ለምን ዙሪያውን እንዞራለን ?  (ጠገናው ጎሹ)

ምን ማለት ነው? የምን ዙሪያ መዞር ነው የምታወራው ? የሚል ተገቢ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርምና  ምን ማለቴ እንደሆነ እንደሚከተለው ልግለፀው  ።

ዙሪያውን መዞር (beating around the bush) በአንድ በዋናነት በሚያወያየን ወይም በሚያከራክረን ጉዳይ (issue) ላይ የሚኖረን አቀራረብና አያያዝ ማሳካት ከምንፈልገው ማዕከላዊ ወይም ወሳኝ ፍሬ ነገር (pivotal and critical point of interest) ላይ ማተኮሩ ይቀርና   ወይም ይዘነጋና   በዙሪው ባሉ ጉዳዮች ላይ እየተሽከረከርን   እውቀትን ፣ ጊዜን ፣ የሰው ሃይል እና የማቴሪያል ሃብትን የምናባክንበት አዙሪት (vicious cycle) ነው ።

ቀጥሎም ይህ ታዲያ ከሰሞኑ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ጋር እንዴት ነው የሚገናኝው ? የሚል ጥያቄ ነውና የሚነሳው ያለኝን ሃሳብና አስተያየት እንደ አንድ የአገርና የወገን ጉዳይ እንደሚያሳስበውና እንደሚያገባው ተራ (ordinary) ኢትዮጵያዊ በተገነዘብኩትና በተረዳሁት መጠን እንደሚከተለው ልቀጥል ።

በህዝብ የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ጥያቄና የትግል ማዕበል የተደናገጠው ገዥ ቡድን ከሥርዓት ለውጥ በመለስ ያሉና ለውጥ መሰል ሽርፍራፊዎችን  ተሃድሶ ብሎ በሚጠራው የፖለቲካ ተውኔቱ እና ትራንስፎርሜሽን በሚል በሚተርከው  የእድገትና ልማት የፕሮፖጋንዳ ትርክቱ አዘናግቶ (አደንዝዞ) ለማለፍ እያደረገ ያለው የሽረት ወይም የሞት ትግል  ከቀን ወደ ቀን ግልፅ እየሆነ መምጣቱን መካድ የሚቻል አይመስለኝም። ከፊት ለፊት ላለው ታዳሚያቸው ስሜት የሚስማማ አገላለፅ ለመጠቀም በሞከሩ  ቁጥር ሃሳባቸው ወጥነት(consistency) የማጣቱ ችግር እንዳለ ሆኖ  ታሪካዊና ድንቅ በተባለለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር  እና  በመሬት ላይ እየሆነ ባለው  እውነታ መካከል ሊኖር የሚገባው መስተጋብራዊ ግንኙነት የህዝብ መሠረታ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ጥያቄን ከመመለስ  አንፃር ሲታይ  የሚነግረን ይህኑ ሃቅ ነው ። ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ የመከራና የውርደት ዋነኛው ምክንያት ሆኖ የዘለቀውን የፖለቲካ ሥርዓት በሽርፍራፊ መሸንገያ (ማታለያ) ጠጋግኖ የማስቀጠል መሪር ሃቅ። ይህ ግንዛቤዬና አረዳዴ  ብዙ ወገኖች እንደሚሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩን የግል ሰብዕና ወይም ባህሪ የመጠጥላትና የመውደድ ጉዳይ አይደለም ።በፍፁም! እንዳይሳካላቸው የሚደረግ የዕብደት ወይም የሴራ  ፖለቲካ ጨዋታም ጨርሶ አይደለም ።

ገዥዎቻችን ካገዘፉትና ካወሳሰቡት የአገራችን ሁለንተናዊ ማለትም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ሥነ-ምግባራዊና ሞራላዊ ቀውስ በእውን ሰብረን መውጣት ካለብን ዴሞክራሲያዊ የሥርት ሽግግርንና ግንባታን በተሃድሶ ተረት ተረታቸው ሊያኮላሹ ሲሞክሩ በቃችሁ መባል አለባቸው ። ይህን ዘመን ያስቆጠረ እኩይ ባህሪና ተግባር ህዝብ ከአሁን በኋላ ጨርሶ  አንፈቅድም ቢል በምንም አይነት መመዘኛ “ጊዜና ፋታ እማይሰጥ ህዝብ” የሚል እጅግ ልፍስፍስ (clumsy) ወይም ደግሞ  እጅግ ቅንነት የጎደለው (disingenous)  ቅሬታ ወይም ትችት ሊቀርብበት አይገባም ። በተለይ ገዥዎቻችንና ግብረ በላዎቻቸው በህዝብ ላይ እንዲህ አይነት ትችት ለመሰንዘር የፖለቲካም ሆነ የሞራል ብቃቱ የላቸውምና የሚበጀው የህዝብን የማያወላዳ ጥያቄ አዳምጦና ተረድቶ ትክክለኛውን መውጫ መንገድ ማመቻቸቱ ላይ መረባረብ ነው ።     አገርና ህዝብ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ ከዘለቁበት የመከራና የውርደት አዙሪት ይወጡ ዘንድ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ሽርፍራፊ ነገሮችን እየያዙ  ዙሪያ ጥምጥሙን ከመዞር በመሠረታዊው ጥያቄ (ጉዳይ) ላይ በሃቅ ፣ በቀጥታ፣ በግልፅና በቅንነት ተነጋግሮ የሚበጀውን የጋራ መውጫ መንገድ (መሸጋገሪያ ድልድይ) መዘርጋቱ ነው የሚሻለው ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህወሃት/ኢህአዴግ እኩይ ድርጅታዊ የፖለቲካ እምነትና አሠራር ተጠርንፈው (እራሳቸውን አስጠርንፈው) በፖለቲካ ተወልደው ያደጉበት የህወሃት/ኢህአዴግ እኩይ የፖለቲካ ሥርዓት ተወግዶ  እውነተኛ ህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ወደሚመሠረትበት መሸጋገሪያ  በመሪነት ይወስዱናል ብሎ ማመን ግን ጨርሶ ከመሪሩ እውነታ ጋር  በአወንታዊነት ሊመሳከር የሚችል ጉዳይ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩና ድርጅታቸው/ህወሃት-ኢህአዴግ (መንግሥታቸው) በውስጣቸው የተወሰነ የፖለቲካ ሃይል ሚዛንን በመፈተሽና የተወሰኑ ጥገናዊ ለውጦችን በማድረግ ሥርዓታቸውን ለማስቀጠል የሚያካሂዱትን “የማረጋጋት ዘመቻ” በተመለከተ አካፋን አካፋ ( calling a  spade a spade) ብለን የምንጠራውን ያህል ግልፅና ቀጥተኛ  መሆን አለብን ። እንዲህ ሲሆን ነው  ትኩረታችን የህዝብ ጥያቄና ፍላጎት  ሁሉ መነሻና መዳረሻ ለሆነው የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ የሚመጥን ትግልን ይበልጥ አጠናክሮ የመቀጠሉ አስፈላጊነት የመኖር ወይም ያለመኖር ጥያቄን ያህል ግልፅና ግልፅ የሚሆንልን።

በዋናው ጉዳይ (ጥያቄ) ዙሪያ ከሚሽከረከሩ ሽርፍራፊ “የተሃድሶ ለውጦች” ጋር አብረን ስንሽከረከር ከስንት መከራና መስዋዕትነት በኋላ የነፃነት ድል ዋዜማ ላይ የደረሰውን ህዝባዊ ትግል የገዥዎቻችን ምርኮኛ እንዳናደርገው በእጅጉ ሊያሳስበን ይገባል ።  ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ግዙፍና ውስብስብ የሆነውን የህግ አስፈፃሚውን የመንግሥት አካል (executive branch of govenment) ለሚመራው ካቢኔያቸውና ለሌሎችም ቁልፍ ለሚባሉ ተቋማት ሹመት ካሰጡበት ሂደትና ከባለተሿሚዎቹ የተበላሸ የፖለቲካ ሰብዕና እና በትክክለኛው ሚዛን ላይ ሲቀመጥ ባዶ ከሚሆነው አቅምና ችሎታቸው አንፃር ሲታይ ገዥዎቻችን የበሰበሰውንና ወንጀለኛ ሥርዓታቸውን ጠጋግነው ከማስቀጠል ያለፈ እርምጃ እንደማይራመዱ  ይበልጥ ግልፅ ያደርገዋል ።

ይህን ሃቅ ለመረዳትና ለማስረዳት ምንም አይነት የትንታኔ ጋጋት የሚያስፈልግ አይመስለኝም ። ይልቁን የሚሻለው መሪሩን ሃቅ  በቅጡ  ተገንዝቦና ተረድቶ ህዝባዊ ትግሉን ለዚሁ ተመጣጣኝ በሆነ ብቻ ሳይሆን በላቀ አደረጃጀትና ስትራቴጅ ማስቀጠልና ውጤታማ በማድረጉ ላይ መረባረቡ ነው ። ሌላው ምርጫ (ምርጫ ከተባለ) የእነሱን (የገዥዎቻችን) የተሃድሶና የትራንስፎርሜሽን ፍርፋሪ (ምፅዋት) ተቀብሎ “ይህችን አታሳጣን” እያሉ መኖር ነው ። ይህ ግን እንደሰው መኖር ሳይሆን ከደመነፍስ እንስሳነት ተራ የሚያውል ነው ።   በዕውነት የምንነጋገር ከሆነ  በየመወያያ መድረኩና በሌሎችም የመገናኛ ዘዴዎች የገዥው ቡድን አልተሳካለትም፣ በውስጥ ቅራኔ ተወጥሯል ፣የህወሃት የበላይነት ዘመን እያበቃ ነው  ጠቅላይ ሚኒስትሩን ህወሃት አላሰራቸው አለ ፣ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር (በነአቶ ለማ ቡድን) እና  በህወሃት መካከል  ግብግቡ ቀጥሏል ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜ ሰጥተንና የዕዮብን ያህል ታግሰን እንያቸውወዘተ የሚለው አመለካከትና አካሄድ በምንም አይነት መመዘኛ የምንፈልገውን መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እውን ለማድረግ አያስችለንም ።

