በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ጉጂ ዞን የጌዴኦ ብሔር ላይ እየደረሰ ያለው የዘር ማጽዳት ተግባር በአስቸክዋይ መቆም አለበት

በደቡብ ኢትዮጵያ በጌዴኦ ዞን አጎራባች በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ጉጂ ዞን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሆኑ የጌዴኦ ብሔር ተወላጆች ከጉጂ ማህበረሰብ ጋር ለዘመናት በወንድማማችነትና ተዋልደው ኖረዋል፡፡ እየኖሩም ነው። ነገር ግን ከወር በፊት በተከሰተ ግጭት ከመቶ በላይ የሆኑ የጌዴኦ ብሔር ተወላጆች ማንነታቸው ብቻ መሰረት ተደርጎ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ተገድለዋል፥ ወደ ሩብ ሚሊዮን የሚሆኑ ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፥ ቤቶቻቸውና ንብረቶቻቸው ተደምስሶባቸዋል። በተጨማሪም በርካታ ሴቶች፥ ወንዶች፥ ልጆችና፥ አዛውንት ለከፋ አካል ጉዳት ተዳረገዋል። ነገርግን የአስቸኳይ ግዜ ስር እየተንቀሳቀሱ ያሉ የፌደራል መከላከያ፥ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል እና የአካባቢው ኮማንድ ፖስት ችግሩን እንዳላየ ለመሆን መሞከሩና የጉዳቱ ሰለባዎች ተጨባጭ ጥቆማን መሰረት ያደረገ ምላሽ አለመስጠቱ በጣም የሚገርምና ስርዓቱ ለምንና ለማን የቆመ ነው? የሚያስብል ነው።

የግጭቱ ዋና ጠንሳሾችና አቀንቃኞች የአካባቢው አስተዳዳሪዎች (በተለይም የቃርጫ ወረዳ አስተዳደሮች እና ካቢኔዎች) ሲሆኑ የአካባቢው ህብረተሰብ ለሚያነሳቸው የልማት (ትምህርት፥ የስራ እድል) ጥያቄዎች ምንም በማያውቁ ነገር ግን ከጉጂ ማህበርሰብ ጋር በወንድማማችነት እየኖሩ ባሉ የጌዴኦ ብሔር ተወላጆች ላይ በማላከካቸው የተነሳ ነው። ሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር ወይም በደል በዋናነት በምዕራብ ጉጂ ዞን ብልሹ አመራር ብቻና ብቻ ነው። በተለይ በሰላም እየኖሩ ያሉ ሕዝቦችን በማጋጨት ርካሽ የፖለትካ ትርፍ መመኘትና ለማግኘት መጣር ኢሰባዊነት ነው።

 

የአገር ሽማግሌዎችና እና የባህል መሪዎች (የጌዴኦ እና ጉጂ ኦሮሞዎች አባ ጋዳዎች) በማሕረሰቡ የቆየ ባሕል መሰረት (የጎንዶሮ ስርዓት በማካሄድ) ጥፋቱን ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ  በማውገዝና የጥፋቱን ጠንሳሾች ወደ ሕግ እንድቀርቡ ተወስኖ፣ ጉዳት የደረሰባቸው (የሕይዎት፣ የአካልና የንብረት) ካሳ ተደርጎ፣ ከሩብ ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች ወደ በቶቻቸው እንዲመለሱ ተወስኖ አጠቃላይ እርቅ ተደርጎ እንቅስቃሴ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም እስከአሁን ድረስ የአገር ሽማግሌዎችና እና የባህል መሪዎችን ውሳኔ በተሳካ መልኩ አልተተገበረም። የዘር ማጥፋቱ ላይ እጃቸው ያለባቸው የምእራብ ጉጂ ዞንና የቀርጫ ወረዳ አመራሮች እንደሁም ግብረአበሮቻቸው እስከአሁን ድረስ አልተጠየቁም። የሕይዎት፣ የአካልና ከፍተኛ የሆነ የንብረት ጉዳት ደርሶባቸው የተፈናቀሉ ከሩብ ሚሊዮን በላይ የሆኑ ህጻናት፣ ሴቶችና አረጋዊያን ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ አልተሰጠም፤ ተመልሰው እንዲቋቋሙ የረባ ድጋፍ አልተደረገም፤ ከዚህ የተነሳና በምግብና መጠለያ እጥረት ተፈናቃዮች እየተጎሳቆሉ ነው።

