ከ100 ሺ በላይ የሚቆጠሩ የጌዲዮ ተወላጆች ከጉጂ ዞን ተፈናቅለው ገደብ ከተማ ገቡ

ከ100 ሺ በላይ የሚቆጠሩ የጌዲዮ ተወላጆች ከጉጂ ዞን ተፈናቅለው ገደብ ከተማ ገቡ

(ኢሳት ዜና ግንቦት 08 ቀን 2010 ዓ/ም) ከሳምንታት በፊት በጉጂ ብሄረሰብ አባላትና በጌዲዮ ብሄረሰብ አባላት መካከል ተነስቶ የነበረው ግጭት ተከትሎ ከ200 ሺ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው የነበረ ቢሆንም፣ ግጭቱን በሽምግልና ለመፍታት በተደረገው ሙከራ ብዙዎቹ ወደ ተፈናቀሉበት ቦታ ተመልሰው ነበር። ይሁን እንጅ ግጭቱ ካለፈው እሁድ ጀምሮ እንደገና በማገርሸቱ ከ 100 ሺ በላይ የጌዲዮ ተወላጆች ዞኑን ለቀው ወደ ገደብ እና ቀረጫ ወረዳዎች በመግባት ላይ መሆናቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል።
ትናንት ምሽት ጎጥጢ አካባቢ ግጭት እንደነበረ የሚገልጹት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ግጭቱን በመፍራት ዛሬም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ገደብ ገብተዋል።
የወረዳው አመራሮችም ሆኑ ለጋሽ ድርጅቶች ለተፈናቃዮች በቂ እርዳታ ባለማድረጋቸው አብዛኞቹ ለልመና እየተዳረጉ ነው።
በጉጂ እና በጌዲዮ ብሄረሰበች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከሁለቱም ወገን የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 200ሺህ መድረሱን የመንግስታቱ ድርጅት በቅርቡ አስታውቆ ነበር። ከሳምንታት በፊት ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከ100 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ መረጃዎች ያሳያሉ። በአሁኑ ግጭት ምን ያክል ሰዎች እንደሞቱ አልታወቀም።
ግጭቱን ተከትሎ የኦሮምያ ክልል ልዩ ሃይል አባላት የማረጋጋት እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን፣ ጥቃቱንም የኦነግ አባላት እንዳስነሱትና የተወሰኑት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ቢናገሩም፣ የጊዲዮ ተወላጆች ግን የሚቀርበውን ምክንያት የሚቀበሉት አልሆነም።
ተፈናቃዮቹ አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግላቸው በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ግፊት እንዲያደርጉ ተፈናቃዮች ጠይቀዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.