ስለ ክቡር ደጃዝማች ብሬ ዘገየ (አባ በጥብጥ) አጭር ማስታዋሻ

ስለ ክቡር ደጃዝማች ብሬ ዘገየ (አባ በጥብጥ) አጭር ማስታዋሻ 1
ክቡር ደጃዝማች ብሬ ዘገየ የወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው ብሬ አያት

አገራችን ኢትዮጵያ ብዙ አገር ወዳድ አርበኛ ዜጎችን አብቃይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ በተለይ በ5ቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ዓመታት አያሌ አርበኞች አገርን በመከላከል ሕያው ታሪክ ሰርተው አልፈዋል፡፡ ከነዚህ ብርቅ እና እውቅ ፋና ወጊ አርበኞች መሀከል ቁንጮው ክቡር ደጃዝማች ብሬ ዘገየ አንዱ ነበሩ፡፡ ክቡር ደጃዝማች ብሬ አገራችን ፋሽስት ጣሊያን በወረረበት ወቅት እምቢ ለነፃነቴና ለሀገሬ ብለው ወንድሞቻቸውን በማስተባበር  የጣሊያን ፋሽስት ሰራዊት እና ባንዶችን በጦርነት እንጂ በሰላም ላለማየት ወስነው በሚያዝያ ወር 1928 ዓ. ም. በረሀ ወረዱ፡፡

ወሳኙን ትግል ለመጀመር በመስከረም 1929 ዓ. ም.  ክቡር ደጃዝማች ብሬ ዘገየ ከአርማጭሆ ወደ ጠገዴ በመሻገር የፋሽስት ጣሊያን ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት ከኤርትራ  ተነስተው በሑመራ በኩል በሞተር ሳይክል እና በብዙ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ታጅበው ወደ ጎንደር ከተማ ጉዞ ላይ እንዳሉ ሹመሪ ላይ ሸምቀው ተኩስ በመክፈት የፋሽስቱን ሰራዊት ድል በማድረግ ወደመጣበት መልሰዋል፡፡  በዚህ ውጊያ  የተለያዩ የጦር መኮንኖች ሞት እና ቁስለኛ ሲሆኑ፣ ብዛት ያለው የጦር መሣሪያ ተማርኳል፡፡  በዚህ ውጊያ የተማረከውን የፋሽስት የኮሎኔል እና ሌሎች ወታደራዊ የማእርግ  ልብሶች፣ እና የጦር መሣሪያዎችን አርማጭሆ ላይ በምርኮኝነት ለህዝብ አበረከቱ፡፡ ሕዝብም ሆ! ብሎ ተነሣ። በሌሎች አካባቢዎች የነበሩ ጀግኖችም ይህን ተጋድሎ በምሳሌነት በመውሰድ ቆርጠው ተነሡ፡፡ ጸረ ፍሽስት አርበኝነቱ  በየቦታው ተቀጣጠለ።

ክቡር ደጃዝማች ብሬ ዘገየ፣ ትግላቸውን በመቀጠል፣  የጣሊያን ሰራዊት፣ “ሳንጃ እና ሥፍራ-ጣሊያን” ካምፕ ላይ ከፍተኛ ሰራዊት አስፍሮ  ስለነበር፣ የአርማጭሆን አርበኞች አስተባብረው  የሳንጃውን ካምፕ በመክበብ በተደረገው ወሳኝ ውጊያ ብዙ የፋሽስት ጦር መሪዎችንና ባንዳዎችን ሲገደሉ ጦር ካምፑን ሙሉ በሙሉ ደምስሰው ብዙ የጦር  መሳሪያና ጥይቶች፣ ቦምቦች ማርከው ነፃ በማውጣት የጠላትን ሀይል እና ሞራል ሰበሩ። የአርበኞችን ሞራል አነቃቁ። ።

በአማራ የኢጣሊያን ገዥ ዲ ኮርፓ ዳርማታ (እዚህ ላይ ወያኔ ትዝ ይሏል) በደጃዝማች ብሬ ክፉ ብትር ስለአረፈበት፣ የአርማጭሆን አርበኞች ለማጥፋት መጠነ ሰፊ ዝግጅት አድርጎ ዘመቻ ከፈተ። ሁኖም ግን፣ በወገራ በኩል የመጣውን የፋሽስት ሰራዊት የመረባና የጃኖራ አርበኞች ደመሰሱት፡፡ በወልቃይት አቅጣጫ የተንቀሳቀሰውን የፋሽት ጦር ጠገዴ ላይ በአዴት አርበኞች ሲደመሰስ፣  በመተማ በኩል ወደ ታች አርማጭሆ የመጣውን ጦር በግንባሩ በተሰለፉ የታች አርማጭሆ አርበኞች ተደመሰሰ።