በባለፉት ሁለት ሳምንታት የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቤታቸው በመመለስ የሟች ቤተስቦቸ ለሟቾቹ የቀብር ሥነ ሥርዓት ማድረግ ላይ የነበሩ ቢሆንም ከባለፉት ሦስት ቀናት ጀምሮ ሁኔታዎች እንደገና በማገርሸት በጌዴኦ ብሔር ተወላጆች ላይ ከፍተኛ የሕይዎት የአካልና የንብረት ጉዳት እየደረሰ ነው።  አቶ ሽብሩ መኩሪያ እና አቶ ታሪኩ በየነ እሰባዊ በሆነ መልኩ ተገድለዋል። ወሮ አማረች አብርሃም የተባሉ ሴት በአራት ወንዶች ተድፍረውና ጭካኔ የሞላበት ድብደባ ደርሶባቸው  እስከ አሁን ደረስ ሕክምና ሳያገኙ በሕይዎትና ሞት መካከል ላይ ናቸው። በቃርጫ ወረዳ ቡቂሳ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጀቦ ጉዬ፣ሽብሩ ጀቦ (ልጅ)፣ አቶ መስፍን አብርሃም፣አቶ አብርሃም ጨነቁ (በሕይዎትና ሞት መካከል ያሉ) ና አቶ ማቴዎስ ደሳለኝ (በሕይዎትና ሞት መካከል ያሉ) ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በርካታ ቤቶች ፈርሰዋል። የቡና ና የእንሰት ማሳዎች ተጨፍጭፈዋል። ወድመዋል። ማንነታቸውን የሚያንቋሽሹ አስነዋሪ ስድብና ዛቻ እየደረሰባቸው ነው። በንግድ ስራና ጥቂት በመንግስት ስራ የሚተዳደሩ የጌዴኦ ብሔር ተወላጆች ከስራ ገበታቸው እንዲፈናቀሉ እየተደረጉ ነው።

የምእራብ ጉጂ ዞንና የቀርጫ ወረዳ አመራሮች እንድሁም ግብረአበሮቻቸው የጌዴኦ ብሔር ተወላጆች እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በራሳቸው ቤት፣ መሬት እና  በአገራቸው ውስጥ የመኖርና የመንቀሳቀስ መብታቸው እሰባዊ በሆነ መልኩ ተገድል። ለዚህ ግዙፍ ጥቃትና የዘር ማጽዳት ምንም የማህደረ (ሚድያ) መረጃ ሽፋን አልተሰጠም። እጅግ በጣም በሚያስደነግጥ መልኩ የፈደራል መከላከያ፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል እንድሁም በአስቸካይ ግዜ አዋጁ መሰረት የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት መረጃ የደረሳቸው ቢሆንም ጥቃቱን ለማስቆም ምንም እርምጃ እየወሰዱ አይደለም።

የጌዴኦ ብሔር ከጥንት ጀምሮ የአካባቢው ነባር ሕዝብ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለመሆኑም በርካታ ታሪካዊና ባሕላዊ ማሳያዎች አሉ። የመጀመሪያው የጌዴኦ ብሔር ታሪካዊ አመጣጥን የሚዘክረው የብሔሩ መዘሙር (ፋጎ) የጌደኦ ሕዝብ በአሁኑ ሰዓት በጉጂና ቦረና ዞኖች ከሚገኙ ከሐርሱ፣ ከሐዋጣ፣ ከቦኮ፣ ቦጬሣ፣ ወዘተ. የሚባሉ አካባቢዎች ከጥንት ጀምሮ ይኖሩ እንደነበረና አብዛኛው የጌዴኦ ሕዝብ አሁን ወደ አሉበት ዞን (የጌዴኦ ዞን)  የመጡትም ከነዚህ አካባቢዎች እንደሆነ ይታወቃል። ይሕ ታሪክ በጉጂ ህዝብ ዘንድም በደንብ የሚታወቅ ነው፡፡ ሁለተኛው በ1952 ዓ/ም በጌዴኦና በፊውዳል ኃይሎች በመሬት ስሪት ላይ የጌዴኦ አርሶአደሮች (ተመሳሳይ የአርሶአደሮች አመጽ በጎጃምና ባሌ ላይ እንደነበረ ይታውቃል) ከፍተኛ ደም መፋሰስ ካስከተለ ተቋውሞ (አመጽ) በኋላና የዘመናዊ የይዞታ ማረጋገጫ (ዲክላራሲዮን) ሲጀመር ባካባቢው ለነበሩ የጌዴኦ ተወላጆች የይዞታ ማረጋገጫ ተሰጥⶆአቸዋል። ሶስተኛው የጌዴኦ፣ ጉጂና ቦረና ሕዝቦች ከአንድ አባት የሚወለዱ ሶስት ወንድማማቾች የዳራሶ (ጌዴኦ)፣ጉጆ (ጉጂ)ና ቦሩ (ቦረና) ትውልዶች ናቸው። በስነሰብ ጥናት መሠረት በዝግመተለውጥ ሂደት የየራሳቸውን ማንነት እየፈጠሩ የመጡ ቢሆንም ጥንት አንድ የነበሩና አሁንም በርካታ የሚጋሩዋቸው የጋራ እሴቶች ያላቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ ስለዚህ በምእራብ ጉጂ ዞንና የቀርጫ ወረዳ አመራሮች እንድሁም ግብረአበሮቻቸው የጌዴኦ ብሔር ለአካባቢው መጤ ነው እያሉ የሚነዙት ፕሮፓጋንዳ በየትኛውም መመዘኛ (በታሪክ፣ በሕግና ሎጅክ) ተቀባይነት የለሌው መሆኑ እንድታወቅ ያስፈልጋል።

