የአድዋ ዘማቾች – ዳንኤል ክብረት

የጉዞው መሥራቾች

ከዛሬ 119 ዓመት በፊት ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን በዓለም ታሪክ ያልተለመደ አዲስ ታሪክ ለመሥራትና ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር የማይደረስበት ከፍታ ላይ ለማስቀመጥ ሲሉ ከመላዋ ሀገሪቱ አንድ ሆነው ወጥተው፣ አንድ ሆነው ወደ አድዋ ዘምተው ነበር፡፡ ያኔ ብዙዎቹ የተጓዙት በእግራቸው ጋራ ሸንተረሩን፣ አረሁን ገደሉን እየተሻገሩ በፍጹም ኢትዮጵያዊ ወኔና ሀገራዊ ፍቅር ነበር፡፡ ያ አንድነትና የሀገር ፍቅር ስሜት ነበር ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችንን ሊደግሙት እንጂ ሊረሱት የማይገባ ታሪክ እንዲሠሩ ያደረጋቸው፡፡ትናንት(እሑድ መጋቢት 13 ቀን 2007 ዓም) በጨጨሆ የባሕል ምግብ አዳራሽ በተደረገ አንድ መርሐ ግብር ተጋብዤ ተገኝቼ ነበር፡፡ ‹ጉዞ አድዋ› ይባላል መርሐ ግብሩ፡፡

ይህንን የአድዋ መንፈስና ዝና፣ ክብርና ላቅ ያለ ኢትዮጵያዊነት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ፤ አድዋ እንደ አንድ ተራ ሥነ ሥርዓት በምኒልክ አደባባይ የአበባ ጉንጉን ከማስቀመጥና ‹አስቦ ከመዋል› የዘለለ ትውልዳዊ ፋይዳ እንዲኖረው ለማድረግ፤ አድዋ እንደ ባለሞያ ጠጅ በየጊዜው ከጥንስሱ እየተቆነጠረ በየትውልዱ እንዲጠጣ ለማስቻል፤ እንደ ሰራፕታ ዱቄት በየዘመናቱ ቡኾ ውስጥ እንደ እርሾ እየተጨመረ እንዲበላ ለማብቃት፣ አድዋ ላይ የታየው የላቀ ኢትዮጵያዊነት አንደ ሜሮን ቅብዐት ከትውልድ ትውልድ ሳይቋረጥ እየፈላ የሁሉ ማጥመቂያ እንዲሆን የተነሡ ወጣቶች ያዘጋጁት መርሐ ግብር ነበር፡፡ እንደ አድዋ ዘማቾች ወኔ እንጂ ሌላ ሀብት የሌላቸው ወጣቶች፡፡

እነዚህ ወጣቶች አንድ አስደማሚ ተግባር ጀምረዋል፡፡ በየዓመቱ የአድዋ በዓል ከመከበሩ ቀደም ብለው ከአዲስ አበባ በመነሣት በእግራቸው ወደ አድዋ መዝመት፡፡ አባቶቻቸውና እናቶቻቸው በእግራቸው የተጓዙትን መንገድ እነርሱም በእግራቸው መከተል፡፡ የቀድሞ የአድዋ ዘማቾችን ስሜት  እየተጋሩ፣ ታሪካቸውን እያጠኑ፣ በየደረሱበት ለሚያገኙት ሁሉ የአድዋን የላቀ ኢትዮጵያዊነት እየሰበኩ፣ የትውልድን ቃል ኪዳን ማደስ፡፡

ተጓዦቹ ከመልስ በኋላ

የዘንድሮ ተጓዦች ስድስት ናቸው፡፡ ከስድስቱ አንዷ ሴት ናት፡፡ ጽዮን ትባላለች፡፡ በጉዞው ስሟ ደግሞ እቴጌ ጣይቱ፡፡ ከአንድ ሺ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆነውን መንገድ በእግሯ አቆራርጣ እንደ እቴጌ ጣይቱ አድዋ ላይ ሰንደቋን ተክላለች፡፡ መድረኩ ላይ ወጥታ የእቴጌን ታሪክና የጉዞውን ትዝታ ስትተርክ የሆነ የሚንፎለፎል ትኩስ ወኔ ከውስጧ እየወጣ ይገርፈን ነበር፡፡ እናለቅሳለንም፣ እንገረማለንም፣ እናጨበጭባለንም፡፡ የማትነጥፍ ሀገር፡፡በድንኳን እያደሩ፣ ያገኙትን እየቀመሱ፣ ከአራዊት ጋር እየታገሉ፣ ከተራራና ገደል ጋር እየተገዳደሩ፣ እየወደቁ እየተነሡ፣ እየታመሙ እየተፈወሱ፣ እየደከሙ እየጀገኑ፣ እያዘገሙ እየፈጠኑ ከአንድ ሺ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆነውን መንገድ በእግር ማቆራረጥ፡፡ አድዋ ላይ ተጉዘው የታሪክ ማርሽ በዘወሩ ጀግኖች ስም ራሳቸው እየሰየሙ፣ የመንፈስ ወራሽታቸን ማረጋገጥ፡፡

