„ቀጥል አብይ!“ ከኢትዮጵያ ቅኖች። ከአቶ አበራ የማነ አብ እና ከዶር ነገደ ጎበዜ የተላለፈ የመልካም ተስፋ ምኞት (ከሥርጉተ ሥላሴ)

ከሥርጉተ ሥላሴ 03.06.2018 (ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ።)

„አስተዋይ መልካም ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል።“ (መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ምሳሌ ፩ ቁጥር ፭)

  • መነሻዬ።

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/91647

„ሊታይ የሚገባው: አበራ የማነ አብ እና ዶ/ር ነገደ ጎበዜ ስለዶ/ር ዓብይ አህመድ ያልተጠበቀ ነገር ተናገሩ“

  • የእኔ ብሩኮች እንዴት ናችሁ? እንዴት ነው አገሩ፤ ሰፈሩ፤ ከብቱ እንዲያው ሁለመናው ጫታን ነውን?

የኔዎቹ ዘሃበሻ የልተጠበቀ አይደለም። የመኢሶን አቋም እኮ ከዶር ነገዴ ጎበዜ SBS ቃለ ምልልስ ቀደም ባሉት ቀናት ከመሼ እንዴት ትዝ እንዳሏቸውም አላውቅም፤ መቼም በኢትዮጵያ ፖለቲካ አንዱ ልጅ ሌላው እንጀራ ልጅ ነው፤ ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ ተብሎ ዕወቅና በተሰጠው በሌላ ሚዲያ አላችሁን ተብለው ከመኢሶኖችን አመራር አካሉ በአንድ ወገኔ አማካኝነት አቋሙን ግልጽ አድርጓል። አሁን ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ስለዚህ ለእኔ የጠበቅኩት ነው የሆነው ስላችሁ ነው የእኔዎቹ ዘሃበሻዎች። ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለሚፈቅድ ሁሉ እኮ ሌላ ቦታ ሳይሄድ የኦህዴድን ሙሉ ቁመና እንደ ድርጅት ማጥናት ብቻ ይበቃው ነበር። ስለምን ግዮን ላይ መንፈሱን ማስመሰጥ ፈቀደ? ያ እኮ OBN መቅድመ የጣና ቅኝት ጥልቅ የፖለቲካ ፍልስፍና ነበረው። ደወልም ነበር ለመዳኛ መንገድ ፍለጋ።

ይህ ከግንዛቤ ተወስዶ በሰከነ ህሊና ኢትዮጵያን ከእስር ማስለቀቅ የወል ዓላማ ሆኖ ቢሆን ያን ያህል ደራጎን እርግፍ ተብሎ ተረስቶ የኔት ጉግስ ባልተገጠመም ነበር። አቅል አብዝቶ ነሳን። ሰው ከኤሌትሪክ አልተሰራም። ብራ ሲባል የሚበራ ጥፋ ሲባል የሚጣፋ። ሰውን ማክበር የተገባ ቢሆንም መልካም ነገርን አፍኖ መዳጥ ግን የጨለማው ጮማ ነው። እንደ ሮበት ተንቀሳቀስ እስከሚባል መጠበቅም ዕብንነት ነው። መመዘን። ሰው ሆኖ መፈጠር ራስን ስብዕናን ሳያስደፍር መሆን አለበት። ለመወስን አቅምን ተጠማኝ ማድረግ ራስን መሰረዝ ነው። ለዚህም ነው አፍንጫህን ላስ አቶ ሂደትም፤ እጬጌ ሂደትም የተጻፉት። ለሰው ለመታገል ሰው ለራሱ ስለራሱ መሆን መቻል አለበት። ህሊናው እንዲመራው መፍቀድ አለበት። ሰው በሪሞት ኮንትሮል እንዲመራ ሳይሆን ተፈጥሮን እንዲመራ የተፈጠረ ታላቅ ፍጡር ስለሆነ። ሮሞት ኮንትሮልን የፈጠረው ራሱ ነው። የፈጠረው የብረት ውጤት ሰውን አህል እጹብ ድንቅ ህሊናን እንዲመራ አቅም መስጠት የመኖሪያ ውቅያኖስ ፕላኔት ያልተበጀለት በደንገል የተሰራ ጀልባነት ነው።