ይህ አባባሌ ከአጠቃላይ እውነታና መርህ አኳያ  ተፈላጊውን ለውጥ እውን ለማድረግ ጊዜና ትግሥት አያስፈልግም የሚል የድንቁርና እና የቀቢፀ ተስፋነትይዘት የለውም። እያልኩ ያለሁት እንደዚህ ነው፤ ) ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ የመከራና የውርደት ቀንበር ተጭኖበት የኖረ ህዝብ   ለእውነተኛ የአገር ሉአላዊነትና ለህዝብ የነፃነትና ፣ ፍትህ ፣ የዜግነትና የሰብአዊ መብት እውን መሆን በጮሁና በታገሉ በይፋዊና ስውር  ማጎሪያ ማዕከላት(ቤቶች) የሚማቅቁትን ሁሉንም ዜጎች  ልቀቁ  (ፍቱ) ብሎ ሲጠይቅ ጊዜና ትዕግሥት ይሰጠኝ(ይሰጠን) ማለት በእጅጉ የሚያም የፖለቲካ ጨዋታ ነው ፥ ) አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (መንግሥታዊ የሽብር አዋጅ ) በማወጅ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጀምሮ ሰላማዊና ታሪካዊ የሥልጣን ሹም ሽር እና ሽግግር ማድረ ጋችን የለውጡን (የተሃድሶውን) መንገድ ጠረጋ እያሳለጥነው ለመሆኑ ምስክር ነውና ትዕግሥተኝነትና ጊዜ ያስፈልገናል”  የሚለው ሰበብም (execuse) የለየለትና አደገኛ የፖለቲካ ቁማር ጨዋታ ነው ፧)   ቀድሞውንም እንኳን መታሰርና የሰቆቃ ሰለባ መሆን  በምንም አይነት ምክንያት  መጉላላት ያልነበረባቸውን ንፁሃን ዜጎች የህዝብ ትግልና የዓለም አቀፍ ጫና መንበረ ሥልጣንን ሲያንገጫግጭ (ሲያርድ) ለተፈፀመው ልክ የሌለው ግፍ ሃላፊነት እንደሚሰማው መንግሥት ቢያንስ ይቅርታ እንኳ ሳይጠይቁ ከስር ፈት ተው የጥልቅ ተሃድሶ በረከት ማለት ይኸው ነውና ታሪካዊ ውዳሴ ይገባናል የሚል ፕሮፓጋንዳ ሃያ አራት ሰዓት ማዥጎድጎድ ከቅንነትና ከምር ከስህተት መማርን ጨርሶ አያሳይም   )   ዛሬ ከሥር ፈትቶ ነገ መልሶ በሚያስር ዛሬ  የፖለቲካ ትርፍ አገኝበታለሁ ከሚል ስሌት አንድ የማሰቃያ ማዕከል ዘግቶ ነገ ሌላ ዘመናዊ የማሰቃያ ማዕከል  በሚገነባ ዛሬ በአዲሱ ጠ/ሚኒስትር አማካኝነት  ወሰን የሌለው አረመኒያዊ ሥልጣኑን እምቢ ባሉ ንፁሃን ዜጎች በተለይም ታዳጊ ወጣቶች ላይ በተፈፀመው የተናጠልና የጅምላ ግድያ አዝናለሁና ይቅርታ እጠይቃለሁ ቢልም ነገ ላለመፈፀሙ ዋስትና በሌለው ዛሬ የደም እንባ ካነቡ ወላጆችና ሌሎች ንፁሃን ዜጎች የሃዘን አውድ ላይ በመገኘት የአዞ እንባ እያነባ ነገ ተመሳሳይ ወንጀል ውስጥ በሚዘፈቅ ፣ ዛሬ የመናገርና የመፃፍ መብት መከበር አለበት ብሎ እየሰበከ ነገ ሰበብ ፈጥሮ የጭቃ ጅራፍ ፖለቲካውን በሚመዝ  የዛሬ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር የአንድ እንሁንና የእንፋቀር ሰበካውን ነገ በአፍ ጢሙ እንደማይደፋው ምንም አይነት ማረጋገጫ  በሌለው    ዛሬ የአገር ጉዳይ ያገባናል የምትሉ ቅረቡና ተነጋግረን አገራችን በጋራ የዴሞክራሲና የብልፅግና አገር እናድርግ ብሎ ነገ የሥልጣን ሚዛኑን በብርቱ የሚያዛባበት መሆኑን ሲረዳ ሰበብ ፈጥሮ አፈርኩ የሚልና የተለመደውን የአፈና እና የግፍ በትሩን በሚመዝ ወዘተ በህወሃት/ኢህአዴግ በሚመራ  ሥርዓት ሥር እውነተኛ የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ሽግግር ይኖራል ብሎ መጠበቅ ወይ የዋህነት ነው፤ ወይም ተሸናፊነት ነው፤ ወይም ደግሞ የምትገኛዋን “የተሃድሶ” ፍርፋሪ ለመቀራመት መዘጋጀት ነው ።

አዎ! ትኩረትንና ሁለገብ ጥረትን በዋናው የህዝብ ጥያቄና ጉዳይ ላይ ሳይሆን በሱው ዙሪያ በሚሽከከሩና በሱው መፍትሄ ሰጭነት ለዘለቄታው መፍትሄ በሚያገኙ ጉዳዮች ዙሪያ የመጠመድ ፖለቲካዊ አባዜ ውጤቱ ይኸው ነው የሚሆነው ።    ፊታችን ላይ የሚያፈጥብንን መሪር እውነት እየፈራንና ለስሜታችን የማይጎረብጥ የሚመስለንን ክስተት እየመረጥን እራሳችንን ለመሸንገል (ለማታለል) ካልፈለግን በስተቀር ከሰሞኑ የምናስተውለው የአገራችን የፖለቲካ ክስተት (ጨዋታ) እውነታው ይኸው ነው።

 ልብ ማለት እየተሳነን ወይም እውነቱን ለመጋፈጥ ድፍረት እያጣን ነው እንጅ  አያሌ መስዋዕትነት የተከፈለበትንና  የጥያቄዎች ሁሉ ማዕከል የሆነውን መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ጥያቄን እየሸሸን ዙሪያውን የመዞራችን ጉዳይ አሁንም  እየተፈታተነን ያለ ብርቱ ፈተና ነው። ገዥዎቻችን ከመቸውም ጊዜ በባሰ አደጋ ላይ ያለውን ሥርዓታቸውን ታድገው ለማስቀጠል ያስችላቸው ዘንድ ከዘየዱት የፖለቲካ ጨዋታ ወጥመድ ውስጥ ሰተት ብለን  እየገባን መሆናችንን ወይም አለመሆናችንን ሰከን ብለን ለማስተዋል በስሜት የመነዳቱ ፖለቲካ ፋታ የሰጠን አይመስልም።

ጥያቄ የሚያስነሱ ጉዳዮች መኖራቸው እንዳሉ ሆኖው ከዶ/ር አብይ አህመድ አንደበት የሚወጡትን  የመልካም ቃላት ቀልብ ገዥነት መካድ ወይም ማጣጣል ትክክል አይደለም።   ከመሬት ላይ ወርደው ሊሸከሙት ከሚችሉት ተግባራዊ ሃቅ በላይ በእጅጉ ገዝፈው ሲስተጋቡ  ሊያደርሱት የሚችሉትን  የማሳሳትና የማዘናጋት ተፅዕኖ ማቃለል ደግሞ እራሱን የቻለ የሚያስከፍለው ከፍተኛ ዋጋ እንዳለ መታወቅ አለበት።   ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ የእነሱን ጥጋብና ድሎት የአገርና የህዝብ ትንሳኤና በረከት ነው እያሉ የመከራና የውርደት ቀንበር ጭነውበት የኖሩና አሁንም የቀጠሉ  ጨካኝ አምባገነን የገዥ ቡድኖች በሚገዙት እንደኛ ባለ አገር  የቃልና የተግባር ተለያይቶ መውደቅ  ያልተለመደ አይደለም ።

