ለ24 አመት በትግራይ ድብቅ የምድር እስር ቤት ታስሮ የሚገኙት ሊቅ መምህር እንደስራቸው አግማሴ! (ጌታቸው ሺፈራው)

መምህር እንደስራቸው አግማሴ ይባላሉ። እውቅ የዜማ እና የቅኔ ምሁር ናቸው። በኢትዮጵያ ብቸኛዋ የድጓ ምስክር ቅድስት ቤተ ልሔም (ታች ጋይንት) ገብተው ድጓ አስመስከረው የድጓ መምህር ሆነው አገልግለዋል። በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ በደብረ ታቦር አሁን ድረስ የእንደስራቸው ዜማ እየተባለ በተክሌ ዝማሜ ውስጥ እንደሚገኝ ይገለፃል። የመምህር እንደስራቸው የተክሌ ዜማ በ9 ካሴት ቀርፆ ተቀምጧል።

ለ24 አመት በትግራይ ድብቅ የምድር እስር ቤት ታስሮ የሚገኙት ሊቅ መምህር እንደስራቸው አግማሴ!

ጎንደርም በነበሩበት ጊዜ የሐዋሪያ ጳውሎስ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ስራ አስኪያጅ፣የካህናት የታሪክ፣የሂሳብና የዜማ መምህር በመሆን ሰፊ አገልግሎት እንደሰጡ ታሪካቸው ያስረዳል። በዓለማዊውም ሥራቸው ደግሞ የኪ.ቤ.አ.ድ/የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት/ ዋና የአስተዳዳር ክፍል ሆነው አገልግለዋል፡፡

በሐምሌ 12/ 1986ዓ/ም 11፡35 አካባቢ ሲሰሩበት ከነበረው ኪቢአድ ቢሮ ከስራ ቆይተው ሲመለሱ የሻዕቢና የህወሓት ደሕንነቶች እንደሆኑ በተነገረላቸውና በትግርኛ ተናጋሪ ታጣቂዎች ታፍነው ተወሰዱ፡፡ህወሓት በወቅቱ ከእርሳቸው ጋር ሌሎች የታፈኑ ሰዎች የነበሩ ሲሆን በበጎንደር ራስ ግንብ ተብሎ ከሚጠራበት ቦታ ስር በሚገኘው ማሰቃያ ቦታ ከሌሎች ታሳሪዎች ጋር ስቃይ ተፈፅሞባቸዋል። በእስር ቤት የገጠማቸውን በአንድ ወቅት ለቤተሰቦቻቸው በሚስጥር በወጣ ደብዳቤ አሳውቀዋል።

እኚህ ሊቅ የታሰሩበት ምክንያትም ‹‹በወቅቱ የቆሰለ የደርግ አመራር አሳክመሃል ›› የሚል እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ መምህሩ ‹‹ ታዲያ ማሳከም ምንድነው ጥፋቱ? ሰው ካጠፋ ለምን በሕግ አይጠየቅም?›› ብለው ቢከራከሩም ይህ ህጋዊ ክርክር ምድር ቤት ከሚገኝ ጨለማ ክፍል ከመታሰር ብሎም ለ24 አመት ደብዛቸው ከመጥፋት አላዳናቸውም።

እምነትን እንደመሳርያ የሚጠቀሙት ገዥዎቹ በወቅቱ ‹‹ሥልጣን እንስጥህ፣ ህዝቡም ካህናቱም ይቀበሉኋል›› የሚል መደለያ ቢቀርብላቸውም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። እንዲያውም መምህሩ ‹‹ኢትዮጵያን ለሚከፋፍል ቡድን ህብረት የለኝም፣ብትፈልጉ ግደሉኝ› የሚል አቋም በመያዛቸው ብዙ ስቃይ እንደተፈፀመባቸው ቤተሰቦቻቸው ይገልፃሉ

የሚያውቋቸው የእስር ቤቱ ሰዎች ማታ ማታ የታሰሩበትን ሰንሰለት እያላሉላቸው ለቤተሰብም በሚስጥር መረጃ ማድረስ ችለው ስለነበር ከታሰሩት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ሲገደሉ፣ ተራው መምህሩ ጋር ሲደርስ እንደቆመ ለቤተሰቦቻቸው አሳውቀው ነበር።

