የአማራ ብሄርተኝነትን በጨረፍታ (የሱፍ ኢብራሂም)

የኢትዩጵያ ፖለቲካ ድባብ ቅርፅ ይዞ መዉጣት የሚገባዉ ነዉ፡፡ የሀገሪቱም ህልዉና በመስቀለኛ መንገድ ላይ ነዉ (It is at the cross-roads)፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ልቅ የሆነ የመብት ጥሰት ስላለ ብቻ አይደለም፡፡ በመሰረቱ እዚህና እዚያ አመጽ ስለተነሳም አይደለም!! እዉነታዉ በጥሩም ይሁን በመጥፎ፤ በራሱ ልጆችም ይሁን ከአማራ ዉጭ ባሉ ግለሰቦች የሀገሪቱ ባለቤት ተደርጎ ይወሰድ የነበረዉ የአማራ ሕዝብ አድስ የሆነ በራሱ ማንነት ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ በመጀመሩ ነዉ፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ከገዥዉ ፓርቲ፤ ከደጋፊዎቹ አንዳንድ ጊዜም የአማራ ተወላጆች ከሆኑ ሰዎች ጭምር የተለያዩ ግንዛቤዎች ተወስደዉበታል፤ የተለያዩ ትርጉሞች ተሰጥቶታል፡፡

የአማራ ሕዝብ በማንነቱ ላይ ተመስርቶ እያደረገ ያለዉ እንቅስቃሴ ቀደም ሲል በአብዛኛዉ በሕዝቡ በራሱ እንደጠባብነትና ሲብስ ደግሞ እንደዘረኝነት ተደርጎ ይወሰድ ነበር፡፡ እንደኢትዩያዊ ብቻ ማሰብና መንቀሳቀስ በሌሎች ህዝቦችና በተለይም በገዥዉ ፓርቲና ደጋፊዎቹ በአድስ መልክ ለተመሰረተዉ የፌደራል ስርአት አስጊና አንዳንድ ጊዜም ትምክተኛና የድሮ ስርአትን በመናፈቅ ዳግም እንዲመለስ ለማድረግ እንቅስቃሴ እንደማድረግ ተደርጎ ይወሰድ ነበር፡፡ እኩይ ፖለቲከኞች በዚህ ረገድ የሀገሪቱ ታሪክ ከአለም ታሪክ የተለየ እንደሆነ አድርገዉ በማቅረብ እና ለዚህም አማራን ተጠያቂ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ ሰርተዋል፡፡ ነገር ግን እዉነታዉ የአለም ታሪክ በዚህ ረገድ ተመሳሳይ መሆኑ ነዉ፡፡ (Rainer Bauböck for instance states that with the possible exception of Switzerland, historic nation-building projects have started out from a particular cultural tradition and territorial heartland that formed the core of an expanding national identity)

ስለሆነም በሌሎች ቡድኖች የነበረዉ (የተደበቀዉ ፍላጎት ይህ እንዳይሆንና አማራ ራሱን የሳተ ሆኖ በሞግዚት ስር እንዲሆን ነዉ) የአማራ ሕዝብ በሀገሪቱ እንዳሉት ወቅታዊ ብሄር ተኮር የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ሁሉ የራሱን ብሄር መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ነበር፡፡ ታድያ የአማራ ሕዝብ አሁን ለረጅም ጊዜ ሲፈለግ የነበረዉን የብሄር ተኮር የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ ሲጀምር ለምን እያየን ያለነዉን ግብረመልስ ማየት ጀመርን? ለዚህ ጥያቄ መልስ ናቸዉ በሚል በርካታ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡-

1// የገዥዉ ፓርቲና የደጋፊዎቹን በተመለከተ የአማራ ህዝብ እንቅስቃሴ በተለመደዉ መልኩ የገዥዉ ፓርቲ በሚፈልገዉና በሚሰጠዉ ይሁንታ፤ ነጻ ባልሆነ መልኩ የትእዛዝ ተቀባይ ሆኖ በተቀየሰዉ የፖለቲካ ስርአት ዉስጥ እንዲከናወን ስለሚፈለግና የአሁኑ እንቅስቃሴ ደግሞ የአማራ ህዝብ ባለቤት ራሱ አማራዉ ብቻ ነዉ የሚል በመሆኑ!

2 // አሁን ያለዉ የአማራ ህዝብ እይታ፣

ይህ እይታ ዋናዉና ሰፋ ያለዉ ሲሆን በርካታ እይታዎችን በስሩ አካትቶ የያዘ ነዉ፡፡ የአማራ ህዝብ እንቅስቃሴ ህዝቡ “እንደኢትዮጵያዊ ብቻ እናስብ” በሚል ለረጅም ጊዜ ይዞት የቆየዉ ሀሳብ በዋናነት ህዝቡን ተስፋፊና የፊደራል ስርአቱ ጠንቅ ነዉ ስላሰኘዉ እንዲሁም ህዝቡ በጥልቀት ስላልተደራጀና ለስም ያክል እንጂ ባለቤት አልባ ስለሆነ ተገቢዉን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅም እንዳያገኝ ከመደረጉም በላይ በንብረቱና በሕይወቱ ላይ በርካታ ጥቃቶችን እና ጥፋቶችን አስተናግዷል፡፡ ይባስ ብሎ የአማራ ሕዝብ ተወላጆች ይኖሩባቸዉ ከነበሩት የሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች በጅምላ ጥቃት ምክንያት ለስደት ተዳርገዋል (ይህ አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል)፡፡ የአማራ ሕዝብ የራሱ ክልልም ጭምር በየአቅጣጫዉ እየጠበበ የሄደና ህዝቡም በሌሎች አዳድስ ሰፋሪዎች እየተተካ ይገኛል፡፡

የአማራ ህዝብ እንቅስቃሴና አደረጃጀት በዉለታ ቢሶች ድርጊት ምክንያት ተገፍቶ የወሰደዉ የመጨረሻ አማራጭ ሲሆን የዚህ እንቅስቃሴ ተቃዋሚዎች ህዝቡን በቀጣይ ለማሳነስ እና ለማጥቃት ያቀናበሩትን እቅድ የሚያከሽፍ ብቸኛዉ መስመር ስለሆነ ነዉ፤ ከዚህም ባለፈ የአማራ ህዝብ ቀድሞ ለደረሱበት ግድያዎችና ጥቃቶች የማስተካከል ብሎም የካሳ ጥያቄ ያቀርባል የሚል ስጋትም ይኖራል፡፡ በዚህ ረገድ የአሁኑ የአማራ ሕዝብ እንቅስቃሴ እንደሚያመላክተዉ ያለዉን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነባራዊ ሁኔታ የማይቀበል ሲሆን በተለይም አገዛዙን ከሚዘዉሩት ጋር ባለዉ የኢኮኖሚ፤የፍትሕና የድንበር ጉዳዮች ላይ የጸና ጥያቄ ያነሳ በመሆኑ ኢፍትሐዊነትን ለማስቀጠል ፍላጎቱ ያላቸዉ ሰዎች የሚቀበሉት አይደለም፡፡ ለዚህም ማደናገሪያ ይሆናቸዉ ዘንድ የሕግና የፖለቲካ ድስኩሮችን እያቀረቡ የሚገኙ ሲሆን በተጨማሪ የፖሊስም ይሁን የወታደራዊ ርምጃወችን ሊወስዱ እንደሚችሉ ይጠበቃል(ይህ ጨርሶ የተነሳ ፍላጎት ነዉ ባይባልም አፀፋዉ ከባድ ሊሆን ይችላል የሚል አንድምታ በመፈጠሩ ራቁት የወጣ ጅምላ ጥቃት እየቀነሰ ሄዷል) ፡፡ የዚህም ዝግጂት አንዱ የሆነዉ ይሄን የአማራ ህዝብ እንቅስቃሴ የሀሳብ ዳርቻ በሌለዉና የማደናገሪያና የመኮነኛ መስመር ላይ በማስቀመጥ የኩነኔና የዳቦ ስም እየሰጡት ይገኛሉ፡፡

በተጨማሪ የአማራ ሕዝብ በታሪክ፤ በጅኦግራፊ፤ በኢኮኖሚና በሰብአዊ ሀብት አኳያ ካለዉ ግንባር ቀደምነት አንጻር የአሁኑ ወቅታዊ የብሄርተኝነት እንቅስቃሴ ከፍተኛ የሆነ ድርሻ ለመጠየቅ በማሰበ የተጠነሰሰ ነዉ የሚሉም አሉ። ይህ እዉነት አይደለም ምክንያቱም የአማራ ህዝብ ንብረቱንና ዉድ ሕይቱን ለዘመናት በመገበር ለሀገሩ ሉአላዊነትና ነጻነት ሲታገል የኖረ ሲሆን ከነጻነት በተጻራሪ ለመቆም የሚያነሳሳዉ ታሪካዊ ዳራ የለም፤፤ እንቅስቃሴዉ የአማራ ህዝብ ታሪክ፤ማንነት፤ዉለታ፤አስተዋጽኦ፤ግዛት(ይዞታ)፤ንብረት፤ህይወትና ክብር እዉቅና ሊሰጠዉ ይገባል፤ ማንነቱን መሰረት ያደረገ ጥቃት ሊደርስበት አይገባም፤ ፍትሕና እኩልነት በሀገሪቱ ሊሰፍኑ ይገባል የሚል ሲሆን ነገር ግን ያልተገባ ድርሻን ለሚጠይቁና ኢፍትሐዊነት እንዲቀጥል ለሚሹ ወገኖች ቦታቸዉን እናጣለን በሚል ስጋት የተለየ ስም እየሰጡት ይገኛሉ፡፡

3// አማራና ኢትዮጵያ

አንዳንዶች ደግሞ በቅን ልቦና ሌሎች ደግሞ በክፉ ልቦና ብሎም ሆነ ብለዉ ለማምታታት በማሰብ አማራ እንደኢትዮጵያዊ ብቻ የሚያስብ ብቸኛ ህዝብ እንደመሆኑ መጠን ከዚያ ባነሰ መልኩ በአማራነት የሚያደርገዉ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያዊነት የመጨረሻ ጥፋት አድርገዉ ይወስዱታል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያዊነትን መሰረት አድርገዉ የፖለቲካ አቋማቸዉን ያንጸባርቁ ለነበሩ ግለሰቦችና የፖለቲካ ስብስቦች የአቋማቸዉ የመጨረሻ እስትንፋስ የሆነዉ መሰረታቸዉ እንደተናደ ይቆጥሩታል፡፡ የቅን ልቦና ተከራካሪዎች ሀሳብ ግልጽ ሲሆን በዚህ ረገድ የክፉ ልቦና ተከራካሪዎች የምንላቸዉ በመርህ ደረጃ የአማራን ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል አቋም ትምክተኝነት፤ የዱሮ ስርአት ናፋቂነት በማለት ሲያንቋሽሹት የነበሩ ሆነዉ ሕዝቡ ደግሞ የራሱን ብሄር መሰረት አድርጎ ሲደራጅ ኢትዩጵያዊነት አለቀለት በማለት ለፍጆታና ለማደናገር ሀሳብ የሚሰነዝሩት ናቸዉ፡፡

4// የጽንሰ-ሀሳብ ትንታኔዎች (Theoretical viewpoints)

በጽንሰሀሳብ ረገድ ደግሞ በዋናነት የሚነሱት የቆዩና አሁንም ያሉ ሀሳቦች ሲሆኑ የብሔር ተኮር ፖለቲካን አንድምታ መሰረት ያደረጉ ናቸዉ፡፡ በዚህ ረገድ የብሄር ፖለቲካ ከፋፋይ ነዉ፤ ለፖለቲካ ድርድርና ለሀገር ግንባታ አይመችም፤ ግጭቶች እ ዲፈጠሩ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፤ የደሞክራሲና የሰብአዊ መብት እሴቶችን ያፋልሳል፤ ፍትሕን ያስተጓጉላል፤ እንድሁም ማንነት ራሱ ቋሚ አይደለም (It is fluid) ፤ ብሔር ተኮር አደረጃጀት ግለሰቦች የተለየ ጥቅም ለማግኘት የሚመሰርቱት ነዉ (To gain access to resources- the instrumentalist view)፤ የብሄር ጥያቄዎች በመደብ ትግል አብረዉ መልስ ያገኛሉ(The Class struggle thesis) የሚሉት ይገኙበታል፡፡

