በሀገራችን ኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ  እንዴት? (ነሲቡ ስብሐት)

ከ፦      (nhsibhat@gmail.com)  (May  12-13,  2018   Vision  Ethiopia   ው ኮንፈረንስ ላይ የቀረበ)

ኢትዮጵያ ሀገራችን  በአንፃራዊነት ሰላማዊ  የመንግስት ልውውጥ  ያየችው በዓጼዎቹ  ዘመን  ነበር  ቢባል ያስኬዳል። ይህም ለውጥ ያለውን ሥርዓት ተሸክሞ ከዘመነ መሳፍንት ዘመን ወዲህ እንኳ አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስ፣ አጼ ምኒልክ፣ ንግሥት ዘውዲቱ፣ አጼ ኃይለ ስላሴ በአገዛዝነት ሲቀያየሩ በሰላማዊ  ሽግግር  እንደነበር  ታሪክ  የዘገበው  ነው።  በአጠቃላይ  ዘመኑ  የነገሥታት  ዘመን  ነበርና አጼነቱም  በዘር  ግንድ  የሚተላለፍ  ነበርና  ነው።  ሆኖም  በመሳፍንቱና  በባላባቱ  የይገባኛል  ጥያቄ ግጭቶችንና ጦርነቶችን  አስከትለው አልፈዋል።

ዓፄ  ኃ/ሥላሴ  ለ40   ዓመታት  ብቻቸውን  ገዙ።  ዕድሜ  እየተጫናቸው  ቢመጣም  እንኳን  ሥልጣኑን በንጉሳዊያን አስተዳደር መስፈርት ለልጆቻቸው ሊያወርሱ አልፈለጉም። አጠገባቸው ያሉትንም መኳንንት  ሊመለከቱ  አልፈለጉም።  ሕዝቡ  ኑሮና  ድህነቱ  እየባሰበት፣  አፈናውና  የመብት  ረገጣው እየከፋ  ሲመጣ  በትንሹ  የተጀመረው  ጥያቄ  (ስለ  ትምህርት  ቤት  አስተዳደር  መሻሻል)   እና  መሰል አካባቢያዊ ጥያቄዎች ሲነሱ በቀና መንገድ ከማስተናገድና መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ሲታፈኑ ኖሩ። ለሀገር መሻሻል ሁልጊዜም የሕዝብን ስሜት ማድመጥ አግባብነት አለው። የት ይደርሳሉና ንቀት አንዱ ጥያቄ ሌላ እየወለደ፣ አካባቢያዊ ንቅናቄዎች ሀገራዊ መልክ፣ ጥያቄዎቹ ፖለቲካዊ ቅርጽ እየያዙ ይመጣሉ። “የመሬት ለአራሹ” መፈክር አደባባይ ሲወጣ በጊዜው ትልቁ ፖለቲካዊና ሥር ነቀል ለውጥ ጠያቂ እንቅስቃሴ ተከሰተ። አሁን ትግሉና ፍጥጫው ከመንግስትና ከሥርዓቱ ጋር መሆኑ  ይፋ ሆነ።  ጊዜ ይወስዳል  እንጂ  የሕዝብን  ኃይል  የሚያስቆመው  የለምና  የንጉሱና  የአገዛዛቸው አቅም  ሳያስቡት  ባዶ ሆነ።  የኃይል  ሚዛኑን  መንግስት ሲያጣ “ጊዜ ስጡኝ”  ፣  “ደሞዝ  ጨምሬአለሁ”፣ “የነዳጅ  ዋጋ  ቀንሻለሁ”፣  “ሴክተር  ሪቪው  ተሰርዟል”  ወዘተ  ቢባል  ጥያቄው  የሥርዓት  ለውጥ  ሆኗልና አድማጭ ጠፋ። የዓፄ ኃ/ሥላሴ  ሥርዓት በተናጥል  ዘውዳዊ  አገዛዝ  በጥቅሉ ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜ አከተመ።

 

የየካቲት  1966   ዓ.ም.  ሕዝባዊ  አብዮትን  ተገን  አድርጎ  ሥልጣን  የተቆናጠጠው  ደርግ  ተቀናቃኙን ብቻ  ሳይሆን  አጠገቡ  ያሉትንም  እየረሸነ  17  ዓመት  ገዛ።  በጊዜያዊነት  ስም  ሥልጣን  የተቆናጠጠው ወታደራዊ አገዛዝ ቀስ በቀስ እራሱን እያጠናከረ ከኢማሌድህ – ኢሠፓአኮ – ኢሠፓ እራሱን በማሸጋገር  ይባስኑም  የኢትዮጵያ  ሕዝብ  ፌደራላዊ  ዴሞክራሲያዊ  ሪፓብሊክ  በማለት  ከወታደርነት የሲቪል መንግስትነቱን አውጆ “ዕድሜ ልክ” ሊገዛ እራሱን አዘጋጅቶ ነበር። በደርግ የአገዛዝ ዘመን በመቶ  ሺህ  የሚቆጠር  ቤተሰብ  በነፃ  እርምጃና  ቀይ  ሽብር  ሕይወቱን  አጣ።  በደርግ  አገዛዝም  ውስጥ በርካታዎች  እየታፈኑና  እየተረሸኑ  አንድ  አምባገነን  ፈላጭ  ቆራጭ  የደርግ  ሥርዓት  ወለደ።  ሀገር በጦርና   ሽብር   ታመሰች።   በመጨረሻም   መንግስቱ   ኃይለማርያም   ጋሻ   ከለላ   የነበሩትን   የራሱን ጄኔራሎች ሳይቀር በግፍ በመረሸን ለሁለት ዓመት ተንገዳገደ። በዚህ 17 ዓመት አገዛዝ ሀገር ያላትን ሀብትና   ገንዘብ   በደርግ  ጋሻ   ጃግሬነት  ለጦርነት   በማዋል  ሀገሪቷ   በአራቱም   አቅጣጫ   በጦርነት ተዘፍቃ፣  በድህነት  በልጽጋ፣  አፈናና  ግድያን  አስተናግዳ፣  ረሃብን  ጎረቤቷ  አድርጋ  ለተረኛ  አገዛዝ ተዳረገች። ደርግ ከጅምሩ በመላው ኢትዮጵያ በደረሰበት ተቃውሞ ጨምሮ በተለያየ አቅጣጫ የሚፋለሙትን   ኃይሎች   (ወያኔ፣   ሻብያ  ለአብነት)   መቋቋም   እያቃተውና  በአመቻቸላቸው   ቀዳዳ ተጠቅመው ሀገሪቷን ተቆጣጠሩ። ኤርትራ ተገነጠለች። ከአዲስ አበባ በቀር አብዛኛው ሰሜናዊ ግዛት በወያኔ/ሻብያ ቁጥጥር ሥር ውሎና አቅሙ ተሟጦ ደርግ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎችን ብላቴን ለሥልጠና ልኮ ነበር። ወያኔ አዲስ አበባን ሊቆጣጠር አንድ እርምጃ ቀርቶት 17 ዓመት ሙሉ  ሲለመን  የነበረው  ደርግ  ስለ  ሰላምና  ዕርቅ  ዘማሪ  በመሆን  ከወያኔ/ሻብያ/ኦነግ  ጋር  ቀጣይ የሥልጣን  ተጋሪ  ለመሆን  ሲደራደር  አምባገነኖች  እስከመጨረሻ  እስትንፋሳቸው  ሥልጣን  መልቀቅ እንደሚያንገበግባቸው ጠቋሚ ነው።