በዕውነት ከተነጋገርን በፖለቲካ ታሪካችን ሂደት ውስጥ ገዥዎቻችን ወደ ሥልጣን ለመውጣት ፣ ሥልጣንን አደላድሎ ለመቀጠልና እንደአሁኑ አደጋ ላይ የወደቀውን መንበረ ሥልጣን በብሔረሰብና በቋንቋ ለያይቶ የመግዛቱን ፖለቲካ ለመታደግ  ከሚጠቀሙበት የፖለቲካ ትርክት አንዱና ለስሜት እጅግ ቅርብ የሆነው ኢትዮጵያዊነትንና አብሮነትን መስበክ ነው  ። በእርግጥ ኢትዮጵያዊነትና አንድነት በመሠረተ ሃሳብነቱ ብቻ ሳይሆን  በተግባራዊ ወሳኝነቱ እንኳን በአገር ደረጃ በየትኛውም ማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ ያለው የእሴትነት ጠቀሜታ በመጠን ከሚለካ ዋጋ በላይ ነው ።  ጥያቄው ያለው በተግባር ከምናራምደው ስትራቴጅና ግብ ጋር እንዴት ይጣጣማል? የሚለው ነው ።  ኢትዮጵያዊነታችን በየብሔረሰባችን፣ በየቋንቋችንና ከዚያም አልፎ በየመንደራችን መንዝረውና ተነጣጥለን ለክፉ አገዛዛቸው እንድንመች አድርገው ከሩ ብምዕተ ዓመት በላይ የሰቆቃና የውርደት ቀንበር ያሸከሙን ገዥዎቻችን ዛሬ ደግሞ “የተሃድሶ” ፍርፋሪያቸውን የፖለቲካ መዝገበ ቃላቸው በማያውቃቸው ስሜት ኮርኳሪ ቃላት አጅበው ያንኑ ቀንበራቸውን እንዳሸከሙን እንድንቀጥል  ዘመቻ ላይ ናቸው።  ይህን እነሱ እያመቻቹ የሚሰጡንን የፍርፋሪ ተስፋ አግተልትለን በዋናው (መሠረታዊው) የህዝብ ጥያቄ ዙሪያ የምንሽከረከር ቁጥራችን ቀላል አይመስለኝም ።

እንደ እኔ ግንዛቤና አረዳድ ቅንና አስተዋይ የአገሬ ሰው  በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የሚያቀርበው ጥያቄና ትችት በደምሳሳው ለምን እቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ በየአደባባዩና በየአዳራሹ የመልካም ተስፋ ንግግር ያደርጋሉ ? የሚል በጭራሽ አይደለም ።

   ወደ አዲስ የታሪክ ምእራፍ ከመሸጋገር ይልቅ የሩብ ምዕተ ዓመት የመከራና የውርደት የፖለቲካ ታሪካ ምዕራፍን  “በተሃድሶ” ስም ተጨማሪ ዓመታትን  እንዲያስቆጥር መፍቀድ እስከአሁን ከተፈፀሙት ስህተቶች ሁሉ የከፋ ስህተት ነው ።  “በአዲሱ  የገዥው ቡድን ጠቅላይ ሚኒስትር በኩል ለውጡ መምጣቱ አይቀርምና ጊዜ መስጠት ፣ የእዮብን ያህል ትእግስት ይስጠኝ ብሎ መፀለይ እና  የማያወላውል ድጋፍ መስጠት ግድ ይላል “ የሚለው የብዙ ወገኖች ድምፅና ብዕር እስከአሁን የተጓዝንበትንና አሁንም እየኖርንበት ያለውን የገዥዎቻችን “የፖለቲካ ተሃድሶ” ትርክትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በእውን የሚገልፀው ቢሆን ኖሮ እንዴት ታላቅ መታደል  ነበር ።

አዎ! በዕውነት እንነጋገር ካልን ከተዘፈቅንበት ሁለንተናዊ ቀውስ ወጣን ስንል ተመልሰን እየተዘፈቅን ዘመን ያስቆጠርንበት አንዱ ምክንያት የምንቆምበት የለውጥ ፈላጊነት ሜዳ በማይናወጥ የመርህ ፣ የአላማ እና ግልፅና ውጤት ተኮር በሆነ የእቅድና የአሠራር ሥርዓት ላይ የተመሠረተ (የተሰናዳ) አለመሆኑ ነው። በሌላ አባባል ምንም አይነት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል ኖሮባት የማያውቀውንና ማንም ከእግዚአብሔር የተላኩ ነኝ በሚል የማጭበርበሪያ ዘዴ ወይም በጉልበት (በግድያ)ለዘመናት ያጎሳቆላትን አገር ለመታደግ የተሳነን ያደረግነው ጥረት ሁሉ በፀና የጋራ መርህ፣ ተነሳሽነትና  እርብርብ ላይ የተመሠረተ  ሳይሆን ከክስተቶች ጋር አብሮ ብልጭና ድርግም በሚል ግልብ ወይም ልክ በሌለው ስሜታዊነት ላይ የቆመ በመሆኑ ነው ። አሁንም የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት (ምደባ) ተከትሎ ከምንሆነውና ከምናደርገው በብዙው የሚስተዋልብን ክፉ አዙሪት ይኸው ነው። ከክስተቶች የሙቀት መጠን ጋር አብሮ የመሞቅና የመቀዝቀዝ አባዜ።  ወደድንም አልወደድንም አሁንም ከዚህ በስሜት የመነዳትና በዋናው የህዝብ ጥያቄ ዙሪያ ባሉ “የማረጋጊያ” ሽርፍራፊዎች ላይ ከመሽከርከር  አባዜ ወጥተን ህዝብ በዕውነተኛ ነፃነት፣ ፍትህ፣ መብት፣ አብሮነት ፣እኩልነት ፣ሰላም ፣ ፍቅርና የጋራ ብልፅግና የሚኖርባትን አገር እውን በማድረጉ ላይ ካላተኮርንና ካልተረባረብን በስተቀር የሴረኛ ፖለቲከኞች መጫወቻነታችን ማቆሚያ የለውም።

ሰሞኑን  የገዥዎቻችን  “አዲስ” የፖለቲካ ክስተትና ትርክት እያየንበት ያለነው  እይታ ከመሠረታዊው የህዝብ ጥያቄ (አጀንዳ) እየራቀ መሄዱን በዕውን ለሚታዘብ እውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ የአገሬ ሰው ከምር ሳያሳስበው የሚቀር አይመስለኝም ። ገዥዎቻችን ዋናውንና  እጅግ ወሳኙን   ( pivotal and critical)  የህዝብ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት  ለውጥ ጥያቄን ወደ እነርሱ የተለመደ ከመሆን አልፎ የከረፋ  “የታድሰናል”  የፖለቲካ ጨዋታ አንሸራተው  የማውረድ ዘመቻውን ተያይዘውታል። ዙሪያውን እየዞርን ጊዜና ሌላም ሃብት ከምናባክን እውነቱ ይኸው መሆኑን ተቀብለን ለሱ የሚመጥን ሥራ ላይ ማተኮሩና መረባረቡ ነው የሚበጀን ።

እነርሱ (ገዥዎቻችን) ራሳቸው በሰበሰና ከረፋ ብለው ከነገሩን ረጅም ጊዜ የሆነውን አገዛዛቸውን እስከአሁን ባልሞከሩትና የህዝብን ዕውቀትና ተሞክሮ (public intelligence and expereince) እጅግ ዝቅ በሚያደርግ የፖለቲካ ጨዋታ ዘዴ የማስቀጠል ሙከራ ሲያደርጉ ማየት የሚገርም ወይም ያልተለመደም አይደለም ።

የሚገርመው ገዥው ቡድን (ህወሃት/ኢህአዴግ)  መንበረ  ሥልጣኑን ከህዝብ የአልገዛም ባይነት ማዕበል ለመታደግ ሲል  የውስጥ የሥልጣን ሚዛኑን ሳይወድ በግድ ለማስተካከል የወሰደውን ፖለቲካዊ እርምጃ “የውስጥ የለውጥ ሐዋሪያት በረከት ነው” እስከማለት የቃጣን ቁጥራችን ቀላል አለመሆኑ ነው ።  ዶ/ር አብይ አህመድ ተአምር ይሰራሉ የሚል አይነት ቃና ባለው የፖለቲካ ትርክት የተጠመደው ተማርኩና ተመራመርኩ የሚለው የህብረተሰብ ክፍል መሆኑን ልብ ስንል  ደግሞ ግርምት ከመፍጠር አልፎ በእጅጉ አሳፋሪም  ነው።

የህዝብን የብሶት ስሜት በአንደበተ ርቱዕ ጠቅላይ ሚኒስትር አማካኝነት ከፍ አድርገውና ደጋግመው በማስተጋባትና አንዳንድ “የተሃድሶ በረከቶችን” በማወጅ  ሥርዓተ አገዛዛቸውን “ብቸኛውና ትክክለኛው መንገድ ዴሞክራሲያዊ  የሥርዓት ለውጥ ነው”   ከሚለው የህዝብ ጥያቄ ለመታደግ እያካሄዱት ያለውን ጥረት ለመገንዘብ የፖለቲካ ወይም ባለ ሌላ ልዩ ሙያ  ልሂቅ መሆንን በጭራሽ አይጠይቅም።