በወቅቱም ባለቤታቸውና ልጃቸው ለማስፈታት ጥረትም ቢያደርጉ ሳይሳካላቸው እንደቀረ ይነገራል። ጎንደር የሚገኝ ድብቅ እስር ቤት ውስጥ የተወሰነ እንደታሰሩ ለቤተሰብ የሚደርሰው መልዕክት ተቋረጠ። ከዛ ጊዜ በኋላ የት እንደገቡም ማወቅ አልተቻለም። ቤተሰቦቹ ባገኙት አጋጣሚ ጉዳዩን ቢያሳውቁም የሚሰማቸው የመንግስት አካል አላገኙም።

ሆኖም መምህሩ የት እንደገቡ ሳይታወቁ 24 አመት ካለፋቸው በኋላ በ2010 ዓም መጀመርያ ትግራይ ውስጥ የሚገኝ ድብቅ እስር ቤት ውስጥ በህይወት እንዳሉ ለቤተሰቦቻቸው መረጃ ደርሷቸዋል።

የመምህር እንደስራቸው ቤተሰቦች፣ በመምህርነትና ሊቅነታቸው የሚያውቋቸው ባለፉት 24 አመታት ጥያቄ ቢያቀርቡም የሚሰማቸው አካል አላገኙም። በቅርቡ መምህሩ በህይወት መኖራቸው ሲሰማም ጥያቄያቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ጎንደር በሄዱበት ወቅት የመምህር እንደስራቸው ቤተሰቦች ጥያቄ ለማቅረብ ፍላጎት የነበራቸው ሲሆን አጋጣሚውን ሳያገኙ ቀርተዋል።

መምህር እንደስራቸው ባለፉት 26 አመታት ስለ እውነት ስለቆሙ ብቻ ደብዛቸው ለጠፋው ንፁሃን ማሳያ፣ ለገዥዎቹ ወደር የለሽ ኢሰብአዊነት ደግሞ ምስክር ነው።

*****************
ታላቁ የደብረ ታቦር ሊቅ የክብር ሊቅ መምህር እንደስራቸው ንቦችን በዜማው ያወረደ በህውኃት ቡድን ከታፈነ 24 ዓመታት ተቆጠሩ፣ ግን አልሞተም።

የክብር ሊቅ መምህር እንደስራቸው አግማሴ መኮነን አጭር የህይወት ታሪክ

ከአባታቸው ከአቶ አግማሴ መኮነን ከእናታቸው ወ/ሮ ሙሉነሽ አይናለም በ1939 ዓ/ም ሚያዚያ 23 ቀን በደብረ ታቦር ልዩ ስሙ “ሰላምኮ” በተባለ ቦታ ተወለዱ። በዚህም ተነሳ አምኃ ጊዮርጊስ ተባሉ።

በእናት እና አባታቸው በዘመድ አዝማድ በጣም ብርቅና ድንቅ የሆኑ ልጅ ነበሩ። እኒህ ሙሁር ዕድሚያቸው ለትምህርት ሲደርስ በአካባቢያቸው ከነበሩ መምህር አባ ባያፈርስ ከመርሻ ዓለሙ ጋር በፊደል እስከ ፆመ ድጓ ተምረዋል። ከዛ በመቀጠል። ክብሩ ሊቅ መምህር እንደስራቸው አግማሴ ፀዋትዎ ዜማ ከአለቃ መሃተም ጌጠየ ተምረዋል፤ ቅኔ ወረታ አካባቢ ከሚገኙት መሪጌታ ጌቴ ተምረዋል። አሁንም ሁለተኛ ቅኔ ከመምህር ጥበቡ ተምረዋል። የተክሌ አቋቋም ከአለቃ ማህተም ጌጤ ተምረዋል። ይህን ካወቁ በኋላ እንደ ገና ድጓ ቤት አዛወር ኪዳነ ምህረት አዋቂ ከሆኑት ትልቅ መምህርት ከመሪጌታ ጀንበር ገብተው ካወቁ በኋላ እንደገና አሁንም ከታች ጋይንት ወረዳ በኢትዮጵያ ብቸኛዋ የድጓ ምስክር ቅድስት ቤተ ልሔም ገብተው የድጓ ምስክራቸውን በምህርት ጥበቡ አስመስከረው የድጓ መምህር ሁነዋል።

