ጉድ ነው ዘንድሮ ይባስ አለና አገርህን አትልቀቅ (ሰርፀ ደስታ)

አቦ ሰውዬው ለራሱ እንኳን አይደብረውም? አንዳንዴ እኮ ዝም ብሎ የሆኑም በሕዝብ ድጋፍ ጠንካራ ይሆናሉ፡፡ ይሄ አብይ የሚባል ሰውዬ ይሄን ያህል ችግር ውስጥ እንደሆነ አላወቅንም የወያኔ ማደጎ እንደሆነ ብንረዳም፡፡ ለመሆኑ አዲስ ሾምኩ የሚላቸውን ሚኒስቴሮች ገብተዋችኋል? ትሻልን ብዬ ትብስን አገባሁ አለ ሰውዬው አቃጣይ የሆነችውን ሚስቱን ፈትቶ ከሷ የባሰቸውን አቃጣይ ስላገባ፡፡ አሁን የሄ ሰውዬ ከኃ/ማሪያም ይሻላል ብላችሁ ነው? ኃ/ማሪያም ሲጀምር እንዲህ ባለ ወቅት አልመጣም የሕዝብም ድጋፍ የለውም፡፡ መለስን ሲያመልክ ኖሮ መለስን የሚያመልኩ ካቢኔ ውስጥ ነው የገባው፡፡ በአጠቃላይ አገርና ሕዝብን ሊመራ ሳይሆን የመለስን አምልኮት ለማስፋፋት ነበር የተሾመው፡፡ አገርንና ሕዝብን ያፈረሰ የአገር ጠላት ባለራዕይ እያሉ ሲዘፍኑብን እኛም አብረን ስናጨበጭብ ነበርን፡፡ ያሳዝናል፡፡ ነገሩ አፍዝ አደንግዝ ሆኖብን እንጂ መቼም አገርን ያለወደብ ያስቀረ፣ ሕዝብን በዘር የከፋፈለ፣ አገር ለዘለቄታው ሰላም እንዳይኖራት ያደረገ፣ ….አቦ ስንቱን አወራዋለሁ፡፡ እያየን እኮ ነው ጭራሽ ልማታዊ፣ በለራዕይ…. አቦ ያናድዳል፡፡ ቁርጥህን እወቅ ወገኔ ብቻ ከዚህ አብይ ከሚባል ሰው ኃ/ይለማሪያም እንደሚሻል ስንታዘብ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ እስኪ ኃ/ማሪያምን ብዙ ያልናቸው ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ ሰወዬው ግን የምርም አዚም አደረጉበት እንዴ? ሚኒስቴሮች ሾሟል፡፡ ምን እያረገ እንደሆነ የገባችሁ ንገሩን፡፡ እኔ እንዲህ ያለ ነገር አይገባኝም፡፡ የአገሪቱ ዋና የልማት ዘርፍ ግብርና ነው ያለው ሰውዬ ሽፈራው ሽጉጤን የግብርናና እንስሳት ሚኒሰቴር አርጎት ቆጭ፡፡