መሰረታዊዉ የጽንሰሀሳብ ክርክር የሚጀምረዉ ብሄር ተኮር ፖለቲካን የቡድን መብት መሰረት ያደረገ ስለሆነና ቡድን ማለት ደግሞ የግለሰቦች ድምር ስለሆነ የግለሰብን መብት መሰረት ያደረገ የሕግና የፖለቲካ አቋም ተመራጭ ነዉ ከሚል መነሻ ነዉ፡፡

በመሰረቱ ከላይ የቀረቡት ክርክሮች አለምአቀፋዊ አንድምታ ያላቸዉ ቢሆንም በኢትዮጵያ ዉስጥም በተለይ በ1960ዎቹ በነበሩት የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ወቅት በሰፊዉ ተነስተዉ እንደነበር እንገነዘባለን፡፡

ይህ ጉዳይ በሰፊዉ ሊቃኝ የሚገባዉ ሲሆን ከላይ በተለያየ አግባብ ለቀረቡት ጉዳዬች እንቅስቃሴዉን የሚደግፉት የራሳቸዉ የሆኑ ተጓዳኝ መልስ አላቸዉ፡፡ በዋናነት ግን የሚከተሉትን ነጥቦች ያነሳሉ፡-(አጠቃላይ አንድምታ ያላቸዉ ቢሆንም ከአማራ ህዝብ አኳያ ያለዉን ነጥለን እንይ!-ምናልባት በፅንሰሀሳቦቹ ላይ ሌላ ጊዜ እንደአግባቡ እንመለሳለን!)

የአማራ ሕዝብ በአግባቡ ባለመደራጀቱ ምክንያት በተወላጆቹ ላይ በርካታ የታቀዱ የሞት፤ የንብረት መዉደም፤ የመሰደድና የጥላቻ ድርጊቶች ተፈጽመዉበታል፡፡ ስለዚህ ጥቃቶችን እንደት ይከላከል? መብቶቹን እንደት ያስከብር? በእኩልነት እንደት በሀገሩ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ግንባታ ይሳተፍ? ህጋዊዉንና ተገቢ የሆነዉን ጥቅም እንደት ያስከብር? ለሚሉት አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልሱ የራሱን ብሄር መሰረት አድርጎ መደራጀትና መንቀሳቀስ ብቻ ነዉ፡፡

አማራነት የለም ብለዉ ለሚከራከሩ ግለሰቦች መልሱ እስኪ ሌላ ብሄር ያለዉ የማንነት መገለጫ በአማራ ሕዝብ ዉስጥ የሌለ አንድ እንኳን ጥቀሱ ቢባሉ ሌጣ የሆነ ሀሳባቸዉን መከላከል አይችሉም( ይሄን በተመለከተ ባለፉት አመታት በእኩይነት ከቀረቡ የክህደትና የፉከራ ወሬዎች ባለፈ ለአእምሮ ቅርብ የሆነ አመክንዬ ማየት አልቻልንም)፡፡ የአማራ ሕዝብ ማናቸዉም ኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉ “ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች” ራሳቸዉን ሊያደራጁ የሚችሉባቸዉን የማንነት መለኪያዎች ባለፈና በተትረፈረፈ መልኩ ያሟላ ሕዝብ ነዉ!!!

ምናልባት አማራነት ኢትዮጵያዊነት ነዉ ለሚሉት ደግሞ ይህ ሀሳባቸዉ በግማሽ ብቻ ነዉ እዉነት ሊሆን የሚችለዉ፡፡ በእርግጥ የአማራ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ነዉ፤ የኢትዮጵያም ባለዉለታ ነዉ፡፡ እኩልነት ይኑር ነዉ ዋናዉ ጥያቄ፡፡ ዘራፍ፣ አፍራሽና ያላዋቂ ትርክቶችና ጥቃቶች ይቁሙ ነዉ። ስለዚህ የአማራ ህዝብ እንቅስቃሴ በይዘቱ አገራዊም ነዉ፡፡ አሁን ያለዉ ብቸኛ ልዩነት በዋናነት ብሄር ተኮር ነጻ አደረጃጀትን በመመስረት ጭቆናንና ግፍን መቋቋም አለብን፤ አማራነትን ትተን ኢትዮጵያ ላይ መንጠልጠል በሁሉም ረገድ ዝቅተኛ ተጽእኖ ሊኖራቸዉ በሚችሉ ቡድኖች(ህዳጣን) ጭምር በአማራህዝብና በማንነቱ ላይ ለሚሰነዘሩ ጥቃቶች ተጋላጭ አድርጎታል፣ በቅን ልቦና ያራምደዉ የነበረዉ የፖለቲካ አመለካከት እንደድብቅ ተስፋፊነት (Nested Nationalism as a disguise) ተቆጥሮበታል፡፡ ስለሆነም የአሁኑ እንቅስቃሴ አማራጭ የለዉም!!!