እኒህ ሊቅ መምህርት እንደስራቸው ድጓን አስመስክረው ከተመረቁ በኋላ እንደገና በደብረ ታቦር ኢየሱስ የተክሌ አቋቋም ምስክር ከሆኑት ከአለቃ ቀለመ ወርቅ ይማም ጥሩ አድርገው ተምረው አስመስክረዋል። መምህር እንደስራቸው ቃለ እግዚአብሔርን በማህሌት በሚዘምሩበት ጊዜ ከልሳናቸው ጣፋጭነት የተነሳ የሰማዩን ልቡና ይማርኩ ነበር።

በቅድሰት ቤተልሔም በአቢይ ጾም ዝማሜ ይሰጥ የነበረው ለመምህር እንደስራቸው ነበር። መምህር እንደስራቸው ደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ፀሎተ ሃይማኖትን በዝማሜ በሚዘምሩበት ጊዜ ንብ ከእጃቸው ላይ ያርፍባቸው ነበር። ወደ ጎንደርም ከመጡ በኋላ በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ለማንም የማይሰጠው የተክሌ ዝማሜ ለመምህር እንደስራቸው ይሰጥ ነበር። ጎንደርም በነበሩበት ጊዜ የሐዋሪያ ጳውሎስ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ስራ አስኪያጅ፣የካህናት የታሪክ፣የሂሳብና የዜማ መምህር በመሆን ሰፊ አገልግሎት ፈጽመዋል። በዓለማዊውም ሥራቸው ደግሞ የኪ.ቤ.አ.ድ/የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት/ ዋና የአስተዳዳር ክፍል ሆነው አገልግለዋል።

እኒህ በምዕመኑ እንደተናፈቁ በጳጳሳቱ፤ በሊቃውንቱ፣ በካህናቱ እንደ ተደነቁ እንቆቅልሽ ሁነው ጠፉ። አንዳንዶቹ መነነዋል ይላሉ። አንዳንዶቹ፣ ተሰውረዋል ይላሉ፣ አንዳንዶቹ ሙተዋል ይላሉ። ምስጢሩ ግን ከቤተሰቦቹ አለ።

መምህር ዘመድኩን በሐምሌ 12 1986 ዓ/ም ሲሰራበት ከነበረው ኪቢአድ ቢሮ ከስራ ቆይቶ ሲመለስ ትግረኛ ተናጋሪ በመሆኑ የህወሃት /ኢህአዴግ/ ተላላኪዎች በመኪና ታፍኖ ተወሰደ። በወቅቱ ከእርሱ ጋር ሌሎች የታፈኑ ሰዎች የነበሩ ሲሆን በጎንደር ራስ ግንበ ተብሎ ከሚጠራበት ቦታ ስር በሚገኘው ማሰቃያ ቦታ ከሌሎች ታሳሪዎች ጋር እንዲሰቃይ ተፈረደበት።የታሰረበት ምክንያት ምን እንደሆነ ሲጠየቅ “በወቅቱ የቆሰለ የደርግ አመራር አሳክመሃል” የሚል ምላሽ ተሰጠው። እርሱም “ታዲያ ማሳከም ምንድነው ጥፋቱ፤ ሰው ካጠፋ ለምን በሕግ አይጠየቅም” በማለት ምላሽ ሰጠ። የህወሃት መሪዎችም “ሥልጣን እንስጥህ፣ ህዝቡም ካህናቱም ይቀበሉኋል” በማለት ድለላ ቀረበለት። እርሱም “ኢትዮጵያን ለሚከፋፍል ቡድን ህብረት የለኝም፣ ብትፈልጉ ግደሉኝ አለ።” እነርሱም ብዙ ስቃይ አበዙበት።ከሦስት ቀናት በኋላ ቤተሰቦቹ ጭንቀት ውስጥ ስለወደቁ “የእስር ቤቱ ጠባቂ ያውቀው ስለነበር፣ ማታ ማታ የታሰረበትን ሰንሰለት እያላላለት፤ በቋራጣ ወረቀት መታሰሩንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንደተገደሉ፣ ከእርሱ ላይ ሲደርስ ግድያ አቁሙ የሚል ትዕዛዝ መድረሱን ፣ጠቅሶ መልዕክት በእስር ቤት ጠባቂው በኩል ላከ። በወቅቱም ባለቤታቸውና ትልቅ ልጁ ለማስፈታት ጥረትም ቢያደርጉ የሚሰማቸው አካል አጡ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የት እንደተውሰደ ሳይታወቅ እንቆቅልሽ ሆኖ ቀረ።

