ክቡር ዶር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር

06/04/2018
ስለ ኢዴህ/EDU አባላት በሱዳን መንግስት ታፍኖ መጥፋት አቤቱታ

ክቡር ዶር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር

                                                                 አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡- ስለ ኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት (ኢዴህ/EDU) አባላት በሱዳን መንግስት ታፍኖ መጥፋትን ይመለከታል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡-

እንደሚታወቀው ሁሉ አገራችን ከ27 አመት በፊት የደርግን ኢስበአዊ አስተዳደር ገርስሶ በምትኩ በህዝብ ነጻ ምርጫ የሚቑቑም ህገመንግስትን መሰረት ያደረገ አስተዳደር እንዲመሰረት በተደረገው ወሳኝ የትጥቅ ትግል ሂደት ውስጥ ኢዴህ/EDU ዋናው እና ግንባር ቀድም ድርጅት እንደነበር ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዴሞክራትክ ህብረት/ኢዴህ/EDU አፋኙ እና ገዳዩ የደርግ መንግስት በፈጠረው ሁኒታ አመራጭ በማጣቱ ተገዶ ወደ ትጥቅ ትግል ገብቷል፡፡ ኢዴህ/EDU ዋና አላማ፣ የኢትዮጵያን አንድነት እና መሰረታዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ክቡር አላማ አንግቦ ይታገል የነበረ ድርጅት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ኢዴህ/EDU፣ በተለይ ጎሳን መሰረት አድርጎ እና የመገንጠል አላማን አንግቦ ይታገል ከነበረው ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ/ህወሀት ጠባብ ተገንጣይ ድርጅት ጋር ከቃላት ባለፈ ከፍተኛ ውጊያ ማድረጉም ይታወሳል፡፡

በ1991 በህወሀት/TPLF እና አልበሽር የሚመራው የሱዳን መንግስት መሀከል ሁለገብ ስልታዊ ወዳጅነት/Strategic Alliance ፈጥረው በከፍተኛ ደረጃ መንቀሳቀስ የጀመሩበት ወቅት ነበር፡፡ በዚሁ ስልታዊ ስምምነት መሰርት፣ የሱዳን መንግስት ወያኔን የሚቃወም ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ሀይል ከግዛትዋ ለማስወገድ ወሰነች፡፡  በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያን አንድነት የሚደግፉ እንደ EDU ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን በወያኔ ጥያቄ መሰረት ለማጥፋት ተስማማች፡፡ በውሳኔው መሰረት ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ሀይል ይሁን ግለሰቦች በህወሀት ጥያቄ መሰረት ሱዳን ግዛት ውስጥ ደብዛቸውን ማጥፋት ተጀመረ፡፡ በጠላትነት ኢላማ ውስጥ ኢዴህ/EDU አንዱ እና ዋነኛው ሆነ፡፡ በሀገር ውስጥ በምእራብ ጎንደር ኢዴህ ላይ ህወሀት/TPLF ጦርነት ሲከፍት፣ በሱዳን በኩል ደግሞ የሱዳን ግዛት ይጠቀሙ የነበሩ የድርጅቱ መስራች እና ትጽእኖ ፈጣሪ አባላት ላይ ታሪክ የማይረሳው የግድያ እና ኣፍኖ የማጥፋት እርምጃዎች ተወሰደ፡፡

አልበሺር የሚመራው የሱዳን መንግስት 02/1991 ሱዳን ግዛት ውስጥ ይንቀሳቀሱ በነበሩ ኢዴህን/EDU ከመመስረት አንስቶ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከፍተኛ ሚና የተጫውቱ እና አገር ውስጥ ተሰሚነት ኣላቸው ተብለው የሚገመቱ አባላት ላይ በተለይ ደግሞ ጎሳን ለይቶ “አማርኛ ተናጋሪዎች ላይ ብቻ” አንጣጥሮ በማፈን ደብዛቸው እንዲጠፋ አድርጝል፡፡

የሱዳኑ የበሽር መንግስት 02/1991 በኢዴህ አባላት ላይ አፍኖ ደብዛ የማጥፋቱን እርምጃ የወሰደው በሱዳን ጦር የመረጃ መምሪያ/Army Intelligence በኩል ነበር፡፡ የሱዳን ጦር መረጃ መምሪያ አባላት ከካርቱም ጠቅላይ መምሪያ በተሰጣቸው ትእዛዝ መሰረት ያልጠረጠሩ የኢዴህ/EDU አባላትን (1) ከገዳሪፍ ወደ ኩኔና ሲጙዙ የነበሩ ዶካ ከምትባል ከተማ ላይ በመጠበቅ (2) ከእምራኩባ ስደተኞች ካምፕ ውስጥ (3) ኩኔና ከምትባል የሱዳን አንስተኛ ከተማ በነበሩ የኢዴህ አባላት ላይ ነበር፡፡ በዚሁ መሰረት፡-

(1) ከኩኔና የታፈነ

(1)ታጋይ አርበኛ አበጀ ፈለቀ

 

