ዉጭ ያላችሁ መአህዶች እና ሀገር ቤት ያላችሁ መአህዶች ከምትካሰሱ ለምን አብሮ ስለ መስራት አትመካከሩም? (ሸንቁጥ አየለ)

የአማራ ድርጅቶችስ በጥቅል የተናበበ አካሄድ ለመቀመር እንዳትችሉ ማን ነዉ አዚም ያደረገባችሁ?
ሸንቁጥ አየለ
በአቶ ሸዋንግዛዉ የሚመራዉ ሀገር ቤት ያለዉ መአህድ ማን ነዉ?
———
መአህድን (የመላዉ አማራ ህዝብ ድርጅት) ገና ከጠዋቱ የገጠመዉ ቁልፍ እና ዋና ፈተና የድርጅቱ መሪ ፕሮፌሰር አስራት በወያኔ መታሰራቸዉ እና እስኪሞቱ ድረስ በወህኒ እንዲማቅቁ መደረጋቸዉ ነበር::

ከዚህ በተጨማሪም መአህድ ሶስት ፈተናዎች ገጥመዉት ነበር::አንደኛዉ ፈተና አቶ ልደቱ የመአህድን ወጣቶች ሰብስቦ የብሄር ድርጅት ሳይሆን ህብረ ብሄራዊ ድርጅት ነዉ የሚያስፈልገዉ ብሎ ከመአህድ ወጣቶችን ሰብስቦ በመዉጣት ኢዴፓን የመሰረተ ጊዜ ነዉ::መአህድ በዚህ ወቅት በወጣት ድርቅ ተመትቶ በጣም ተመናምኖ ነበር::ሆኖም እነ ቀኝ አዝማች ነቀአ ጥበብ እና እነ አቶ ሸዋንግዛዉ ባደረጉት ርብርቦሾ መአህድ እንደገና ተጠናክሮ መቀጠል ችሎ ነበር::

ሁለተኛዉ የመአህድ ፈተና ደግሞ ኢ/ር ሀይሉ ሻዉል መአህድን ወደ መኢአድንነት ለመለወጥ የወሰኑ ጊዜ ነዉ::ኢ/ር ሀይሉ ሻዉል መአህድን ወደ መኢአድ በሚለዉጡበት ጊዜ በቀኛዝማች ነቀአጥበብ እና በአቶ ሸዋንግዛዉ የሚመራ ሀይል ኢ/ር ሀይሉ ሻዉልን በመቃወም ወደ መኢአድንነት ሳይቀላቀሉ በመአህድነት ጸንተዉ ቆይተዋል::ሆኖም የመአህድን ቢሮ: የዉጭ ድጋፍ እና ብዙሃኑን ደጋፊ ኢ/ር ሀይሉ ሻዉል ይዘዉት ስለሄዱ የእነ ቀኛዝማች ነቀአጥበብ ልፋት ብዙም በህዝብ አልታዬም ነበር::በወቅቱ የነበረዉንም የመአህድ ብሶት አሁን በአካል ያሉት አቶ ሸዋንግዛዉ ሁለት ሶስት ጊዜ አግኝተዉኝ አነጋግረዉኝ ነበር::አቶ ሸዋንግዛዉ በጣም ጽናት ያላቸዉ ግን በጥቂቱ የሚናገሩ ናቸዉ::አቶ ሸዋንግዛዉ መአህድን የሚያገለግሉት እንደ አንድ ታላቅ የሀይማኖት ተልዕኮ አድርገዉ ነዉ::ይሄን የአቶ ሸዋንግዛዉን ሀሳብ ለመረዳት ከአቶ ሸዋንግዛዉ ጋር ቁጭ ብሎ በማዉራት ብቻ ነዉ ማወቅ የሚቻለዉ::

መአህድ ከዚያ ብኋላ በዶክተር አስራት (ፕሮፌሰር አስራት ማለቴ አይደለም) ፕሬዝዳንትነት : በእስክንድር ነጋ ጸሃፊነት እንዲሁም አሁን ዉጭ ሀገር በሚገኘዉ ሀይለ ገብርኤል አመራርነት ለማገገም ብዙ ታግሎ ነበር::