የእያንዳንዱን ዜጋ  የቤት ጓዳ ብቻ ሳይሆን ህይወትንም ጭምር ምስቅልቅሉን እያወጣ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረውን የህወሃት/ኢህአዴግ እጅግ እኩይ አገዛዝ ከምር ለተከታተለ እና አሁን ደግሞ “ይህን ክፉ አገዛዝ ወይም ሥርዓት አስወግዶ ወደ አዲስ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሸጋገሪያውን የሚያመቻች ፖለቲከኛ ከራሱ  ከህወሃት/ኢህአዴግ ማህፀን ተወለደ” የሚለውን  የፖለቲካ እይታ ሽባነትን ፣ የሥነ-ልቦና ዝቅጠትን እና የሞራል ልፍስፍስነትን በቅንነትና ከምር ለሚያስተውል የአገሬ ሰው “ከየት ወደየት ነው እየሄድን ያለነው?” የሚል እጅግ ፈታኝ ጥያቄ ሳይሞግተው የሚቀር አይመስለኝም ።

ይህን ስል አንድ ፖለቲከኛ  አባል የሆነበትን ድርጅት እኩይ ባህሪና ተግባር በመፀየፍ ፣  በመቃወምና ከህዝብ ጎን በመቆም ታሪካዊ ሥራ ሊያስመዘግብ በፍፁም አይቸልም እያልኩ አይደለም ። ። ዶ/ር አብይ አህመድ  የሥርዓቱ የረጅም ጊዜ አባል ስለሆኑ አይታመኑም ከሚል ደመሳሳ አስተሳሰብ መነሳትም ትክክል አይሆንም ። ይህ ግን አጠቃላይ እውነታ እንጅ አሁን እያስተዋልነው ያለነውን የእኛኑ የፖለቲካ እውነታ የሚገልፅ አይደለም ።

ይህ ደግሞ ብዙ ወገኖች ለመተርጎም እንደሚፈልጉት  ዶ/ር አብይ አህመድን በግል ማንነታቸው ወይም የገዥው ቡድን አባል በመሆናቸው ብቻ የመጥላትና የመውደድ ጉዳይ ጨርሶ አይደለምተጠምቀው ያደጉበት ድርጅታቸውን እኩይ የፖለቲካ እምነትንና  አሠራርን ለስሜት የሚስማሙ ንግግሮችን በርቱዕ አንደበት እያሽሞነሞኑና በሽርፍራፊ “የተሃድሶ” ለውጦች እያጀቡ ጨርሶ ከመውደቅ  ለመታደግ የሚጫወቱት  የፖለቲካ ጨዋታ ግን የሚጠላ እንጅ በጭራሽ የሚወደድ አይደለም ። የድርጅታቸውና የመንግሥታቸው ተፈጥሮ፣ ባህሪና አሠራር እንኳን በሚናገሯቸው ግዙፍና ጥልቅ ቃላት ልክ ይቅርና በግማሹም ሊያሠራ የሚችል አለመሆኑን ጠንቅቀው እያወቁ የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትርነት መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ሽግግርን ያመቻቻል ብሎ መቀበል/ማመን ወይ የፖለቲካ ቂልነት ነው ፤ ወይ የለየለት አድርባይነት ነው ፥ ወይም ደግሞ የተሻለ ነገን ለማየት የሚያስችል ራዕይ ድህነት ነው። ይህን አይነቱን ሃቅ ለመናገር/ለመግለፅ   ዙሪያውን መዞር ጨርሶ አያስፈልግም።

ህወሃት  ሶስት አስርተ ዓመታት ሊሞላው ትንሽ ጊዜ የቀረውን የመከራና የውርደት ሥርዓት ከመጨረሻ ውድቀት ለማዳን በሚያደርገው ብርቱ ጥረት ውስጥ የህወሃት/ኢህአዴግን  ድርጅታዊ እምነትንና አሠራርን በማይጋፋ አኳኋን ሊያስፈፅምለት የሚችልና በህዝብ ዘንድም በግል ባህሪውና በአንደበተ ርዕቱነቱ ከሌሎች ሁሉ የተሻለ እና በተለይ ደግሞ የለውጥ ማዕበሉ ከየትኛውም የአገሪቱ ክፍል በባሰ ሁናቴ እየተካሄደ የነበረበትን ክልል (ኦሮሚያን) የሚያረጋጋ ፖለቲከኛ  ደስ ባይለውም መቀበል ነበረበት ።  በእውነት ለመናገር ለዚህ ተልኮ ዶ/ር አብይ አህመድ በእጅጉ የሚመጥኑ ፖለቲከኛ መሆናቸውን ማስተባበል የሚቻል አይመስለኝም ።  

ሌላም መጠቀስ ያለበትን አሳማኝ ምክንያት በአጭሩ መጥቀስ ይቻላል ። ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ አሁኑ ከፍተኛ የሥልጣን እርከን  ከመሸጋገራቸው በፊት የአቶ ለማ መገርሳ እየተባለ በሚጠራው “የለውጥ ፈላጊ ቡድን” በኩል በኢህአዴግ ውስጥ በተለይ ደግሞ በህወሃትና በኦህዴድ መካከል በተካሄደው የሥልጣን ሚዛንን  የመፈተሽና የማስተካከል እርምጃ ) (assessment and readjustment of the balance of power) እና ከህወሃት  የተፅዕኖ ቀንበር ለመላቀቅ በተካሄደ  የውስጥ ፍትጊያ ሂደት የነበራቸው ሚና  ጉልህ እንደነበር ግልፅ ነው ። በተለይም በኦሮሚያ የነበረው ከባድና ተከታታይ የህዝብ እምቢተኝነት  ኦህዴድ የሥልጣን ድርሻውን ለመፈተሽ ፣ ትርጉም ባለው ሁኔታ ህወሃትን ከጫንቃው ለማውረድና የሃይል ሚዛኑን ለመስተካከል ላደረገው (ለሚያደርገው) ጥረት ቁልፍ ሚና ተጫውቶለታል  ። እድሜ ለቄሮ ! ህወሃትም ተያይዞ ከመውደቅ የኦህዴድን ጥያቄ ተቀብሎ እንደ ኢህአዴግ በሥልጣን ላይ የሚያቆይ ስልትና ስትራቴጅ መቀየስ ይሻላል የሚል ፖለቲካዊ ድምዳሜ (ውሳኔ) ላይ እንደደረሰ ለማወቅ የተለየ ምርምር የሚጠይቅ አይመስለኝም።

በዚህ የሃይል ሚዛንን የመፈተሽ ፣ የማስተካከልና ቢቻል ወደራስ ለማምጣት ካልሆንም በአቻነት ለመውጣት በተደረገ የውስጥ ፍትጊያ ሂደት ኦህዴድ የህዝብን እምቢተኝነት በሚገባ ተጠቅሞ አሁን ለደረሰበት አንፃራዊ አሸናፊነት መብቃቱ እውነት የመሆኑን ያህል ህወሃትም  ዶ/ር አብይ አህመድን የመሰለ ፖለቲከኛ ተጠቅሞ “የህወሃት/ ኢህአዴግ ሥርዓት ተወግዶ እውነተኛ ህዝባዊ ሥርዓት የሚመሠረትበት በር ይከፈት” የሚለውን የህዝብ ጥያቄ ለጊዜውም ቢሆን ቀዝቃዛ ውሀ ቸልሶበታል ።  እንደእኔ ግንዛቤና አረዳድ የተደረገውና የሆነው ይኸው ነው ።  ለዘመናት በዘለቅንበት የፖለቲካ አዙሪት ዙሪያውን መዞር ካልፈለግን በስተቀር ።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር  ከክልል ክልል እየተዘዋወሩ የሚያደርጉትን “የማራጋጋት” ንግግር (ዲስኩር) በንግግርነቱ እሰየው የማይል አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የሚኖር አይመስለኝም ። መልካምና ተስፋ የሚሰጥ  ንግግርን (ቃልን) መስማት  እንኳን ለረጅም ዘመን የመከራና የተስፋ ቢስነት ሰለባ ሆኖ ለኖረው የአገሬ ሰው እንደሰው ተከብሮና  ተስፋውም እውን ሆኖለት የሚኖረውን ሰብአዊ ፍጡር  ቀልብ ቢስብ  የሚገርም አይሆንም።

ችግሩ ግን በገሃዱ የፖለቲካ ዓለምና በተለይም  ባለሥልጣናቱ በእውነተኛ የህዝብ ፍላጎትና ምርጫ ሳይሆን በአፈና እና በማጭበርበር ሥልጣን ላይ የሚወጣው ገዥ ፓርቲ ወይም ቡድን የራሱን ፖለቲከኞች መርጦ ሥልጣን ላይ በሚያስቀምጥበት እንደኛ ባለ  አገር ቃልና ተግባር ተዋህደው ለአገር ሉአላዊ ክብር እና ለህዝብ እውነተኛ ነፃነት ፣ ፍትህ ፣ እኩልነት ፣ መብት፣ ሰላምና ብልፅግና ዋስትና ይሆናሉ ማለት ከምኞት የማያልፍ ስለመሆኑ ከእኛው ከራሳችን የበለጠ ማስረጃ ያለ አይመስለኝም። አዎ! አሁንም እውነቱን በድፍረት ከመጋፈጥ ይልቅ በእሱ ዙሪያ ባሉና ለስሜት ቅርብ በሆኑ ክስተቶች ዙሪያ መሽከርከሩን የሙጥኝ ካላልን በስተቀር የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እውነታው ይኸው ነው