 

በኢሕአዴግ 27 ዓመት አገዛዝ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በማህበራዊ ሕይወት የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን አገኘ? ሀገር ምን እድገት አስመዘገበች? ወያኔ/ህወሓት ኢትዮጵያን በዘርና በቋንቋ ከፋፍሎ ኢትዮጵያዊነትን  ብሔራዊ  ስሜት  ለማጥፋት  ለአለፉት  27   ዓመታት  ሳይታክት  ሠርቷል።  “እኛ (ህወሓት)   ከሌለን   ኢትዮጵያ   ትበታተናለች”   የሚለውን   ሰንካላ   ስነልቦናዊ   ግንዛቤ   በሕዝብ   ላይ በመርጨት   በተለያዩ  ነገዶች  መሃል   ፍርሃትና  ጥርጣሬ  እንዲሰፍን   አድርጓል።  ዘርዘር  አድርገን ብንመለከት፦

 

 • በፖለቲካው ረገድ ስናይ የህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ሲጀመር ሀገሪቷን በቋንቋና በዘር ከመከፋፈሉም  በላይ   ኢትዮጵያዊነት   ብሔራዊ   ስሜትን   በማሽመድመድ   ዘረኝነት   ጎልቶ እንዲወጣ ጥረት አድርጓል። ለ27 ዓመታት በማጭበርበር፣ በጉልበት፣ በንቀት ያለምንም ተቀናቃኝ ዴሞክራሲን  ሽፋን አድርጎ የገዛ ብቸኛ  አገዛዝ ነው። ለዚህም ምሳሌ የ1997  ዓ.ም. የተሸነፈበትን  ምርጫ  በጉልበቱ  ወስዶታል፣  በቀጣይነት  የመጡትን  ምርጫዎች  አንዴ  99.6 ቀጥሎ 100  በመቶ አሸነፍሁ እያለ ሀገርና ሕዝብን የናቀ አገዛዝ ነው።
 • በኢኮኖሚው መስክ በአገዛዝ ዘመናቸው የሀገሪቷን አንጡራ ሀብት ሲዘርፉ፣ በሊዝ ስም ለባዕዳን ባለሀብቶች  ሲሸጡ  ኖረዋል።  ምስኪን  ነዋሪውን  ባልተጠና  መንገድ  ከኖረበት  ቀዬ እያፈናቀሉ የላስቲክና የጎዳና ተዳዳሪ በማድረግ እነሱ ቦታውን ለባለሀብቶች እየቸበቸቡ ጥሬ ገንዘብ ሲያካብቱ ኑረዋል። በማህበራዊ ሕይወት (ዕድርና የመሳሰሉት) ተጣብቆ የኖረውን የከተማ  ነዋሪ  በማፈናቀል  የነበረውን  የጠበቀ  ግንኙነት  በጣጥሶታል።  በማዳበሪያ  ስም  አርሶ አደሩን ከማሰቃየት አልፈው የሀገራችንን ብርቅዬ ሰብሎች እያመከኑና በመጤ ዲቃላ ዘሮች እየበረዙ ይገኛሉ። በዚህና የሌሎች ጥርቅሞች ውጤት ሀገሪቷን ወደ ዕድገትና ስልጣኔ ጎዳና ከመውሰድ ይልቅ ዛሬ የተራበውን ሕዝብ፣ በቀን አንዴ ተመጋቢውን፣ ከየምግብ ቤቱና ሆቴሉ  ትርፍራፊ  ገዥውን  ቤቱ  ይቁጠረው።  ኩሩ  ወገናችን  ዛሬ  ከቆሻሻ  ገንዳ  የሚበላ ሲፈልጉ ማየት ምን ያህል የወያኔ አገዛዝ ሕዝባችንን አዘቅት ውስጥ እንደከተተ አመላካች ነው።
 • በባህሉ ብንቃኝ የሀገራችን አኩሪ ባህልና ሰው አክባሪነት እንዲጠፋ፣ አኩሪ የክርስትናና እስልምና ሃይማኖት  ዕምነታችን  እንዲበረዝ፣  ሕፃናት  በየትምህርት  ቤቱ  ከሀገራቸው  ታሪክ ይልቅ  የባዕዳኑን  አምላኪ  እንዲሆኑ  የሚደረገው  ጥረት፣  ወጣቶችን  የተለያየ  ሱስ  ተጠቂዎች ይሆኑ  ዘንድ  የተሸረበው  ተንኮል  ዛሬ  ላይ  ሆነን  ስናየው  ሀገራችን  ጠንካራ  ተተኪ  ትውልድ እንድታጣ በወያኔ በኩል የተደረገው ጥረት ቀላል አይደለም። የሀገር ተተኪ ትውልድ ከተኮላሸ ዕድገት ሳይሆን ውድቀት እንደምታስመዘግብ አያጠያይቅም።

በአጭሩ  እነኚህን  ሁኔታዎች  ስንቃኝ  ወያኔ  ገና  በትረ  ሥልጣኑን  እንደያዘ  ይዞ  የተነሳው  ኢትዮጵያንና ሕዝቧን የማዳከም ዕቅዱ ነው ዛሬ ላይ ለውድቀት እያንደረደረው ያለው።

በጥቅሉ በወያኔ አገዛዝ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በማህበራዊ መስኩ ኢትዮጵያ ተጎድታለች ተዳክማለች።

ህወሓት/ወያኔ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንዳትኖር ከሥልጣን ዘመኑ ጀምሮ ታሪኳን ሲያንቋሽሽ፣ ሰንደቅ  ዓላማዋን  ሲያራክስ  እንደነበር  አይዘነጋም።  በሩቅ  ጊዜ  ትልማቸውም  የኢትዮጵያን  አንድነትና ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ስሜትን ለማጥፋት አነጣጥረው  የመጡባቸው ሦስት ጉዳዮች  አሉ። እነሱም፦

 1. የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን     ማጥፋት።   ለዚህም   ይረዳቸው  ዘንድ                   ቅርሶች መዝረፍ፣ ገዳማትን ማዳከም፣ ማውደም፣ ምእመናንን ማሰደድ
 2. የአማራን ዘር ማጥፋት። በረቀቀ የዘር ማጥፋት አማራውን መፍጀት፣ ማደህየት፣ ማደንቆር። አማራው በሌሎች ጎሳዎች/ነገዶች እንዲጠላ መዝመት፣ የአማራ ሴቶች እንዳይወልዱ ማምከን
 3. 3. የዓፄ ምኒልክን  ታሪክ  መበረዝ።  ለኢትዮጵያ  አንድነትና  ለግዛት  ሉዓላዊነት  የጥቁር  ሕዝብ ታሪክ  የሠሩትን  ምኒልክ  በወራሪነት  ታሪካቸውን  መበረዝ፣  “በጡት  ቆራጭነት”  ሐውልት ማቆም

ይህ  በ27   ዓመታት  የወያኔ  አገዛዝ  ተግባራዊ  ሆኗል፣  እየሆነም  ይገኛል።  በዚህ  መልኩ  ኢትዮጵያን በዘርና በቋንቋ ከፋፍለው በመንግሥት ስም የሀገሪቷን አንጡራ ሀብት በመዝረፍና ያቃታቸውን በማውደም  ሊገዙ  ካልሆነም  በጠነሰሱት  የዘር  ፖለቲካ ሀገሪቷን  ሊበትኑ  ለኢትዮጵያ  መዳከም  ከሚጥሩ ባዕዳን ጋር በዕቅድ የሚጓዙ መሆናቸው በሚገባ ሊጤን ይገባዋል።