ከጉዞ አስተባባሪዎች አንዱ የሆነው መሐመድ ስለ ጉዞው ዓላማና ሂደት ሲገልጥ እርሱ ራሱ ከዐፄ ምኒሊክ ሠራዊት ጋር የዘመተ ነበር የሚመስለው፡፡ መቼም መሐመድ ስለ ኢትዮጵያ ሲያወራ መስማት በባለሞያ ካህን የተከሸነ ቅዳሴ እንደመስማት ያለ ነው፡፡ ያወጣዋል፣ ይተርከዋል፣ ያውም ከዕንባና ከስሜት ጋራ፡፡

እነዚህ ወጣቶች የዛሬ ዓመት በ2008 ዓም አንድ ታላቅ ታሪክ ሊሠሩ አስበዋል፡፡ የአድዋ አንድ መቶ ሃያኛ ዓመት ሲከበር አንድ መቶ ሃያ ተጓዦችን ይዞ ወደ አድዋ በእግር ለመዝመት፡፡ ወጣቶች ናቸው፡፡ ግን ልባቸው ሸምግሏል፤ ብዙ ሊስቧቸው የሚችሉ  ብልጭልጭ ነገሮች ነበሩ፤ ነገር ግን ሀገራዊውን ታሪክ መርጠዋል፡፡ ከሺ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆነውን መንገድ በእግር አቆራርጠው፣ የሀገራችንን ባንዴራ ከፍ አድርገው ፣ በየደረሱበት አድዋ ላይ የተገለጠውን ያንን ሁላችንንም የሚያኮራ ኢትዮጵያዊነት እየተረኩ በእግራቸው ሊጓዙ ተነሥተዋል፡፡

ጽዮን – እንደ እቴጌ ጣይቱ

የጉዞው አስተባባሪ ያሬድ ሹመቴ

እንደ እኔ እንደ እኔ አንድ ትውልድ ታሪኩን ሲያነሣ፣ በማንነቱ ሲኮራ፣ ታሪክም ለመሥራት ሲቆርጥ መደገፍ ይገባል እላለሁ፡፡ ወጣቶች ከሥነ ምግባር ሲወጡ፣ ማንነታቸውንና ታሪካቸው ሲረሱ፣ ለሀገራዊ ነገሮችም የእኔነት ስሜት ሲያጡ እንደምንወቅሰውና እንደምናዝነው ሁሉ፤ በሀገር ፍቅር ስሜት ሲነሡና ታሪካችንን ከፍ አድርገው በአዲሱ ትውልድ አዲስ መንፈስ ውስጥ ሊጽፉት ሲተጉም አብረናቸው መሥራት ይገባናል፡፡ ታሪካችንና ማንነታችን እንደማይዘነጋ ማረጋገጥ የምንችለው ተተኪው ትውልድ የእኔ ነው ብሎ በራሱ መንገድ ሊገልጠው ሲሞክር ካየን ብቻ ነው፡፡

እናግዛቸው፣ አብረናቸውም እንቁም፤ የቻልን የጉዟቸውን ወጭ እንጋራ፣ ያልቻልን በሚደርሱበት ቦታ ሽሮ ሠርተን ውኃ ቀድተን በማስተናገድ የጥንት አያቶቻችን የአድዋ ዘማቾችን የሸኙበትን ታሪክ እንድገመው፡፡ በሚደርሱባቸው ቦታዎች ያሉ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ወጣቶቹ ከተጓዦቹ  ጋር ስለ ታሪካቸው እንዲወያዩ መርሐ ግብር ያዘጋጁ፡፡ የእምነት ተቋማት ደግሞ በሚደርሱባቸው ቦታዎች በመቀበል ለታሪካችንና ማንነታችን ያለንን የከበሬታ ሥፍራ እናሳይ፡፡ በየቦታው የምንገኝ ኢትዮጵያውያንም በየደረሱበት ቦታ እየተቀበልን ባንዴራውን ከፍ አድርገን በማሻገር የታሪክ ተረካቢነታችን እናረጋግጥ፡፡ አንድ መቶ ሃያኛውን የአድዋ በዓል፣ በ2008 ዓም ከአበባ ማኖር በዘለለ በማይረሳ የወጣቶች ታሪካዊ ጉዞ እናክብረው፡፡

ጠቢብ አስቦ ይሠራል

ጎበዝ ደግሞ ከሚሠሩት ጋር ያብራል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.