የአማራ ህዝብ ልጆችም ማንነታቸዉን መሰረት ባደረገ መልኩ ለሚሰነዘርባቸዉ ጥቃት ከሌላዉ ልል ከሆነ አደረጃጀት ይልቅ በተሻለ መልኩ በቆራጥነት አንዱ ከሌላዉ ጎን ይሰለፋሉ (ርዳታን ያቀርባሉ፤ ጥቃትን ይከላከላሉ፤መልሶ የቋቋም ተግባራትን ይፈፅማሉ፤ ሀዘናቸዉን ይገልጻሉ፤ በወኔ ይከራከራሉ ወ.ዘ.ተ!)

በዋናነት በአማራነት ላይ የሚመሰረተዉ አደረጃጀት ነባራዊ የሆነዉንና በተለመደዉ መልኩ የሚፈጸሙትን በማንነት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶችና የመብት መተላለፎች እንዳይኖሩ ያስችላል (Deterrence Effect)፡፡ ይህ በቲዎሪ ብቻም ሳይሆን በርግጥም የተፈፀሙና እየተፈፀሙ ያሉ የአማራ ህዝብ የማበር ትዉፊቶች መሆናቸዉን እማኞች ነን፣ ናቸዉ!!!

ይህ ብሄር ተኮር አደረጃጀት በብሄረሰቡ በራሱ አባላት ዉስጥ ያሉትን የፖለቲካ፤ የሀይማኖት፤ ወ.ዘ.ተ ልዩነቶች የተሻገረ ይሆናል፡፡ በአማራነት ጠንክሮ በመደራጀት ኢትዮጵያን በተሻለ መንገድ መገንባት ይቻላል!!!

በመሰረቱ የአማራ ህዝብ እሳቤ ብቻ ከኢትዬጵያዊነት ተነስቶ ወደ አማራነት እንዲሆን ለምን ይፈለጋል? ምንስ ፋይዳ አለዉ? በማለት የዛሬዉን እንቋጨዉ፡፡

ለማጠቃለል ያክል የአማራ ብሄርተኝነት አሁን እንኳን እዚህ ላይ ደርሶ ይቅርና ገና “ሀ” ተብሎ የሚጀመር ቢሆን እንኳን ብቸኛዉና አዋጩ የአማራ ህዝብ መስመር ስለመሆኑ አንጠራጠርም። ይህ ስለመሆኑ ቅንጣት ታክል የሚጠራጠር ወይንም የማይቀበል ሰዉ ሊሆን የሚችለዉ:-

1/ በአማራ ህዝብ ላይ በማንነቱ መሰረት ታቅደዉ የሚደርሱበትን ጥቃቶች ፈፅሞ አያዉቃቸዉም፣ ለማወቅ ፍላጎቱም የለዉም፣ የቆየ ፖለቲካ ቀኖና አቀንቃኝ የሆነ ነወ።

2/ ጥቃቶቹን ቢያዉቃቸዉም ምንም ስሜት አይሰጡትም፣ ምናልባት የሌላ ብሄር ተወላጅና በራሱ አደረጃጀት ዉስጥ ያለና የአማራ የሆኑ የማይታዩት ነዉ።