የወያኔ  አስተዳደርና የገጠሙት መሰናክሎችን  በተለያየ ወቅት ከፍሎ ማየቱ  ጠቀሜታ ይኖረዋል። መነሻ ፦  ወያኔ ኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ስሜት የጎደለው

 ኢትዮጵያ በወያኔ አገዛዝ እስከ ከ1994

 

ወያኔ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረበት 1983 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1994 ዓ.ም. ድረስ ሀገሪቷን በማራቆትና በማደህየት  የተሞረከዘ ፖሊሲ  ይዞ  የተጓዘ  አገዛዝ  ነው። በዚህ  ወቅት ወያኔ  ከጣምራ  አጋሩ ሻብያ ጋር ኢትዮጵያን መዝብረዋል። በርካታ ንብረቶች ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ ተሻግረዋል። ኤርትራ ዋናዋ የቡና ላኪ የነበረችበትን ወቅት እናስታውሳለን። ይህ ዘመን በሻብያ የበላይነትና በወያኔ አጋርነት ኢትዮጵያን  የማድቀቅ  ዘመቻ  ነበር።  ጊዜ  ወደፊት  የተካሄደውን  ምዝበራ  ሠነድ  ተደግፎ  ለሕዝብ እንደሚያወጣው ይገመታል።

 

ቅንነት ቢኖር ወያኔና ሻብያ አምባገነኑን ደርግ ጥለው የኤርትራ መገንጠል ባላስፈለገም። ለዚህ ግንጠላ  ዋናውን  ሚና  በወቅቱ  የተጫወቱት  በጠ/ሚር  መለስ  ዜናዊ  የሚመራው  ወያኔ  ነበር።  ኤርትራ ተገነጠለች፣  “አሰብ  ለኢትዮጵያ  ከግመል  መጠጫ  ያለፈ  አገልግሎት  የለውም”  ተባለ  በወቅቱ  ጠ/ሚ። ሁለት አምባገነን መሪዎች በአንድ ሀገር ሊኖሩ አይችሉምና ወያኔም የሻብያ ጥገኛ መሆኑን አይመርጥምና ያለው መፍትሄ በአፋጣኝ የኤርትራን መገንጠል ዕውቅና ሰጥቶ ኢስአያስ አፈወርቂ እዚያው ኤርትራን ይዘው እንዲቀመጡ ማመቻቸት ነበርና ተደረገ። የሁለት አምባገነኖች ዝርፊያና ይገባኛል ባይነት ወደ ፀብ መጓዙ አይቀርምና በመሃላቸው መሻከርና መናቆርን ፈጠረ።

 

 ከ1994  – 1997  ፦ ወያኔ የሠበረው የመጀመሪያው አጣብቂኝ

ይህ  ወቅት  ወያኔ  በሁለት  ጉዳዮች  አጣብቂኝ  የገባበት  ነበር።  በአንድ  በኩል  በኤርትራ  የተጀመረው የድንበር  ይገባኛል  ጥያቄ  ሲሆን  በሌላ  በኩል  የወያኔ  መከፋፈል  ነበር።  ሻብያ  በወቅቱ  የነበረውን ወታደራዊ   አቅም   በመተማመንና   ኮትኩቶ   ያሳደጋቸውን   ወያኔዎች   በመናቅ   ጦርነት   በመቀስቀስ የሚፈልገውን  ድንበር  ሳይሆን  የኢትዮጵያን  መንግስት  በራሱ  አኳያ  ለመተካት  እንደሚችል  ተማምኖ ከበባውን እጅግ በተጠናከረ ምሽግ፣ ትጥቅና ስንቅ ጀመረ።

 

በወቅቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ አዲስ አበባን ጨምሮ በየከተማው ያለው ነዋሪ በሻብያ የሚደረገው ዝርፊያ  አንገብግቦትና  አስመርሮት ነበርና፣  በተጨማሪም  በየትኛውም  የሀገሪቷ  ክፍል  የኤርትራውያን “ነፃነት  ተቀዳጅተናልና  እኛ  ብቻ”  የሚል  ትዕቢት  ነዋሪውን  እያበሳጨና  እያስመረረ  የነበረ  ጉዳይ የተፈጠረው  ግጭት ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረለት።

 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳር ድንበሩ ሲነካና ሲደፈር እንደ ንብ አውራ ሆ! ብሎ መነሳቱ ታሪካዊ ሂደት ቢሆንም  ይበልጥ  በወያኔና  ሻብያ  ጣምራ  ዘረፋና  አፈና  መከራውን  ያየው  ሕዝብ  ቢያንስ  ከአንዱ ለመገላገል ከዳር እስከዳር ለመዝመት ተነሳ። በዚህ ሂደትም ሻብያን ተገላገለ። በወቅቱ በወጣቶች ዘንድ የነበረው መፈክር “ መልስ ወደ መለስ” እንደነበር አይዘነጋም።

 

ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ልጆች መስዋዕትነት የኤርትራን ወራሪ ድባቅ መትቶ ባድመን ተቆጣጠረ። በዚህ በኩል የነበረበትን ውጥረት በመጠኑም ቢሆን በወቅቱ ወጣት የነበሩ ዘር ሳይገድባቸው፣ ክልላችን አይደለም ሳይሉ  ባድመ መሬት ላይ በ10  ሺዎች የሚቆጠሩ አሸልበዋል።

 

በተያያዥነት  ህወሓት  በውስጡ  ክፍፍል  የተፈጠረበት  ወቅት  ነበር።  ይህ  ክፍፍል  ዋናዎቹንና  ወሳኝ የአመራር አካላት ያካተተ በመሆኑ ወደ ከፍተኛ ብጥብጥ ሊያደርሳቸው ይችል ነበር። ሆኖም ደካማ ጎናቸውን  ጠንቅቆ  የሚያውቀው  መለስ  ዜናዊ  ለእነሱም  ባላሰቡት  ሁኔታ  አውላላ  ሜዳ  ላይ  ጣላቸው። ህወሓትንና  አገዛዙን  ሙሉ  በሙሉ  በቁጥጥሩ  ሥር  አዋለ።  መለስ  ዜናዊ  “  በስብሰናል...” በሚሉ ቃላቶች አገዛዙን አወገዘ።

 

ከዚህ በኋላ እስከ 1997 ዓ.ም. መለስ ዜናዊ መንግስታዊ መዋቅሩን በተለይ ዋና ዋና የስለላ መረቦችን በቁጥጥሩ ሥራ አዋለ። ሁሉም ለሱ ይገዙ ዘንድ በተዘዋዋሪ መንገድ ቆላልፎ ያዛቸው። የፈለገውን ይሾማል፣ ያሻውን ይሽራል። በተሟላ መደላደል ህወሓት/ኢሕአዴግንና የአገዛዝ ሰንሰለቱን ተቆጣጠረው።

 

 ከ1997  –  መለስ ዜናዊ ዕረፍት ፦ ወያኔ የሠበረው ሁለተኛው አጣብቂኝ

 

