አስቸኳይ መልእክት ለአማራና ኦሮሞ ሕዝብ! (ነፃነት ዘለቀ)

ጠ/ሚ ዶክተር አቢይ አህመድ በወያኔው አከላለል ወደ አማራው ክልል ሊሄዱና የሥራና የትውውቅ ጉብኝት ሊያደርጉ እንደሆነ ሰምተናል፡፡ መልካም ጉብኝት፡፡

ይህን ጉዞ በሚመለከት አንድ የማስጠንቀቂያ ጽሑፍ ከዘሀበሻ ድረገፅ ዛሬ ሌሊት አንብቤያለሁ፡፡ ጥሩ ማሰጠንቀቂያ ነው፡፡ እኔም ትንሽ ነገር መናገር ፈለግሁና መጣሁ፡፡

ወያኔዎች እንደገቡ ሰሞን አምቦ አካባቢ አንድ ስብሰባ ተጠርቶ ነበር፡፡ በዚያ ስብሰባ ላይ የኦህዴድ ይሁን የኦነግ ካድሬ ተሰብሳቢው የኦሮሞ ሕዝብ በአማራ ላይ ጥላቻ እንዲያሳድርና ከየአካባቢው ገርፎ እንዲያስወጣው ብዙ ይወተውት ገባ አሉ፡፡ ከካድሬው አቆራቋሽ የቅስቀሳ ንግግሮች መካከል “ ‹ጋላ ሲሰለጥን በጨረቃ ጥላ ይዞ ይሄዳል፡፡› እየተባልን ስንናቅ ኖረናል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በላይ ምን ትጠብቃላችሁ? …” የሚል ነበረበትና አንድ ሽማግሌ ብድግ ብለው “እናንተ የመጣችሁት አብረን በሰላምና በፍቅር ተሳስረን፣ ተጋብተንና ተዋልደን ከኖርነው ሕዝብ ጋር ልታጨፋጭፉን ነው እንዴ?….” አሏቸው፡፡ ሕዝቡም በሽማግሌው ንግግር በመመሰጥ አጨበጨበላቸውና ስብሰባው በዚያ ተበተነ፡፡ ካድሬውም አፍሮ ተመለሰ፡፡ ያን ሽማግሌ ግን ደብዛቸውን አጠፏቸው፡፡ እነዚያን በመሰሉ አበጣባጭ የካድሬ ስብሰባዎችና ስብከቶች ብዙ ሕዝብ ተጎድቷል፡፡ ብዙ ንብረት ወድሟል፡፡ ብዙ ጥፋት ደርሷል፡፡ አሻራው እስካሁንም አለ፡፡

የአማራ ገበሬ ለራሱ ሰለጠነ በሚባለው የኅብረተሰብ ክፍል የተናቀና በድህነት የተዘፈቀ ሕይወት የሚመራ ነው፡፡ ይህን ሕዝብ ሰውን እንደሚንቅ የሀሰት ወሬ እየነዙ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጨራረስ ቆርጠው የተነሱ በተለይም ወያኔዎችንና ግብረ አበሮቻቸውን መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ አማራ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ጨዋ ሕዝብ ነው፡፡ ባህል ያለው፣ ሃይማኖት ያለው፣ ወግና ልማድ ያለው፣ ሰውን አክባሪ፣ እንግዳን አብልቶና አጠጥቶ በቤቱም አሳድሮና ስንቁን ሰንቆ የሚሸኝ ግሩም ሕዝብ ነው፡፡ ይህን ሕዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ለማጋጨትና በትርፉም የሥልጣንና የዘረፋ ዕድሜያቸውን ለማራዘም የሚፈልጉ ወገኖች አሁንም ድረስ አላረፉለትም፡፡ አሁን አሁን በተለይ ከተንጠለጠሉበት ጣፋጭ የሚመስል ኑሮ የመውረጃቸው ዘመን በመቃረቡና ለዚህ ውድቀታቸውም አማራውን በዋና ሰበብነት በመፈረጃቸው እርሱን ለማጥፋት የማይሸርቡት ሤራ የለም፡፡ ከሤራዎቹም አንዱ ከኦሮሞ ወንድሞቹ ጋር ማጋጨት ነው፡፡ መለስና ተተኪዎቹ ዕድሜያቸውን የሚቀጥሉት ዜጎችን በማጋጨት መሆኑ ደግሞ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡

በአማራ አካባቢ ፀረ-ኦሮሞ ንግግርም ይሁን የስድብና የዛቻ ቃል ቢሰነዘር የዚህ ዕኩይ ድርጊት ጠንሳሽና አራጋቢ ወያኔ እንጂ አማራ ሊሆን አይችልም፡፡ አማራ ማንንም በመሳደብ ጥቅም እንደማያገኝ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ አማራ እንኳንስ ተዋህዶና ተዛምዶ የሚኖረውን የራሱን ኦሮሞ መሳደብ ይቅርና የውጭ ዜጎችን ሳይቀር አክባሪ ሕዝብ ነው፡፡ አማራን ከሌላው ጋር በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ የሚያግበሰብሱት ወያኔዎች ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ድርጊታቸው ደግሞ ወደፊት ብዙ ዋጋ ያስከፍላቸዋል፡፡ ሰውን በሀሰትና በፈጠራ ወሬ ማጋጨት እንደፈለጉ በሚዘውሩት የመሬት ህግ ባያስቀጣ በሰማይ ቤት የሥራቸውን ማግኘታቸው አይቀርም፡፡

