በኢትዮጵያ ታሪክ ተሰራ :- በግንቦት 20 የአርበኞች ግንቦት 7 ታሪክ ደምቆ ዋለ !

በመጭው ግንቦት ሁላችንም እንድንደመር የዶክተር አብይ ቡድን በነሃሴው የኢሕዲግ አጠቃላይ ጉባኤ እራሱን ከወያኔ በማግለል ታሪክ ይድገም!!

የደደቢቱ ወንበዴ ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የዜጎች እምቢተኝነት የወለደውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የነጻነት የተጋድሎ ታሪክ የግሉ ገድል እና የድል ውጤት አድርጎ ለዘመናት ሲመጻደቅበት ኖሯል :: ለሁሉም የዘንድሮው የግንቦት 20 ዓመታዊ በዓል በአርበኞች ግንቦት 7 አንጸባራቂ ድል ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሃገር ውስጥም በውጭ የምንኖር እንድናከብረው ላደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ምስጋና በማቅረብ ነው ጽሑፌን የምጀምረው :: የትግራይ ተገንጣይ ቡድን ነኝ እያለ እራሱን የሚጠራው እና በኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ ተንሰራፍቶ ሃገሪቱን ዘር እና ቋንቋን ባማከለ የማክሲሚሊያን የከፋፍልህ ግዛ መርዘኛ የፌዴራሊዝም ጽንሰ-ሃሳብ ለዘመናት በፍቅር እና አንድነት የኖሩ ሕዝቦቿን ከፋፍሎ በብሔር እና ሃይማኖት ግጭቶች እያባላ በግድያ ዘረፋ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት የሰለጠነው የባንዳዎች ሥርዓት ወያኔ በዚህ በሚመጻደቅበት ወርሃ ግንቦት የውርደት ማቁን ይበልጥ ተከናንቦ ለማየት ችለናልና ይህች ቀን እውን እንድትሆን ዳር እስከዳር የሕይወት ዋጋ ለከፈሉ ድንቅ የኢትዮጵያ ሰማዕታት ሁሉ ክብር እና ምስጋና ይገባቸዋል እላለሁ :: ከ 60 ሺህ በላይ የትግራይ ወጣቶችን አስገድዶ ሕይወታቸውን በማስገበር ሃገር ያስገነጠለው እና ዛሬ በእዳ ተዘፍቀን በየዕለቱ ለኬንያ ሞምባሳ ለሶማሌ ላንድ በርበራ ለጅቡቲ እና ሱዳን በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር የምንገፈግፍበትን ይኸውም 105 ሚልዮን የኢትዮጵያን ሕዝብን ያለ ወደብ ያስቀረው ከሃዲው ወያኔ ብዙ ሚልዮን ዶላር ለየመን የጸጥታ ሃይሎች ከስክሶ ዓለማቀፍ ሕግጋትን በሚጥስ መልኩ አንዳርጋቸው ጽጌን አግቶ በመውሰድ በማሰቃያ እስር ቤቶቹ ቆልፎ ቶርች እያደረገ የለመደውን የቴሌቪዥን ድራማ በማቀናበር የግንቦት 7 ትግልን እና የነጻነት ታጋዮችን ለማኮሰስ እጅግ ብዙ ደክሟል:: ይሁን እንጂ በሕዝብ ትግል እና በዶክተር አብይ ጥረት ከእስር የተለቀቀው መንፈሰ ጠንካራው ፋኖ አንዳርጋቸው አሳሪዎቹ የፈጸሙትን ክህደት እና አሳፋሪ ተግባር እዛው እፊታቸው ” ፊልም ቆራርጣችሁ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሰራችሁትን ሰምቻለሁ :: እንደነ ለገሰ አስፋው እና ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ፍቱኝ ብዬ አለምናችሁም የፈረዳችሁብኝን የሞት ፍርድ እንድታጸኑት ነው የምጠይቃችሁ :: ይህንንም ቃሌን በእስር ላይ በነበርኩበት ወቅት ለእንግሊዙ አምባሳደር ነግሬው ነበር ሲል” የማፍያ እና የክህደት ተግባር የፈጽሙትን ነፍሰ በላ እና የኢትዮጵያ ጠላት ወያኔዎችን በአደባባይ ተጋፍጧቸው እንዲሁም አዋርዷቸው እንሱንም ደጋፊዎቻቸውንም ቅስማቸው እንዲሰበር አድርጓል:: ጀግናን የሚያከብረው እና ነጻነት የተጠማው የኢትዮጵያ ሕዝብም ለነፍሱ ሳይሳሳ በወታደራዊ እዝ ማርሻል ሎው ድንጋጌ በምትመራው እና ማናቸውም እንቅስቃሴ በተገደበበት ሃገራችን ለነጻነት ታጋዩ አንዳርጋቸው የጀግና አቀባበል ከማድረግ አልፎ ” ግንቦት 7 ነኝ የአንዳርጋቸው ነኝ ….” በሚል ጭፈራ እና ሆታ ታሪክ የማይረሳውን አንጸባራቂ ድል አስመዝግቧል :: በተለይም የቄሮ ፋኖ ዘርማ ነብሮ እና የሰማያዊ ፓርቲ ትንታጎች ቆራጥ የሃገሪቱ የቁርጥ ቀን ልጆች ብሔር እና ሃይማኖት ሳይለዩ ለእናት ምድር ኢትዮጵያ እየሰሩት ያለው እና አሁንም የሚሰሩት የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ በወርቅ መዝገብ ተጽፎ ትውልድ ሲዘክረው የሚኖር ነው ::

በአሁኑ ወቅት የእነ ዶክተር አብይ ለማ እና ገዱ ቡድን ኢትጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ለማዳን የሚያደርጉት የለውጥ እርምጃ ከፍተኛ ድጋፍ እና ሕዝባዊ ወገንተኝነትን እያገኘ የመጣ ጉዳይ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም :: እንዚህ ታሪክ እየሰሩ የሚገኙ ወገኖች ሙሉ ድጋፍን እና ይሁንታን ለማግኘት ከፈለጉ እንዲሁም ለትውልድ የሚተርፍ ዘላለማዊ ታሪክ ትተው ለማለፍ አንድ ወሳኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል :: ይህም ውሳኔ ሃገሪቱን ከፋፍሎ ብሔረሰቦችን እያባላ እየዘረፈ እያሰረ እና ሰብአዊ መብት እየጣሰ ዛሬም ዳር እስከዳር የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ እንቢተኝነት ወደጎን ትቶ የስልጣን ዘመኑን በጥገናዊ ለውጥ ለማጠናከር ከሚሯሯጠው በትግራይ ጭቁን ሕዝብ ስም ከሚነግደው ወያኔ ሕወሃት ከሚባለው ሰብአዊነት ከጎደላቸው ያረጁ ያፈጁ የማፍያዎች ቡድን ራሳቸውን ማግለል ይጠበቅባቸዋል :: ውድ ዶክተር አብይ:- ለሃገሩ እና ለዜጎቹ የሚቆረቆር መሪ የናፈቀው ሕዝባችን እርሶንም ይሁን በዙሪያዎ ያሉትን የለውጥ አራማጆች በጽኑ ይፈልጋል :: ከነ አቶ ለማ እና ገዱ ጋር የጀመራችሁትን የለውጥ እንቅስቃሴም በታላቅ አድናቆት እና ክብር እየተከታተለው ነው :: ሆኖም የሕወሃት ነገር ” ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ ” ነውና ብዙ ዋጋ ከፍላችሁ የምትጓዙበትን አንጸባራቂ ታሪካዊ ገድል የሚያሰናክል እጀ ሰባራ እንድትሆኑ የሚያደርግ እና የምትከተሉትን የለውጥ መንገድ አቅጣጫውን ካሳተም ከ 85 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ተጋምደው በሚኖሩባት ኢትዮጵያም ይሁን በሕዝቦቿ መጻኢ ዕድል ላይ የሚያስከትለው መዘዝ እጅግ የከፋ ነውና በቀጣዮቹ ሁለት ወራት አንድ ታሪካዊ ውሳኔ በማሳለፍ የጀመራችሁትን ታሪክ በድል እንድታጠናቅቁ ምክራችንን እንለግሳችኋለን :: ወያኔ ሃገር የለውም :: ወያኔ ዘመድ አያውቅም :: ወያኔ የገዛ ነባር የትግል አጋሮቹን በስልጣን ጥማት እና በጥቅም ግጭት እየበላ እዚህ የደረሰ የማፍያ ስብስብ ነው :: ዛሬ በሕዝባዊ ተቃውሞ እና በዓለማቀፉ ማሕበረሰብ መገለል ቆስሎ አንገቱን ደፍቶ የሚታየው ወያኔ አብቅቶለታል ብሎ የሚዘናጋ ቢኖር እሱ የዋህ እና የወያኔን ተፈጥሯዊ ማንነት ሳያውቅ በተዳፈነ እሳት የሚጫወት አላዋቂ ሰው ብቻ መሆን አለበት :: ጅብ እስኪነክስ ያነክስ እንደሚባለው ብሂል በልተው ሆዳቸው የማይጠረቃው የሰው ጅቦቹ ወያኔዎች እንደ አንድ አጭሬ እግሩ ጅብ አቅመ ቢስ መስለው እያነከሱ አዘናግተው ጠላቶቻቸውን አንድ በአንድ ለቃቅመው ይበሉ እንደሆነ እንጂ ይለወጣሉ ይታረማሉ ብሎ መድከም በራስም ሕይወት በሕዝብ እና በሃገር ላይ ጭምር መቀለድ ነው የሚሆነው :: በትግራይ ነጻነት ስም የሚነግደው ወያኔ ከሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጀምሮ እራሳቸው በአንደበታቸው የመሰከሩልንን እንደነ አቦይ ስብሃት በረከት ሥምዖን ቴዎድሮ አድሃኖም አባይ ወልዱ ሕላዊ እና ሌሎችም ግማሽ እና ሙሉ ኤርትራውያንን በውስጡ ሰግስጎ ኢትዮጵያውያንን በፈጠራ ታሪክ እርስ በእርስ እያባላ እና ደማቸውን በአደባባይ እያፈሰሰ የስልጣን ዘመኑን አደላድሎ ለመኖር የቆረጠ አደገኛ ቡድን ነውና ከእንግዲህ በቃ ይበቃል ሊባል ይገባዋል :: እራሱን እና አመራሩን በስብሻለሁ ገምቻለሁ ኪራይ ሰብሳቢነት በውስጤ ተንሰራፍቷል ሙስና ነግሷል እያለ እያቄለን ዛሬም በእነ አብይ ቡድን አንቀልባነት የመጣበትን ክፉ ቀን ለመሻገር ውስጥ ውስጡን ሴራ የሚጎነጉነው ወያኔ ሕወሃት ይለወጣል ለዛች ሃገር ቀና ያስባል ብሎ መድከም የዋህነት ብቻ ሳይሆን ከቂልነትም የሚያስቆጥር ነው :: በቅርቡ በውጭ የሚኖረው ዲያስፖራው የፊታችን ጁን እና ኦገስት ወራቶች በአሜሪካ እና ጀርመን በሚካሄዱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሚታደሙበት የስፖርት ፌስቲቫሎች ዶክተር አብይ በእንግድነት እንዳይገኙ ከውሳኔ ላይ የተደረሰው በተለይም በአሜሪካው ሴኔት እንዲጸድቅ እና የወያኔ ባለስልጣናት በዜጎቻችን ላይ በሚፈጽሟቸው ግፎች እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዓለማቀፋዊ የወንጀል ተጠያቂነት እንዲኖርባቸው ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለበት ኤች አር 128 የተባለው ረቂቅ ሰነድ እንዳይሰናከል በመፍራት እንጂ የለውጥ እርምጃ የጀመሩትን የእነ ዶክተር አብይ ቡድን በመጥላት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባዋል ::