የሆኖ ሆኖ የ1997 ዓም ምርጫ እና የቅንጅቱ ገኖ መዉጣት ሌላዉ የመአህድ ሶስተኛ ፈተና ነበር::መአህድ ከምርጫ 97 ብኋላ በጣም ተዳክሞ እና በእነ አቶ ሸዋንግዛዉ አመራር ብቻ እየታገዘ እስካሁን ድረስ ቆይቷል::እንዲያዉም በርካታ ሚዲያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ እንኳን እንዳያገኝ ሲያከላክሉት የእኛ ሚዲያ የነበረችዉ የቀለም ቀንድ ግን የመአህድ አመራሮችን (እነ አቶ ሸዋንግዛዉን ) እያፈላለገች ወደ ህዝብ ለማዉጣት ብዙ ጥረት አድርጋለች:: ለዚህም ምስክር በወቅቱ የጋዜጣችን ዋና አዘጋጅ የነበረዉ ጋዜጠኛ በለጠ አንዱ ነዉ::በተለይም መአህድን ወደ አደባባይ ካወጣንዉ ብኋላ በቀለም ቀንድ ላይ ይዘንብባት የነበረዉ ትችት የአማራ ጋዜጣ ነች::ጋዜጣዋ መአህድን (የመላዉ አማራ ህዝብ ድርጅትን) እና መኢአድን(የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትን) ወደ መድረክ ማምጣቷ የአማራን ሀይል ወደ ስልጣን ለማዉታጣት አላማ ስላላት ነዉ የሚል ትችት ይዘንም ነበር:: ለዚህም ትችትም በወቅቱ ምላሽ ሰጥቼበት ነበር::

ከዚህ በተጨማሪም ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋዉ እራሱ እንደሚመሰክረዉ የጥፋት ዘመን የሚለዉ መጽሃፉን በሚጽፍበት ጊዜ የመአህዱ መሪ አቶ ሸዋንግዛዉ እና የመኢአዱ መሪ አቶ ማሙሸት አማረ ከፍተኛ እገዛ አድርገዋል:: ሙሉቀን ይሄን ሀቅ የማሳወቅ ሀላፊነት ይጠበቅበት ይመስለኛል::መኢአድ እና መአህድ በዘረጉት መስመር እና ድርጅታዊ መዋቅር ባይሆን ኖሮ የጥፋት ዘመን መጽሃፍን ማዘጋጀት በጣም ከባድ ይሆን ነበር::ስለዚህም እነ አቶ ሸዋንግዛዉ በአሁኑ ሰዓት እንደ ወያኔ ተላላኪ ተደርገዉ የሚሰደቡት ስድብ እጅግ ነዉር ነዉ::የቀደሙት ጀግኖች ላበረከቱት ዉለታ ምስጋና ሳታቀርብ ጀግና ነኝ ብትል አንተ ፈሪ እንጅ ጀግና አይደለህም::እነ አቶ ሸዋንግዛዉ የአማራን ህዝብ ያገለገሉት እና ስለ አማራ ህልዉና የታገሉት በነዲድ እሳት ዉስጥ እየተረማመዱ ነዉ::እኔ ሁል ጊዜ ለመአህድ ሰዎች እና ለመኢአድ ሰዎች ያለኝ ክብር በአንድ ምክንያት ብቻ ነዉ::በፈተናዉ ሰዓት በእሳቱ ነዲድ ፊት የቆሙ እንዲሁም በእሳቱ ነዲድ ዉስጥ ለህዝባቸዉ ሲሉ የተመላለሱ ጀግኖች ናቸዉ::

በአጠቃልይ ግን አቶ ሸዋንግዛዉ የሚመሩት የመላዉ አማራ ህዝብ ድርጅት (መአህድ) ከፍተኛ መስዋዕት ሲከፍል እየንበረ እና ላለፉት ሃያ ስድስት አመታት የታገለ ድርጅት ነዉ::ሳያቋርጥ እና ሳያሰልስ::