እርግጥ ነው ከሰሞኑ በአገራችን እየሆነ ያለውን ፖለቲካዊ ሁኔታ ደምሳሳ በሆነ አወታዊም ሆነ አሉታዊ እይታ ለማስተናገድ መሞከር ትክክለኛ ገንቢ አቀራረብ አይደለም። ሁለቱንም እይታዎች ከሂደት ተሞክሮና  አሁንም በግልፅና በግልፅ እየታየና እየተሰማ ካለው እውነታ ጋር እያስተያዩ (እያመሳከሩ) የማየትን ፣ የመተንተንን ፣የመረዳትንና ተገቢ የሆነ የመፍትሄ ሃሳብ የማካፈል ፍቃደኝነትንና አቅምን ይጠይቃል ። እንዲህ ሲሆን ነው በግራም ሆነ በቀኝ የምናስተጋባቸው አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ትርጉም ወደ እሚሰጥ ይዘትና ቅርፅ ተለውጠው ወደፊት የምንሄድበት መንገድ የተቃና እና ግባችንም የተሳካ የሚሆነው ።እንደ እኔ ግንዛቤና አረዳድ የሰሞኑን የገዥው ቡድን የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መንበረ ሥልጣን ከአቶ ኅይለማርያም ደሳለኝ ወደ ዶ/ር አብይ አህመድ የማሸጋገሩን እርምጃ ተከትሎ የሚቀርቡ ሃሳቦችና አስተያየቶች በሚከተሉት ጥያቄዎች ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮችን ከምር ለመመርመር ፍቃደኝነቱና አቅሙ ከሌላቸው የዕውነተኛ ለውጥ ምኞታቸን ምኞት ብቻ እንደሆነ ይቀጥላል። ።

