ሕዝባዊ እፎይታን የዋጀው የዶክተር አብይ ሚና (ከ ሙሉጌታ ገዛኸኝ)

ክቡር አብይ ሆይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት አክብረሃልና ስምህ በታሪክ መዝገብ ይሰፍራል፡፡ ለሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብር በተግባር ቆመህ አይተናልና በእጅጉ እናመሰግናለን!!!

የነጻነት ታጋዩን አንዳርጋቸው ፅጌ[ኢትዮጵያዊው ማንዴላ]ን ከዚያ ድቅድቁ የጨለማ እስር መንጥቀህ ለባለ አደራው ሕዝብ አስረክበሀልና ደስታችን ወደር የለውም፡፡ የአንዳርጌ መፈታት አንድምታው ሚሊዮናት ሕዝብ እስራትን ይዋጃልና፡፡ እስራኤላውያንን በዚያ የጭንቅና የመከራ ዘመን ከግዞት እሮሮ ከሆነችው ምድረ ግብፅ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከነዓን ከመራው ሙሴ የማይተናነስ ኣርአያነትህ መቼውንም ቢሆን ሊዘነጋ አይችልም፡፡ በአንድ ወቅት ብልሁ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን “ጃ ያስተሰርያል!” በተሰኘ አልበሙ ላይ ባሰፈረው አጭር ማስታወሻ “ኢትዮጵያ የተማረ ብቻ ሳይሆን የተባረከም መሪ ትፈልጋለችና ብናገኝ አንጠላም” ብሎ ነበር፡፡ ግሩም ነው፡፡

ባለፉት የአገዛዝ ዓመታት ብዙሃኑ የአገራችን ሕዝብ እጣ ፋንታው ተረገጥ ሆኖ ስንቱ አበሳውን ቆጥሯል፡፡ የተጋዘው፣ የታገተው፣ የተሰደደው፣ የታሰረውና ያልታሰረው ወዘተርፈ ህልቆ መሳፍርት ነውና ለይቶ በቅጡ ለማወቅም ሁናቴው እጅግ አዳጋች በመሆኑ አንድ አገር አቀፍ አፈላላጊ ኮሚቴም ማቋቋም ሳያስፈልግ የሚቀር አይመስልም፡፡ እንዲያው የሆነው ሁሉ ሆኖ ፈጣሪ አመላክቶህ ሁሉን ነገር በበጎ ቅኝት ጀምረኸዋልና ስልጣንህን አምላክ ይባርክ፡፡ በፓርላማው አሸባሪ ተብለው እንዲፈረጁ የተደረጉ የተቀናቃኝ ድርጅቶች በሙሉ ወደ አገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ መታገል እንዲችሉ ማመቻቸቱ የዲሞክራሲ ዓይነተኛው መገለጫ ነው፡፡