አምኃ ጊዮርጊስ ዛሬም በህውኃት ድብቅ እስር ቤቶች አለ። አንዳንዶቹም ኤርትራ፣ ትግራይና በሌሎችም አስር ቤቶች ዜማ የሚጮኸ ሰው እንሰማለን እያሉ በየጊዜው ለቤተሰቦቹ መልዕክት ይናገራሉ። እርሱ አልሞተም፣ አለ። ከእርሱ ጋር የታሰሩ እና የተገደሉ በሙሉ ለቤተሰቦታቸው አስከሬናቸውን እንዲወስዱ ተነግሯቸዋል። እርሱ ግን አልተገደለም። ለቤተሰቦቹም ምንም አልተባለም። ይህም ጉዳይ በወቅቱ በጋዜጣ ወጥቷል።

መምህር እንደስራቸው

በደብረ ታቦር አሁን ድረስ የእንደስራቸው ዜማ እየተባለ በተክሌ ዝማሜ ውስጥ ይገኛል። ለዚህም አሁን በቦታው ያሉት መምህር ምስክር ናቸው።

መቋሚያ ይዞ ሲዘም እንኳን ሰውን ንቦችንም ይመስጣል። ድምጹ ልዩ ነው። መቋሚያ አጣጣሉ ልዩ ነው። ከበሮ አመታቱ ልዩ ነው።
መምህር እንደስራቸው የተክሌ አቋቋሙ ዜማ ከጊዜ በኋላ ቢጠፋ ወይም እኔ አንድ ነገር ብሆን ብለው 9 ካሴት የሚሆን ዝማሜ በካሴት ቀርጸው አስቀምጠዋል።

ስለ መምህር እንደስራቸው

– ብፁዕ አቡነ እንድርያስ የሊቃውንት ጉባዔ ሰብሳቢ/በወቅቱ ጓደኛ የነበሩ/
– ብጹዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
– አቡነ መርቆሪዎስ የቀድሞው የጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አሁን አሜሪካ የሚገኙት
– ክብር ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኮነን የጎንደር መ/መ/መድኃኔዓለም የአራቱ ጉባዔ መምህር የነበሩት አሁን በህይወተ ሥጋ የሌሉት
– ክቡሩ ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሐዲስ የጎንደር መ/መ/መድኃኔዓለም የአራቱ ጉባዔ መምህር
– መላከ ታቦር ኃይለ ኢየሱስ የደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪና በጎንደር የመገኙ ታላላቅ ሊቃውንት ስለ መምምህር እንደስራቸው ቢያነሱም አይጠግቡም፣ ያለቅሳሉ፣ ያነባሉ፣ ይቆጫሉ። ህውኃት ኦርቶዶክስን የማጥፋት አንዱ ዘዴ ብርቅየ ሊቃውንትን በዚህ መንገድ ድምጻቸውን በማጥፋት ተስፋ ለማስቆረጥ መጣሩ ነው።

በነገራችን ላይ ማህበረ ቅዱሳን ደብረ ታቦር ኢየሱስ ላይ የሆነ ጊዜ በነበረው የቴሌቪዝን መርሐ ግብር የመምህር እንደስራቸው ሥም ከዜማ ጋር ተያይዞ በሰፊው ይነሳ ነበር።

ህወሃት/ኢህአዴግ የቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ሊቅ የነበሩትን አፍኖ ድምጻቸውን አጥፍቷል። ግን በእስር ቤቱ ውስጥ አለ። እርሱም ገና ሳይታሰር፤ “እታሰራለው ግን አልሞትም” ይል ነበር። መምህር ዘመድኩን ዛሬ ያንተን ገጽ አይቸ ይህንን ጽሁፍ የላኩልህ ሁሉም የተዋህዶ ልጅ ይህንን መምህር ካለበት እንዲጠቁም፣ ፍትህም አግኝቶ የቤተ ክርስቲያኗ ብርሃን እንዲመለስ ነው። ይህን ጉዳይ ሊቃውንት አያውቁም፣ ህዝቡም አያውቅም ሁሉም በያለበት ይፈልገው። የእርሱ መመለስ በርካታ በቤተ ክርስቲያናቸውን የአብነት ትምህርት እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ለውጥ ይመጣል። ሊቃውንቱም የናፈቁትን ዝማሬ እንዲያገኙት ሁሉም በየፊናው እንዲተባበር፣እስር ቤት ካለ ፣የሚያውቀው ካለ ሁሉም በየፊናው እንዲረባረብ በማሰብ ነው።

ቤተ አማራ

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.