የዐውደ ኣመት ሽሙጥ! (ከ ሙሉጌታ ገዛኸኝ)

የዘመን ወረቱ በእድሜ ዥረት እንደ በቅሎ እየሰገረ አንዱን ከአንዱን ሲያስማማና ሲያላጋ ይነጉዳል፡፡ ለአፍታ ብልጭ ድርግም፤ በአንዳች የስብዕና ምስቅል ቅል ጡዘት ግብ ግብ ሌላማ ምንስ ትርፍ ይኖራል፡፡

በየትኛውም አገር ሕብረተሰብ የሚታነፅበት የራሱ ረቂቅ ሥነ ልቦናዊ ባህሪያት ይኖሩታል፡፡ ደግሞም ከሌላው ጋር የሚመሳሰልበትና የሚቃረንበት እንዲሁ፡፡ እንደዛሬው ዘመን ቅጥ አምባሩ ሳይጠፋ የቀደሙት ኢትዮጵያውያን አበውና እመው ሳይጠናኑ እየተጋቡ ውስኬታማ ህይወት ይኖሩት ነበር፤ ዛሬ ላይማ ይጠናናል ያለዚያም ይጣናን፡፡ ከሠርገኛው አጀብና ሽርጉድ ጋር ድግሱ ቅልጥልጥ ብቻ የምግብ ኤክስፖና ባዛርን ይተካከላል ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ መጠናናቱ ያጣመረው ሙሽራ አፍታም ሳይቆይ ወደ እውን እዝነ ልቦና ሲመለስ እንደገና ሌላ ወረት፡፡ አጃኢብ!

ከሰሞኑ በዓብይ ፆም ዓቢይ የተሰኘ መልከ መልካም ጠቅላይ ሚኒስትር ብቅ ቢል ተስፋ አንበሸበሸንና ሀሴት ሻትን ፌሽታ ብጤም መቼም ቃጣን፡፡ ግና አበው ያው በገሌ እንዳሉት እንዳይሆንብን ፈጣሪ ይርዳን፡፡  እንዴት ከረማችሁሳ! እስቲ ወጉ በደረቁ እንዳይሆን እናዋዛው፡፡ የመኖር ህልውና ተስፋቸው በዓብይ ፆም ምክንያት የለመለመው ዶሮዎች ትዕይንተ ህዝብ ወጡና እንዲህ ሲሉ መፈክር አሰሙ “ስንኖር ዶሮ ስንሞት ደግሞ ዶሮወጥ መሆን ሰለቸን፤ ጾም ለዘላለም ይኑርልን አቦ!!!”፡፡ የቅርጫ ሠንጋ አራጁ ሥጋውን አሰናድቶ ሲያበቃ ጨጓራና ሳንባ አልተገኙም፡፡ ታዲያ ሲጠየቅ “በሬውም እንደ ሰው በዋጋ ግሽበት በመበሳጨቱ ጨጓራ አልባሆነ፤ ‘የጿሚና ፀላይ’ ሥጋ አምሮት ጉጉት ምስኪኑን በሬ አስጨነቀው መተንፈሻም አሳጣው” ብሎ እርፍ፡፡ ለክርስትና እምነት ተከታዮችም የትንሳኤ በዓል አውደ ኣመት ነበርና እንዲሁ የተለያየ ገጠመኝም አይጠፋም፡፡

በዓሉ በዓል ሲመስልና ተፍ ተፍ ጋብ ሲል የኑሮና ብልሃቱ ዜይቤ ከብርንዶ ሥጋው ወደ ጎድን ጥብሱ ከዚያም ወደ ሽሮ በሥጋ…ሽሮ…ሽሮ ፈሰስ… እያለ ያጋድላል፡፡ ሁኔታው አልጥም ቢለኝ አንድ ወዳጄ “ወግ አጥባቂ ጿሚ በፋሲካ በዓል ሽሮ አምጡልኝ ይላል” ሲል ሰማሁት፡፡ ብቻ በዚህም ተባለ በዚያ ኣውደ ዓመት ድርድር አያውቅምና መፍጨርጨርን ከመጤፍ አይቆጥርም፡፡

አይቀሬው ጥድፊያ ይቀጥልና የሕይወት ዕለት በዕለት ዐውድ ናላውን ያዞረው አባውራ የቤቱን ጣጣ አጠናቆ ወጣ ሲል ማህበራዊ ኑሮ፤ እድር፤ ሰንበቴ፤ የተረሳ ወዳጅ ጥያቆ፤ ወዘተርፈ…ግንኙነቶች፡፡ በዘመናት የኋሊት ሽምጥ ግልቢያ ቁዘማቸውን አንድ አዛውንት ዘመኑን አብሰለሰሉት ‘ያኔሽንጥ ሥጋ አንድ ብር ከአምሳ ኧረ እንዲያውም በብር ከሃያ አምስት ይሸመታል፤ ዶሮይቱማ ጭራሽ ለገበያ አትቀርብም ዝም ብሎ አፈፍ አርጎ ይዞ ሲያምር ሽክ ነበር’ ዛሬ ላይማ እንዲያም እንዲያም ተብሎ የበዓል ወጉ እንዳይቀር ብቻ ገበያ ይወጣል ታዲያ አንጀት አያርስ፤ የትአባቱንስ አሲዳም ዘመን…፡፡ ምናባችንን መለስ ብለን ወግ ብጤችንን ልንቀጥል ስንል….አይ ኑሮና ብልሃቱ ሲሉ ቋጩት፡፡ ቸር ይግጠመን!!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.