የፌዲራል አወቃቀር ለውጥ ደረጃ በደረጃ  (ግርማ ካሳ)

 

አዲስ አድማስ ጋዜጣ «ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣውን ጎሠኝነትና ብሔርተኝነት ከሃገራዊ ማንነት ጋር ማስታረቅ የሚቻልበትን የመፍትሄ ሐሳብ እንዲያፈላልጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ለምሁራን ጥሪ አቀረቡ፡፡ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች የተወሳሰቡ በመሆናቸው ችግሮቹን አገናዝቦ መውጫ መንገድ የሚያሳይ ምሁር ያስፈልገናል፤ ብለዋል» ሲል ዘግቧል።

ለአንድ ችግር መፍትሄ የሚገኝለት ችግር እንዳለ ማመን ሲቻል ነው። ብዙዎቻችን ችግሮች እንዳሉ ብንጽፍና ብንናገርም የኢሕአዴግ መንግስት ግን “የኪራይ ሰብሳቢኒት፣ ሙስና …ችግር ነው” በሚል ዋናውን ጉዳይ ለማድበስበስ ሲሞክሩ፣ ምንም አይነት በዘር ላይ የተመሰረተ ችግር እንደሌለ ሲክዱ ነው ስንሰማቸው የነበረው። ሆኖም ዶር አብይ ችግር እንዳለ ገልጸው ለችግሩ መፍትሄ ምሁራን ጥናት እንዲያደርጉ ጥሪ ማድረጋቸው አሌ የሚያስብል ነው።

ጥናት ማድረጉ መልካም ነው። ግን ከዚህ በፊት የተደረጉ ጥናቶች እንዳሉ ዶር አብይ ያጡታል ብዩ አላስብም።

ማንም የማይክደው ነገር ቢኖር ፣ በሕገ መንግስቱ ዘርና ጎሰኝነት ማእከሉን ቦታ የያዘ መሆኑን ነው። አገሪቷ በዘርና በጎሳ የተከፋፈለች ናት። ዘርና ጎሰኝነት systemized ሆኗል። ለምሳሌ የሶማሌ ክልል ለሶማሌዎች፣ የኦሮሞ ክልል ለኦሮሞዎች፣ የትግራይ ክልል ለትግሪዎች….ተብሎ የተሸነሸነ ነው። በሶማሌ ክልል ከሶማሌዎች ውጭ ፣ በኦሮሞ ክልል ከኦሮሞዎች ዉጭ ፣ በትግራይ ከተጋሩ ዉጭ ያሉት ሌሎች ነዋሪዎች…. በሶማሌ ክልል ከሶማሌው፣ በኦሮሞ ክልል ከኦሮሞው፣ በትግራይ ከትግሬው እኩል አይታዩም። መጤ ወይንም እንግዳ ተደርገው ነው የሚወሰዱት።

አንድ ሰው ፣ እንግዳ ከቤቱ ቢመጣ፣ በፈለ ጊዜ እንግዳዉን “ከቤቴ ውጣልኝ ” ቢለው መብቱ ነው። ሶማሌዎች በሶማሌ ክልል ኦሮሞዎችን፣ ኦሮሞዎች በኦሮሞ ክልል ኦሮሞ ያልሆኑትን፣ “መሬታችሁ አይደለም። መጤ ናችሁ” ቢሉ በሕግ መንግስቱ መሰረት ተሳስተዋል ማለት አይቻልም። አንድ ዜጋ ለርሱ ዘር ከተሸነሸነው መሬት ውጭ ከሌላው እኩል ሆኖ የመኖር ዋስታናው በምንም መስፈርት በሕግ የተረጋገጠ አይደለም።

እንግዲህ የዘር ችግሮችን ከስሩ ለማከም ከተፈለገ የችግሩ ዋና መሰረት ላይ ማተኮር ያስፈለጋል። ሕገ መንግስቱ መሻሻል አለበት። በሕግ መንግስቱ መሰረት የተዋቀረውም የዘር አወቃቀር መፍረስ ይኖርበታል።

አንደኛ- በፌዴሪሽ ግዛቶች የሚኖሩ ነዋሪዎች እኩል መታየት አለባቸው። የዚህ ዘር፣ የዚያ ዘር፣ የዚህ ብሄር፣ የዚያ ብሄር ብሎ ነገር መኖር የለበትም። በግዛቶቹ ላይ የሚወስኑት ሁሉም ነዋሪዎች መሆን አለበት።