ስለዚህ በምዕራብ-ጉጂ ዞን የሚኖሩ ከግማሽ ሚሊዮን (በ1999 ዓ.ም በተደረገው ሕዝብና ቤቶች ቆጠራ መሰረት) በላይ በሚቆጠሩ የጌዴኦ ብሔር ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን የተደራጀ የዘር ፍጅት በመቃወም እኛ በሰሜን አሜሪካ ያለን የማሕበረሰቡ ተወላጆች ይህንን የአቋም መግለጫ አውጥተናል።

  1. የጌዴኦ ብሔር ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለዉን ማንነታቸውን መሰረት ያደረገ የዘር ጥቃት በአጽንኦት እንቃወማለን። በተጨማሪም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች (በቤንሻንጉል ክልል፣ በሶማሌ፣ ሞያሌና ሌሎችም ቦታዎች) አጥብቀን እንቃውማለን።
  2. የአካባቢው አመራሮች እንደሁም ግብረአበሮቻቸው የዘር ፍጅቱ ዋና ተጠያቂ ናቸው።
  3. የፌዴራል መንግስት፣ የአኦሮሚያ መንግስትና የአከባቢው ዞነና ወረዳ አመራሮች የመንግስት ሃላፊነታቸውን መወጣትና የጎሳውን ጥቃት በአስቸኻይ ማስቆም አለባቸው።
  4. ከተለያዩ ድርጀቶችና የማሕበረሰቡ የተውጣጡ ገለልተኛ ቡድን (ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶችን ጨምሮ) የዘር ማጽዳትን መንስኤና የጥፋቱን መጠን እንድመረምሩና ሪፖርት እንዲያደርጉ ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል።
  5. በዘር ማጥፋት ተግባር ላይ የተሳተፉ ግለሰቦችና አመራሮች ባስቸኻይ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው።
  6. ከአካባቢው ነዋሪዎች እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተገኘው ድጋፍ (በቂ ባይሆንም ) እጅግ በጣም እናደንቃለን። የፌዴራል መንግስት፣ የኦሮሚያ መንግስትና የአከባቢው ዞንና ወረዳ አስተዳደር በከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቆ ለሚገኘዉ ህዝብ አስቸኻይ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው።
  7. የፌዴራል መንግሥት፤ የክልል እና የአካባቢው አመራሮች የጌዴኦ ብሔር ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለው ማጎሳቆል እና ማስፈራራት በአስቸኻይ ማስቆም አለባቸው። ኢተዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ኮንቬንሽን ፈራሚ ሀገራት አንዷ እንደመሆና በሕገ መንግስትዋ በተገለጸው መሰረት የጌዴኦ ብሔር ተወላጆች ልጆች ባፍ መፍቻ ቋንቋ የመማር ሰብአዊ መብታቸው ልጠበቅና ጥያቄያቸው በአፋጣኝ ልመለስ ይገባል።
  8. እንደማንኛውም በሀገርቱ እንዳሉ ሕዝቦች በቋንቋቸው የመጠቀም መብት፣ ባሕላዊ ስርዓትቸውን የመፈፀም እና ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመዘዋወር መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል።

1 COMMENT

  1. this problem of cleasing has taken long time in Amaro, and burji woreda because of this same people, guji. Government and its bodies in different regions are not acting to the level of the problem. any body please…..

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.