ብሔረተኝነትን እኛ አማሮች አልጀመርነውም፤ የምንቋጨው ግን ይመስላል

ልሣነ ዐማራ

የ1960ዎቹ ትውልድ ንጉሳዊውን ስርዓት በመታገል ያነሳቸው የነበሩት የለውጥ ጥያቄዎች በዋነኛነት የሚቀመሩት ኤርትራን ከኢትዮጵያ የመገንጠል ስውር አደረጃጀትና ተልእኮ በነበራቸው ኢትዮጵያ ጠል ግለሰቦች እንደነበር ታሪክ ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል ።

እነዚህ ስውር እጆች ከንጉሳዊ ስርአቱ መውደቅ በኋላም የኢትዮጵያ ፖለቲካ የፊት መስመር ተሰላፊ ሆነው የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የክብር ዘብ በነበረው አማራ ማህበረሰብ ላይ ነጣይ የማጥቃት ስልት ነድፈው አፈጻጸሙን ለማስተግበር በመታተር በጥቁር ድርሳን ላይ ተመዝግበዋል ።

በባለ ስውር እጆቹ ዘሪሁን ክሸ እና ጓደኞቹ የተጠነሰሰው የጥላቻ ፖለቲካ በእነ ዋለልኝ መኮነን ቀማሽነት አዋጭነቱ ተረጋግጦ ለፍጆታ ውሏል ።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ጭቆና ከአለማቀፉ እሳቤ ባፈነገጠ ሁኔታ ከመደባዊ ባህሪው ተፋቶ ከብሔር ጋር ተጋብቶ ‘ብሔራዊ ጭቆና’ ተብሎ በአለም የፖለቲካ መድረክ ተከስቷል ።

የዚህ ዘባተሎ እሳቤ ዋነኛ ግብ በዘመኑ ለኢትዮጵያ አንድነትና ክብር ዋነኛ ባለድርሻ በመሆን ለስውሩ ኤርትራን ከኢትዮጵያ የመገንጠል ትግል መካች ይሆናል በማለት ስጋት የፈጠረባቸውን የአማራ ብሔረሰብን ከሌላው ኢትዮጵያዊ አጋሩ ጋር ማቃረንና በውስጣዊ ግጭት አገሪቱን በማተራመስ ውጫዊ የወንድ በር ማግኘት ነበር ።

እናም የትህነግንና ጀብሃን አማራ ጠል ስውር ግብ ጎፈሬውን ነቅሶ በግንባር ቀደምነት ያስፈጸመው ያ- ትውልድ በዚህ በእኛ ዘመን አፍርቶ የጎመራው የብሔር ፖለቲካ ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን የፈጠራ ባለቤትም ጭምር በመሆን ሸመታው በደራበት መድረክ ሁሉ እየቸበቸበ የአገራችንን የፖለቲካ ገበያ ተቆጣጥሮ ቆይቷል ።

ትልቁ ብሔር አማራ በእነዚህ በዘር ፖለቲካ ባበዱ የዘር ልሂቃኖች አጥማቂነት ስጋ ወደሙ ተቀብለው ዘራቸውን ባደራጁ የጎሳ ባለወንበሮች ያለርህራሔ ሲታደንና ያለ ታዛቢ ሲሳደድ የዘር ፖለቲካዉ ልሂቃን አማራን እንደሲጋራ መጠን ረግጠን ጥለነዋል ወዘተ እያሉ ከመሳለቅና ከመኮፈስ ያለፈ ኢትዮጵያዊ አጋራችን ነው በሚል ስሜት ጥቃቱን አልመከቱለትም ፤ እምባውን አላሰቡለትም ።

ይህ ብቻ አይደለም አነዚያ በዚያን ዘመን የነዘሪሁን ክሸ ካፖርት ተሸካሚ በመሆን ከካፖርቱ የውስጥ ኪስ የተደበቀውን ምጽአተ አማራ ሳያስተውሉ አንዳንዶቹም በግደለሽነት ውጤቱን እያወቁ ጭምር ጥፋቱን በአጋርነት የፈጸሙ ዋለልኛዊያን አማራ ባለፋት 26 አመታት የተቀመረለትን ፍዳ ሲከፍል በአጋርነት ሲያጨበጭቡ ተስተውለዋል ። የውድቀታችን ማሳረጊያ የሆኑት ፖሊሲና ግብ ሲነደፉ ከወጣኝነት እስከ ፈጻሚነት ተሳትፈዋል ።

የተፈጸመብንንና ሊፈጸምብን የታቀደውን ምጽአት መክተን መዳን የምንችለው የምጽአቱ ፊታውራሪዎች የታጠቁትን የዘር ትጥቅ ታጥቀን በእነሱ ልክ ተለክተን ስንገኝ እንደሆነ ዘመን አስተምሮናል ።

ጉዟችን የት እንደሚያደርሰን እርግጠኞች መሆን ባንችልም ያለፈው የግፍ ዘመናችን ፈውስና የወደፊቱ በደል አስተማማኝ መክት አማራዊ ጥምረታችን እንደሆነ ህይወት አስተምሮናል ። የጀመርነው የምልሰተ አማራ ጉዞም የድል ጮራ እያሳየን ነው ።

እኛ የማንም ፍልስፍና መሞከሪያ አይደለንም ። ባለፈው አጥፊ ፍልስፍናው ያጠፋን ጥፉ ትውልድም የመዳናችንን መፍትሔ ይሰንቅልናል ብለን ዳግም አንዘናጋም ።

ዳሩ ግን ተዛዝበናል ። ከአርባ አመት በፊት ያጎፈራችሁበትን የዘር መንገድ ከ 26 አመት የፍዳ ትምህርት በኋላ ተረድተነው ነፍስ ገዝተን ፣ ልብ ሸምተን መንገዳችሁን መከተል ስንጀምር መምህራኖቻችን ስለምን አንገበገባችሁ ? ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ መቅደሙስ አባት አደር አይደለምን?

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.