ከቤንሻንጉል ጉምዝ ለተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች የተዋቀረው ኮሚቴ ውሳኔ አሳለፈ

ከአካባቢው ነዋሪዎች ፣ከወረዳው አመራሮችና ከተፈናቃዮች ጋር ኮሚቴው ውይይት አካሂዷል፡፡

ባሕር ዳር፡ግንቦት 11/2010 ዓ/ም(አብመድ)ከቤኒሻንጉል ጉምዝ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆችን በተመለከተ የተዋቀረው ልዩ ኮሚቴ በሎይ ጅጋንፎ ወረዳ ተገኝቶ የደረሰውን የህወትና የንብረት ጉዳት ተመልክቷል፡፡
ኮሚቴው በመቀጠልም ተፈናቃዮች ይኖሩበት ከነበሩት ቀበሌ ነዋሪዎችና አመራሮች ጋር ሠፊ ውይይት አድርጓል፡፡ 
በውይይቱ ላይ የወረዳው አስተዳዳሪ በተወካያቸውና የካማሽ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተገኝተዋል፡፡

ውይይቱን የተከታተሉት የኮሚቴው አባላት እንደተናገሩት ጥቅምት 16 እና 17 ቀን 2010 ዓ/ም በአማራ ተወላጆች ላይ መፈናቀል መድረሱን አረጋግጠዋል፡፡
በሁለቱ ህዝቦች መካከል መቃቃር እንዲፈጠር ያደረጉት አንዳንድ የቀበሌዋ ነዋሪዎችና ውስን የወረዳው አመራሮች መሆናቸውን በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡
በዚህም መሠረት ኮሚቴው መረጃውን በመያዝ ከክልሉ ርእሰ መስተዳደር ክቡር አቶ አሻድሊ ሀሰንና የክልሉ አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ ዲንሳ በየነ ጋር በመወያየት የመፍትሄ አቅጣጫ አመላክቷል፡፡
በመፍትሔነት የቀረበውም ፡-
• የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መንግስት ለተፈናቀሉት መጠለያ እንዲያዘጋጅ እና ምግብ እንዲያቀርብ ፤
• የጸጥታ መዋቅሩ ገለልተኛ በሆኑ አካላት ከሁለቱም ወገኖች በማሳተፍ እንዲዋቀር ፤
• የአማራ ተወላጆች ከበሎይ ጅንጋፎ እንዲወጡ የሚያዘውን የቀበሌ ደብዳቤ የጻፈውን አካል በአሻራ እንዲጣራ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ሲሆን በማፈናቀሉ ተግባር የተሠማሩ እና ችግሩን ያባባሱ 67 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል፡፡

በቀጣይም ክትትል እየተደረገ የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድ ሲገለጽ ፤ለተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች የደህንነት ዋስትና ለመስጠት ውሳኔ ተላልፏል፡፡
በዚህም መሠረት ኮሚቴው የተፈናቀሉት ዜጎች ወደነበሩበት ቦታ ተመልሰው የተረጋጋ ኑሮ እስኪጀምሩ ድረስ የሚከታተል ይሆናል ፡፡

በቀጣይም የሁለቱ አጎራባች ክልል መንግስታት በሁለቱ ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን አበክረው እንደሚሠሩ ተስማምተዋል፡፡

በዛሬው ዕለት በባሕር ዳር ከተማ ኮሚቴው ሪፖርቱን ለተፈናቃዮች ሲያቀርብ የተገኙት የኮሚቴው አባል የአማራ ክልል ሚልሻ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ መኳንንት መልካሙ እንደገለጹት ለወደፊት ችግሮች እንዳይፈጠሩ ሁሉቱም ክልሎችና ህዝቦች በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

የአካባቢው ማህበረሰብም ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው በሰላምና በፍቅር አብረው መኖር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡በተከሰተው ችግር ቤታቸው ለተቃጠለባቸው የአማራ ተወላጆች የክልሉ መንግስትና የአካባቢው ማህበረሰብ በቆርቆሮ መልሰው እንደሚገነቡ ቃል ገብተዋል፡፡

ኮሚቴው ከምሁራን፣ከሃይማኖት አባቶች እና ከልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ ሲሆን ከተፈናቃዮች ጋር እየተደረገ ያለው ውይይት ነገም ይቀጥላል፡፡

በባህርዳር ፈለገ ገነት ቅ/ጊዮርጊስ ካቴድራል አስተዳዳሪ በመልዓከ ገነት ቆሞስ አባ ገብረ-ፃድቅ ታረቀኝ የሚመራው ኮሚቴ ያጣራውን መረጃ ዛሬ ለተፈናቃዮች በባህርዳር ከተማ ተገኝቶ አቅርቧል፡፡

የአማራ ክልል መንግስት ከሁለቱም ወገኖች የተውጣጡ የኮሚቴ አባላት ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ላደረጉት ያለሰለሰ ጥረት ምስጋና አቅርቧል፡፡
ዘጋቢ፡-የሺሃሳብ አበራ

Amhara Mass Media Agency

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.