 ለምሳሌ ያህል ልጠይቅ ፣ እንደአስፈላጊነቱም አስተያቴን ላክልበት

 • ለሙሆኑ ቃል ለምን ዓላማ ? ቃል የሚጨበጥ የህይወት ፍሬ የሚሆነው እንዴት ነው ? ቃል ተዘርቶ የሚበቅለው በማን ተሳትፎ ፣ እንክብካቤና የውሳኔ ሰጭነት ነው?
 • ቃል በየትኛው ዘርቶ የማብቀያና የማጎልበቻ የፖለቲካ አውድ ነው የህይወት ፍሬ የሚሆነው?  ህወሃት/ኢህአዴግ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት በተግባር (የካቢኔ ተብየውንና የሌሎችንም ከፍተኛ ሹመቶች ልብ ይሏል) እየነገረን ያለው “ስህተቴን አርሜና በተሃድሶ ታድሼ እቀጥላለሁ እንጅ ከኔ ሌላ መልካም መንገድ የለም” ነው ።  ቃል ተዘርቶና ጎልብቶ የገሃዱ ዓለም ህይወት ማበልፀጊያ ለመሆን የሚችልበት ምቹ አውድ በሌለበት ሲነገር ውሎ ሲነገር ቢያድር ከቃልነቱ አያልፍም። አለፈ እንኳ ቢባል ያለፈ የሚያስመስሉ ሽርፍራፊ ክስተቶችን ከማሳየት ከቶ አያልፍም።እየገጠመን ያለው ፈተናም ይኸው ነው ።
 • ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ የዕውነት ቃልን የጮሁና ያስተጋቡ አያሌ ንፁሃን ዜጎችን ቃላቸውን ብቻ ሳይሆን የዕውነት ቃል ምንጭ የሆነውን ውድ ህይወታቸውን ድራሹን ባጠፋ ሥርዓት ውስጥ እንደተጠረነፉ ያሉት  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እጅግ ማራኪ ቃላትን   ወደ እውነተኛ የህይወት ፍሬነት (መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ) የሚለጧቸው በምን አይነት የመፈፀምና የማስፈፀም የሥልጣን አቅምና ስትራቴጅ ነው?  ግዙፍና ጥልቅ ፅንሰ ሃሳብ የተሸከሙ ቃላትን በየአደባባዩ ሲያስተጋቡ የፖለቲካ ፓርቲ ሥልጣንና ተግባርን ከመንግሥት ሥልጣንና ተግባር ጨርሶ መለየት በማይቻልበት ሥርዓት ውስጥ መሆናቸውን እየረሱ ነው እንዴ ? ወይስ ይህን አስከፊ ሥርዓተ ፖለቲካ ከሥረ መሠረቱ ነቅሎ በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመተካት ከህዝብ ጎን የሚቆምና  ታሪክ ሠሪ መሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ድፍረቱ ኖሯቸው ነው?  መልሱ ሁለተኛው ቢሆን ኖሮ እንዴት ታላቅ የድል አድራጊነት ብስራት ነበር ። ከመሬት ላይ ያለው ግልፅና ግዙፍ እውነታ  ግን  ይህ ትክክለኛው መልስ መሆኑን አይነግረንም። አይደለምም ። የመጀመሪያውም የሚያሳምን አይደለም ።  እውነታውን በትክክል የሚገልፀው መልስ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓላማና ተግባር “ከመቸውም ጊዜ በተሻለ” ሁኔታ የተሃድሶ ሽፍራፊዎችን(ምፅዋቶችን) በማቅረብ እና አንዳንድ ተቀዋሚዎችን ሥርዓቱን ሥጋት ላይ በማይጥሉበት ሁኔታ የገፅታ መልሶ ግንባታ አጃቢ እንዲሆኑ በማሳተፍ የተሰጣቸውን ሥርዓቱን የማሰንበት ተልኮ መወጣት ነው
 • የህዝብ ቃላት (ጬኸት) መነሻና መዳረሻ በመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ላይ የሚገነባ አዲስ ሥርዓት እንጅ እንዴት በበሰበሰ (በከረፋ) ሥርዓት የፖለቲካ ጨዋታ ሜዳ ላይ  ይሆናል ?   ለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መቼና የት ነው የህዝቡን የሥርዓት ለውጥ ጥያቄ ቢያንስ  በአንድ ወይም በሌላ ፖለቲካዊ አገላለፅ እንኳን ለመንካት ድፍረት ወይም ወኔ ያሳዩት ? ባዘጋጁት የራት ግብዣ ላይ እንደማነኛውም ተጋባዥ የተገኙትንና በግብዣው ወቅት ሰላምታ ሲለዋወጡ “ተቀራርቦ ለመሥራት እንዲቻል እጥረት እናደርጋለን” የሚለውን የእግረ መንገድ አስተያየት (passimg remark)  እንደቁም ነገር ማስነገራቸው ደግሞ የፖለቲካውን ጨዋታ በጣም ዝቅ ያደርገዋል ።  “እኛ ኢህአዴጎች እዚህ ያደረስነውን የዴሞክራሲና የልማት ግስጋሴ የህዝቡን ብሶት እያዳመጥንና ከስህተታችን እየተማር እናስኬደዋለን“  ነው እንጅ የሚሉን የህዝቡን መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ ጥያቄ አግባብ ባለው መንገድና አሠራር ለመመለስ ሁኔታዎችን አመቻቻለሁ አይደለም ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢያንስ ግልፅ በሆነ የመርህ መነሻነት  ይህን የህዝብ ጥያቄ ከህዝብና ከባለድርሻ ኢትዮጵያዊ ተቀዋሚ ድርጅቶች ጋር እየተመካከርን የማንፈታበት ምክንያት የለም/አይኖርም ብለው በይፋና የተጨባጭነት ትርጉም ባለው አኳኋን በአሁኑ ደረጃ  እንዲናገሩ አይጠበቅባቸውም የሚል አይነት ልፍስፍስ  አስተያየትና መከራከሪያ የሚያቀርቡ ወገኖች ጥቂቶች አይደሉም።  ከድል በር ላይ የደረሰውን ህዝባዊ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ ለጊዜውም ቢሆን ወደ ኋላ እንዲመለስ እያደረጉ ያሉት ገዥዎቻችን ብቻ ሳይሆኑ እንደዚህ አይነት ልፍስፍስነትና ፍርሃት የተጫነው (clumsy and cowardly)  የፖለቲካ አስተሳሰባችን ጭምር ነው ።
 • በራስ ተነሳሽነትና አነሳሽነት ሳይሆን በህዝብ የለውጥ ፈላጊነት ማእበል አስገዳጅነት ከተከሰተው የውስጥ የሃይል ሚዛን ፍተሻና ማስተካከያ ንትርክ በኋላ ተዘጋጅቶ የሚቀርብለትን መልእክት እንኳ እንደአንድ ርዕሰ መንግሥት በቅጡ ተረድቶ ማስተላለፍ የተሳነውን ጠቅላይ ሚኒስትር  በሌላ የላቀ አንደበተ ርዕቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የተተካበትን ክስተት  “ታሪካዊና አርአያነት ያለው ሰላማዊ የሥልጣን  ሽግግር” ብሎ በህዝብ ዕወቀትና የማገናዘብ ችሎታ ላይ የተሳለቀ (የሚሳለቅ) ማነው ?  ለመግለፅና ለመረዳት በሚያስቸግር አኳኋን አገርንና ወገንን ለመከራና ለውርደት እየዳረጉ ንስሃ ሳይገቡ  በሞት የተለዩትንና አሳፋሪ በሆነ ደካማነት የሚሰናበቱ የገዥው ቡድን ባለሥልጣናትን በሠሩት  ሥራ ከፈጣሪ በስተቀር የሚበልጣቸው የሌለ እስኪመስል ድረስ  ማሞካሸት ህዝብን ጥሩውንና መጥፎወውን የማይለይ አድርጎ መገመት አይደለም እንዴ ?
 • ለመሆኑ ይህን አንዱን ከሥልጣን የማውረድና ሌላውን የማውጣት ድርጅታዊ አሠራር እንደዚህ ያሞካሹልን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ስለመጭው ምርጫ ዘመቻ ከመጀመራቸው በፊት  የአገራችን ጉዳይ በእውን ያሳስበናልና ያገባናል ከሚሉ ( ተገደው ሁለገብ ትግል ላይ የሚገኙትን ጨምሮ) ተቀዋሚ የፖለቲካ ድርድቶች ጋር ለመነጋገር ፣ ለመደራደርና እና በብሔራዊ እርቅ መንፈስ ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ የሽግግር ሂደት ለመግባት የሚያስችል ፍኖተ ሃሳብና የተግባር እቅድ እንዳላቸው ወይም እንደሌላቸው  ሊነግሩን ያልፈለጉት ወይም ድፍረት ያጡት ለምድን ይሆን ? ይህን ጥያቄ ችላ ብለው በሌሎች ሽርፍራፊ “የተሃድሶ” እርምጃዎች ዙሪያ አብረናቸው እንድንሽከረከር በየሄዱበት “የማረጋጋት” አደባባይ ውሏቸው ለምን ይማፀናሉ ? ይህ አይነቱ አካሄድ  ህዝብን የአብርሐም አይነት በግ እንደሆነ ወይም  “የፍርፋሪው ተሳታፊ (ተቋዳሽ)  ከሆነ ምን አነሰው” ከሚል የፖለቲካ ሰብዕና የሚመጣ አስተሳብ ውጤት አይደልም  እንዴ? እንደኔ ግንዛቤና አረዳድ የህዝብ መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ ጥያቄ የመፍቻ ቁልፉ ያለው ከዚሁ የአገሬ ጉዳይ ይገደኛል ከሚል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተቀዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ጋር በድፍረትና በቅንነት የመነጋገሪያና የጋራ መፍትሄ ማፈላለጊያ መድረክ ከነገ ሳይሆን ከዛሬ ጀምሮ ከማማቻቸቱ ላይ ነው ። የጠቅላይ ሚኒስትሩና የድርጅታቸው(የመንግሥታቸው) ከባዱ ፈተና ያለውም እዚሁ የትግል ፈርጅ ላይ ነው።
 • እንዴት? ቢባል ጠቅላይ ሚኒስትሩና ድርጅታቸው ከምር ይህን የማድረግ የፖለቲካና የሞራል ድፍረትና ብቃት ኖሯቸው እውን ቢያደርጉት እና የእውቀቱም፣ የሞራሉም ፣ የክህሎቱም፣ የተሞክሮውም፣ የአገርና የወገን ፍቅሩም፣ የመልካም ሥነ ምግባሩም ችግር የሌለባቸው እና ለትውልድ አርቆ የማሰቡና በአጠቃላይ አገርን የእውነተኛ ኩራትና ክብር ምድር ለማድረግ የሚችሉ የአገሬ ዜጎች ከያሉበት ተጠራርተው አዲስ አበባ ላይ ክተት ቢሉ ከህዝብ ፍላጎት አንፃር የሚሆነውን መገመት በጭራሽ ከባድ አይደለም ። ህዝብ ከምርጫ በፊት በይፋ ባልታወጀ  ድምፅ የህወሃት/ኢህአዴግን የከረፋ የፖለቲካ ሥርዓት ማሰናበቱን ለማወቅ የሚያስችል ሁኔታ ያለምንም ጥርጥር ይፈጠራል። ይህ ማለት ገዥው ቡድን ወይ እራሱን ለዚህ  የማያወላዳ ሃቅ በሰለጠነ መንገድ  ማዘጋጀት አለበት፤ ያለዚያ ደግሞ እንደለመደው አካኪ ዘራፍ ብሎ ወደ መጣበት የጥፋት እብደት ይመለሳል ማለት ነው ። እዚህ ላይ ነው እንግዴህ የዶ/ር አብይ አህመድ ውብ ቃላትና ርቱዕ አንደበት ፋይዳነት ወይም ባዶነት የወርቅን ያህል የሚፈተኑት ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የህዝብ ቁልፍ ጥያቄ ትርጉም በሚሰጥ መልኩ  ያለመድፈራቸውን ጉዳይ ልብ ለሚል ነፃነት ናፋቂ የአገሬ ሰው ከድርጅታቸው የተቀበሉት ተልኮ ከመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ድረስ እንደማይዘልቅ  ለመገንዘብ የሚቸገር አይመስለኝም። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንቅ ቃላትና ርቱዕ አንደበት “የተረጋጋው” ህዝባዊ ትግል ከባድ ፈተና የገጠመውም (የሚገጥመውም) እዚሁ ላይ ነው ። በፊትም ቢሆን የአገር አቀፍ አብሮነት ትስስርና  የማይናወጥ ድርጅታዊ መርህና አላማ ጥንካሬ የሚጎለው ህዝባዊ እምቢተኝነት ይህን እጅግ ፈታኝ የትግል ፈርጅ  እንዴት እንደሚወጣው በትክክል መገመት የሚቻል አይመስለኝም ።  በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀልብን የሚገዙ ንግግሮች ከትግል የመዘናጋቱ አደጋ እዚህ ላይ ነው ያለው ።
 • ለሩብ ምዕተ ዓመት በአገርና በወገን ላይ ለተፈፀመው ልክ የሌለው መከራና ውርደት  ማን ምን አይነት ድርሻ ነበረው ? ማንስ ምን አይነት ሃላፊነትና ተጠያቂነት ወሰደ ? ማንስ ማንን በሃላፊነትና በተጠያቂነት ጠየቀ ?   የይቅርታ (apology) ይዘትና አላማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሹመታቸው ወቅት ባሰሙት ታሪካዊ የተሰኘለት ንግግርና በሌሎች መድረኮች “አዝናለሁና ይቅርታም እጠይቃለሁ” ብለው በተናገሩት ቃል ብቻ የሚለካ አይደለም ።  እውነተኛ ይቅርታ የሚጀምረው በክፉ ግጭት ውስጥ የሚተረማመሰውን የየራሳችን ህሊና ይቅርታ በማጠያየቅና ሃላፊነትን በመውሰድ ነው ። በድርጅት ደረጃ ደግሞ የእያንዳንዳችን የተሳሳተ እምነትና ድርጊት ለአስከተለው ጉዳት ሌላውን አካል ወይም ህዝብን ይቅርታ ከመጠየቃችን በፊት የጋራ ስህተትን አምኖ በጋራ ከልብ ይቅርታ ከመባባልና የጋራ ሃላፊነት ከመውሰድ ነው የሚጀምረው።  ለፖለቲካ ፍጆታ ሳይሆን ከራስ የውስጥ ነፍስ ከሚመነጭ ፀፀትና ለሚያስከትለውም ሃላፊነትና ተጠያቂነት ዝግጁ ከሆነ ጠንካራ ሰብዕና የሚመነጭ ነው። እውነኛ ይቅርታ (real sense of apology)። ይህ አይነት ደፋርና ቅን የይቅርታ ሂደትና ይዘት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተናገሯቸው የይቅርታ ቃላት ውስጥ በዕውን መኖራቸውን የሚያረጋግጥ ጉልህ ተግባር በበኩሌ አላየሁም ።
 • የይቅርታ ምንነት በአገርና በህዝብ ላይ የተፈፀመን ግዙፍና መሪሪ ግፍ (በደል) የሚመለከት ሲሆን ደግሞ ሊሰጠው የሚገባው ክብደት የዚያኑ ያህል ከባድ ነው ።  በግለሰብ (ግለሰቦች) መካከል የሚደረግ ይቅርታ ተበላሽቶ የነበረውን ግንኙነት መልሶ በማስተካል ለወደፊቱ መተባበርን የግድ አይልም ። በተፈፀመ ስህተት ላይ በግልፅ ተነጋግሮ ፣ የየራስን የስህተት ወይም የጥፋት ድርሻና ሃላፊነት ወስዶና በቂምና በጥላቻ ላለመተያየት ተማምኖ/ተስማምቶ መለያየት በቂ ሊሆን ይችላል ። የአገር/የህዝብ ጉዳይ ግን በፍፁም እንደዚህ አይደለም ።ሊሆንም አይችልም ። የአገራችን ሁኔታ አስመልክቶ  የሚደረግ ይቅርታ የችግሩ መንስኤ ለሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮች ልባዊና ዘላቂ የጋራ መፍትሄ የሚገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸትንና ተግባራዊ ማድረግን ይጠይቃል ። ይህ ሁኔታ ደግሞ የሚወስደን የአገር ጉዳይ ያሳስበናልና ያገባናል ከሚሉ ተቀዋሚ  የፖለቲካ ፖርቲዎች ወይም ስብስቦች ጋር ተነጋግሮና ተደራድሮ ሥልጣንን የመጋራት ፈቃደኝነትንና ዝግጁነትን ይጠይቃል ወደ ሚለው ትልቅ ቁም ነገር ነው ። ስለውነተኛ ይቅርታ እያወራን ከሆነ ከዚህ ያነሰ  የይቅርታ ሄደትና ይዘት  በህዝብ ስቃይና መከራ መቀለድ ነው የሚሆነው ። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን የይቅርታ ቃልንም ከዚህ ባነሰ ደረጃ አምኖ መቀበል በተለይ አሁን ላለንበት የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አይመጥንም ።  ተመልሰን ይቅርታ የተጠየቀበትን እጅግ ዘግናኝ ግፍ እየደገምንና መልሰን የውሸት ይቅርታ እየጠየቅን ከምንኖርበት አዙሪት የመግባት ክፉ የታሪክ ስህትት  መውጣት አለብን  ።
 • ማን በማን ላይ ስንት ጊዜ የግፍና የመከራ ዶፍ አወረደ ? “ለህዝብ ነፃነትና መብት ስል ያልሆንኩት የለም” የሚል ድርጅትና መንግሥት እንዴት ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ እጅግ አሰቃቂና ተደጋጋሚ ከሆነ ስህተት ትምህርት ለመወሰድና የተሻለ ሆኖ ለመገኘት ተሳነው? ይህ አልበቃ ብሎ አሁንም ህዝብ ይህ ሥርዓት ጨርሶ መወገድና በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መተካት አለበት ብሎ በወሰነበት ሰዓት “አይ! መጠነኛ(ጥገናዊ) ለውጥ አድርጌ ሥልጣኔን ካላስቀጠልኩ ሞቼ እገኛለሁ“በሚል የህዝብን ብሶትና እንባ ቀምቶ በየአደባባዩ የአዞ እንባ ማንባት ምን ይሉታል ?
 • የሰላምን ፣ የመተሳሰብንና የፍቅርን አስፈላጊነትና ሃያልነት ለሩብ ምዕተ ዓመት በብርቱ ሲጠማ ለኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ የጥማቱ ዋነኛ ምክንያት የሆኑት ገዥዎቻችን  “የተጠማኸው ሆን ብለን በሰራነው ስህተት ሳይሆን ከአፈፃፀም ወይም ከመልካም አስተዳደር ግድፈት ነውና ይቅር ብለኸን በምንችለው ሁሉ እንክስሃለን” ብለው ሲሳለቁበት ከማየት  የበለጠ የፖለቲካ ክርፋት አለ እንዴ?
 • ማን ነው የህዝብን በምርጫ (በሰላማዊ መንገድ) የራሱን ሥርአተ ፖለቲካ የመምረጥና የመወሰን መብቱንና እድሉን በማጨበርበር ብቻ ሳይሆን እስከ ነፍስ ግድያ በየሄደ እጅግ አስከፊ ግፍ በተደጋጋሚ ያመከነ? ማነው ይህን አይነቱን አስከፊ ወንጀል ከፈፀመ በኋላ  የመቶ ፐርሰንት የምርጫ ድል አዋጅ ማወጁ ሳያንስ ወደፊትም  “ለመሬት አርዱ ድል” እንቅፋት ይሆኑብኛል ያላቸውን የተቀዋሚ ድርጅቶች ሁሉ ያፈራረሰና የተረፉትም ሽባ እንዲሆኑ ያደረገ
 • ዶ/ር አብይ አህመድ የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋትን ጥያቄ ከተቀዋሚ ድርጅቶች ወይም ቡድኖች ወይም ስብስቦች ተሳትፎ አስፈላጊነት ጋር አያይዘው ሲነግሩን እራሳቸው እውስጡ ያሉበት ድርድታቸው ወይም መንግሥታቸው በዚህ ረገድ የፈፀመውን ወንጀልና አሁንም በመንግሥታዊ የሽብር አዋጅ ሁሉንም ተቀዋሚ ድርጅቶች ከስም በስተቀር የሌሉ እስኪመስል ድረስ ፀጥና እረጭ እንዲሉ ማድረጉን እያመኑ ነው ወይስ እየካዱ ? በዚህ ላይ ግልፅና ግልፅ የሆነ አቀራረብ ከሌለ “ተቀራርበን ለመነጋገር ዝግጁ ነን” የሚለው አባባል ከርካሽ የፖለቲካ ፍጆታ አያልፍም። ምንም እንኳ ተቀዋሚ ድርጅቶች በተለይም አመራሮቻቸው መውሰድ ያለባቸው ሃላፊነትና ተጠያቂነት ቢኖርም በገዥነት መንበር ላይ የተሰየመው ድርጅት ወይም መንግሥት የሚኖርበት ሃላፊነትና ተጠያቂነት በምንም አይነት መልኩ ከተቀዋሚዎች ጋር የሚነፃፀር አይደለም ። ዛሬም የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የእንገናኝና የእንነጋገር ጥሪ ከዚሁ ሃቅ አኳያ መታየት ይኖርበታል ። “ተናግሬያለሁ ወይም ጥሪ አስተላልፌያለሁና ድርሻየን ተወጥቻለሁ” በሚል  የፖለቲካ ግብዝነት ምህዳር አይሰፋም ። በፍፁም!
 • አሁንም ምንም እንኳ ሳይወደድ በግድና ሥልጣንን ከህዝብ የለውጥ ማዕበል ለመታደግ ሲባል የተወሰኑ የፖለቲካ እስረኞችን ( በደፈናው እስረኞች እየተባለ ነው የሚነገረን) ፈትቶ እጅግ በርካታዎቹን በየማጎሪያ ማዕከሉ አጉሮ ግፍ መፈፀሙን የቀጠለበት ማን ነው ?
 • እንደ አንዳርጋቸው ፅጌ የመሰሉና ከግላቸው ህይወት በላይ ስለአገር ክብርና ስለወገን ነፃነትና መብት መስዋዕትነት የከፈሉና እየከፈሉ ያሉ የነፃነት አርበኞችን በየማጎሪያ ቤቱ አጉሮ የግፍ ሁሉ መሞከሪያ ያደረገና እያደረገ ያለን ሥርዓትን በየአደባባዩና በየስብሰባ አዳራሹ በሚደሰኮር ፖለቲካዊ ዲስኩር እንዴት መሸፋፈን ይቻላል ?
 • ማነው ለሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ የተዘረጉ ጣቶችን እቆርጣለሁ ብሎ መፎከር ብቻ ሳይሆን ከጣትም አልፎ የስንት ንፁሃንን ህይወት በአጭሩ የቆረጠው? የአሁኑስ “የተሃድሶ ዘመቻ” ይህን እጅግ ዘግናኝ የፖለቲካ እብደት ጨርሶ እንዳይደገም የማድረቅ ፍላጎቱና ብቃቱ ምን ያህል ነው ?
 • የግፍ ፣ የሰቆቃ ፣ የውርደት ፣ የተስፋ ማጣትና ልክ የሌለው ጉስቁልና ይብቃ ብሎ በጠየቀ ህዝብ ላይ በተለይ  ላለፉት ሁለት/ሦስት ዓመታት ከጅምላ ነፍስ ግድያ እስከ የጅምላ ሰቆቃና እስራት የፈፀመው ማን ነው? ይኸስ ከባድ ቁስል በመልካም ንግግር (ቃላት) እና በተሃድሶ ሽርፍራፊ እንዴት ታክሞ ይድናል ?
 • አንጋፋና ጠንካራ የሲቭል ፣ የሙያ እና የሠራተኛ ማህበራትን  በካድሬዎችና አደገኛ አድር ባዮች በማስጠርፍና  የወንጀለኛ ፖለቲካ ሥርዓቱ መሣሪያዎች በማድረግ መሠረታዊውን በነፃነት የመደራጀት መብት ገድሎ ወደ መቃብር ያስገባው ማነው?   አንጋፋዎቹን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበርንና  የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበርን በጉልህ ምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል ። ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ የመከራና የውርደት ዶፍ ሲወርድና በተለይ ደግሞ ከሁለት/ሦስት ዓመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በህዝብ ላይ እጅግ ዘግናኝ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ሲፈፀም እነዚህ ማህበራት ቢያንስ  ትርጉም ያለው የአንድ ቀን አገር አቀፍ የሥራ ማቆም አድማ አለመሞከራቸውን ከልብ ለሚታዘብ የአገሬ ሰው የሥርዓት ለውጥ ጥያቄውን ምን ያህል ከባድ እንደሚያደርገው ለመረዳት አይቸገርም።እንግዲህ የሰሞኑ “የታሪክ ተሠራ” ፖለቲካ ትርክት የሚተረክልን እንዲህ አይነቱ የበከተና የከረፋ የማህበራት አደረጃጀትና ተግባር እዚያው ቤተ መንግሥቱ ሥር ይበልጥ እየበከተና እየከረፋ ባለበት ሁኔታ ነው። ታዲያ ይህ እንዲሆን መፍቀድ ብቻ ሳይሆን ትልቁን ሚና የተጫወተውና እየተጫወተ ያለው ማነው? ታዲያ ይህ ሁሉ የግፍ ቁልል ያለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ እንዴት ይናዳል ? በስሜት አማላይ የፖለቲካ ንግግርና የተሃድሶ ፍርፋሪ ? በጭራሽ!
 • ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልሳናቸው እስኪደክም ድረስ ስለመብት መከበር ወይም ጥበቃ ሲሰብኩ ይህን አፍንጫቸው ሥር ያለውንና በድርጅታቸውና በመንግሥታቸው ክፉ እምነት ፣ እኩይ ባህሪና አጀንዳ ምክንያት ሞልቶ እየፈሰሰ ያለውን የመሠረታዊ መብት ድፍጠጣ ልብ ብለውት ይሆን በበኩሌ “የተከበራችሁ መምህራንና ሠራተኞች ፦ በትምህርትና በሌሎችም  የሥራ መስኮች ቀልጣፋና ጥራት ያለው ሥራ እንዲኖር እናደርጋለን” ከሚል ደምሳሳ ዲስኩር ያለፈና ቢያንስ የችግሮችን ምንጭና ያን ምንጭ ከሥሩ ስለማድረቅ የተባለ ነገር አልታዘብኩም ።  ቢያንስ ከመቶ ዘጠና በላይ የውድቀቱ ምንጭ ድርጅታቸውና መንግሥታቸው መሆኑን አሳምረው እያወቁ በግልፅ (በይፋ) ለመናገር ወይ ድፍረቱ የላቸውም ወይም በዚያው እኩይ ድርጅታዊ ዲሲፕሊን በብርቱ እንደተሸበቡ ናቸው ። ታዲያ ቅንና እውነተኛ ነፃነት ናፋቂ የአገሬ ሰው “የለውጥ ሐዋርያነታቸውን“ አጥብቆ መጠራጠር ብቻ ሳይሆን በትግሉ ፍጥነትና ጥንካሬ ላይ ለጊዜውም ቢሆን አሉታዊ ተፅኖ ያደረሱ ፖልቲከኛ ናቸው  ብሎ ቢቆጣ  “እድሜ ልኩን ማየት የተሳነው ነገ ይበራልሃል ቢሉት እንዴት ብየ አድራለሁ አለ “ የሚል አጉል ተረት የሚተርትበት የትኛው የፖለቲካና የሞራል የበላይነት ያለው የፖለቲካ ልሂቅ ነው ?
 • ታዲያ በዚህ አካሄድ “የእውነተኛ ለውጥ ሐዋርያ ናቸው ወይም ጊዜ ይሰጣቸውና ሆነው ይገኛሉ ” የሚለው መከራከሪያ እንዴት የማሳመን አቅም ይኖረዋል? ወደ የትኛው አቅጣጫና እስከየትስ ድረስስ ይወስዳል?  የጉዳያችን ሁሉ የማዕዘን ድንጋይ የሆነውን መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ እየሸሸን በሱው ዙሪያ ባሉና የገዥው ቡድን በሚያስተጋባቸው “የተሃድሶ ሽርፍራፊ በረከቶች” ዙሪያ እንረባረብ (እንራኮት) ካላልን በስተቀር ይህ አይነቱ በስሜት የመነዳት የፖለቲካ ቁመና የትም አያደርሰንም።
 • መንግሥታዊ የሽብር አዋጅ በማወጅ እንባውን አፍስሶ ያልጨረሰውን መከረኛ ህዝብ ተገናኝቶ እንኳ እንባውን እንዳይራጭ ያደረገውና እያደረገ ያለው ማን ነው ? ከጠቅላይ ሚኒስትሩ “ታሪካዊ ንግግር” ጎን ለጎን እንዲህ አይነቱን ግፍ እየተጋፈጠ ያለው የአገሬ ህዝብ ህወሃት/ኢህአዴግ በሚቆጣጠረው የፖለቲካ ሥርዓት በኩል እውነተኛ ለውጥ ይመጣል ብሎ እንዴት ይመን ?
 • ኢትዮጵያን በመላ እንደፈለገ የሚያስርባት ፣ የሚያሰቃይባት ፣ የሚገልባት ፣ በርሃብና በድንቁርና የሚቀጣባት ሰፊ እስር ቤቱ አድርጎ ጠባቡንና በአያሌ ንፁሃን ዜጎች ላይ ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ ለመግለፅ የሚያስቸግር ግፍና ሰቆቃ የፈፀመበትን ማዕከላዊ ዘጋሁ እና ሙዚየም ላደርገው ነው የሚል ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማትረፍ የሚቅበዘበዘው ማን ነው?  ሙዜየም የሚሆን ከሆነ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እውን ድርጅታቸውና መንግሥታቸው የፈፀሙት እያንዳዱ (አንድም ሳትቀር) አሰቃቂና አሳፋሪ ተግባር በመሪር የታሪክ ትምህርት ሰጭነት ለህዝብ በግልፅ እንደሚቀርብ ሊነግሩን ይችሉ ይሆን ? ይህን ለመግለፅ የፖለቲካና የሞራል ድፍረቱ (ወኔው) ከሌላቸው ሥልጣኑን በተረከቡበትና  በየሄዱበት አደባባይ ሁሉ  የጠየቁት የይቅር በሉን ተማፅኖ ርካሽ ፖለቲካዊ ትርፍ ከመሆን የሚዘል አይሆንም ።