በተለይም እነ ቀኛዝማች ነቀአ ጥበብ ላይ የወያኔ ፕሮፖጋንዲስቶች የሀሰት ስም ማጥፋት እያደረጉ ብዙ ከህዝብ እንዲነጠሉ ሰርተዋል::ነቀአጥበብ የወያኔን ደህንነት ለአንድ ቀን እሰረኝ እና እዉቅና ላግኝ ብለዋል እየተባለ በሀሰት ስማቸዉ ሲጠፋ ነበር::አሁንም አንዳንዶች እዉነት እየመሰላቸዉ ይሄንኑ ነገር ያራግቡታል::እዉነታዉ ግን ቀኛዝማች ነቀ አጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሄር ያላቸዉ እና ኩሩ :እንዲሁም ደፋር ጀግና እንጅ የማንንም የወያኔ ሀላፊዎችን እሰሩኝ እና እዉቅና ላግኝ የሚሉ ሰዉ አልነበሩም::በመአህድ የተነሳ በርካታ የንግድ ድርጅቶችን ያጡ ቆራጥ ሰዉ ናቸዉ:: ቀናዝማች ነቀዓጥበብ ሀብታም ነጋዴ የነበሩ ታላቅ ሰዉ ሲሆኑ መአህድን ከፕሮፌሰር አስራት ጋር ሆነዉ ካቋቋሙ ብኋላ ግን በወያኔዎች ሀብታቸዉ በብዙ መልክ ተዘርፏል:: በርካታ የንግድ ድርጅቶቻቸዉም እንዲከስሩ ተደርጓል::ከኢ/ር ሀይሉ ሻዉል ጋርም ባልተስማሙ ጊዜ በክብር እና ያለ ብዙ መዘላለፍ መአህድን አስከብረዉ የቀጠሉ የአቋም ሰዉ ነበሩ::ሌላዉ ቀርቶ በሀሳብ ቢለያዩም ከኢ/ር ሀይሉ ሻዉል ጋር በሚያቀራርባቸዉ ነገር ላይ የሚመክሩ ታላቅ ሰዉ ነበሩ::ሆኖም ስማቸዉን ወያኔ ሲያጠፋ አማራ ነኝ የሚለዉም ምሁር አብሮ የኝህን ታላቅ አባት ስም አብሮ ያጠፋል::አሁንም ስማቸዉን ማጥፋቱን ቀጥሏል::በተለይም የብአዴን ተላላኪዎች የወያኔን ፕሮፖጋንዳ ማራገብ ልማዳቸዉ ነዉ::

ዉጭ ሀገር የሚገኘዉ መአህድ
———–
የሀገር ቤቱ መአህድ በተዳከመበት እና ድምጹን እንኳን በደንብ አድርጎ ማሰማት ባልቻለበት ሁኔታ በተለይም ወያኔ የአዉራ ፓርቲ ፖሊሲዉን አዉጆ ሁሉንም ሀገር ቤት ያሉ ፓርቲዎችን ጸጥ ባደረገበት እና ባፈረሰበት ወቅት ግን ከዉጭ ሀገር የመአህድ መልሶ የመመስረት እንቅስቃሴ ተፋፋመ::በተለይም በዉጭ ሀገር የሚገኙ እና የመአህድ ድጋፊዎች መአህድ በሀገር ቤት መዳከሙን በማወቅ ይመስላል በዉጭ ሀገር እንደገና እንዲያንሰራራ ጠንካራ ስራ መስራት ቻሉ:: በዚህም ተስጭ ወጣቶች የሚገኙበት እና በርካታ በዉጭ ሀገር የሚገኙ ምሁራን የተሰባሰቡበት እንቅስቃሴ መጀመሪያ ዳግም መአህድ በሂደትም መአህድ ብሎ ተጠናክሮ ወጥቷል::ይሄ ሀይል አሁን በዉጭ ሀገር ካሉት የአማራ ድርጅቶች መልካም መሰረት የጣለ ይመስለኛል:: በተለይም በሚዲያ እንቅስቃሴ ይበል የሚያስብል ስራ እየሰራ ነዉ::