ሁለተኛ- ፌዴራሊዝሙ የሕዝብን ፍላጎትና አሰፋፈር፣ ኢኮኖሚን፣ የአስተዳደር አመችነትን፣ ጂዮግራፊን፣ ታሪክንና ባህልን እንዲሁም ቋንቋን ባካተተ መልኩ፣ ዘመናዊ የአስተዳደር ፌዴራል ግዛቶችን ያቀፈ መሆን አለበት።

ዋናው ግባች ምን እንደሆነ ቢታወቅም በአንዴ ከግባችን ላንደርስ እንችላለን። ፌዴራል አወቃቀሩን መሰረታዊ በሆነ መልኩ ለመቀየር ሂደት ያስፈልጋል። ማለትም ደረጃ በደረጃ ማድረጉ ነው የሚያዋጣው። በአንዴና በፍጥነት ሁሉንም መቀየር አላስፈለጊ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ የተጣመመውን በአንዴ እናቃናው ብንል ልንሰብረው እንችላለን።

በአንደኛ ደረጃ የእትወሰኑ ክልልሎች ላይ የአወቃቀር ለዉጦች ማድረግ ይቻላል። በተለይም ችግሮች በብዛት የሚከሰቱባቸውንና ሕብረ ብሄራዊ የሆኑ አካባቢዎችን ሕብረ ብሄራዊ ክልሎች ውስጥ ማካተቱ በጣም ይረዳል። በዚህ መስረት የበዘር ላይ የተዋቀሩ አስተዳደሮች በተወሰነ መልኩ ማስቀጠሉ ለጊዜው አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። የሶማሌ ክልል፣ የኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምእራብ ተብሎ፣ የአፋርና የትግራይ ክልል ለጊዜው ይቀጥላሉ። ከነዚህ በተጨማሪ ዘጠኝ ሕብር ብሄራዊ ክልሎችን ይኖራሉ። በአጠቃላይ አስራ አራት ክልሎች ይሆናሉ ማለት ነው””” የአማራና ክልልና የደቡብ ክልል ለአራት ለአራት መበታተናቸው የአማራም ሆነ የደቡብ ክልል ሕዝብ የሚደገፈው ይመስለኛል። ኦነግና ሕወሃት ናቸው እነዚህን ሁለት ክልሎች ያለ ሕዝቡ ፍላጎት የመሰረቱትና።

1. – አዲስ አበባን፣ የኦሮሞ ክልል ሰሜን ሸዋ ፣ ምስራቅ ሸዋ ፣ ደቡብ ምእራብ ሸዋ ፣ አዳማ ልዩና ቡራዩ ልዩ ዞኖች፣ የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ከሚሴ ከተማ ያለችበትን ኦሮሚያ የሚባለውን ዞን ደቡብን ክፍል እና የአርጎባ ልዩ ወረዳን ያካተተ ፣ የስራ ቋንቋ ኦሮምኛና አማርኛ የሆነበት፣ ዋና ከተማዉን አዳማ ያደረገ ሸዋ የሚባል ሕብረ ብሄራዊ ክልል

2. – የድረዳዋ ከተማ፣ የሃረሬ ክልልን፣ የሶማሌ ክልል ሽንሌ ዞንን፣ በሃረርና በድረዳዋ መካከል ያሉ የኦሮሚያ ወረዳዎችን፣ በሶማሌና ኦሮሞ ክልል ውስጥ ለሁለት ተከፍለው የተካተቱት የሚኤሶ. ጉርሱምና ባቢሊ ወረዳዎች ያካተተ፣ አማርኛ፣ ሶማሌኛና ኦሮምኛ እንዲሁም አደረኛ የስራ ቋንቋዎች የሆኑበት፣ ዋና ከተማዉን ሃረር ያደረገ ሃረርጌ የሚባል ሕብረ ብሄራዊ ክልል

3. – ቀድሞ የበጌምድር የነበረውና አሁን የትግራይ አካል የሆነው፣ ከተከዜ በስተምእራብ ያለው፣ የትግራዮች ብቻ ከሆነው የትግራይ ክልል የተለየና ራሱን የቻለ ፣ ትግሪኛና አማርኛ የስራ ቋንቋ የሆነበት፣ ዋና ከተማው ሁመራ የሆነ ሰሜን የሚባል ሕብረ ብሄራዊ ክልል