እናም ይህን ከምር አለመረዳትና ህዝባዊ አልገዛም ባይነቱን ይበልጥ አጎልብቶ አለመቀጠል    ከአድማስ ባሻገር ሳይሆን ከፊት ለፊታችን ባሉ የተራሮቸ ሰንሰለት መካከል ደምቆ የወጣውን የነፃነት ፣ የፍትህ ፣ የሰብአዊና የዜግነት መብት ፣ የእኩልነት እና የወደፊት ብሩህ ተስፋ ፀሐይ ተመልሶ ለመውጣት በሚያስቸግር አኳን የገዥዎች ከባድ ግርዶሽ ሰለባ ማድረግ ነው የሚሆነው ። እንደእኔ ግንዛቤና አረዳድ ሰሞኑን ከዥው ቡድን ሰፈር የሚስተዋለውን የህዝብን  የለውጥ ፈላጊነት የእሳት ነበልባል በቁጥጥር ሥር የማዋልና የሥልጣን ዕድሜን የማራዘም ዘመቻ በከፍተኛ ንቃትና ከመሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር በሚመጥን አኳኋን ካላየነውና ተገቢውን ካላደረግን በስተቀር የግርዶሹ አደጋ ከቶ የሚቀር አይሆንም ። ይህ ግንዛቤዬና አረዳዴ የተሳሳተና አላስፈላጊ ሥጋት ሆኖ ቢገኝ ደስታውን ባልቻልኩት ። መሬት ላይ ያለው እጅግ ፈታኝ ሁኔታ ግን ይህን የሚያሳይ አይደለም ።   እናም ይህ እንዳይሆን በዋናው ወይም የመነሻችንና መዳረሻችን ማዕከል የሆነውን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ላይ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ማተኮር ይኖርብናል ።  የገዥውን ቡድን “ጊዜ ይሰጠኝና ትብብርም ይደረግልኝ  እንጅ በጥልቁ ተሃድሶ  ተአምር እንሰራለሁ”  የሚለው አማላይ ዲስኩር እውን ይሆናል ብለን የምንጠብቅ ከሆነ ያው ዙሪያውን የመዞር ልክፍት በብርቱ ተጠናውቶናል ማለት ነው ።

