ከትግሬ-ወያኔ አገዛዝ ለኢትዮጵያ በጎ ነገር ይመጣል ብሎ ማሰብ ከዕባብ ዕንቁላል እርግብ ይፈለፈላል ብሎ ማመን ነው

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት አርብ መጋቢት ፲፰ ቀን ፪ሺህ፯ ዓ.ም. ቅፅ ፫ ፣ ቁጥር ፲፫

ሠሞኑን በትግሬ-ወያኔ፣ በግብፅ አረብ ሪፑብሊክ እና በሱዳን እስላማዊ አገዛዝ መካከል በአባይ ወንዝ የውኃ አጠቃቀም ላይ የሚያተኩር የጋራ የሥምምነት ሠነድ ተፈርሟል። የሥምምነቱ ሠነድ ለሕዝብ ይፋ የሆነው ማክሰኞ መጋቢት ፲፭ ቀን ፪ሺህ፯ ዓ.ም. (Tuesday March 24, 2015) ነው። ሆኖም የሥምምነት ሠነዱ የወጣበት የካቲት ፳፮ ቀን ፪ሺህ፯ ዓ.ም. (Thursday March 5, 2015) እንደሆነ በሠነዱ ራስጌ ላይ የሠፈረው ጽሑፍ ያመለክታል (ምንጭ፦http://aigaforum.com/documents/Final-full-text-of-egypt-sudan-ethiopia-agreement-on-nile-use.pdf)። ሥምምነቱን የተፈራረሙት የሦሥቱ አገዛዞች ገዢዎች እስካሁን ድረስ ዘግይተው ሠነዱን ለሕዝብ ይፋ ያደረጉበት ምክንያት ምናልባት ከሚገዟቸው አገሮች ሕዝብ ሊነሣባቸው የሚችለውን ተቃውሞ ለማለዘብ ታስቦ ይሆናል፣ ወይም ሌላ የተደበቀ አጀንዳ ይኖራቸዋል። ወጣም ወረደ ሠነዱ ለእያንዳንዱ አገር ሕዝብ፣ በተለይም ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የሚያመጣው በረከትም ሆነ የሚያወርደው መቅሠፍት ካለ ያንን በጥልቀት መመርመሩ እና ተገቢውን እርምጃ መውሰዱ የእያንዳንዱ ኃላፊነት የሚሠማው ዜጋ ግዴታ ነው።

የትግሬ-ወያኔ አገዛዝ በአባይ ወንዝ የመብት ጥያቄ ላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሉዓላዊነት አሣልፎ የሠጠው ገና ወደሥልጣን ከመጣ ሦሥት ዓመት ሣይሞላው ነው። በሰኔ ፳፬ ቀን ፲፱፻፹፭ ዓ.ም.  (Thursday July 1, 1993) የያኔው የትግሬ-ወያኔ የሽግግር አገዛዝ ፕሬዘዳንት መለስ ዜናዊ ካይሮ ድረስ ሄዶ ከያኔው የግብፅ አምባገነን ገዢ ሆስኒ ሙባረክ ጋር አንድ ሠነድ ተፈራርሟል (ምንጭ፦ http://ocid.nacse.org/tfdd/tfdddocs/521ENG.pdf)። የዚያ ሥምምነት ዓላማ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ እና በገባር ወንዞቹ ላይ ያላትን ተፈጥሯዊ እና ሉዓላዊ መብት አሣልፎ የሚሠጥ መሆኑን በተለያዩ ባለሙያዎች እና ፖለቲከኞች የተተቸበት ጉዳይ ነው።

ሆኖም ከአራት ዓመታት በፊት ሟቹ የትግሬ-ወያኔዎች መሪ መለስ ዜናዊ በድንገት ተነስቶ «አባይን እንገድባለን» ሲል በኢትዮጵያውያን መካከል ያልተጠበቀ መከፋፈል ተፈጠረ፦ ከፊሉ «የዚህ ግድብ መገንባት ተገቢ ነው፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠቅማል፣ ወያኔንም በገንዘብ እና በማናቸውም መንገድ ልንደግፈው ይገባል» ብሎ ተነሣ። ከፊሉ ኢትዮጵያዊ ደግሞ «የትግሬ-ወያኔ ለኢትዮጵያ የሚያስበው መልካም ነገርም ሆነ የሚያመጣው ጠቃሚ ነገር የለውም፤ እንዲያውም ለአሁኑ ብቻ ሣይሆን ለተከታዮቹም ኢትዮጵያውያን ትውልዶች የማይነቀል እና የተወሣሠበ የችግር ነቀርሣ ይተክላል» ብለው አምርረው ተቃወሙ። በዚህ መካከል ገለልተኛ ሆነው ከሁለቱም ወገን የሚወረወረውን የቃላት ጦርነት በትዝብት የሚከታተሉም አይጠፉም። ወጣም ወረደ መለስ ዜናዊ ያንን ያልተጠበቀ ቃሉን ከሠጠ ከዓመት በኋላ ቅዳሜ መጋቢት ፳፬ ቀን ፪ሺህ፫ ዓ.ም. (Saturday April 2, 2011) በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አቅራቢያ በ15 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የግድቡን ሥራ አስጀመረ።