1997   ዓ.ም.   የምርጫ  ሂደት  ለወያኔ  የመጨረሻው  ግብአት  ነበር።  ሆኖም  አልሆነም።  በነበረው የምርጫ  ሂደት  አዲስ  አበባን  ጨምሮ  መላ  ኢትዮጵያን  (ከትግራይ  በቀር)   በጋራ  የተቆጣጠሩት ቅንጅትና   ኅብረት   በጉልበት፣   በማስፈራራትና   ብሎም   በማሰር   ወያኔ   የነበረውን   ሂደት  ቀልብሶ ሊቀጥል  አስችሎታል። በትንሹ የ196  ወገኖችን ሕይወት የቀጠፈው  የወያኔ  አሸናፊነት አሳዛኝ  ቁጭት ለሕዝብ  ጥሎ  አልፏል።  በወያኔ  አስቸኳይ  ጊዜ  አዋጅና  በመለስ  ዜናዊ  “ጣት  ቆረጣ”  የተደናገጠው ተቃዋሚ  ቤቱ  እስርቤት፣  ጉዞው  ስደት  ሆነ።  ምንም  ከማድረግ  ወደ  ኋላ  የማይለው  ወያኔ  ለሁለተኛ ጊዜ የአገዛዝ ዘመኑን በንጹሃን ደምና ሕይወት አስቀጠለው። የተጋረጠበትን የስልጣን አደጋ አከሸፈው።

 

በቀጣይነት  ለ1997  ዓ.ም.  ምርጫ  መሸነፍ  ምክንያት  የሆነውን  በመቃኘት  ወያኔ  አስመሳይ  አካሄዱን “ለማስተካከል” እና ሕዝባዊ መልክ ለመስጠት ብልጭታ አሳየ። እስከ 1997 ዓ.ም. ዝርፊያው ጦዞ ምንም  ዓይነት  የልማት  እንቅስቃሴ  ያልታየው  ወያኔ  ሙሉ  በሙሉ  ከመዝረፍ  በመጠኑ  “እያሳዩ መዝረፍ” እሚለው ፖሊሲው ላይ ተሰማራ።

 

ባለቤትነታቸው  በአብዛኛው  ከትግራይ  ተወላጆች  ያላለፈ  የሕንፃ  ግንባታ  በተለይ  በአዲስ  አበባና በከተሞች ተጧጧፈ። የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት በአዲስ አበባና በየክፍለ ሀገሩ በሠፊው ይካሄድ ጀመር። አንዳንድ ልማታዊ ፕሮጀክቶችም ተጀምረው ተግባራዊ ይሆኑ ጀመር። በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ  የልብ  ትርታና  የብሔራዊ  ማንነት  መግለጫ  የሆነውን  ዐባይ  የመገንባት  ሂደት  መለስ  ዜናዊ እጅጉን   ተጠቀመበት።   እናቶች   ከመቀነታቸው፣   አባቶች   ከውስጥ   ኪሳቸው፣   ሠራተኞች   የወር ደሞዛቸውን፣  ነጋዴዎች  ከካዝናቸው  እጅግ  በመረባረብ  ሁሉም  ከአቅሙና  ከችሎታው  በላይ  “ባይ  ሲሳይ”  እያለ  ለገሠ።  የመለስ  ዜናዊ     “     መንግሥት”  ሠመረለት  የሚፈልገውን አቅጣጫ  አስያዘለት።  ከዚህ  ጋር  በተጨማሪ  የናቀውን  ባንዲራ  “  ቀን”  ብሎ  እንዲታወስ አደረገ ” ሌላው ትልሙ ውስጥ ተካተተ።

 

በዚህ  ወቅት  አፈናውና  እመቃው  እንደተጠበቀ  ለሀገሪቷ  የተዘረጋውና  የታሰበው  ዕድገትና  ልማት የኑሮ  ውድነቱን  ከሚገመተው  በላይ  አሻቀበው።  ለውጭ  ምንዛሬ  ሲባል  ወደ  ውጭ  የሚላኩ  ምግቦች ለሕዝቡ   መቸገርን   አከናነቡት።   የውጭ   ምንዛሪ   እጅጉን   መጨመር   መካከለኛ   ገቢ   ያለውን የኅብረተሰብ  ክፍል  አደኸየው፤  በጥቅሉ  ሕዝቡ  መብላት  እስኪያቅተው  ደኸየ።  በዚህ  ወቅት  ነበር ወቅቱን  ለማስታወስና  መብላት  አለመቻልን  ለመግለጽ  “ቁም”  የሚል  ቃል  አየር  ላይ  የዋለው። በተለይ  በምርጫ  1997   ዓ.ም.   ሙሉ  በሙሉ  በአዲስ  አበባ  የተሸነፈው  ወያኔ  ነዋሪውን  በምግብ ቀጣው፣ በልማት ስም እያፈናቀለ ማህበራዊ ህይወቱን አመሰቃቀለው።

 

መለስ ዜናዊ  የስልጣን እርከኑን  በሚገባ ለማጥበቅ ከ1997  ዓ.ም.  ወዲህ ይበልጡን ሠርቷል። አንዳንድ የህወሓት መስራች አባላትን ከአጠገቡ በማራቅ በሌሎች ተክቷል። ለዚህም ሂደቱ እንዳሻው እንዲያሾራቸው  ጠ/ሚ  ኃይለማርያምን  አጠገቡ  አምጥቶ  ሾማቸው።  መለስ  ዜናዊ  ወደ  አንድ  ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ገዢ እያደገ ሲመጣ “ነፍሱን ይማረውና” ሞት ቀደመው።

 

 ከመለስ ዜናዊ ዕረፍት – ኢሬቻ 2009 ዓ.ም.

 

ከመለስ  እልፈት  በኋላ  የህወሓት  አመራር  ጠንካራና  እንደመለስ  ጮሌና  ብልጥ  አመራር  ተሳነው። ህወሓት እርስ በርሳቸው ላለመበጣበጥና ላለመባላት ኃይለማርያም ደሳለኝን ጠቅላይ ሚኒስቴር አድርገው   መቀጠሉን   ተያያዙት።   ግና   በዘመናቸው   ጀመርነው   ያሉትን   “ልማታዊ   መንግስት” ለማስቀጠል ከመጣር ይልቅ ዝርፊያው ላይ እጅጉን ዘመቱበት። እያንዳንዷ የሀገሪቷ እንቅስቃሴ ከታች   እስከላይ   በጉቦ   ተዘፈቀ።   የዝርፊያው   ሽሚያ   ከቁጥጥር   ውጭ   በሆነ   አኳያ   ተካሄደ። የመጨረሻው  ዘመናቸው  ደርሷልና  የገቡበትን  የሕዝብ  ቤት  መዝረፍ  ቀጠሉ።  አሁን  በልማት  ስም ቤት እያደሱ እንደማይኖሩ ተገንዝበውታልና ያለውን ንብረት በመሸጥ በጥሬ ገንዘብና ዶላር ዝርፊያ ተጧጧፈ።  በተቃራኒው  ሕዝቡ  የሚላስ  የሚቀመስ  አጣ።  ሕጻናት  ከትምህርት  ይልቅ  ወደ  ልመና ገቡ። በጫት፣ በሐሺሽ፣ በሺሻ እንዲደነዝዝ የተፈረደበት ወጣት ትውልድ ይበልጥ ተስፋው እንዲሟጠጥ  የሚደረገው  ዘመቻ  ተበራከተ።  ሃይ  ባይ  የሌላት  ሀገር  ተራቆተች።  ልጆቿ  ዝርፊያውን፣ ረሃቡን፣ እንግልቱን፣ እሥሩን፣ ግርፊያውን፣ ግድያውን፣ስደቱን፣… ሊቋቋሙት አልቻሉምና የመጨረሻ   ኃይላቸውን   አጠናክረው   በየአቅጣጫው   ወያኔ   ላይ   ተነሱበት።   ከጊዜ   ወደ   ጊዜ እየተጠራቀመ  የመጣው  ቁጣ  በተለይ  በኦሮሞ  ልጆች  አካባቢ  አድማሱን  እያሰፋ  ይነጉድ  ጀመር። ከዚህ ጋር ተያይዞ በ2009 መስከረም 22 ቀን በተከበረው ኢሬቻ በዓል የአገዛዙ ወታደሮች በከፈቱት ተኩስ   የተፈጠረው   አሰቃቂ   ዕልቂት   ይበልጥ   የትግሉን   ሞተር   አንቀሳቀሰው።   ወያኔ   የማይፈራ የወረቀት ላይ ነብር እንደሆነ ኢትዮጵያ ልጆቿ በደማቸው ማሳየት ጀመሩ። አገዛዙ ማመን እስኪያቅተው እምቢ ያለ ሕዝብ ጥይት እንደማይበግረው አሳየ፤ እያሳዩ ይገኛሉ።

