ዶ/ር አብይ አህመድ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን የስፖርት በዓል ላይ ለመገኘት ጥያቄ ማቅረባቸውን ሰማሁ (መሳይ መኮነን

መሳይ መኮንን (የኢሳት ጋዜጠኛ)
መሳይ መኮንን (የኢሳት ጋዜጠኛ)

በተመሳሳይም የአውሮፓውን የኢትዮጵያውያን ፌደሬሽንንም በደብዳቤ እንደጠየቁ ይነገራል። አስገራሚ ነገር ነው። መጠየቃቸው ባልከፋ። ወገናቸውን ለማነጋጋር በዚህ ደረጃ መፈለጋቸው የሚወገዝ አይደለም። ነገር ግን ምን አስበው ነው? ውጭ ላለው ኢትዮጵያዊ እስከአሁን በሀገር ቤት ከተናገሩት የተለየ ምን ሊነግሩት ነው? ቢያንስ የተወሰኑ በህዝብ ዘንድ የሚጠየቁ እርምጃዎችን ከወሰዱና መንገዱን ካለሳለሱ በኋላ ቢሆን አይሻልም? መድረክ እንዲህ የጠማቸው ለምን ይሆን?

የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌደሬሽን የራሱን መተዳደሪያ ደንብ ጥሶ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥያቄ ይቀበላል የሚል ግምት የለኝም። ፌዴሬሽኑን ለሁለት ከፍሎት ላለፉት 7 ዓመታት የዘለቀው ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን በክብር እንግድነት በጋበዘ ወቅት ከህወሀት ደጋፊ የፌዴሬሽኑ አመራሮች በኩል ተቃውሞ በመቅረቡ ነው። እንደመፍትሄም የፖለቲካ ሰው ከየትኛውም ወገን መጋበዝ አይቻልም የሚል መመሪያ ደንቡ ውስጥ አስቀምጦ ነው የቆየው። በዚህ ዓመትም አቶ በቀለ ገርባን ለመጋበዝ ታስቦ ይህ መመሪያቸው እንደከለከለቸው ሰምቼአለሁ። እስክንድር ነጋ ጋዜጠኛ በመሆኑ ሊጋበዝ እንድታሰብ ታውቋል።

ታዲያ ዶ/ር አብይ ያቀረቡትን ”በእንግድነት ጋብዙኝ” ጥያቄን ፌዴሬሽኑ ምን መልስ ሊሰጥ ይሆን? መመሪያውን ጥሶ ጥያቄአቸውን ሊቀበል? ወይስ ለደንቡ ተገዝቶ በአቋሙ መጽናት? ይህ ፌዴሬሽን በዚህ ውሳኔ ከሁለት ዳግም እንዳይከፈል ስጋት እንዳለ ይሰማል። ዶ/ር አብይ አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት የኢትዮጵያውያን መሰባሰቢያ የሆነውን መድረክ ከአደጋ ጋር አፋጠውታል። ዲያስፖራውን ለማዳከም ህወሀት ብዙ ሙከራ አድርጓል። አልተሳካለትም። ዶ/ር አብይ ይህን ያደርጉታል ብዬ አልጠብቅም። ካደረጉት ግን አካሄዳቸውን ብቻ ሳይሆን ያደነቅነውንና ያጨበጭብልነትን አመጣጣቸውንም በጥያቄ እንድንመረምረው የሚያደርገን ይሆናል።

ዶ/ር አብይ መድረክ አብዝተዋል። በእምነት ህይወታቸው የቀሰሙትን የማነቃቂያ ንግግር ክህሎታቸውን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ጉዟቸው አጥበቅው እየተጠቀሙበት ነው። ሆኖም እንዲህ መድረክ የሚያስጠና ውጤት አስመዝግበዋል ብዬ አላምንም። ስራው መቅደም ነበረበት። ቢያንስ ደጋፊዎቻቸው አደረጉ ብለው ነጥብ ከሚሰጧቸው አንዳንድ እርምጃዎች ተሻግረው መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ እርምጃዎችን በሂደት ደረጃ ሳያሳዩ በየመድረኩ መከሰትና፡ ጋብዙኝ ማለት የሚደገፍ ውሳኔ አይደለም።