በነገራችን ላይ ግብርናና እንስሳት ማለት ግን ምን ማለት ነው? ወይ እንሰሳ! አብዛኞቹ ሚኒስቴር ተብዬዎች ምንም አይተ ዕውቀት የሌላቸው ከመሆኑም በላይ ወንጀለኞችም ናቸው፡፡ ሽፈራው ሽጉጤን እኮ ሕዝብ በጉራ-ፈርዳው የሕዝብ እልቂት ለፍርድ እንዲቀርብለት የሚፈልገው ወንጀለኛ ነው፡፡ አብዲ ኢሌ አልተሾመም? የከብቶች፣ ፍየሎች፣ ዋንኬ በጎችና ግመሎች ሚኒስቴርነት ይገባው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በአለም ዓቀፍ ደረጃ ሳይቀር ትላልቅ ወጤትን ያመጡ ሳይንቲስቶች አገር ነች፡፡ ለአብነት የ2009ኙን የዓለም የምግብ ሎሬቱን የፐርዱ ዩኒቨርሲቲውን ፕሮፌሰር ገቢሳ እጄታን መጥቀስ በቂ ነው፡፡ በተባበሩት መንግስታት የተለያዩ ኤጀንሲዎችም ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ምንጩ እየደረቀ ስለሆነ ከኢትዮጵያ እነሱን የሚተካ የለም፡፡ በኢኮኖሚክስ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ብዙዎቻችን በየአቀማችን አገርን ሊቀይር የሚችል ዕውቀትና ንድፈ ሀሳብ አለን፡፡ ከእነዚህ ወንበዴዎች ጋር ግን መሥራት ስለማይቻል ሁሉም የሌላ አገር አገልጋይ ነው፡፡ ፕ/ር ገቢሳ የተወሰነ ሞክሮ ነበር ግን በፍጹም እንዲጠጋቸው አልፈለጉም፡፡ ሌሎች ብዙ እንዲሁ ሞክረዋል፡፡ የደስታ በሽታን ክትባት ያለ ማቀዝቀዣ እንዲጓጓዝ ኢንጂነር ያደረገው ፕ/ር ጥላሁን ይልማ ሌላው መጥቀስ የምፈልገው ሰው ነው፡፡ ጥላሁን ይልማ ደ/ዘይት (ቢሾፍቱ) ላይ በቢሊየን ዶላር የሚንቀሳቀስ ላብራቶሪ ሊያሰራ አስቦ የወያኔው መሪ መለስ ነው የከለከለው፡፡ በኋላ ያ ላብራቶሪ አፍሪካ ውስጥ መሰራት ስለነበረበት ከይሮ ላይ ነው የተሰራው፡፡ ወገኖች ብዙ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን መርዳት ያልቻሉት እንዲህ ያሉ ወሮበሎች አገራችንን ስለወረሱት ነው፡፡

በንግዱም ዘርፍ ታላላቅ ችሎታና አስደናቂ ውጤታማነት የነበራቸው በርካቶች ሥራቸው እንዲበላሽ ሆኗል፡፡ ብዙዎቹም ለእስርና ሌሎች እንግልቶች ተዳርገዋል፡፡ የታዋቂውን የኮሞዲቲ ንግድ ሰው የኢትዮጵያን አማልጋሜትድ ባለቤት የነበሩትን ገብረየስ ቤኛን እንዴት አርገው ከኢትዮጵያ እንዳሰወጧቸው እናውቃለን፡፡ ገበየሁ የአለምን ገበያ ሳይቀር ያነቃነቁ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡ ይህ ለብዙዎቻችን አይገባንም፡፡ ኤርሚያስ አማልጋ ሌላው  ምሳሌ ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት የለም ወሮበሎች ሥር ነች፡፡