3/ አማራና የአማራነት እሴቶችን የሚክድ፣ ያላዋቂ ተንታኝ የሆነና አማራ “የለም” ለማለት ጭምር የሚደፍር ነዉ።

4/ ከአማራ ህዝብ ይልቅ ለፍጆታ የተሰለፈበት የፖለቲካ አደረጃጀት መሰረት ሊናድ ይችላል ብሎ የሚሰጋ ነዉ።

5/ ከግፈኞች ጎራ ተሰልፎ ያለ፣አማራንና አማራነትን የማጥቃትና የማጥፋት ማኒፌስቶ አቀንቃኝ የሆነ ነዉ።

6/ ወደፊት ሊኖር ስለሚገባዉ የፌደራል ስርአት አግባብ ግንዛቤ የሌለዉ ነዉ።

7/ ከቡድን ይልቅ በግለሰብ መብቶች ላይ ያተኮረ ፍልስፍና ያለዉ፣ ሆኖም የፍልስፍናና የነባራዊ ዝርዝሮችን በተገቢዉ ክብደት መዉሰድ የማይፈልግ፣ ለምን ጉዳዩ የአማራ ሲሆን ልዩ እንደሚሆን ተጓዳኝ ልዩ ምክንያት የማያቀርብ ነዉ።

8/ አማራ አብቅቶለታል፣ ሊደራጅ አይችልም የሚል እምነት ኖሮት አሁን የአማራ ብሄርተኝነት ሲመጣ በድንጋጤ በመራድ የአማራ ልል ስሜትን በማቀንቀን ብሄርተኝነቱ እንዲከሽፍ የሚተጋ፣ የአማራ ብሄርተኝነት ከእኩልነትና ከፍትህ ጥያቄ ባለፈ “የካሳ ጥያቄ” ሊያቀርብ ይችላል በሚል ስጋት ያለበት ነዉ።

9/ ቀደም ሲል በሀገሪቱ የነበሩ ብሄርተኛ ድርጂቶች ህዝብን የሚፈርጁ፣ አፍራሽ አቋም ያላቸዉና አዉዳሚ ዉጤት ያስከተሉ መሆናቸዉን በማየት እንዳይደገም የሚሰጋ ነዉ።

በመጨረሻ:- ዝርዝሩ ያለቀለት ነዉ ማለት አይደለም፣ እናንተም ጨምሩበት(መቀነስም፣ ማዳበልም ይቻላል!)

ሆኖም የመጨረሻዉ መጨረሻ የሚሆነዉ ግን ለቅን ልቦና ባለቤቶች አላማችንን እና አቋማችንን በተመለከተ በቀጣይና በተከታታይ የምናስገነዝብ መሆናችንን እየገለፅን የአማራ ብሄርተኝነት ግን በነባራዊ፣ በታሪካዊ፣ በብሶት እና በህልዉና እንዲሁም በመርሆ ተኮር ምክንያቶች የአማራ ህዝብ የፍትህ፣ የእኩልነትና የመዳን ትግል ብቸኛዉ መስመር ነዉ እያልን ብሄርተኝነቱን ለማደናቀፍም ይሁን ለማክሸፍ መሞከር ኢፍትሀዊ ከመሆኑም በላይ እጂግ አደገኛ የሆነ ዉጤት እንደሚያስከትል ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል እንላለን!

በተለይ የአማራ ህዝብ “ኢትዮጵያዊነት” በሚል ሰፊ ስሌትና ስሪት ሲያደርገዉ የነበረዉ ትግል ደንጋራ ምላሾችን ብቻ ያተረፈለት ሲሆን ይሄም በሌሎች ህዝቦችና በተለይም በገዥዉ ፓርቲና በደጋፊዎቹ በኩል የአማራ ኢትዮጵያዊ ነኝ የማለት አንድምታ አሁን ላለዉ የፌደራል ስርአት አስጊና አንዳንድ ጊዜም ትምክተኛነትና የድሮ ስርአት ናፋቂነት ተደርጎ ሲነገርና ሲወሰድ ቆይቷል፡፡ ሆኖም በዋናነት ይህ አስተሳሰብ ተጨማሪ ጥቃቶችን ከመጋበዝ ባለፈ ለአማራ ህዝብ ይህ ነዉ የሚባል ለዉጥ ሊያመጣለት አልቻለም፡፡

ስለሆነም ከረጂም ጊዜ ቆይታ በኋላ አድሱ የአማራ ሕዝብ እንቅስቃሴ በአማራዊ እሳቤና አሰራር ጋር ተዋህዶ ተወለደ!!!