አሁንም ገዥዎቻችን “በተሃድሶ ለውጥ” ስም የፕሮፓጋንዳ ስልት ቀይረው ዘመቻውን በሚያጧጡፉበት ወቅት መከራውና ህይወት ማጣቱ በቁጥር ስሌት እንከራከር ካላልን በስተቀር ቀጥሏል ።   በመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ  ይህ የበሰበሰና  ጨርሶ የተበከለ የሴረ ኛ ፣ የዘርኛና ጨካኝ የገዥዎች ቡድን የፖለቲካ ሥርዓት ወደ መቃብሩ ሳይወርድ እውነተኛና  ዘላቂ እፎይታ ይገኛል ብሎ ማመን ሽንፈትንና ግፍን ተሸክሞ ለመቀጠል መዘጋጀት ማለት ነው ። አይደለም ዶ/ር አብይ አህመድ ከግማሽ በላይ ዕድሜውን ታማኝ አገልጋይ ሆኖ ለቆየው ከደሙ ጨርሶ ንፁህ ነኝ የሚልና  እንከን የሌለው ሰብእና አለኝ የሚል የአገሬ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆን በዚያው የበሰበሰና የተበከለ የፖለቲካ ቅርጫት ውስጥ እስካለ ድረስ ህዝብን በማይጨበጥ ፕሮፓጋንዳ  ያደነዝዝ (” ያረጋጋ”) እንደሆን እንጅ የሚፈይደው ህዝባዊ ፋይዳ ከቶ አይኖርም ።

ከመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርአት ለውጥ ያነሰ  በምንም አይነት  ፍርፋሪ ነፃነቴንና የሰብአዊ መብቴን መደራደሪያ አላደርግም በሚል የትየለሌ መስዋዕትነት የተከፈለበትን ህዝባዊ የለውጥ ማእበል አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ወይም በሌላ ተጨማሪ ምክንያት መልሰን አዙሪት ውስጥ እንዳንደፍቀው የሚል ሥጋት ቢኖር ትክክልና ተገቢ ስጋት ነው ባይ ነኝ ። ከዚህ አዙሪት ሰብሮ የመውጫው ብቸኛው ዋስትና ህዝባዊ ትግሉ ከመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ባነሰ ሽንገላ (ማታለያ) ፈፅሞ እንደማይቆም ለገዥው ቡድንና አጫፋሪዎቹ በተግባር ማሳየቱን ይበልጥ አጠናክሮ ማስኬድ ነው ።

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.