ፍቅርን ፈልጎ ጣና ላይ አንድ ሚዲያ ሲሄድ ልዩ መልዕክት ነበረው። የእኔ ካላልከው አይደለም መሄድ ማዬቱን እራሱ አትፈቅደውም። ቢታወቅ ብዙ በርካታ የእኛዊነት ጠረን በኢጎ የተጠቀለሉ አሳንጋላዎችን ጆሯችን ከነፈግናቸው ከሁለት ዓመት በላይ ሆኗል።

ብልህነት ከወቅት ማድመጥ ጋር ሲሆን፤ ብልህነት ጥገኛ መንፈስን ያልተጠለለ በራሱ ላይ የቆመ ከሆነ የራስ ውሳኔን ብቻ ነው የሚጠይቀው አቅም ለላው ባለክህሎት የፖለቲካ ሰው። ኦህዴድ እንደ ድርጅት አገር የመረከብ ብቃቱ ሙሉ ነው። ለዚህም ነበር እኔ ኦህዴድ ጭንቅላት ብቻ ሳይሆን ዐዕምሮ አለው የሚለውን ጽኑ አቋሜ መፈክር ያደረኩት። ለማውያን የሆንኩትም በዚኸው አግባብ ነው። ቀድሞ ነገር ለመልካምነት መንፈስ ቅድመ ሁኔታ አያስፈልገውም። ፍቅር መጣሁ ተቀበሉኝ እጅን ዘርግቶ እንደ አባት አደሩ ጎዝጉዞ አንጥፎ መጠበቅ ግድ ይላል። ፍቅር ያለተቀረበ ማን ይቀረብ?

ለበሰሉ የፖለቲካ ሊሂቃን ክህሎታቸው ምራኝ ካሉ እነሱም ሙሉ ዕድሚያቸውን የገበረቡትን መሠረታዊ ፍላጎት በኦህዴድ ህሊና ውስጥ ያገኙታል። በተጨማሪም የሁለቱን ብርሃኖች የአቦ ለማ መግርሳ እና የዶር አብይን ገጸ ታሪክ በመመርመርም ግብረ ምላሹ ሁለመናችን የገበርንበት ፍሬ ነገርን ከግብ ሊያደርሱ እንደሚችሉ ቅንጣት ያህል ጥርጥር አያሳድርም። ስለሆነም እኒህ ቅን ሁለት ሊሂቃን በትክክልም ያሳለፉት ተጋድሎ ለእውነተኛ የኢትዮጵያ ነፃነት እንጂ ለግል ሥም እና ዝና አለመሆኑ ይመሰክራል። አቦ ለማ መግርሳ እኮ ፖለቲካን በልምድ በተመክሮ ያመጡት ሳይሆን ሙያቸው ነው። ተምረውታል። ተመርቀውበታል። ማስተር ያደረጉት በዓለም አቀፍ ግንኙነት ነው። የቆዩበት የሥራ ዘርፋቸው ደግሞ ሌላ የሚሰጠው አቅም አለው። ለድርጅታቸው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ዘላቂ የደህንት ጉዳይም ቋሚ አቅም አለው። ለነገሩ እኔ ቁስል ስል የከርመኩበትን ፍርጥ አድርገው ሰሞኑን የልባቸውን አውጥተው ነግረውልኛል። በዶር አብይ አህመድም ቢሆን እንደ አባይ ፏፏቴ በዬዕለቱ የሚቀዳው አዲስ ብሩኽ ህሊናዊ ክህሎት በዬትኛውም ዘመን ያልታዬ ነው። ግን የዛሬ አልነበረም።

እሳቸውን ገፋ አድርጎ ሲያጠና የቆዬ የቀደመው ክትትል ቢኖር፤ በአንድ ድርጅት ወይንም ሚ/ር መ/ቤት የተናገሩትን፤ ያለሙትን አሁን ብሄራዊ መልክ ሰጡት፤ ዕውቅናው ለማረጋጋጥ አዲሱ ማንነታቸው ከማድረግ አቅም ጋር አጎናጸፋቸው እንጂ የቀደመ ነው። „ጎንደር ከተማ የከተሞች ባዕል በ2009 ሲከበር፤ ንባብ ለህይወት ባዕል ላይ፤ ከርምጃ ወደ ሩጫ ሞቶ፤ ለቀለም ትምህርታቸው ምረቃ የሰሩት ዓለም ዓቀፍ ጥናት እና የምርምር ማህበራዊ ቀውስ እና መፍትሄውን“ ያጠኑበት መንገድ ያ ሁሉ ከበቂ በላይ የዳበረ እርሾ ነበር። አንድ ቦታ ላይ የልምድ ማነስ የሚል አድምጬ ሎቱ ስብሃት አሰኝቶኛል። በዚህ ዕድሜ የሾለከ ቀን የለውም።