የአማራ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴ ዘረኛ ነዉ በማለት ሀሳብ የሚሰነዝሩት ሰዎች የተለያየ አጀንዳ ያላቸዉ ሲሆን በአብዛኛዉ ስም አዉጭዎቹ ራሳቸዉ ዘረኞች የሆኑና ዘረኝነታቸዉን ያለገደብ ለማስቀጠል የሚፈልጉ ናቸዉ፡፡ በነገራችን ላይ ዘረኝነትና ለማህበረሰብ እኩልነትና ፍትሕ መታገል የተለያዩ መሆናቸዉን ማወቅ ያስፈልጋል!!! ጥቃቱንና ማንነቱን እዉቅና ሳይሰጡ፤ እዉነተኛዉን ችግር የማደናገሪያ ቀለም በመቀባት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንደሆነ አድርገዉ በመሳል (caricature) በዚህ ላይ ቀስት እንድንወጥር ጥሪም ያቀርባሉ፡፡ ይሄ በአመክንዮ ትምህርት (stand up-knock down- the straw man fallacy) በሚባል የሚታወቀዉን የግንዛቤና ትንታኔ ስህተት ያለበትን አረዳድ መሰረት ያደረገ ነዉ፡፡

ነገር ግን እንደዚህ አይነት አቀራረብ የራሱ ተጽእኖ የለዉም ማለት አይደለም፡፡ በተለይ በግልቡ ለሚረዱ ሰዎች ተጽእኖዉ ከባድ ነዉ! በተለይ ተደጋግሞ ከመነገሩ አንጻር፤ አማራጭ የመረጃ ምንጮች በማይደርሱበት ጊዜና ቦታ የዚህ አይነት ገለጻ ተጽእኖ ሰለባ የሚሆኑ መኖራቸዉ አይቀርም፡፡ እንዳሉም እንገነዘባለን።

አሁን የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የሚያተኩረዉ የአማራ ህዝብ ታሪክ፤ ማንነት፤ዉለታ፤አስተዋጽኦ፤ግዛት(ይዞታ) ወይንም ድንበር ፤ንብረት፤ሕይወትና ክብር እዉቅና ሊሰጠዉ ይገባል፤ማንነቱን መሰረት ያደረገ ጥቃት ሊደርስበት አይገባም፤ ፍትሕና እኩልነት በሀገሪቱ ሊሰፍኑ ይገባል የሚል ስለሆነ በዚሁ አግባብ መፍትሔ በመስጠትና ከአፍራሽ ድርጊቶች በመቆጠብ (Positive and Negative obligations) ጥየቄዉን መፍታት አማራጭ የለዉም፡፡

ችግሩን መካድ፤ ሌላ የችግር መስዋእት ማቅረብ፤ ችግሬ ይህ ነዉ በማለት በግልፅ እየጠየቀና እየተንቀሳቀሰ ያለዉን የአማራ ሕዝብ ለማደናቀፍና ለማጥቃት መሞከር አድስ በሽታን ጊዜዉ ባለፈበት መድሀኒት ለመፈወስ እንደመሞከር የሚቆጠርና አደገኛ ዉጤትን የሚያስከትል ነዉ!!!

ይሄን ጉዳይ በተመለከተ አሁን በምንነጋገርበት ሰአት እንኳን እጂግ በርካታ የአማራ ልጆች በማንነታቸዉ ተለይተዉ እየተገደሉና እየተፈናቀሉ መሆኑን ልብ ይሏል!!!

የአማራ ብሄርተኝነት በዋናነት የህልዉና ጥሪ መልስ ነዉ!!!!
—–
ሰላም!!!

https://www.facebook.com/yesuf.ebrahim.1044/posts/150097925840729

የሱፍን ያግኙ [Contact Yesuf ] | Yesuf Ibrahim

“The plausible approach therefore should not be the building of a common identity at the larger level but the pursuit of common federal citizenship synthesized on the reflection of the asymmetric views of the diverse groups in the federal framework.”

(Yesuf Ebrahim(LLB, LLM):- “All Units of the federation have equal rights and power”s?) The issue of asymmetry under the Ethiopian Federalism, An emperical study!!!

May 9 2018

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.