጉዳዩን ወደ ጎን ለማድረግ መሞከራቸውንም፣ ከእሳት ጋር እንደመጫወት አድርጌ ነው የምወስደው። በወልቃይት ጉዳይ ላይ ግልጽ አቋም ያላቸው፣ እነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባይደግፏቸው ኖሮ፣ ዶር አብይ ጠቅላይ ሚኒስተር መሆን አይችሉም ነበር። ሕወሃቶች ለእርሳቸው ድጋፍ እንዳልሰጡ መቼም ይረሱታል ብዬ አላስብም። ታዲያ አሁን ሕወሃትን ለማስደሰት፣ የሕወሃትን ያረጃ ዘረኛ ፖሊሲ ለማስቀጠል፣ ከኦሮሞ ማህበረሰብ ባልተናነሰ ሲደግፋቸው የነበረውን ማህበረሰብ ጥያቄ ማጣጣላቸው፣ ያጎረሱትን እጅ እንደ መንከስ ነው።

የወልቃይት ጉዳይ መፍትሄ ያስፈልገዋል። ተሸፋፍኖ፣ ተደባብሶ የሚቀር ጉዳይ አይደለም። ይሄን ስንል፣ የመፍትሄ ሐሳቦችን ሳናቀርብ ቀርተን አይደለም። የመፍትሄ ሀሳቦችን ብዙዎቻችን በተለያዩ ጊዜ አቅርበናል። ብዙ ሕብረ ብሄራው የሆኑ፣ ብዙ ብሄረሰቦች በብዛት የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ልክ እንደ አዲስ አበባ፣ ሕብረ ብሄራዊ በሆኑ አስተዳደሮች ስር እንዲሆኑ ጠይቀናል። ወልቃይት የትግሬዎች ብቻ አይደለችም። ወልቃይት የአማራ ብቻ አይደለችም። የአማራ ፣ የትግሬ የሚል ነገር የኋላቀርነት አስተሳሰብ ነው። ወልቃይት ሕብረብሄራዊ ናት። ወልቃይት የሁሉም ናት። ወልቃይት የወልቃይቴዎች የነዋሪዎቿ ናት። በመሆኑም ሁሉንም እኩል የሚያደረግ፣ ፍቅርን የሚያመጣ አስተዳደራዊ መፍትሄ ያስፈለጋል።

ለምሳሌ

– በአማራ ክልል ሁሉም ዜጎች እኩል ናቸው። የአማራ ክልል ሕብረብሄራዊ ክልል ነው። የክልሉ ሕገ መንግስት የአማራ ክልል የአማራዎች ነው አይለም። በመሆኑም ወልቃይት ጠገዴ፣ ልክ እንደ አዊ፣ ኦሮሚያ/ከሚሴ ..ዞኖች ልዩ ዞን ሆና፣ አማርኛና ትግሪኛ የዞኑ የስራ ቋንቋ ተደርጎ እንድትቀጥል ማድረጉ አንዱ አማራጭ ነው።

– ሌላው አማራጭ ወልቃይት ጠገዴን አማርኛና ትግሪኛ የስራ ቋንቋ የሆኑባት፣ ትግሬ፣ አማራ ሳይባል ሁሉም እኩል የሚታዩባት ራሷን የቻለች ወይም ልክ እንደ ድሬዳዋ የፌዲራል ልዩ ዞን ማድረግ ነው። በድሬዳዋ የኦሮሚያ መንግስት ድሪዳዋ የኦሮሞ ናት ሲል፣ የሶማሌ ክልል መንግስት ድሪዳዋ የሶማሌ ናት ሲል፣ ሊስማሙ ባለመቻላቸው በፌዴራል ስር መተዳደር መጀመሯ የአደባባይ ሚስጠር ነው።

– ሶስተኛው፣ እኔ የተሻለ አማራጭ ነው የምለው አማራጭ፣ የአማራ ክልልን አፍርሶ ወልቃይት ጠገዴን ያካተተ የቀድሞ የበጌምድርን አስተዳደርን መልሶ መዘርጋት ነው። ያኔ በበጌምድር ሰላም ነበር፣ ፍቅር ነበርና። የያኔው ፍቅርና መተሳሰር ይበጃል ባይ ነኝ።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.