ከምርጫ 97 ወዲህ ለያዥ ለገራዥ አስቸግሮ ለድርድር አልመች ያለው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ለቀጣይ ረጅም ዓመታት ብቸኛው አውራ ፓርቲ ሆኖ የመፅናት ፍላጎቱን የተገነዘቡት እነ ዶክተር ብርሀኑ ነጋ፣ አንዳርጋቸው ፅጌ እና ሌሎችም ከቅንጅት ፓርቲ ወደ አማራጭ የትግል ስልት ለማካሄድ እንደተገደዱ በይፋ ገልፁ፡፡ ግንቦት ሰባት የተሰኘ የትግል ግንባር ፈጥረው በውጭ አገራት መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ ሁኔታዎች እንዲህና እንዲ እየተለዋወጡ በአንዲት ጎዶሎ ቀን ከፍተኛ አመራራቸው የሆነው አንዳርጋቸው ፅጌ ሰነዓ ላይ በቁጥጥር ስር ለመዋል በቃ፡፡ታጋይ ይሞታል፤ ትግል ግን አይሞትም መርሁ ቀጥለ በአጋሮቹ ዘንድ ቀጠለ፡፡ በዚያው ሰሞን በአደባባይ የታሰሩ የፖሊቲካ ታሳሪዎች ይፈቱ ብሎ መጠየቅ ቀርቶ ስማቸውን እንኳ በሹክሹክታ መጥራትና መጻፍ እንደ ወንጀል ይቆጠር ነበር፡፡ ያለመታደል ሆኖ ከኢቢሲ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች አንስቶ እስከ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ድረስ ‘አንዳርጋቸው’ ለማለት ቃሉ መርዕድ ሆኖባቸው “እንዳርጋቸው” እያሉ አጎላድፈው ሲጠሩት መስማት የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በእንግሊዝ ዓለማቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ አገራችን እየተነቀፈች መመጣትን አስከተለ፡፡ ብሎም ያለማቋረጥ ሲጎርፍ የነበረው የፓውንድ ስተርሊንግ እርዳታ ወደ አገራችን ጠብ ሳይል እነሆ ለአራት ዓመታት ቆዬ፡፡ ሁኔታዎች ባጭር ጊዜ ተቀያይረው ዶክተር ዐብይ አህመድ የመራሄ መንግሥትነቱን ስልጣን ከተረከበ በኋላ የማሻሻያ እርምጃ አበክሮ ወሰደ፡፡ በዘመነ ኢህአዴግ ፈፅሞ ይሆናል ተብለው ያልተጠበቁ ለውጦችን በተግባር ማሳየት የቻለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ብቻ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ከእርሱ በፊት የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን በቃኝ ማቅረቡ የሚያስመሰግነው ቢሆንም አስከትሎት የሄደው ምስቅልቅል ግን ገና ለዶክተር አብይ የሚጠብቃቸው ከባድ የቤት ሥራ እንደሚሆን ግልፅ ነው፡፡ አንድ አዛውንት በያ ሰሞን እንዲህ ሲሉ ሰማሁ “ፊትአውራሪው አብይ አዝማቹማ ለማ፤ አስፈጅቶን ነበር ያነማ [ሀይለማርያም?] ቆልማማ፡፡”

ጠንቀኛዋ የመን ከእኛው “ልማጣዊ መንግስት” ባገኘችው ረብጣ ገንዘብ የዛሬ አራት አመት ገደማ  አንዳርጋቸው ፅጌ በጉዞው ወቅት እንግዳ ሆኖ ብቅ ቢል አሳልፋ ሰጠችው(ሸጠችው)፡፡ በወቅቱ የየመን ፕሬዝዳንት የነበረው አሊ አብደላ ሳላህ የፀረ ሽብርተኛ ስምምነት ቢያደርግም በአገሩ የሁቲ አማፅያን አናቱ በተምዘግዛጊ ሚሳዔል ተበጠረቀ፤ አሟሟቱም ሳያምር ቀረ፡፡ የሁቲ አማፅያን ብርቱ ጥቃት መቋቋም ከባድ ፈተና ሲሆንና የመን እንደ አገር መቀጠል ስለተስናት ወደ መፈራረስ አዝማሚያ ደረሰች፡፡ ፕሬዝዳንቷ አብደላ ሳላህም በአዲስ አበባ መኖር እንዲችል ቪላ መኖሪያ ቤት ተመቻችቶለት እንደነበርም ይጠቀሳል፡፡ ምናልባት አሳልፎ በሰጠው  የግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራር አባል (አንዳርጋቸው ፅጌ) ውለታ ሊሆን እንደሚችል በርካቶች ግምታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ይህችው የጨነገፈች አገር የመን ክፉ ልማድና ልክፍት ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን በ16ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይም የአጼ ልብነ ድንግልን ልጅ ሚናስን በባርነት አፍና ወስዳ ካሰቃየች በኋላ በመናኛ ዲናር ልዋጭነት ድርድር መመለሷ በታሪክ ይታወሳል፡፡ በዚህች የባሕር ስምጥ ወሽመጥ የፖሊቲካ ቀውስና ሞት እጣ ፋንታዋ ሆኖ እነሆ እስከዛሬም ድረስ ህልውናዋ የተናጋው የመን የምትበጀን ጎረቤት ልትሆን የምትችል አልመስል አለች፡፡ ምናልባት የፈረደበት የጫት ምርት በገፍ ከማጋበስ ባለፈ ይህ ነው የሚባል የምጣኔ ሀብት ስትራቴጂ  ጠቀሜታ ለእኛ የላትም፡፡ ስፍር ቁጥር የሌለውን የአገራችን ስደተኛ በሙሉ እምሽክ አድርጋ የበላች እርጉም አገር ስታስጠላ፡፡ ታዲያ ከየመን ምን ዓይነት በጎ ጉርብትና እንጠብቅ ያሰኛል? ቸር ያሰማን፡፡

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.