መሬት ላይ ከህዝብ ጋር መሥራት በራሱ የሚያጎናጽፈው አቅም አለው። አሁን አንድ የካሴት ሊስት ሲያወጣ የሚውልን አምጥተህ ተጨባጩን ተንታኝ ብታደርገው ከዬት ያመጣዋል። ከእሱ ይልቅ አንድ ገበሬ ማህበር ውስጥ በአንድ አንስተኛ ኮሜቴ ተመርጦ ህዝብን ያገለገለ ይበልጣል። የህዝብን  የአስተዳደር ጠረን ያውቃዋል። ፖለቲካው እኮ ህዝብን ማስተዳደር ነው። ለህዝብ ህሊና አመራር መስጠት ነው እንጂ ለሲዲ ወይንም ለቪዲዮ ቅደም ተከተል ማውጣት ማለት አይደለም።

የአብይ መንፈስን ተስፋ ሰንቆ ለመደገፍ የዚህ መሰል ተመክሮ ብቃት ከምቀኝነት የጸዳ ህሊናን ይሻል። ግን የዶር አብይ አህመድ ከአቅም በላይ የሆነው ብቃታቸው ግዙፍ ስለሆነ ሲልፈሰፍስ ለኖረው ባለ ራዕይ አጀንዳ አልባ እንደሚያደርገው ታውቆ ጥቃቱ በዬአቅጣጫው ተኮለኮ። ማመጣጠን ቀርቶ ማጠጋጋት አይቻልም። ስለሆነም ትንሽ ጥሪት ያለውም // የሌለውም ሁሉም ድንጋይ ወርዋሪ ሆነ፤ ፍርሻን ናፋቂ ሆነ። ስለምን በፍላጎታችን ውስጥ ለመኖር ፍላጎታችን ለማጥናት አቅሙ ስላልነበር። ፍላጎታችን ብናጠነው ከፍላጎታችን በላይ ካሰብነውም፤ ካለምነውም አቅም በላይ ነበር ዕድሉ። ፈጣሪ ይመስገን ያ አቋራጭ መንገድ ቀርቶ የአብይ መንፈስ መደላደል ጀምሯል።

እንዲህ ምቀኝነት የሌላቸው፤ አቅምን ተጠግተው ለማዋጥ ያላደቡ ቅን ሊሂቃኑ እዬደገፉት፣ እዬቀረቡት፣ እያስጠጉት ሲሄዱ ደግሞ ትውልድ የሰከነ የፖለቲካ አቅም ያለው ትውልድ መገንባት ይቻላል። ሩጫው የአብይ መንፈስ ይሄው ነው። የተቃጠለው ትውልድ እንዳይቀጥል። አዲስ ብሩህ የፍቅር ትውልድ መፍጠር። ከቂም ከቁርሾ ትርፍ የለም። ትርፍ አለ ቢባል ከፍቅር ብቻ ነው። ትርፍ አለ ቢባል ከመደማማጥ ብቻ ነው። ትርፍ አለ ቢባል በራስ አቅም ከቆመ ጽኑ የአገር ፍቅር ሰብዕና ብቻ ነው። ትርፍ አለ ቢባል ከአድመኝነት ጸድቶ መልካም ነገርን ለማድመጥ ከመፍቀድ ላይ ብቻ እና ብቻ ነው። ትርፍ አለ ቢባል የሚበልጡ ሳተናዎችን ዘመን ባልተቋረጠ ሁኔታ ሊሸልም እንደሚችል አምኖ ከመቀበል ነው። ትርፍ አለ ቢባል ዝቅ ብሎ ለመመራት ከመፍቀድ እና ከመወደድ ብቻ ነው። ትርፍ አለ ቢባል ከአራት እግር የእንጨት ውርክብ ወጥቶ ማግስትን በማኖር በህብረ ቀለም መጥለፍ ከመቻል ነው። ትርፍ አለ ቢባል አናንቆ፣ አጣጥሎ፤ አንቺ እና አንተ ብሎ ከአክብሮኝ ሳይሆን ሰው በመሆኑ ሰውን አክብሮ ከመነሳት ብቻ እና ብቻ ነው።