ትላንት በኤምባሲ በተጠራ ስብሰባ ላይ ኢሳትና አባይ ሚዲያ እንዳይገቡ ተደርገዋል። ለኢትዮጵያውያን በሙሉ በተጠራው መድረክ ላይ ለምን እንዲህ ዓይነት ክልከላ እንዳስፈለገ ግራ ያጋባል። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር የለውጥ ምልክት ማሳየት ካለበት ከዚህ መጀምር ይኖርበታል። ኤምባሲው ባልተለመደ መልኩ ደጋፊና አባል ብሎ ልዩነት ሳያደርግ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ያቀረበው ጥሪ የሚበረታታ ነበር። ሆኖም ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ ነገር ሆኖ የህወሀት ሰዎች ከተጣበቀባቸው አባዜ ባለመላቀቃቸው ታጥቦ ጭቃ ሆነው አርፈዋል። ኤምባሲው በር ላይ የሚገባና የሚወጣ የሚለዩ መሆናቸውን ዳግም አሳይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በነሃሴ ወደ አሜሪካ ይመጣሉ በሚል በዋሽንግተን ዲሲ ሽር ጉድ እያሉ ያሉ ግለሰቦችንም ካየን የተለመደው የካድሬ ግርግር ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አይከብድም። ከስርዓቱ ጋር በጥቅም የተሳሰሩ ሰዎች ኮሚቴ አቋቁመው ለአቀባበል ወገባቸውን አጥብቀው እየሰሩ ነው። እንደምንሰማው ጠቅላይ ሚኒስትሩም እየመረጡ አንዳንድ አክቲቪስቶች ጋር ስልክ ደውለው እያነጋገሩ ነው። መለየቱ ለምን እንዳስፈለገ አይገባኝም። ለመፍትሄና ለዘላቂ ለውጥ ከልብ የተነሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ እንዲህ ዓይነት ከፋፋይ መንገድ ተመራጭ አይደለም።

መሪነታቸው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩል መሆኑን ማሳየት የእሳቸው ግዴታ ነው። እዚህ ያለውን አንድነት በማንኮታኮት ላይ የተመሰረተውን የህወሀት ታክቲክ ዶ/ር አብይ እንዳይከተሉት የቅርብ ወዳጆጃቸው ቢመክሯቸው ጥሩ ነው። ኢህአዴግ ከሚባለው የግዑዛን ስብስብ እሳቸውና ቲም ለማ እንደሚለዩ በዚያም የኢትዮጵያን ህዝብ ድጋፍ እንደሸመቱ አይጠፋቸውም ብዬ አስባለሁ። አሁንም በኢህ አዴግ ዜማና ቅኝት እንድንደንስ እየፈለጉ ከሆነ ብዙም ርቀት የሚወስዳቸው አይሆንም። እሳቸው እንዳሉትም ይህ ትውልድ በአዲስ አስተሳሰብ እንጂ ባረጀው ሊመራ አይፈቅድም።

በአጭሩ መድረክ የመጠማታቸውን ያህል ለተግባራዊ መሰረታዊ ለውጦች ቅድሚያ ሰጥተው እንዲተጉ ያስፈልጋል። ዙሪያቸው ተኮልኩለው አላሰራ ያሉ የህወሀት እንቅፋቶችን በሂደት እየጠራረጉ በቃላቸው የዘመሩትን ኢትዮጵያዊ ለውጥ በተግባር እንዲያሳዩ ይጠበቃሉ። ያን ጊዜ በአንደበታቸው ብቻ ሳይሆን በውጤታቸው የሚማረክ ከጥግ እስከ ጥግ ያገኛሉ።
#ግንቦት20የጨለማቀን

ዶ/ር አብይ: ጊዜው አሁን አይደለም!! (መኮንን ሀብተጊዮርጊስ ብሩ (ዶ/ር)

3 COMMENTS

 1. ይህ ሰው በአገር ውስጥ ስራ የለም ማለት ነወ አንደ ቱሪስት የሚዘረው?