ወድ ዶክተር አብይ :- ሰብ አዊ መብት እንዲረጋገጥ እና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ የዜጎች መብቶች እንዲከበሩ እና ኢትዮጵያችንንም ከመበታተን አደጋ ለመጠበቅ የጀመራችሁት ታሪካዊ ሂደት የሚመሰገን ነው :: ይህ የብዙዎቻችንን ቀልብ የሳበ ጥረታችሁ በውጭም በሃገር ውስጥም ሙሉ ድጋፍ እና ትብብር እንዲኖረው በመጪው ነሃሴ ወር ላይ በሚካሄደው የኢሕአዲግ አጠቃላይ ጉባኤ አንጸባራቂ ታሪክ እንድትሰሩ እንማጸናችኋለን :: የኢሕአዲግን ግንባር የመሰረቱት አራቱ አውራ ድርጅቶች ማለትም የትግራይ ወኪል ነኝ የሚለው ሕወሃት የኦሮሞው ኦሕዲድ የአማራው ብአዲን እና የደቡብ ሕዝቦቹ ደሕዲን አብሮ መቀጥል ወይም አለመቀጠል ላይ ውሳኔ በሚሰጡበት ታላቅ ጉባኤ ሕዝባዊ ወገንተኝነትን እየተቀዳጀ የመጣው የእነ ለማ ገዱ ቡድን ባንዳ እና የኢትዮጵያ መሰረታዊ ጠላት ከሆነው ወያኔ-ሕወሃት እራሱን በማግለል ታሪክ ይሰራል ብለን እናምናለን :: ይህ ወሳኝ እድል ካመለጠ ግን ዛሬ የእነ ዶክተር አብይን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማስጠላት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በሃገሪቱ የብሔሮች ግጭቶች መፈናቀሎች እና ግድያዎች እንዲጠናከሩ በማድረግ እና ሕዝቡ እንዲማረር አሁን በስልጣን ላይ ያለውን የለውጥ ሃይል ለመግደል እና ለማስወገድ ከባድ የሞት ሽረት ትግል ለሚያደርገው የሕወሃቶች የማፍያ ቡድን ማረጃ ካራ የማቀበል ያህል ነውና ነገሮችን በጥልቀት እንዲመረምሩ ምክራችንን እንለግሳለን :: ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ያስቀደመው ኦሕዲድም ይሁን አንዳንድ የብአዲን አመራር አባላት መላው ሕዝብ አንቅሮ ከተፋው ወያኔ ይልቅ ከፍተኛ ሕዝባዊ ድጋፍ እያገኙ መምጣታቸውን አምነው እና ተቀብለው የሕዝብን እና የሃገርን ጥቅም በማስቀደም በመጭው ነሃሴው ታሪካዊ ጉባኤ ላይ ታሪክ እና ድል ያስመዘግባሉ ብለንም እናምናለን :: ያን ጊዜ በሃገር ውስጥም ይሁን በውጭ ያለን ኢትዮጵያውያን በሙሉ ሳንቀነስ ተደምረን የእነ ለማ-አብይ-ገዱን ኢትዮጵያዊነትን ያማከለ መርሕ ለማሳካት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እንተጋለን :: የዘንድሮውን ግንቦት 20 በአርበኞች ግንቦት 7 የነጻነት መንፈስ እንዳሰብነው ሁሉ መጭውንም ግንቦት ሃያ በወያኔ ግብአተ መሬት ላይ አኩሪ ታሪካዊ ገድል ያለን ኢትዮጵያውያን በታላቅ አንጸባራቂ ድል እንደምንዘክረው ባለሙሉ ተስፋ ነን ::

ኢትዮጵያዊነት ያሸንፋል !!!!!

መይሳው ሳልሳዊ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.