 

የሙስሊሙ  ህብረተሰብ  “ድምፃችን  ይሰማ”  እንቅስቃሴ  ያለማቋረጥ    በተጠናከረ  መልኩ  መቀጠሉ በርካታዎችን ለእስርና ለእንግልት መዳረጉ በዚሁ ወቅት የተከሰተ ክስተት ነበር።

 

 ከ 2009  ዓ.ም.  – 2010  አጋማሽ ወያኔ የሚሠብረው ሦስተኛው አጣብቂኝ ???

 

ወያኔ/ህወሓት ሕዝባችንን ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው ዘርና ቋንቋን መሠረት ያደረገው ክፍፍል ወደ ራሱ ዞረበት። ይህ የዘር ክፍፍል በጥቅሉ አንዱ ዘር ከሌላው እንዳይስማማና ተራርቆ እንዲተያይ፣  ኢትዮጵያዊነት  ስሜቱን  እንዲያጣ፣  ብሎም  አካባቢያዊ  ግጭት  እያደረገ  እንዲዘልቅ የታቀደ  ሤራ  ነበር።  ሆኖም  የኢትዮጵያ  ሕዝብ  ትዕግስት  ቢላበስም  የሚታለል  አይደለም።  የሁሉም ችግር አንድ ነው። ረሃብ፣ ድንቁርና፣ በሽታ፣ መታፈን፣ ስደት፣ እስር፣ ግርፊያ፣ ግድያ.  .  .። የትም ዞር  ቢሉ  በደም  የተሳሰረበት  አንድነቱ  አብሮት  አለ።  አንዱ  ሲገረፍ  ሌላው  ያመዋል።  27   ዓመት የተቀጠቀጠበትን ዘረኝነት በጥሶ ወያኔን በፈጠረው ክልልና ዘር ምላሽ ይሰጠው ጀመር። እንቅስቃሴ የኦሮሞ   ልጆች   በኦሮሞነታቸው   ተሰባስበውና   “ችን   ደማቸው”   ብለው   ሁለት   እጆቻቸውን

 

አጣምረው ተነሱበት።  አማራው  በነገዴ  ላይ  የሚደረገው  ዕልቂት ይብቃ  ብሎ  “ክተት”  አለበት።  በዘር ከፋፍሎ ሊገዛ ትልሙ የሆነ ወያኔን በዘር ተደራጅቶ አጣደፈው። ቄሮና ፋኖ የትግል ዓርማ ሆነ።

ይህ አካባቢያዊ እንቅስቃሴ አድማሱን እያሰፋ ወያኔን ፋታ አሳጣው። የአጋዚ ዱላ ቢቀጠቅጠው፣ ጥይት ቢዘንብበት “እምቢ ለሀገሬ” ያለ ጀግና ትውልድ ሀገር ዳግም አፈራች። የህወሓት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይበልጥ ለትግሉ  ጥንካሬ ሰጠው። የተለያዩ  የኢትዮጵያ ነገዶች/ጎሳዎች  ፀረ-ወያኔ  ተጋድሎ እንደተጠበቀ  በተለይ  በኦሮሞና  በአማራው  በኩል  የሚደረገው  ተጋድሎ  አድማሱን  እያሰፋ  አገዛዙን የመጨረሻ  የሞት  አፋፍ  ላይ  አደረሰው። ትግሉ  አሁን  እንደ ኦሮሞ  ልጆች “ዳውን  ዳውን  ወያኔ”  ሆነ! መፍትሄው  የወያኔ  መውደቅ  ብቻ  እንደሆነ  የተገነዘበው  ሕዝባችን  በየአቅጣጫው  ዋናው  ጠላቱ  ወያኔ ላይ  አነጣጠረ።  ትግሉ  ጥንካሬ  ባገኘ  ቁጥር  ወያኔና  ጋሻ  ጃግሬዎቹ  የሚይዙ  የሚጨብጡትን  አጡ። ቢያስሩት፣   ቢገርፉት፣   ቢገድሉት፣   አዋጅ   በአዋጅ   ቢንጋጋ   ጊዜው   የወያኔ   ማብቃት   ነውና አልተቻለም። የአጋዚ ጥይት ትግሉን ሊገድል አልቻለም። ከሕዝብ ኃይል በላይ ምንም እንደሌለ ልጆቻችን አሳዩ፤ እያሳዩ ይገኛሉ። ይህ ሕዝባዊ ተጋድሎ አዲስ ክስተት ብቅ አደረገ “ኢትዮጵያዊነት” በልጆቿ ተጋድሎ  በጥሶ ወጣ። ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ብቅ አሉ።

 

 ከጠ/ሚ/ር ዶር ዐቢይ አህመድ በቀጣይነት

 

የወያኔ 27 ዓመት ዘረኝነት እንዳልሰራና የትም እንደማይደርስ ክብር ለኢትዮጵያ ልጆች ይበልጥ የታየበት  ወቅት  ቢኖር  ያለፉት  ሁለትና  ሦስት  ዓመታት  ጉዞዎች  ናቸው።  ኢትዮጵያዊነት  አቀንቃኝ እነ በቀለ ገርባን፣ ለማ መገርሳን፣ ዐቢይ አህመድን ብቅ አደረገ። የነ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ መራራ ጉዲና፣ እስክንድር ነጋ፣ አንዱዓለም አራጌ፣ ተመስገን ደሳለኝና ሌሎች መከራና ስቃይ ሳይዘነጋ። ግራ የተጋቡት “ምን ውስጥ ከተተኝ” ያሉት የዋህም፣ አስቂኝም የሆኑት ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቢሉት…ቢሉት እንደማይሆን አውቀው “በቃኝ፣ ልቀቁኝ” ድምጻቸውን አሰሙ። በሕዝብ ተጋድሎ አጣብቂኝ  የገባው  አገዛዝ  እራሱ  የመናጋት  ምልክት  ሆነና  የዕዝ  ፖለቲካው  ገለባ  ሆነበት።  መላ የህወሓት  አባላት  እጅ  ቢነፍጓቸውም  የሕዝብ  አመጽ  ያየለባቸው  ዶር  ዐቢይ  አህመድን  ለጠቅላይ ሚንስትርነት መረጡ።