 2. ጠ/ሚ አብይ ተገኝተው ንግግር አደረጉና “አደገኛነቱ” ምኑ ላይ ነው?
  ሁሉን ነገር ማጨለም ለምን አስፈለገ?
  መቸ ይሆን የምናድገው?
  ዶ/ር ብርሃኑ ፓርላማውን ሁሉ ካላስረከቡኝ በስተቀር ባሸነፍነው አብላጫ ወንበር
  ብቻ አልሳተፍም አለ፤ ሁሉንም አጣው!
  ዶ/ር አብይ ስለ ኢትዮጵያ አገራችን ከዚህ ቀደም
  አረመኔው መለስ ሲቀልድብን የኖረውን ቀለበሰው።
  እንደ ቴዲ አፍሮ ማለት ነው፤ እንደ በቀለ ገርባ።
  የታሪክ አጋጣሚ ደጋግሞ ለምን ያመልጠናል?
  ጠ/ሚንስትሩን እንስማና ካልተስማማን መተው ነው!
  እኔ የሚመስለኝ የተቃዋሚው ጎራ ህዝቡን በጥላቻ ካልሆነ
  ማስተባበር አይችልምና ነው። ህወሓት/ወያኔን መጥላት ካልሆነ
  ህዝብ አይሰባሰብም። ዶ/ር አብይ የህዝቡን ቀልብ እንዳይስብና
  ያለ አጃቢ እንዳያስቀረን ፈርተን ነው። ምሥጢሩ ይኸው ነው!
  ዶ/ር ብርሃኑ ለምሳሌ፣ ጠ/ሚ አብይ ሰባት ነጥቦችን ካላሟላ አንተባበረውም ብሎናል።
  ባያሟላ ምን ማድረግ ይችላልና ነው የሚደነፋው? ያው ወደ ኢሳይያሱ ጋ መሄድ ካልሆነ።
  ነአምን ቢቢሲ “ሃርድቶክ”ላይ እንዲያውም ለኤርትራ ጥብቅና ቆሞ አላሳፈረውም።
  ባጭሩ፣ ዶ/ር አብይ መጥቶ ንግግር ቢያደርግ ምንም አደገኛነት የለውም።
  የኢትዮጵያ ህዝብ ክዳር ዳር ተገልብጦ መነሳቱ ህወሓትን አስደንግጦታል።
  ስዩም መስፍንን አድምጣችሁታል? ህዝብ ህወሓትን ማየትና መስማት አይፈልግም!!
  ትልቁ የፖለቲካ ድል የተገኘው አሁን ነው። ዶ/ር አብይ እና ገዱ እና ለማ
  ቁም ነገር እንዲሠሩ የህዝብ መነሳሳት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
  ህዝብ ተገልብጦ ቢሰማውና ልቡ ቢወሰድ አደገኛነቱ “መሪዎች” ነን የሚሉትን ሥራፈት ያደርጋቸዋልና ነው!
  ይልቅ ጉልበታችንን ለሌላ ዋነኛ ጉዳይ እናውል። ለምሳሌ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማ ስለ አሰብ ያነሳውን
  በዶ/ሩ አስተባባሪነት ኮሚቴ ተቋቋሞ በዓለም ፍርድ ቤት ፋይል መክፈት ይቻላል። ህወሓት የኢትዮጵያን ጥቅም
  አሳልፎ ሰጥቷል፤ ወንጀል ነው። ህወሓት በመሪዎቹ በኩል ያሸሸውን ንዋይ ለማስመለስ ዘመቻ ሌላኛው ሥራ ነው።
  በዐረብ ምድር ለብዙ እንግልትና በደል ለተጋለጡት ወገኖች፣ ያለ ወላጅ ፈቃድ ህጻናትን ለውጭ አገር የሸጡትን ጉዳይ። ወዘተ።