ሀገር ወዳድ እና ሃቀኛ ኢትዮጵያን አስቀድመው እንዳስጠነቀቁት፣ በግድቡ መገንባት ሥም የትግሬ-ወያኔ ዘርፈ-ብዙ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅሞችን አካበተበት፦ በመዋጮ ሥም በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ ወደካዝናው አስገባ፣ በፖለቲካው ረገድ «ተቃዋሚ ነን» የሚሉትን ለመከፋፈል እና ለማዳከም ተጠቀመበት። ነገር ግን የግድቡ ሥራ በትክክል ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ሣይታወቅ ይኼው አራት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ቀርቶታል። የግድቡ ሥራ ከመጀመሪያውም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለታሪካዊ ጠላቶቿ አሣልፎ ለመስጠት መሆኑ አያጠራጥርም። ስለዚህ የትግሬ-ወያኔ ኢትዮጵያን አፈራርሶ፣ ዜጎቿን ከፋፍሎ፣ ግዛቷን ለውጭ ኃይሎች የመቸብቸብ የመጨረሻውን ግቡን ሣያሣካ እንደማያርፍ ማሰብ የማይችል ኢትዮጵያዊ ካለ የአዕምሮው ጤንነት የተቃወሰ ብቻ ነው።

ይህ በዚህ እንዳለ፣ የትግሬ-ወያኔዎች የተፈጥሮ ባሕሪያቸው የሆነውን የአገር ክህደት ድርጊታቸውን በመቀጠል፣ ባለፈው ሰኞ ዕለት መጋቢት ፲፮ ቀን ፪ሺህ፯ ዓ.ም. (Monday March 23, 2015) የሠሞኑን የሥምምነት ሤራቸውን ሠነድ በድረ-ገፃቸው ላይ ይፋ አርገዋል (ምንጭ፦ (http://aigaforum.com/documents/Final-full-text-of-egypt-sudan-ethiopia-agreement-on-nile-use.pdf)። ስለሆነም «በዚህ የሤራ ሠነድ ካሉት አንቀፆች በተለይ የኢትዮጵያን እና የኢትዮጵያውያንን ኅልውና በእጅጉ የሚፈታተኑት የትኞቹ ናቸው?» ብሎ በጥንቃቄ መመርመሩ ተገቢ ነው። በተለይ፦

  • አንቀፅ 3፦ ፍትኃዊ የውኃ አጠቃቀም መርሆ (III. Principle of Equitable and Reasonable Utilization)
  • አንቀፅ 4 ሌላውን አካል ያለመጉዳት መርሆ (IV. Principle of Not to Cause Significant Harm)
  • አንቀፅ 5 የግድቡን ወኃ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሙላት ስለሚያስፈልገው የትብብር ሥራ (V. Principle to Cooperate on the First Filling and Operation of the Dam)

በሚሉት አንቀፆች ላይ ኢትዮጵያውያን በጥልቀት ተወያይተው ብሔራዊ መግባባት እና የጋራ አቋም ላይ መድረስ ይገባቸዋል። እኒህ አንቀፆች እርስ በእርሣቸው በሚቃረኑ፣ በተድበሰበሱ እና የኢትዮጵያንም የወደፊት ኅልውና አደጋ ላይ በሚጥሉ አረፍተተገሮች የታጨቁ ናቸው። ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያውያን በሠከነ መንፈስ፣ ሣንዘላለፍ፣ ነገሮችን በጥልቀት እየመረመርን ለችግሩ መውጫ መንገድ መፍትሔ የሚሆኑ ኃሣቦችን ማፍለቅ ይጠበቅብናል።

የዚህ የአዲሱ ሥምምነት ዓላማው በግልፅ፦ «እኛ ወያኔዎች በኢትዮጵያ ላይ ማንም አዛዥ-ናዛዥ የሌለብን ገዢዎች ነን፣ ምን ታመጣላችሁ!» ለማለት ነው። ለነገሩ ከትግሬ-ወያኔ አገዛዝ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን መልካም ነገር ይመጣል ብሎ ማሰብ ከዕባብ እንቁላል እርግብ ይፈለፈላል ብሎ የማመን ያህል ቂልነት ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቆመን ተገቢውን የተግባር ምላሽ ልንሠጥ ይገባል። ይህንን ማድረግ ካልቻልን ግን የዚህ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ከአገር አፍራሹ እና ሻጩ የትግሬ-ወያኔ ባልተለየ ከሃዲዎች በመሆናችን በታሪክ ከተጠያቂነት አናመልጥም።

 

ኢትዮጵያ በታማኝ እና ቆራጥ ልጆቿ መስዋዕትነት ለዘለዓለም ፀንታ ትኖራለች!

Comments are closed.