በዋናነት `ተመርጦ እና በልዩ ዝግጅት ተደራጅቶ ወደ መሀል አርማጭሆ የተንቀሳቀሰው የፋሽስት ጦር፣ ደብረሲና ላይ ሲደርስ  አርበኞች በሰነዘሩት ጥቃት  መንቀሳቀስ ሳይችል ቀረ። በዚህ ግንባር ውጊያ አርበኛው ወደ ምሽጉ በመግፋት በተደረገው እልህ አስጨራሽ የጨበጣ ውጊያ ዋናው የፋሽስት ሰራዊት ጦር መሪ ጣላያናዊው ዲፋሶ ቲንንቲ ከብዙ የጦር መሪዎችና ወታደሮች ጋር ተገደለ፡፡  ብዙ የጦር መሣሪያ፣ ጥይት፣ ቦምብ ሲማረክ  ከሞት እና ቁስለኛ ከመሆን  የተረፈው ባንዳ  ሰራዊት ወደ መጣበት ተበታትኖ ተመለሰ።

የጣሊያ መንግሥት ከሑመራ – ጎንደር የሚወስደውን መንገድ መልሶ ለመቆጣጠር ሳንጃ ላይ ጦሩን አጠናክሮ መሽገ። ክቡር ደጃዝማች ብሬ ዘገየ አርበኛውን አስተባብረው ምሽጉን በመክበብ ለ12 ቀናት ያልተቋረጠ ጦርነት አካሂደው ብዙ የጣሊያ የጦር መሪዎችና ባንዳዎች ሲገደሉ፣ ቁጥሩ  ብዛት ያለው ጠብመንጃ፣ ጥይትና ቦንብ ተማርኮ የጦር ካምፑን ተጣቆጥረውታል። ከዚህ ውጊያ በኋላ ፋሽስት ጣሊያን  በደረሰበት ተደጋጋሚ ሽንፈት ምክንያት ከጎንደር ከተማ ውጭ መንቀሳቀስ ተሣነው።

ክቡር ደጃዝማች ብሬ ዘገየ የትግል አድማሳቸውን በማስፋት  ጦርነቶች ባየሉባቸው ሁሉ በሚያቀርቡላቸው ጥያቄ መሰረት እየተዘዋወሩ በብዙ የጦር ሜዳዎች ላይ ማለትም ፣ በጠገዴ፣ በወልቃይት፣ በወገራ፣ በጭልጋ አውራጃዎች እና በሌሎችም እጅግ አኩሪና አስደናቂ ውጊያዎችን በመምራት ብዙ ድሎችን በአሸናፊነት ደምድመዋል፡፡ የጣልያን ጦር የአርበኛውን የደጃዝማች ብሬን  ስም ሲሰማ በፍርሀት መሸሽት የተለመደ ነበር፡፡

“ያለ እዳው ዘማች ብሬ ደጃአዝማች”  እየተባለ በባንዳዎች ዘንድ ይቀነቀን ነበር።

ክቡር ደጃዝማች ብሬ ዘገየ በአርበኝነታቸው ወቅት፣ በውስጣቸው ብዙ ፊታውራሪዎች፣ ቀኛዝማቾች፣ ግራዝማቾች፣ ብላታዎች፣ ባለአምባራሶች  እንዲሁም የፖለቲካ እና ፍርድ ሰጭ ዳኞች ነበሯቸው።