የሆኖ ሆኖ ግን አሁን ሰሞኑን ክስና ወቀሳ ሀገር ቤት ባለዉ መአህድ እና ዉጭ ሀገር ባለዉ መአህድ መሃከል ተጀምሯል::አንዱ አንዱን የማጠልሸት አይነት ነገር::ይሄ የመካሰስ ነገር ሳይባባስ እንዲሁም ሰሚ ከተገኘ ብዬ ይህችን ጽሁፍ አዘጋጀሁ::እኔ እንደ ማስበዉ ሀገር ቤት ያለዉ መአህድ እና ዉጭ ሀገር ያለዉ መአህድ ተመጋጋቢ እና ተወራራሽ እንጅ የሚጠፋፉ አይደሉም::ሁለቱም ለአንድ ህዝብ እና ለአንድ አላማ የቆሙ ሀይሎች እስከሆኑ ድረስ የግድ መናበብ እና መደማመጥ አለባቸዉ::

ስለሆነም አደባባይ ላይ ከመዘላለፍ በጋራ በተጠና መልክ የምትነጋገሩበትን እና የምትደጋገፉበትን መስመር መዘርጋቱ መልካም ይሆናል::ከሁሉም በፊት መከባበር እና እዉነተኛ ህዝባዊ ሰፊ ግብን ማንገቡ እና በሚያግባቡ ሁኔታዎች ላይ መስራት መልካም ብቻ ሳይሆን ግድ ነዉ::እንዴያዉም እንዲህ ያለ የተመጋገበ እና የተናበበ አጋጣሚያዊ ሂደት በመከሰቱ አብሮ ለመስራት ያተጋል እንጅ የሚያጠፋፋ አይሆንም::

እንዲሁም አሁን በሀገር ቤት አዲስ የሚመሰረተዉ የአማራ ድርጅት : በዉጭ ያሉ የተለያዩ የአማራ ድርጅቶች ብሎም ዉጭም ሀገር ቤትም ያሉ የአማራ ሀይላት ሁሉ በጥንቃቄ በመነጋገር የጎደለዉን በማሟላት ላቅ ያለ ፖለቲካዊ አንድነትን ለመፍጠር ቢንቀሳቀሱ ለአማራም ህዝብ ህልዉና እንዲሁም ለኢትዮጵያ ህዝብ የዲሞክራሲን ብሎም የብልጽግናን መስመር ማፋጠን ይቻላሉ::

ከእፉኝት ፖለቲካ መዉጣቱ ጥሩ ነዉ::ወንጌል አንደምታ አስገራሚ በሆነ መልክ እንደሚያትተዉ እፉኝት ስትጸነስ አባቷን ትገላለች::ስትወለድ እናቷን ትገላለች::ዘሯን ስትተካ በልጆቿ ትገደላለች::እናም የትዉልድ ፈሰት የላትም:: ሳይጠፋፉ እና የግድ እኔ ብቻ ያልኩት ነዉ ትክክለኛዉ መንገድ ሳይሉ ሰፋ እና ላቅ ያለ ፖለቲካዊ ሂደትን መከወን ይቻላል::ወደ ሶሻሊስታዊ የመደብ መጠፋፋት ጽንሰ ሀሳብ ለመግባት መፋጠኑ ሁሉንም ሀይል ያጠፋዋል ብሎም ህዝብን ክፉኛ ይጎዳዋል እንጅ ማንም አሸናፊ አይኖርም::ስለዚህ ከሶሻሊስታዊ የመደብ ፖለቲካዊ የመጠፋፋት እና አንዱ ገኖ የመዉጣት ሰይጣናዊ የፖለቲካ ፍልስፍና መታቀብ ይገባል::

የዚህ ጽሁፍ መደምደሚያ አንድ ነዉ::ከመነቃቀፍ እና ለመጠፋፋት ከመፋተን አብሮ መስራት የሚቻልበትን ሂደት እና ስልት ተቀራርባችሁ ብሎም እረጅም ጊዜ ወስዳችሁ ቀይሱ::ይሄም የመአህዶች ግዴታ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የአማራ ድርጅቶች የጋራ ግዴታ ነዉ::

ነጥቤን ባነሳሁት ጥያቄ ልደምድመዉ:: ዉጭ ያላችሁ መአህዶች እና ሀገር ቤት ያላችሁ መአህዶች ከምትካሰሱ ለምን አብሮ ስለ መስራት አትመካከሩም?
የአማራ ድርጅቶችስ በጥቅል የተናበበ አካሄድ ለመቀመር እንዳትችሉ ማን ነዉ አዚም ያደረገባችሁ?

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.