 3. “ታዲያ ዶ/ር አብይ ያቀረቡትን ”በእንግድነት ጋብዙኝ” ጥያቄን ፌዴሬሽኑ ምን መልስ ሊሰጥ ይሆን? መመሪያውን ጥሶ ጥያቄአቸውን ሊቀበል? ወይስ ለደንቡ ተገዝቶ በአቋሙ መጽናት? ይህ ፌዴሬሽን በዚህ ውሳኔ ከሁለት ዳግም እንዳይከፈል ስጋት እንዳለ ይሰማል። ዶ/ር አብይ አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት የኢትዮጵያውያን መሰባሰቢያ የሆነውን መድረክ ከአደጋ ጋር አፋጠውታል። ዲያስፖራውን ለማዳከም ህወሀት ብዙ ሙከራ አድርጓል። አልተሳካለትም። ዶ/ር አብይ ይህን ያደርጉታል ብዬ አልጠብቅም። ካደረጉት ግን አካሄዳቸውን ብቻ ሳይሆን ያደነቅነውንና ያጨበጭብልነትን አመጣጣቸውንም በጥያቄ እንድንመረምረው የሚያደርገን ይሆናል።”
  ብለው አቶ መሳይ መኮንን የከተቡትን አነበብኩ አውጥቼ አውርጄ ይህን ማለት ፈለኩ:: አቶ መሳይ መኮንን በሰው እጅ የተጻፈ ህግ (ደንብ) እንደ ግዜውና እንደ ወቅቱ የሚሻሻል መሆኑን ለአንተ መንገሩ ድካም ነው ብዪ ትቸው ነበር ቆይቼ ሳስበው ግን እንደገና ይህችን መጫጫር ጀመርኩ እንደ እውነቱ ከሆነ የጠቅላይ ሚንስቴር አብይ መምጣት በውጪ ያለነውን ኢትዮጵያዊ ልከፋፍል የሚችልበትን ምንም ዓይነት መረጃ አንድ ሁለት ብለህ ያስቀመጥከው ነገር ባለማየቴ የአንተ ስጋት “እባብ የነከሰው በልጥ ይደነብራል” እንደሚሉት ነው የሆነብኝ:: ሌላው ደሞ በዊጪ ያለውን ኢትዮጵያዊ አላዋቂ አድርጎ መገመት ጭምር ይመስለኛል ለምን ብትለኝ ለምንድን ነው የጠ/ሚ መጥቶ በአሉን ከህዝቡ ጋር ማክበር እኛን ለሁለት የሚከፍለን መጀመሪያውንስ በሰላማዊ ትግል መንግስትን መለወጥ ይቻላ የሚልና የዛ ተቃራኒ የሆነ ደሞ መንግስትን መለወጥ የሚቻለው በጦርነት ነው የሚለው ክፍል እስከ አሁኑ መች አንድ ሆንን::
  በውጪ ያለነው በሁለት ጎራ የተከፈልን ስለሆነ በዶ/ር አብይ ማሳበቡ በኔ እምነት ውሃ አያነሳም ባይ ነኝ:: በሌላ በኩል “የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌደሬሽን የራሱን መተዳደሪያ ደንብ ጥሶ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥያቄ ይቀበላል የሚል ግምት የለኝም።” ለሚለው ፍራችህ የማይለወጥ የማይሻር የአምላክ ቃል ብቻ ነው በቅዱስ መጽሐፍም ውስጥ አለም ታልፋለች እንጂ ቃሌ አታልፍም “ይላልና በእኛ በሰዎች የሚጻፉ ህጎችም ሆነ ደንቦች እንደ ወቅቱና እንደየግዜው ሊሻሻሉ የሚችሉ ናቸው:: እርግጥ ኢጎ ያለበት ሰው እኔ ያልኩት ካልሆነ ሞቼ እገኛለው ሊል ይችላል ነገር ግን እንደዚ ዓይነት ሰው ከግዜ ጋር የማይራመዽና ያለበትን ግዜ የማያስተውል ሰው ነው ባይ ነኝ::
  ቸር ይግጠመን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.