‘አዋቂ የሚያስበው ሃሣብን እንጂ ቡድንና በቡድን አይደለም!’ (ሐይሉ አባይ ተገኝ)

ማንም ያምጣው ማንም የሃሣብ ጥራትና ገንቢነት የሚለካው ሃሣቡን ሃሣብ ባደረገው መረጃና ማስረጃ ነው። ሃሣብን በሃሣብ መሞገት የስልጣኔ ምልክት ነው። የሃሣብን ባለቤት ያለመረጃና ማስረጃ ማብጠልጠል አምባገነንነት ብቻ ሣይሆን ድንቁርና ነው።

የሰውን የማሰብ ነፃነት እያዋከቡ፤ ሃሣብን በሃሣብ ሣይሆን በቡድንና በደቦ የሚያስቡ በፌስቡክ ሜዳ በርክተዋል።
በነርሱ የራስ ቅል ሃሣብን እንድንቀዳና እንድንሞላ ይፈልጋሉ። የቡና ፈረጃዎቹ ወጣ ያለን ሃሣብንና ሰውን በወያኔነትም ይፈርጃሉ። ለኔ ወያኔ በአንድ በኩል የሚወገዘው ሃሣብን በማፈኑ ከሆነ ሃሣብን እያፈኑ ናቸውና ወያኔዎቹ እነርሱ ናቸው። በዚህኛውና በእዛኛው ገፅ ሃሣብ አትስጡ፤ ላይክ አታድርጉ እያሉስ
በኢንቦክስ (inbox) መልዕክት ይቀያየራሉ። ላይክ የሚያደርጉት ለሃሣብ ሳይሆን ለጀሌያቸውም ነው። በመንጋነት ለታጎሩበት በረት ነው። አውራ ጣታቸውን ቀስረው ብዙ ተከታይ ያላቸውን በመፈለግ ሃሣቡን ሳይረዱ ለመታወቅ ሲሉ ያራግባሉ። በፌስቡክ መንደር የተሰለፉትም ለማወቅና እውቀት ለማካፋል ሣይሆን የላይክ (like) አውራ ጣት ለመሰብሰብም ነው።

ከሁሉም በላይ በዚህ የሶሻል ሚዲያ የተራቡ ብዙዎች ለማወቅ ሣይሆን ለመታወቅ ያኮበኮቡ ናቸው። እነርሱ “ብሄረተኛ ” ወይም ግንቦት 7 ወይም ሌላ ከሆኑ ሁሉም ሠው እነርሱ የሆኑትን መሆን አለበት ብለው የፈረስ ጌኛ አጥልቀው ሲደናበሩ እናስተውላለን። ስለኢትዮጵያ አንድነት ካነሳህ ጭራሽ “ዲቃላዎች” ሲሉም ይደመጣሉ። በድምሩ የነርሱን ድጋፍ ለማግኘት ወደነርሱ ገደል መግባት ያስፈልጋል። ይህ አላዋቂነት ብቻ ሳይሆን ተልዕኮም ነው።

‘አላዋቂነታቸውን እየሸፈኑና “አዋቂም” ሆነው ከሌላው ለመማር የሚፈልጉ “ብሩህ” ለመምሰል ዘዴኛ ጥያቄዎችን እያነሱ ይኮፈሣሉ – የሶቅራጥስ ምፀት (Socratic Irony) እንደሚባለው።

ኢትዮጵያዊ ነን። ልክ የኦነግና የወያኔ ካድሬዎች እንደሚሉት ‘ኢትዮጵያዊ ነን፤ በኢትዮጵያ አንድነት እናምናለን’ የሚሉትን አማራ ኢትዮጵያዊ ምሁራንን እንደዚህ እያሉ ወያኔያዊ ፕሮፓጋንዳና ስድብ ያወርዱባቸዋል።

ለምሳሌ ‘ሚኪያስ ሰለሞን’ ነኝ በሚል የፌስ ቡክ ፕሮፋይል እራሱን “ምጡቅ ምሁር” አድርጎ ከሠየመ ግለሰብ ገፅ ይህ ተለጥፋል።
(Screenshot posted on comment section)