የአቶ አበራ የማነ አብ እና የዶር ነገዴ ጎበዜ ፖለቲካዊ ውሳኔ አንድ ቡቃያ ብቅ ሲል በጥላቻ፤ በቁርሾ በበቀል፤ በመተራመስ ውስጣችን ሲገዘግዘን የኖረውን፤ ኢትዮጵያንም ከማትወጣበት እረግረግ ውስጥ ከቷት የነበረውን እምቅ፤ ድብቅ የሴራ ሂደት ሁሉ ነው የናደው። አቶ አበራ የማነ አብ እና ዶር ነገዴ ጎበዜ በራሱ የኢትዮጵያ ችግር ምን ያህል ውስጣቸው እንደ ነበር ያመላከት ፍሬ ነገር ነው ይህ አቋም። ለዚህ መትጋታቸው፤ ወጣትነታቸውን መገባራቸው ደግሞ ሊያስከብራቸው፤ የበለጠ መሪዎቼ ሊያሰኛቸው የሚችል ነው። እንኳንም በህይወት ኖረው እኛም እነሱን የበለጠ እንድናውቃቸው፤ እነሱም ወጣትነታቸውን፤ ኑሯቸውን የገበርቡት ተጋድሎ መልካም ጅምር ላይ ስለመሆኑ ለማዬት አበቃቸው። ለወደፊትም ድንግልዬ ጥላ ከለላ ሆና ለአገራቸው መሬት በክብር እና በላቀ ግርማ ሞገስ ታብቃልኝ። አሜን! እርግጥ ነው እኔ እማላውቃቸው አቶ አበራ የማነ አብን እንጂ ዶር. ነገዴ ጎበዜን በአካል አውቃቸዋለሁኝ። በተደጋጋሚ አግኝቻቸዋለሁኝ። በወጣትነት ስብሰባቸውን ታዲሜያለሁኝ። የአገር ናፍቆተኛ አብዝቶ አለባቸው።

በዬትኛውም ዘመን እና ጊዜ ሙሉ አቅም እያለህ ከእድሜህ በታች ያለውን የፖለቲካ ሊሂቅ  ይምራኝ ብለህ ወስነህ ፊት ለፊት ስታመጣ ይህ ብቻ በቂ ነው ለንጽህናቸው። በታሪካችን ማምጣት ቢቻል እንኳን አይቀጥልም። በውስጥ ሰላም እጦት ያ ቀድም ብሎ የተፈቀደው ዕወቅና ሲያገኝ፤ ሲወደድ፤ ሲከበር እንዲሰበር ተግቶ በመሥራት የዓላማው ስኬታማነት ፈርሶ እንዲቀር ሲደረግ ነበር የተኖረው። ተኮርኩዶ ራዕያችን የኖረውም በዚኸው ነው።

በእያንዳንዱ ሰው ህሊና ውስጥ እኮ አቅም አለ አነሰም በዛም። ያን አቅም ወደ አንድ አምጥቶ የሚመራ ሙሴ ነው ያልነበረን እንጂ ኢትዮጵውያን በሥነ – ተፈጥሯችን በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ ዝንባሌያችን ትውፊታችን ነው። እያንዳንዱ እናቱን ቢያወያይ  ከእኛ የተሻለ ሃሳብ እንዳላት ማግኘት ይቻላል። ሳትማር፤ ሳተመራመር።

እኔ አቬቶ ሰማያዊ ፓርቲ ጎንደር ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቶ ሳለ እንዴት ነበር ብዬ እናቴን ስጠይቃት፤ ያን ጊዜ ጫናው ትንሽ ሻል ይል ስለነበር ደውዬ አገኛት ነበር። ለወ/ሮ አልማዝ ለክብርት ብርቱካን ሜዲቄሳ እናትም እንዲሁ እደውልላቸው ነበር።