ትግሉ አየጎመራ ሲመጣ እና  አብዛኛው ጎንደር ከፋሽስት ጣሊያን ነፃ መውጣት ሲጀመር፣ በስደት ሱዳን የነበሩ ወገኖች ትግሉን ለመርዳት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ወደሚገኙ አርበኞች በመዘዋወር ቅስቀሳ ማካሄድ ጀመሩ ። ይህ በሱዳን በኩል የሚመጣውን እንቅስቃሴ  ለማስተባበር ስብሰባ ተደረገ ፡፡ ሁኖም በዚህ ስብሰባ ወቅት፣ ደጃዝማች ብሬ ዘገየ የተለየ ሀሳብ አነሱ፡፡ “ነጭን ጠልተን እየተዋጋን እንደገና ከኋላችን ሌላ ነጭ ማስገባት ለምናደርገው ትግል አደጋ አለው በማለት በእንግሊዞች የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደማይስማሙ ግልጽ አደረጉ”። ሆኖም ብዙ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ደጀዝማች ብሬ ዘገየ እንግሊዞች ትብብር የማድረጋቸውን ሃሳብ ተቀበሉ። የእንግሊዙ ሻለቃ በንቲክ እና ጸሐፊ ትእዛዝ ኃይሌ ወልደሩፋኤል ግን በክቡር ደጃዝማች ብሬ የመጀመሪያ አቋም ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እንደተሰማቸው ቀረ።

በ1933 ዓ. ም. አርበኛው በጎንደር ከተማ ላይ የሰፈረውን የጣሊያ ምሽግ ሰብሮ ለመግባት ወስኖ አባ-በጥብጥ ብሬ ሠራዊታቸውን ይዘው ከፍተኛ ውጊያ አደረጉ፡፡ ሁኖም፣ ፋሽስት ጣሊያን ያለ የሌለ ተጨማሪ ሰራዊቱን ከሌላ አካባቢዎች ሁሉ በማሰባሰብ ጎንደር ከተማን መከላከል ሲጀምር፣ በአንጻሩ አርበኛው የውጊያ ስልቱን በመቀየር፣ የጣሊያን ሰራዊት ከጎንደር ከተማ እንዳይወጣ  እየተከላከለ እንዲቆይ ተደረገ። ጣሊያንም ጎንደር ከተማ ውስጥ ብቻ ተወስኖ ከረሞ በ1934 ዓ. ም. ሕዳር ወር መጀመሪያ ላይ እጁን ሰጥቶ የጎንደር ከተማ ነፃ ወጣ።

አገር ነጻ ከወጣ በኋላ እነ ጸሐፊ ትእዛዝ ኃይሌ ወልደሩፍኤል፣ ክቡር ደጃዝማች ብሬ ዘገየ በትግሉ ጊዜ “ከነጭ ጋር እየተዋጋን ሌላ ነጭ አንቀበልም” ያሉትን በማስታወስ በሥራ ድልድል ወቅት ለደጃዝማቹ  ለአርበኝነታቸው የሚመጥን የስራ ድልድል በመንሳት ይልቁንም ከጣሊያን ጋር ወግነው ሲወጓቸው ከነበሩት ባንዳዎች በታች መድበዋቸው ነበር፡፡ መላው አርበኛም በነ ኃይሌ ወልደሩፍኤል ድርጊት በጣም ቅሬታ ተሰማው። ክቡር ደጃዝማች ግን እኔ የተዋጋሁት ለአገሬ እንጂ ለነኃይሌ ወልደሩፋኤል አይደለም፣ ለጃንሆይም ስልጣን አነሰኝ ብየ ቅሬታ አላቀርብም በማለት  ቅር ሳይላቸው ቀረ፡፡

በዚህ ሁኔታ በተለያየ ጊዜ ክቡር ደጃዝማች ብሬ ዘገየ፡-

  1. የላይ አርማጭሆ ምስለኔ
  2. የጎንደር አውራጃ ነጭ ለባሽ ጦር አዛዥ
  3. የአርማጭሆ ወረዳ ገዥ
  4. የስሜንና በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ነጭ ለባሽ ጦር ዋና አዛዥ ሆነው አገራቸውን በቅንነት አገልግለዋል።

በመጨረሻም በ1959 ዓ. ም.  ከንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘንድ ተጠርተው ከልዩ ልዩ ሽልማቶች ጋር አንድ ላንድሮቨር መኪና ተሸልመው ወደ ጎንደር ሲመለሱ በደረሰባቸው  የመኪና አደጋ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በዚሁ ዓ. ም. አንድም ለቤተሰብ የሚተርፍ ንብረት ሳይኖራቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ክቡር ደጃዝማች ብሬ ዘገየ የወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው ብሬ አያት ናቸው፡፡

ሊቁ እጅጉ

አዳነ አጣናው

ህዝብ የማወቅ መብት አለው !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.