 

ዶር    ዐቢይ    አህመድ    የጠ/ሚንስተርነቱን    ሹመት    ሲረከቡ    ባደረጉት    ንግግር    በ27     ዓመት የህወሓት/ኢሕአዴግ   አገዛዝ   ዘመን   ተደርጎ   የማያውቀውን   ኢትዮጵያዊነትን   የንግግራቸው   ምሰሶ አደረጉት። ደጋግመው ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ስሜት በተላበሰ መልኩ አደመቁት። በብዙዎች ዘንድ መልዕክታቸው  ተወደደላቸው።  ስለ  ኢትዮጵያዊነት  መሰበኩ  ለብዙ  ዓመታት  ሰምቶት  አያውቅምና፤ ከጆሮው   የራቀውን   ሕዝብ   የልብ   ትርታ   አገኘ።   በተዘዋወሩበት   አካባቢ   ሁሉ   ኢትዮጵያዊነትን አስመልክቶ ሲናገሩ የደመቀ ምላሽ ምልክቱ ሕዝባችን ሀገሩን፣ ኢትዮጵያን መፈለጉን ያንፀባርቃል።

 

በኦሮሞ፣ በደቡብ፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአዲስ አበባ አካባቢ በአደረጉት ንግግር ሁሉም ኢትዮጵያዊ  አንድነቱን  አሳይቷቸዋል።  አንድነቱ  እንደማይናጋ  በስሜቱ  አንፀባርቋል።  ህወሓት/ወያኔ በተለይ   አማራውንና  ኦሮሞውን   ለማቃቃርና   ለማፋጀት   ገና   ሥልጣን   ከጨበጠ  ማግስት   ጀምሮ ያልፈነቀለው  ሤራ የለም። በዚህ  ሂደቱም  የንፁሃን  ሕይወት ተቀጥፏል። ይህ  የዘር  ዕልቂት አድማሱን እያሰፋ ይጓዝ ዘንድ የወያኔ ግብ ቢሆንም ከሽፎበታል። በኦሮሞና በአማራ መካከል የርስ በርስ ግጭት እንዲነሳ  ምኞቱ  የነበረው  ወያኔ፣  ይህንን  እልቂት  እንዲያጋግሉለት  ጥረት  ቢያደርግም  በተቃራኒው ኢትዮጵያዊነት  ማዕተባችን፣  ኢትዮጵያዊነት  ክብራችን  ያሉ  ብቅ  አሉበት።  ወደ  አላስፈላጊ  አቅጣጫ ሊጓዝ  የሚችለውን  አደጋ  አስቆሙት።  ለሁላችንም  የሚበጀው  ኢትዮጵያዊነት  ነውና  ኦሮሞን  ከአማራ አንድነቱን  አጠበቁት፣  ዋናው  ጠላት  ወያኔ  ላይ  አነጣጥሮ  ሀገሩን  እንዲያድን  የሚደረገው  ጥረት በአንዳንድ  ቅን  ኢትዮጵያውያን  ጥረት  ጎልቶ  ብቅ  አለ።  የወያኔ  ኢትዮጵያዊነትን  የመደምሰስ  ሤራ የውሃ  ሽታ  ሆነ።  ዛሬ  በሀገራችን  በሁሉም  አቅጣጫ  ስለ  ኢትዮጵያዊነት  ሲዘመር፣  ሰንደቅ  ዓላማዋ ሲውለበለብ ጭብጨባው ይደምቃል። ይህ ነው የሕዝብ ምላሽ።

 

 የጠ/ሚር ዶር ዐቢይ አህመድ ንግግሮች፦

 

ዶር  ዐቢይ  አህመድ ጠ/ሚር  ከሆኑበት ወቅት አንስቶ  ያሰሟቸው  ንግግሮች  በኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ስሜት መታጀቡ እንደተጠበቀ አንዳንዴ በጥያቄ (???) ምልክት እንዲቀመጡ ያደረጓቸው ሁኔታዎች ይስተዋላሉ።

 

 • ቀዳሚው ተግባራችን  በየአካባቢው  የተነሳውን  “ብጥብጥ”  በማስቆም  የተጀመረውን  ልማት በማስቀጠል ለቀጣዩ ምርጫ መዘጋጀት
 • ስለ ወልቃይት ጉዳይና ስለ ዲያስፖራው ያደረጉት
 • ስለ ትግራይ ሕዝብ ወርቃማነት ከመለስ ዜናዊ ባላነሰ መደስኮር

 

በቀጣይነት ከሀገር  በመውጣት በሱዳን አሁን ደግሞ በኬንያ እያደረጉ ያሉት ጉዞ ምናልባት ከአካባቢና አጎራባች ሀገሮች ጋር ቀና  ግንኙነት ለመመስረት የታሰበም ቢሆን  በሀገር  ቤት የተንጠለጠሉ  ጉዳዮችን ቅድሚያ መስጠት አይገባቸውምን?  የሚል ጥያቄ ቢያስነሳ አግባብነት አለው።

 

 ጠ/ሚሩ “የዘነጓቸው” ሊያነሷቸውና ሊተገብሯቸው የሚገቡ ጉዳዮች፦

 

 • ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሁሉም ፖለቲካ እስረኞች መለቀቅ። እዚህ ላይ በግለሰብ ደረጃ ከተኬደ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለምን ተረሳ?
 • የአስቸኳይ ጊዜ  አዋጁ  ሙሉ  በሙሉ  መነሳትና  የህወሓት  አጋዚ  ሠራዊት  ከየአካባቢውና ከተለያዩ ተቋማት (በተለይ ትምህርት ቤቶች) ለቆ መውጣት
 • ሀገር ቤት ያሉትን ብቻ ሳይሆን በውጭው ዓለም ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች በሀገር ቤት ገብተው እንዲንቀሳቀሱ በአግባቡ ጥሪ ማድረግ

 

ጠ/ሚሩ  በስልጣናቸውና  የአቅማቸውን  ሊተገብሩ  የሚገባቸውን  እንኳ  ትኩረት የሰጡት  አይመስሉም። 27 ዓመት ተቀጥቅጦ የተነሳ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በምንም ማታለያ እንደማይቆም መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል። ሕዝባችን እጅግ አስተዋይነቱ የህወሓት/ወያኔን ባህሪ ከማንም በላይ እየተረዳ መታለል ሳይሆን አሁንም ለጠ/ሚሩ ጊዜ እየሰጣቸው ይገኛል። በመላዋ ሀገሪቷ በተለይ በኦሮሞ፣ በአማራው፣   በጋምቤላውና   በደቡቡ   ሕዝባችን   የሚደረጉት   ፀረ-መንግስት   እንቅስቃሴዎች   ሕዝቡ እራሱን   በራሱ   እየመራ   እንደሚያካሂደው   ሁሉ   የሚፈልገውን   ምላሽ   እስኪያገኝ   እንደሚቀጥል ይጠበቃል።

 

 የሕዝብ ጥያቄ፦

 

ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ተዛማጅ የፖለቲካ ጥያቄዎች እንደተጠበቁ

 • የህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ማብቃት
 • የህወሓት/ኢሕአዴግ ሕገ መንግስት ማብቃት
 • በህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን ያለ አግባብ ለተቀሰፉ ሕይወቶች ተጠያቂዎችን ለፍርድ ማቅረብ
 • በህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ   ዘመን   ያለ   አግባብ  የተዘረፉ   የሀገርና  የሕዝብ                            ንብረቶች መመለስና ዘራፊዎቹን ለፍርድ ማቅረብ

እነዚህ  መሠረታዊ  ጉዳዮች  በጥቅሉ  ሲተረጎሙ  የሥርዓት  ለውጥ  ጥያቄ  ናቸው።  ከላይ  የተጠቀሱት ሁኔታዎች ተግባራዊ ሲሆኑ።

በቀጣዩ ዘመን

 • ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶች ያሳተፈ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ተግባራዊ ይሆናል
 • በተለያዩ አገዛዞች ዘመን በሀገሪቷ ለተፈጠሩ ችግሮች ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄ ለመስጠት ብሔራዊ ዕርቅ ይካሄዳል
 • ያለምንም ገደብ የኢትዮጵያን ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተግባር ላይ ማዋል
 • ከትውልድ ወደ   ትውልድ   የሚተላለፍ  አዲስ  ሕገ  መንግስት   የተለያዩ  የሚመለከታቸውን አካላት አካቶ ማርቀቅና በሕዝባዊ ውይይት ለሕዝበ ውሳኔ ማቅረብ
 • በመጨረሻም በአዲሱ ሕገ መንግሥት መሠረት አስፈላጊ ተቋማትን መሥርቶና አጠናክሮ በነፃ ፖለቲካዊ ውድድር ነፃ ምርጫ ተካሂዶ ሕዝብ በመረጠው ፓርቲ ሀገሪቷ እንድትተዳደር መንገዱን ማዘጋጀት

 

 ቀጣዩ መንግሥት

 

ከህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ በኋላ ቀጣዩ መንግስት ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜ የኢትዮጵያንና የሕዝቧን   ችግር   የሚፈታ   መሆን   ይኖርበታል።   ችግሮቹን   ተሸክሞና   አለባብሶ   በለውጥ   ስም ኢትዮጵያዊነትን  እየደሰኮሩ  ብቻ  መጓዝ   የትም  እንደማያደርስ  ሊሰመርበት  ይገባል።  የመንግስት ለውጥ ተደረገ ማለት መሠረታዊ ጉዳዮች እስከ አልተመለሱ ድረስ ነፃነት መጣ ማለት አይደለም። መሠረታዊ የሀገሪቷና የሕዝብ ጥያቄዎች መመለስ ጉዳይ ቀዳሚ ለማድረግ የሁሉንም ጥረት ይጠይቃል።  ይህ  ጥረት  በጋራ  ተመክሮ  ተግባራዊነቱም  ላይ  ቅንነትን  ከተላበሰ  መጪዋ  ኢትዮጵያ የልጆቿ  ትሆናለች።  ቀጣዩ  መንግስት  በለውጥ  ስም  ሀገር  ላይ  የሚከመር  ከሆነ  ትግሉ  ይቀጥላል። ኢትዮጵያና  ሕዝባችን  ለግማሽ  ምዕተ  ዓመት  የተሸከሙትን  መከራና  ችግር  መፍትሄ  ለመስጠት ለቀጣዩ መንግሥት ጥርጊያ ጎዳና ለማመቻቸት ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች በቅንነትና በመተማመን መንፈስ መምከር ይጠበቅባቸዋል።

 

 ቀጣይ ሂደትና የታጋይ የፖለቲካ ድርጅቶች ሚና

 

 • በዶር ጠ/ሚር ዐቢይ አህመድ እየተቀነቀነ ያለውን ኢትዮጵያዊነት ለማጠናከር መረባረብ
 • በሀገሪቷ ብቅ  እያሉ  የመጡትን  ሀገር  ወዳድ  ኢትዮጵያውያን  ለማ  መገርሳ፣  በቀለ  ገርባ፣ እስክንድር ነጋ፣ አንዱዓለም አራጌ፣ ተመስገን ደሳለኝ እና መሰሎችን የጀመሩትን ትግል አጠናክረው ይገፉበት ዘንድ እገዛ ማድረግ
 • ከFebruary  16-19,   2018   በሲያትል  የተካሄደው  የባለድርሻዎች  ጉባኤ  በአሳለፈው  ውሳኔ መሠረት ቀጣዩ ጉባኤ በአፋጣኝ በሀገር ቤት እንዲካሄድ መጣር
 • በሲያትሉ ጉባኤ ያልተካተቱ በሀገር ቤትም በውጭው ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ዳግም ጥሪ ተደርጎላቸው ጠንካራ ህብረት ለመፍጠር መዘጋጀት

 

 አዲሱ ትውልድና ኢትዮጵያ

 

ትውልድ ይመጣል ትውልድ ይሄዳል። ቀጣይ ኢትዮጵያ የአሁኑና የአዲሱ ትውልድ ናት። ከአለፉት ትውልዶች  የትግል  ታሪክ  ጠንካራና  ደካማ  ጎን  በመነሳት  ለሀገራችን  አዲስ  አቅጣጫ  ይዞ  መነሳት ይኖርበታል። ዘረኝነትና የቋንቋ አከላለል አክትሞ ኢትዮጵያ የበርካታ ቋንቋ፣ ጎሳዎችና ነገዶች ባለሀብትነትዋን ተረድቶ  በጋራና  በአንድነት ሀገሩን ዘላለማዊ ለማድረግ ብቃቱን ማሳየት ይኖርበታል። የሁሉም  ጎሳዎች/ነገዶች  ክልል  ኢትዮጵያ  ትሆን  ዘንድ  ትውልዱ  ሀገራዊና  ሕዝባዊ  ኃላፊነት  አለበት። ወያኔ  27  ዓመት  በዘር  ፖለቲካ  የቀጠቀጠውና  ያሳደገው  ትውልድ  ዛሬም  ሳይበገር  ኢትዮጵያዊነቱን ከፍ አድርጎ እየተፋለም ሲታይ ያኮራል፤ እውንም “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!” ያሰኛል። በየጊዜው ለእስር፣ ለድብደባና፣ ለግድያ የተዳረጉት ወጣቶች ደግሞ ለዚህ ምስክር ናቸው። ዛሬ

 

ኢትዮጵያዊነት ዳግም እያበበ ነውና  አጠንክረን ልንይዘው  ይገባል። ኢትዮጵያዊነት ከፍ ሲል  ዘረኝነት ይቀበራልና። ዘረኝነት ሲቀበር ወያኔ/ህወሓት በነበር ይታወሳልና። ትግል ከሆነ ተግባራዊ መሆን ያለበት  ይህ  ነው።  ትግሉ  ለመብትና  ነፃነት  ከሆነ  ሥልጣን  የሕዝብ  እንዲሆን  የዛሬው  ትውልድ በአዲስ መንፈስና ራዕይ ተደራጅቶ ብቅ ማለት ይጠበቅበታል። የዚህ ጊዜ ሽርፍራፊና የጥገና ለውጥ ሳይሆን መሠረታዊ  የሥርዓት ለውጥ በሀገራችን እውን ይሆናል።

 

 መደምደሚያ

 

 የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግልና የሥርዓት ለውጥ

 