ወደ ቀደመው ስመለስ መልሷ „ቀዝቃዛ ነበር አሉ። ከእኛ የሄደ የለም አለችኝ።“ ያው ከእኛ ስትል የተገላበጡ የጎንደር ባላባቶች ስለሆኑ መላ ቤተሰቡ አልተገኘም ይመስለኛል። ምነው ስላት „ቢጫው እስኪመጣ እዬጠበቅን“ አለችኝ። በጣም በሳል ነው የኢትዮጵያ ህዝብ። ያው በቅንጅት ፍርሻ የሰው ልብ ክፉኛ ተጎድቷለኝ። „ቢጫ“ ያለችው ፓርቲ ሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለውን አገናኝ ቀለሙን ቢጫን ይሁን፤ አድዮ የያዘ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ይሁን አላውቅም። አሁን ባገኛት እምጠይቃት ነበረኝ። ያን ቢጫ ዘመነ አብይ ከሆነ፤ ለነገሩ ትንቢቷ የተሳካም ይመስለኛል የእምዬዋ።

  • የሁለት በሳል ሊሂቃን ህሊናዊነት ጣዕሙ።

ከኢትዮጵያ ህዝብ ፍቅር ናፍቆት፤ የሳቅ ናፍቆት የተነሱት እኒህ መንትዮሹ የፖለቲካ ሊሂቃን ማቄን ጨርቄን አላሉም፤ ቅድመ ሁኔታ አላስፈለጋቸውም። የቁጥር ተማሪ ሆነውም በፕርሰንት አልሸነሸኑትም። ሲሞቅ ወስኖ ሲቀዘቀዝ የሚፍረከረከ፤ ለብ ሲል ደመቅ የሚልም አይደለም አቋማቸው። ቁልጭ ያለ ፅኑ ቀጣይ አቋማቸውን ነው የገለጹት።

ሂደቱን በስክነት አጠኑ፤ ያልዞረበት፤ ብጥብጥ ያልሆነ አምደ ውሳኔ ወሰኑ። ዶር ነገደ ጎበዜን እና አቶ አበራ የማነ ብርሃን የሰጡት መግለጫ በትክክልም ኢትዮጵያ ሙሉዋ በመንፈሳቸው እንዳለች፤ ሳቋን ማዬት ሲሹ፤ ሲመኙ እንደኖሩ አውራ ምስክር ነው። የደከሙበት የተጉበት ወርቅ አመክንዮ ይሄው ነው። ስለዚህም ለእነዚህ ባለ ንዑድ ቅናዊ መንፈስ፤ ለእኛዊነት ሊሂቃን ትሁታዊ ምስጋና ከጭምቷ ሲዊዝዬ ይድረስልኝ ነው የዛሬው የኮቤዬ ቀለም መልዕከተ ዮሖንስ።

ሌላው ቁም ነገር የህዝብን ደስታ ከመፈልግ ጋርም ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ይምራኝ ማለታቸው ድንቁ የክህሎታቸው ፍጹም ልዩ ጸጋ ነው። ህዝቡ ደስ ብሎት አዬን። መንፈሱ ተሰብስቦ አዬን፤ ስለሆነም በትክክለኛው የምርጫ ሂደት ሥርዓቱ ቢዘረጋ እኛ ድምፃችን ለዶር አብይ አህመድ እንሳጣለን ነው ያሉት። ዋው! ዋው! እጹብ ድንቅ ነገር ነው።

እንኳን ደስ አለዎት ዶር አብይ አህመድ! እንኳን ደስ አለህም እንደ ድርጅት ኦህዴድ! እንኳን ደስ አለህም የአዲሱ መንፈስ መሪ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ እንኳን ደስ አላችሁም 108ቶቹ የአብቹ አንበሶች! እንኳን ደስ አለህ „የኦሮሞ ፕሮቴስት አንበል ሊጋባው ቄሮ“ „እንኳን ደስ አለህም የአማራ የህልውና ተጋድሎ ጥሪኝ“ የእነኝህ የፖለቲካ ሊሂቃን ድጋፍ ልዩ ዕንቁ ነው። ተመስገን!

ይህ የግልጽነት የእውነተኛ ኢትዮጵያዊነት ንጹህ መንፈስ ለባለ ቅኔው ጠ/ ሚር አብይ አህመድ ሌላ ፍጹም ሌላ የህሊና የመቅኖ አቅም ነው። ለነገሩ ባለቅኔው ጠ/ ሚር አብይ አህመድ ዕድለኛ ናቸው። በአጭር ጊዜ ነው ህዝብ ሆ! ብሎ የደገፋቸው። ከጎናቸውም የተሰለፈው በፍጥነት ነው። ምልዕቱ ልቡን በፍቅር ሸለማቸው። የታደሉ ደማም!