የሆነ ሆኖ ይሄ አብይ የተባለው ግለሰብ ጊዜ ሥጡት ለምትሉን እናንተ ሥጡት የተረፋችሁ ከአላችሁ፡፡ በአጠቃላይ እሱ ቢቻም ሳይሆን ወያኔ ሥርዓት ውስጥ ምለው የገቡ ብዙዎች በየቦታው እያጃጃሉን ነው፡፡ ለመሆኑ ግን ይሄ የኢሳቱን ኤርምያስ ለገሰ የሚባልን ሰው እንዴት ነው የምታዩት፡፡ የወያኔ ሚኒስቴር ዴዕታ የነበረ፣ ሊያውም የበረከት ማደጎ ዛሬ ዋና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፖለቲካ ተንታኝ ሆኖ ቁጭ ብሏል፡፡ መቼ ነው የሚገባን፡፡ ይህ ግለሰብ እኔ እንደተረዳሁት ለወያኔ የሚሰራ ከውስጥ መረጃ እየተቀበለ ታላቅ ተንታኝ እንዲሆን ወያኔ የሰተችውን ተልዕኮ እያከናወነ ነው፡፡ ልብ በሉ በአለፈው በረከት መልቀቂያ ሲያስገባ እኔ አውቃለሁ በረከት አይለቀም አለ፡፡ አይምሰላችሁ ይሄ ኢንተለጀንሲ ሳይሆን መረጃውን ከመጀመሪያውም ያገኘው ከራሱ ከበረከት ነው፡፡ አስቂኙ ነገር ደግሞ በረከት መልቀቂያ አስገባ ተብሎ እንዲወራ ስለተፈለገ ድራማ ነበር እንጂ ከመጀመሪያውም በረከት እንደማይለቅ ይታወቅ ነበር፡፡ እና ከድራማው ተዋናይ አንዱ ኤርሚያስ ነበር፡፡ ከትናንት በፊት ደግሞ ሽፈራውን የእንስሳ ሚኒስቴር እንደሚያደርጉት እርግጠኛ ሆኖ ሲያወራ ነበር፡፡ እንዲህ ቀድሞ መረጃ እየተሰጠው እንዲያወራ የተፈለገው ሚስጢር ያውቃል እየተባለ ጥሩ የሕዝብ ጆሮ እንዲያገኝ ነው፡፡ ባለፈው አብይ የምርም ኢትዮጵያዊ ሊሆን ይችላል በሚል ስጋት ብዙ መርዞችን ሲነዛ ነበር፡፡ ለምሳሌ አብይ ስለኢትዮጵያ ተስፋ ሰጭ ነገሮችን ተናግሮ ህዝብ ሁሉ ደስ በአለው ጊዜ እሱ ነገሮች ሁሉ በጥርነፋ ስር እንደተደራጁና እነ አባይ ጸሀይዬ እጅ እንደቆለፉት ሲዘፍን ነበር፡፡ አብይ የራሱ ችግር እንጂ ብዙ እድሎች ነበረት፡፡ ወዲያው አብይ ሲሳሳትለት ነጥብ ጣለ የሚል ደስ ብሎት ሲነዛብን ነበር፡፡ ቀደም ብሎ ሕወሀት ለሶስት ተከፍሏል ምናምን ወሬ እየፈጠረ ለሕዝብ ውዥንበር ሲነዛ ነበር፡፡ የጻድቃንንና አበበ የወያኔ ጀነራሎችን  ሴራዊ መልዕክትን ኢሳት በበጎ ሀሳብ ሲያራግብ ነበር፡፡ ሰሞኑን ተመችቶታል፡፡  ኢትዮጵያዊ የሆንክ ሁሉ እንደነዚህ ያሉ ቅጥረኞችን ነቅተህ ጠብቅ፡፡ የወያኔ ተቃዋሚ የሚመስሉት ሁሉ ወያኔ አይመሰሉህ፡፡ ወያኔን መቃብር መጨመር የሚቻልበትን ነገር እኮ አሁን ተረድተናል፡፡ እስከዛሬ እርስ በእርስ እየተነታረክን እንጂ ወያኔ አንድም ቦታ ባልኖራት፡፡ አሁን እኮ እስረኛም ቢለቀቅ፣ እርስ በእርስም ቢሆን ተቀይረናል ለማለት ያደረሰው የሕዝብ አንድነት ነው፡፡ አሁንም ተጠናክሮ ይቀጥል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳደር በአብይ የሴራ ሰንሰለት እንዳይወድቅ ስጋት ይዞኛል፡፡ በጣም ሹምሽር በዛ፡፡ እርግጥ ነው የተሾሙትን አላውቃቸውም፡፡ አንዳንዶቹ በዝና ጎበዝ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡ የነገሪ ሌንጮ ከፌደራል ወደ ኦሮሚያ መሄድ ግን ዲሞሽን ነው ወይስ ሴራ? ፌደራል ላይ ያሉ የኦህዴድ ተወካዮች አብይን ጨምሮ ተስፋ የሚጣልባቸው እንዳልሆኑ አይተናል፡፡ በነገራችን ላይ አሁን በትግሬ ወያኔ ሕወሀት መመካኘት ራሱ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ጎዲፈቻዎቿ ናቸው አሁን አብዛኛውን ስልጣን እየያዙ ያሉት፡፡ ኦህዴድ በጣም ብዙ ቦታ ይዘዋል፡፡ ግን እየሆነ የሚመስለው የትግሬ ወያኔዎቹን ወንጀል ለመሸፈንና ትግሬ ወያኔዎቹ የዘረፉትን ሁሉ ይዘው እንዲወጡ  ይመስላል፡፡ ከአገር ለይሆን ይችላል ግን ለተወሰነ ኦሕዴዶች በበላይነት እንዲይዙና ለወያኔዎቹ ከለላ በመስጠት ውለታ የተዋዋሉ ነው የሚመስለው፡፡ የወያኔ ጎዲፈቻ የኦሕዴድ አባላት በትግሬ ወያኔ ምትክ ቀሪ ዘረፋዎችን እንዲለቃቅሙ ታስቦ እየተሰራ ይመስላል፡፡ ከዚያ ወንጀሉ የኦህዴድ ሰዎች ስለሚሆን ኦሮሞ ናቸው በሚል በኦሮሞ ሕዝብ ተከልለው እድሜ ማግኘት እንችላለን በሚለው ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ያው የኖረበት ችግሩ ቢቀጥልም ኦሮሞ ነው የተሾመው በሚል እንደ ትግሬ ለወያኔ እንደሆነው የኦሮሞ ቀጣይ ዘራፊዎችን ሽፋን እንዲሆን ነው፡፡ እውን ግን የኦሮሞን ሕዝብ እንዲህ በቀላሉ ማታለል ይቻል ይሆን? እነ መረራናስ ዝም ይላሉ? ይህን የምለው ለዘረፋ ያሰፈሰፉትን ማለቴ ነው፡፡ ሆኖም በኦሕዴድ አንጀታቸው የተቃጠለ ብዙዎች አሉ፡፡ ችግሩ ወደላይ ከፍ ወደአለው ቦታ እየመጡ ያሉት ከእነዚህ ወገን ሳይሆን እንደነ አብይ ያለው ነው፡፡ አብይ ሰላማዊ ሽግግር እያለ ያለማፈር እየነገረን እኮ ነው፡፡ ቀልደኛ ነገር አልሆነባችሁም? ልብ በሉ ወያኔዎች በዚህ ስልት ራሳቸውን ከዘረፉት ሀብት ጋር እያወጡ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ መሪ ቢመጣ ግን እያንዳንዷን በሰራችው ወንጀል ለፍርድ ያርብ ነበር፡፡

ለነገሩ ያም ተባለ ያ እነሱ ስለመሰላቸው እንጂ አይቀርም፡፡ በፍጥነት ይወርዳሉ፡፡ እስከሚቀጥለው ምርጫ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይለይላቸዋል፡፡ እኔ የምለው ያ አብይን አይዞህ አለው ሲባል የነበረው ሽማግሌ የወያኔ የጡት አባት የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላት አሜሪካዊው ሄርማን ኮሆን ሰሞኑን ቲዊት ያደረገውን አይታችኋል፡፡ የሰሜን ሶማሌ ከ1991 ጀምሮ ነጻ  ወጥታለች በሂደት ኦጋዴን ነው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ይላል፡፡ ይሄ የዘር መሰረቱ የት ነው? በባለፈው አዳሜ ከኢትዮጵያ ጋር ሆነ እያልክ አብረህ ስተዘፍን ነበር፡፡ አንሳሳት፡፡ እባብ ሞኝን ሁለት ጊዜ ነደፈው ነው፡፡ ሁሉንም በትኩረት እንይ፡፡

ልዑል እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው! በእሱ ሁሉንም እንጥላቸዋለን!

ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ተራዳ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.