በአጠቃላይ     ከላይ    የተዘረዘሩት     የሥርዓት    ለውጥ     ጥያቄዎች    ተግባራዊ     ይሆኑ     ዘንድ ህወሓት/ኢሕአዴግን   ባልተቋረጠ   ሕዝባዊ   ዐመጽ   ማስገደድ   አስፈላጊ   ነው።   ህወሓት/ኢሕአዴግ ከአልፉት አገዛዞች ትምህርት ቀስሞ የመጣበትን ሕዝባዊ ማዕበል በጉልበትና በኃይል ሊመክት እንዳልቻለው  ተገንዝቦ፣  በብልጣብልጥነትም  እወጣዋለሁ  ብሎ  ካሰበ  ዛሬ  ሕዝባችን  በተለይ  ወጣቱ ትውልድ በቆራጥነት የአገዛዙን መለውጥ እንደፈለገ ተገንዝቦ፤ በመጠኑም ቢሆን በጠ/ሚር ዐቢይ አህመድ እየተቀነቀነ ያለውን ለየት ያለ አካሄድ በመጠቀም ከሀገርና ከሕዝብ ጋር ሥልጣን ለማስረከብ ይታረቅ     ዘንድ    የመጨረሻ     ዕድሉን     ይጠቀምበት።    ይህ     ካልሆነ     የመጨረሻው    ጉዳት ለህወሓት/ኢሕአዴግ  እንደሆነ  አያጠራጥርም።  የመንግሥት  ዘላለማዊ  የለምና  የህወሓት/ኢሕአዴግ የውድቀቱ መጨረሻ አፋፍ ላይ ነውና ሕዝብንና ሀገርን ይመልከት።

 

ዶር ዐቢይ አህመድን ጠቅላይ ሚንስትር ያደረገው የኢትዮጵያ ልጆች ያልተቋረጠ ትግልና መስዋዕት ነት ነውና።  ካባ እን

 አድርጎታልና ትግሉ እጁን እስኪሰጥ መቀጠል ይኖርበታል። አካባቢያዊ እንቅስቃሴው ዶር ዐቢይ አህመድን ለሥልጣን  እንዳበቃ ወደ ሀገራዊ  መልክ ተቀናጅቶ  የኢትዮጵያን ሕዝብ  የሥልጣኑ  ባለቤት ማድረግ ይኖርበታል። የዚህ ጊዜ ሕዝቡ የዜግነት መብቱን አስከብሮና ጥያቄዎቹን መልሶ እራሱ በመረጠው መንግስት እፎይ ብሎ ለልማትና ለእድገት ሆ! ብሎ ይነሳል።

 

የሀገራችንን መሠረታዊ ችግሮች እልባት ሰጥቶ ኢትዮጵያ የልጆቿ እንድትሆን፣ የዜግነት መብት የተከበረባት ሀገር ከተመኘን፣ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት/ፓርቲ በነፃ ተንቀሳቅሶ ሕዝብ በመረጠው ሀገር ከተዳደረች፣ ለትውልድ ዘለቄታ ያለው ሕገ መንግሥት በአግባቡ ተቀርጾና በሕዝብ ጸድቆ ተግባራዊ እንዲሆን፣ ሕዝባችንን ከረሃብ፣ ከችግር፣ ከድንቁርና፣ ከበሽታ ወዘተ ለማላቀቅ ካሰብን በቅድሚያ ዘርን መሠረት ያደረገው የወያኔ አገዛዝ መወገድ አጠያያቂ አይደለም።

በተለይ ለአለፉት ሦስት ዓመት እጅግ የከረረ ሕዝባዊ ተቃውሞ በመላው የሀገሪቷ ክፍል ያጋጠመው ህወሓት/ኢሕአዴግ የችግሩ ቁርሾ ሥርዓቱና አገዛዙ መሆኑን ተገንዝቦ ለበርካታ ጊዜ ሲጠየቅ የነበረውን ሰላማዊ የሽግግር መንግስት ሊሰማም አልፈለገም። ከጊዜ ወደ ጊዜ ወታደራዊ ኃይሉን በመጠቀም ሕዝብ እየፈጀ ይታያል። የከተማውንም ሕዝብ አሁንም ተመጣጣኝ ያልሆነ ግብር ከአቅም በላይ በመጫን፣ የያዙትን የንግድና መኖሪያ ቤት በልማት ስም እያፈናቀለና እያሸገ በመቸብቸብ ላይ ነው።  በጥቅሉ  ሀገርን  ሊያወድም፣  ታሪክ  ሊያጠፋ  በኢትዮጵያ  ላይ  የመጣ  አገዛዝ  መሆኑን  በመረዳት ያለምንም ማቅማማት ታግሎ መጣል ዋነኛ መፍትሄ እንደሆነ ይታያል። በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ በአትኩሮት እየተከታተለ ያለውን የጠ/ሚር ዶር ዐቢይ አህመድ አካሄድን በመጠቀም ከሕዝብ ጋር ለይቅርታ ካልተዘጋጀ የተጀመረው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ቀጥሎ የድሉ ባሌቤት ሕዝባችን እንደሚሆን ጥርጣሬ አይኖርም።

 

 • ምስጋና
  • ለቪዝን ኢትዮጵያ፣ ለኢሳት
  • እዚህ ለተገኛችሁ ታዳሚዎች በሙሉ
  • ይህንን ኮንፈረንስ በቀጥታ ስርጭት እየተከታተላችሁ ላላችሁ
  • በትግሉ ጎዳና ሕይወታችሁን ለከፈላችሁ ውድ ወገኖቻችን
  • ለኢትዮጵያችን የግዛት  ሉዓላዊነትና  ለሕዝባችን  አንድነት  ከህወሓት/ኢሕአዴግ  አገዛዝ ጋር ያላቋረጠ ትግል እያደረጋችሁ ላላችሁ ወገኖች
  • ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ
  • ለአንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ አመራር አካላትና ለሁሉም አባላት

 

 • የጽሁፉ አቅራቢ ነሲቡ ስብሐት (አቶ)
  • ሰኔ 28-29፣  2004   በዳላስ  የተመሠረተው  የ«ያ  ትውልድ  ተቋም»   ቦርድ  ሰብሳቢ (yatewlid.com)
  • መስከረም 16    ቀን    2008     ዓ.ም.     የተቋቋመው     “አንድ    ሀገር!     አንድ                ሕዝብ!

ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ” ሊቀመንበር (www.ethiopiachen.org)

 • መስከረም 2007 “ፍፁም ነው እምነቴ የከፍተኛ 15 (ካዛንችስ አካባቢ) ቀይ ሽብር እውነተኛ ታሪክ” መጽሐፍ ደራሲ
 • በሙያ በሀገር  ቤት    በኢትዮጵያ   ጂዮሎጂካል    ሰርቬይ   ከ1978    –    1995             ዓ.ም. በጂዮፊዚስትነት ያገለገልኩ
 • በሰሜን አሜሪካ   ከ1997    ዓ.ም.    (2005)      ጀምሮ   እስከ   አሁን             በጂዮፊዚስትነት እያገለገልኩ እገኛለሁ።

 

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!! እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!

ነሲቡ ስብሐት፤ አንድ ሀገር!  አንድ ሕዝብ!  ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ቅዳሜ ግንቦት 4 ቀን 2010 ዓ.ም. (May 12, 2018)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.