  • መድረሻዬ።

የዛሬ ብቻ ሳይሆኑ የወደፊቱ ቀጣይ የኢትዮጵያ መሪ ባለ ቅኔው ጠ/ ሚር ዶር አብይ አህመድ! እልልልል! እልልልል! እልልል! እልልልልልል! መወደድን የመሰለ፤ መፈቀርን የመሰለ፤ መታመንን የመሰለ፤ ተስፋ መሆንን የመሰለ፤ አግባቢነትን የመሰለ፤ አስታራቂነትን የመሰለ ከቶ ታላቅ ሥጦታ ምን አለና ለገሃዱ ዓለምስ ለምድሩስ ለሰማያዊው እዮርስ፤ ዶር አብይ አህመድ እስቲ ይጠዬቁ፤ ለዛውም ሃዘን በባጀበት በኢትዮጵውያን የወል ዕንባ። ክስተት! መሆን መቻል። ዋው! ባለ ቅኔው ጠ/ ሚር ሆይ! ግን ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ ስለማያከስር ለእኛ ሲሉ እንዲኖሩልን ጠንቃቃ ይሁኑ። አደራ!

ፍቅር ከምልአቱ፤ መወደድ ከምልአቱ፤ ታይቶ አለመጠገብ ከምልአቱ፤ መናፈቅ ከምልአቱ በዚህ በጠብ እና በቁርሾ፤ በጥላቻ እና በመጠላለፍ በተከዘነ የኢትዮጵያ የፖለቲካ አረንቋን ተሻግሮ ይህን መሰል ክብር እና ሰብዕና የተጎናጸፈ ጸጋ የሰማይ እንጂ የምድር ነው ማለት ይቸግራል። ቅብዕው የፈጣሪ ለመልካምም ነው እኔ ያልኩትም ለዚህ ነበር። ኢትዮጵያን በቃሽ ብሏታል አማኑኤል በጥበቡ። ተመስገን!

አቤቱ ሰማያዊ ፓርቲ ሆይ! „ከሦስቱ እሳቸው ይሻላሉ“ ነበር አይደል ያለን፤ እንግዲህ አቤቱ ሰማያዊ ፓርቲ ከዚህ ሰብዕና የላቀ፤ የመጠቀ አቅም ከሰማያ ሰማያት አውርዶ፤ ስድስት ክንፍም አብቅሎ ለማምጣት ስንት ዘመን መጠበቅ እንዳለበት አማኑኤል ይወቅለት። እስተ አሁን ባለው ጊዜ እኔ መንፈሴን የሚገዛ ገጠመኝ ኑሮት አያውቅም ከጣይቱ ነፍሶች ሰላማዊ ሰልፍ በስተቀር። ለዚህ ነው በደንበር የነበረው የእኔ እና የአቤቱ ሰማያዊ ፓርቲ የሃሳብ መስመር።

ሊደመጥ የሚናፈቅ፤ ሊታይ የሚጓጓለት፤ ስለ እለታዊ ጉዞ ምልዕት ጭንቅ ጥበብ የሚልለት መሪ፤ ሙሴ፤ የአሮን በትር ዛሬ ኢትዮጵያ ዛሬ አላት። እንኳን ደስ አለሽ ኢትዮጵያት! ለዚህም ነው ሥርጉተ ሥላሴ የሥርዓት መዘርጋትን እንጂ የሽግግር የጥምር የአደራ መንግሥት ልግጫ ቀጥ ብላ ስትሞግተው የከረመችው። ለአብይ መንፈስ ቀጣይነትም ከተኖረ ይቀጥላል … „አንተ ለሽግግር እንጂ ከዚያ በኋዋላ አታስፈልገነም በዛ ተለለጠጠም¡“ ደቀቀ፤ ፋታ ለተመጠነ ጊዜ የተባለ ብቃት ዛሬ ምን ያህል እጁ አብይ የእኔ እንዳለ ይታወቃል። መሬትም ሰማይም ምስክር ናቸው።

የኔዎቹ ለነበረን ምቹ ጊዜ ዝቅ ብዬ አመስግኛችሁ በትህትና ልሰናበት።

ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!

„መሪ ማለት መሪ እንጂ ነጂ ማለት አይደለም!“

„ሚስጢር! ታምራላችሁ! ስትስቁ ያምርባችኋል!“

ከተስፋ በር ከባለቅኔው ጠ/ ሚር የተወሰደ።

የኔዎቹ ኑሩልኝ። መሸቢያ ጊዜ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.