ዳኛ የደበደቡት የወልዋሎ ክለብ ቡድን መሪ የዕድሜ ልክ እገዳ ተጣለባቸው

BBN news May 12, 2018

የወልዋሎ አዲራት ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ ክለብ ቡድን መሪ የዕድሜ ልክ እገዳ ተጣለባቸው፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ስታዲዬም ወልዋሎ የተባለው የትግራይ ክለብ እና መከላከያ ግጥሚያ ባካሄዱበት ወቅት፤ አቶ ማሩ ገብረጻዲቅ የተባሉት የቡድኑ መሪ፣ በመሐል ዳኛው ላይ ከፍተኛ ድብደባ መፈጸማቸው ይታወሳል፡፡ በዕለቱ በመከላከያ እና ወልዋሎ እግር ኳስ ክለቦች መካከል የተደረገውን የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የመሩት የመሐል ዳኛ ኢያሱ ፈንቴ ነበሩ፡፡ በጨዋታው 84ኛ ደቂቃ ላይ የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ሁለተኛ ጎል ማስቆጠሩን ተከትሎ፤ የወልዋሎ ቡድን መሪ አቶ ማሩ ገብረጻዲቅ፣ ጎሉን ያጸደቁትን የመሐል ዳኛ እያሳደዱ መደብደባቸው አይዘነጋም፡፡ ‹‹ኳሱ መስመር አላለፈም›› በማለት ለዱላ የተጋበዙት የትግራይ እግር ኳስ ክለብ ቡድን መሪ፤ ዳኛውን በማሳደድ በቦክስ ሲያጣድፉት የሚያሳይ የቪድዮ ማስረጃ ወጥቶ፣ ብዙዎች ድርጊቱን ሲያወግዙት ቆይተዋል፡፡

የተፈጸመውን ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደለው ድርጊት ሲመረምር እንደቆየ የገለጸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን ኮሚቴ ትላንት በሰጠው መግለጫ፤ ዳኛ ደብዳቢው የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እግር ቡድን መሪ አቶ ማሩ ገብረጻዲቅ፣ ከማንኛውም የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ወይም ውድድር ዕድሜ ልክ እንዲታገዱ ማድረጉን ይፋ አድርጓል፡፡ ቡድን መሪው ዳኛውን ሲደበድቡ ከማገላገል ይልቅ፣ አበጀህ በሚል ስሜት ቆመው ሲመለከቱ የነበሩ ሰባት የወልዋሎ ተጫዋቾች ላይም የዲሲፕሊን እርምጃ መወሰዱን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ እንደ ፌዴሬሽኑ ገለጻ፤ በረከት አማረ፣ አለምነህ ግርማ፣ አስሪ አልማህዲ፣ ማናዬ ፋንቱ፣ በረከት ተሰማ እና አፈወርቅ ኃይሉ የተባሉት የክለቡ ተጫዋቾች ለስድስት ወራት ከጫወታ እንዲታገዱ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

በተጨማሪም እያንዳንዳቸው በነፍስ ወከፍ የአስር ሺህ ብር ቅጣት የተጣለባቸው ሲሆን፤ ዳኛው ሲደበደቡ ከማገዝ ያልተናነሰ ትብብር አድርጓል የተባለው እና ዋለልኝ ገብሬ የተባለው የወልዋሎ ተጫዋች በበኩሉ የ15 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እና የሁለት ዓመት እገዳ ተጥሎበታል ተብሏል፡፡ በተጨማሪም ክለቡ የ250 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት የተጣለበት ሲሆን፤ በዕለቱ የተደረገውን ጨዋታም በፎርፌ እንዲሸነፍ መወሰኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ አስታውቋል፡፡ የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ቡድን መሪ በዳኛ ላይ ድብደባ ከፈጸሙ በኋላ፣ የኢትዮጵያ ዳኞች እና ታዛቢዎች ማኅበር፣ ማንኛውንም ጨዋታ ላለመዳኘት ወስኖ ነበር፡፡ ዳግም ጨዋታዎችን መዳኘት የሚችለው ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሲፈጸሙ ብቻ መሆኑን የገለጸው ማኅበሩ፤ አለበለዚያ ምንም ዓይነት ጨዋታ እንደማይዳኝ እና እንደማይታዘብም አስታውቆ ነበር፡፡

ማኅበሩ ያስቀመጣቸውን ቅድመ-ሁኔታዎች መገምገሙን የገለጸው እና ጉዳዩ የሚመለከተው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፤ በማኅበሩ የቀረበለትን ቅድመ-ሁኔታዎች ተቀብሎ፣ ማኅበሩ ለሶስት ሳምንታት ለማካሄድ ያቀደውን የስራ ማቆም አድማ እንዲተው ማድረጉ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የጨዋታ መርሐ-ግብር መሠረት ግጥሚያ ለማካሄድ ከዚህ ቀደም ወደ ትግራይ ክልል ሄደው የነበሩ ክለቦች፣ በክልሉ ስር በተቋቋሙ ክለብ ደጋፊዎች እና ተጫዋቾች ተደብድበው መመለሳቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡ ድብደባ ከተፈጸመባቸው የእግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች መካከል ወልድያ እና ፋሲል ከነማ ይጠቀሳሉ፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.