ሚኪያስ “በብሄረተኝነት” ስም እንዲህ ያጓራል።

“አብዛኞቹ የአማራ ምሁራን ማለት:

1. የመማር ተግባራዊ ጠቀሜታው (application) ሳይገባቸው የተማሩ ናቸው፡፡

2. በዘረኝነት ይሉንታ እራሳቸውን የሚሸውዱ ፥ እየሞቱ አለን ብለው የሚያስቡ ፥ የተምታታባቸው ዘገምተኞች ናቸው፡፡

3. በህዝባቸው በአማራ ጥቅም እና ደኅንነት ላይ የሚቀልዱ እና ጊዜያቸውን በከንቱ የሚያሳልፉ ቸልተኞች ናቸው።

4. እራሳቸውን ለማንቃት ፥ ከወቅቱ ጋር ለመራመድ ፥ መፍትሄ ለማፍለቅ በጣም የተቸገሩ እና ሜዳው ገደል የሆነባቸው ጨለምተኞች(pessimists) ናቸው፡፡

5. እንዲህ ይላሉ “የአማራ አገሩ ኢትዮጵያ ናት ተገንጥሎ እንዴት ይኖራል?…አሁን እንደምረዳው ከሆነ ኢትዮጵያ የአማራ አገሩ ሳትሆን #መቃብሩ እየሆነች ነው። #ብሔረተኛ ከመሆን ውጭ ምንም አማራጭ የለንም እራሳችንን ለማዳን።” ይለናል። ይህ የለየለት የጅምላ ፍረጃና የባህሪ ጥቃት (adhominum fallacy) ነው።

የአማራ ምሁራንን ማብጠልጠል ላለፉት 27 ዓመታት በወያኔ ፕሮጀክት የተወጠነና የተተገበረ ዛሬም በሚኪያስና በመሣዮቹ የቀጠለ የቅዠት መንገድ ነው። ከኢትዮጵያዊነት ጋር የሚጣረስ የአማራ ብሄረተኝነት ወያኔ ሠራሽ ነው። አማራ ኢትዮጵያን እንደ ህወሃትና ኦነግ ቅዠት አፍርሶ እራሱን አይበትንም። አባቶቹ በደም በአጥንታቸው የሠሯትን ሃገረ ኢትዮጵያ በማፍረስ እራሱ ላይ እሣት አይለኩስም። አማራ እንደሌሎቹ የሃገሩ ልጆች ኢትዮጵያዊም ነው። በዚች ሃገርም የፓለቲካ ስርዐት እንጂ ግዑዝ የሆነችው ኢትዮጵያ የበደለችው ጎሣም ይሁን ግለሰብ የለም።

የሚገርመው አሃዙን እንዳለ ብንቀበል እንኩዋን ከ3,400,000 (CSA) ህዝብ ውስጥ ከግማሽ በላይ አማራ (~+56.01%) በአዲስ አበባ እንደሚኖር ልብ ማለቱ ይጠቅማል። በኦሮሞ ክልል ከ34 ሚሊዮን ህዝብ 9.1% ወይም 3 ሚሊዮን ህዝብ አማራ ነው። በተለያዩ ክልሎች በድምሩ ከ9 ሚሊዮን በላይ አማራ እንደሚኖር ይገመታል።

የሚገርመኝ ነገር (irony) ሃሣብን በነፃነት የሚገልፁትን የነርሱን የቡድን ማሊያ ካለበሱ የሚያወግዙ ከሆነ መስማት የሚፈልጉት እራሳቸውንና መስማት የሚፈልጉትን ሆኗል። የሚገባኝ ነገር ቢኖር እነዚህ በፌስቡክ ሜዳ የሚፈነድቁትን እምቦሣዎች ያልተገሩ ናቸውና ያመንበትን ሃሣብ ከመግለፅ አንቆጠብ። ተሸማቀው ሊያሸማቅቁን ከሚፈልጉ ደናቁርትና ተላላኪዎች አንበገር።

‘አዋቂ የሚያስበው ሃሣብን እንጂ ቡድንን አይደለም!’

‘በቡድን የሚግጥና በጋራ የሚያስብ ከብት ብቻ ነው።’

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.