4. – የደቡብና የሰሜን ጎንደር ዞኖችን ያካተተ፣ ዋና ከተማው በታሪካዊቷ ጎንደር የሆነ በጌምድር የሚባል ክልል

5. – የአማራ ክልል የምስራቅና ምእራብ ጎጃም፣ የባህር ዳር ልዩ፣ የአዊ ዞኖችን ጨመሮ የሚፈርሰውን የቤኔሻንጉል ክልል ያካተተ፣ ዋና ከተማ ደብረ ማርቆስ የሆነ ጎጃም የሚባል ክልል

6 – የአማራ ክልል ዋግ ሁመራ፣ የሰሜን እና የደቡብ ወሎ ዞንን ያካተተ፣ ዋና ከተማው ደሴ የሆነ ክልል

7. የወላጋ አራቱ ዞኖች፣ የጅማ ከተማን እና በጂማ ከተማና በደቡብ ክልል መካከል ያሉት ወረዳዎች ሳይጨምር የተቀረውን የጂማ ዞን ወረዳዎች ፣ ከሆለታ ገነት በስተምእራብ ያለውን የምእራብ ሸዋ ዞንና የኢሊባቡር ዞኖችን ያካተተ፣ ዋና ከተማው ነቀምቴ ወይም መቱ የሆነ የምእራብ ኦሮሚያ ዞን

8. አርሲ፣ ምእራብ አርሲ፣ ባሌ፣ ምእራብ ሃረርጌ፣ የባቢሌ፣ የጉርሱም፣ የሜኤሶ ወረዳዎችና በሃረርና በድረዳዋ መካከል ያሉ ወረዳዎችን ሳያካትት፣ የምስራቅ ሃረርጌ ዞንን የጠቀለለ፣ ዋና ከተማው ጨርጨር ወይም አሰላ ወይም ጎባ የሆነ የምስራቅ ኦሮሚያ ክልል

9. የጋምቤላ ክልልን፣ የጂማ ከተማና በጂማ ከተማና በደብብ ክልል መካከል ያሉ የኦሮሚያ ወረዳዎችን፣ የከፊቾና የቤንቺ ማጂ ዞኖችን ያካተተ፣ ዋና ከተማው ጂማ የሆነ ከፋ የሚባል ክልል

10. የደቡብና የሰሜን ኦሞ ዞኖችን፣ የደራሼ፣ ቡርጂ፣ አማሮና ኮንሶ ወረዳዎችን ያጠቃለለ፣ ዋና ከተማው አርባ ምንጭ የሆነ ጎሙ ጎፋ የሚባል ክልል

11. የጉራጌ የስልጤ፣ የከንባታና ጥንባሮ፣ የየም፣ የሃዲያ ዞኖችን ያካተተ ፣ ዋና ከተማው ሆሳና ወይም ወልቂጤ የሆነ ደቡብ የሚባል ክልል

12. የሲዳማ፣ ጌዴዮ ዞኖችን ጨምሮ ከኦሮሚያ የጉጂና የቦረና ከሶማሌ ክልል የሊበን ዞኖች ያጠቃለለ ፣ ዋና ከተማው አዋሳ የሆነ የሲዳማ ክልል

13 – ወደ ሲዳማ የተጠቃለለውን የሊበን ዞን፣ ወደ ሃረርጌ የተጠቃለሉትን የባቢሌ፣ የጉርሱም፣ የሚኤሶና የሽንሌ ዞኖችን ሳያካትት፣ አሁን ያለውን የሶማሌ ክልል የያዘ ዋና ከተማ ጂጂጋ የሆነ ኦጋዴን የሚባል ክልል

14. ዋና ከተማ ሰመራ ሳይሆን ታሪካዊዋ የአፋር ከተማ አሳይታ የሆነባት አሁን ያለችው የአፋር ክልል

በሂደት፣ በሁለተኛ ደረጃ መሻሻል ያለባቸውን በመሻሻል አገሪቷ ሙሉ ለሙሉ ዘር ተኮር ከሆነ አወቃቀር እንድትወጣ ማድረግ ይቻላል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.