አሁን ግን እኛ ሕዝቡ ጠንቀቅ ማለት አለብን፡፡ በየትኛውም ስብሰባና መድረክ ምንም ነገር ቢነገር የወያኔ ሥራ እንጂ የአማራው ሊሆን እንደማይችል መረዳት አለብን፡፡ በ“እንዲህ ተባልን” የስሜት ጡዘት ወንድሞቻችንን አላግባብ እንዳንጎዳ መጠንቀቅ አለብን፡፡

እንዲህ ስል ከየጎሣውና ከየነገዱ ባለጌና ወስላታ የለም ማለቴ አይደለም፡፡ እንደሕዝብና እንደማኅበረሰብ ባለጌና ጨዋ የሚባል ነገር የለም፡፡ እንደግል ግን አንዱ ባለጌ ሌላው ጨዋና ትሁት ይሆናሉ፡፡ የሚፈረደውም በግል እንጂ  በአጥፊው ግለሰብ የነገድ ዳራ ወይም የቋንቋ ቤተሰብ ሊሆን አይገባም፡፡ የቶሎሣ ጥፋት በቶሎሣነቱ ይበየንበታል እንጂ “አሃ! ኦሮሞ ስለሆነ….” እየተባለ በሠላሣና ዐርባ ሚሊዮኖች የሚገመት ሕዝብ በአንድ ተራ ዜጋ ሊወቀስ አይገባም፡፡ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ አማራ ግለሰብ በስካርም ይሁን በዕብደት አንዳች አስቀያሚ ነገር ቢናገር ወይ ቢያደርግ አማራው ሁሉ እንደዚያ ሰውዬ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ እንኳስ ማሰብ የሚችለው ሰው ይቅርና ማሰብ የማይችሉ እንስሳት እንኳን በምግባርና በጠባይ አንዱ ከሌላው ይለያያሉ፡፡

ስለዚህ ጠ/ሚኒስትሩ ወደ አማራው አካባቢ ቢሄዱና በዘርና በሃይማኖት ምክንያት አንዳች ሁከት ሊፈጠር ቢችል መንስዔው ወያኔው የሚያሰማራቸው የራሱ የጥፋት ልዑካን እንጂ አማራው ሊሆን እንደማይችል ወንድሙ ኦሮሞ ሊገነዘብና አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል፡፡ የማሰብ ኃይላችንን በሚገባ መጠቀም ይርብናል፡፡ በኋላ መጸጸት ዋጋ የለውም፡፡ ወያኔ ኢያጎ ነው፡፡

በሌላም በኩል አማራ ጭቆናንና በደልን ይጠላል እንጂ ወንበሩን ማን ያዘው ማን የሚጨነቅ ግብዝ ሕዝብ አይደለም፡፡ በአንድ ወንበር ላይ ከአንድ ሰው በላይ ሚሊዮን አማራ ሊቀመጥበት እንደማይችል የሚገነዘብ ሕዝብ ነው፡፡ እንኳንስ በግማሽ አማራ የሆነ ጠ/ሚኒስትርና ይህ ጣጠኛ ወንበር ላይ ጎሽና ጉማሬም ቢቀመጡበት ሀገርን አስተካክለው በፍትህ እስካስተዳደሩ ድረስ የአማራው ጭንቀት አይደለም፡፡ አማራው አፄ ኃ/ሥላሤ አማራ አለመሆናቸውን ሳያውቅ ቀርቶ አልነበረም፡፡ አማራው አፄ ዮሐንስ ትግሬ መሆናቸውን ዘንግቶት አልነበረም፡፡ አማራው አፄ ምኒልክ የኦሮሞ ዘር እንዳለባቸው ሳያውቅ ቀረቶ አልነበረም፡፡ አማራው አፄ ገላውዴዎስ የኦሮሞ ልጅ መሆናቸውን ረስቶት አልነበረም፡፡ አማራው የመንግሥቱ ኃ/ማርያምን ኦሮሞነት ስቶት አልነበረም፡፡ … ዛሬ ታዲያ ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ነው አማራ ኦሮሞ አይገዛኝም ሊል የሚችለው? እንደጥሩ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ይህ አዲስ ጠ/ሚ በሃይማኖቱም ፣ በዘር ሐረጉም፣ በትምህርቱም፣ በዕድሜውም፣ በተሞክሮውም፣… ከተጠቀመበት በተለይ … ሁሉንም የሚያካትት ስብዕና ስላለው በሁሉም ዘንድ የሚኖረው ተቀባይነት እስካሁን ከነበሩን መሪዎች ቢበልጥ እንጂ አያንስም፡፡ ስለሆነም ለወያኔ መርዘኛ ቅስቀሳና ስብከት እንዲሁም ለወያኔ ወለድ ጠብና አምባጓሮ ሳንረታ እውነቱን እንወቅና ፍቅራችንንና መተሳሰባችንን እናጠናክር፡፡ የብልጦች መሣሪያ መሆን መጨረሻው አያምርምና ጠንቀቅ እንበል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.