(2)ከእምራኩባ ስደተኞች ካምፕ የታፈኑ፣-

(1)ታጋይ አርበኛ ጌታቸው ይርጋ

(2)ታጋይ አርበኛ አስራደ በየነ

(3) ታጋይ አርበኛ መከታው አዛናው

(4)ታጋይ አርበኛ ሀጎስ ጌታሁን

 

ከገዳሪፍ ወደ ኩኔና በጉዞ ላይ የነብሩ ዶካ ላይ የታፈኑ

(1) ታጋይ አርበኛ ፈንቴ አራጋው

(2) ታጋይ አርበኛ አለበል አንዳርጌ

ሲሆኑ በዚህ ታሪክ የማይረሳው የሱዳን እና ህወሀት የጥፋት ዘመቻ ስማቸው ከላይ የተዘረዘረው በድምሩ 7 ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው የኢዴህ አባላት በሱዳን እጅ ደብዛቸው ጠፍቷል፡፡

ከአፈናው ማግስት በጊዜው የነበረው መረጃ እንደጠቆመው ከሆነ፣ የታፈኑት የኢዴህ አባላት፣ ዶካ ከሚገኘው የሱዳን ጦር ካምፕ ውስጥ እንደሰበሰቧቸው ታውቑል፡፡በመቀጠልም፣ የሱዳን መንግስት በሻለቃ መስጦፋ የ4ኛ ብርጌድ ወታደራዊ መረጃ ሀላፊ ከገዳሪፍ ወደ ዶካ በመጙዝ፣ዶካ ላይ ለህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወኪሎች ተላልፈው እንደተሰጡ ይጠቁማል፡፡ ታጋይ አርበኞቹ ከታፈኑበት ቀን ጀምሮ ምን እንደደረሰባቸው የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

በኢዴህ/Edu ታጋይ አርበኞች ላይ የሱዳን መንግስትን ወክለው የአፈና እርምጃውን የወሰዱ የሱዳን ጦር መረጃ/Military Intelligence  አባላት ስም ዝርዝር፣-

(1) ኮለኔል አብደርኺም ካርቱ ጠቅላይ መምሪያ

(2) ሌ/ኮሎኔል ሙሳ የምስራቅ እዝ ወታደራዊ መረጃ ሀላፊ አልፋው/El Faw ጦር መምሪያ

(3)ሻለቃ መስጦፋ የ4ኛ ብርጌድ የወታደራዊ መረጃ ሀላፊ -የአፈናው ዋና አስተባብሪ -ገዳሪፍ

(4)አምሳ አለቃ ወደል በሺር ዶካ የወታደራዊ መረጃ ሀላፊ -የአፈናው ዋና መሪ

(5)የኩኔና ወታደር ካምፕ ወታደራዊ መረጃ ተጠሪ ወታደር

 

ክቡር ጠሚ ዶር አብይ አህመድ፡-

ባልፉት ጥቂት ወራት የስልጣን ጊዜዎ በውጭ በሚገኙ ኢትዮጵያን እስረኞችን የማስፈታት እርምጃዎ እና በውጭ የታረዱ ኢትዮጵያዊን ዜጎችን አጽም ወደ ሀገር ለመመለስ ያሳዩትን ፍላጎት ይህን ደብዳቤ ለመጻፍ መነሻ ሆኗል፡፡

 

ከላይ የተዘረዘሩት ኢትዮጵያውያን አርበኞች ለሀገራቸው በነበራቸው የጋለ ፍቅር  ምክኒያት፣ የሞቀ እና መልካም ኑሮቸው ሳያባብላቸው  አገሪቱ በጊዜው በደረሰባት የደርግ ኢሰበአዊ አረመኔአዊ አገዛዝን በመቃወም ብሎም ለማስወገድ በተለያዩ የጦር ሜዳዎች የቆሰሉ እና በብርቱ የደከሙ አገር ወዳድ ዜጎች ናቸው፡፡ከሁሉም በላይ የተጠቀሱት የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት/ኢዴህ አባላት በአካብባያቸው የሚታወቁ እና በመልካም ምግባራቸው ምስጋናን ያገኙ ናቸው፡፡

 

ለ27 አመታት ጉዳያቸው ፍትህ ሳያገኝ፣ የድርጅት ጙዶቻቸውም ይሁኑ ቤተሰቦቻቸው በታላቅ እሳታዊ-መቆርቆር አና ታላቅ ሀዘን ላይ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም የእርስዎ አስተዳደር ጉዳዩን ከሱዳን መንግስት እና አጋራቸው ከሆነው የመንግስትዎ ዋነኛ አጋር የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት/ህወሀትን በማነጋገር የአርበኞቹን የመጨረሻ እጣ ፈንታ/Fate ምን ላይ እንደደረሰ እልባት እንዲሰጡን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡ ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ሙሉ ዝግጁ ነን፡፡

 

አዳነ አጣናው ዋሴ

 

ማሳሰቢያ፡- ደብዳቤው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ተልኻል፡፡ ጉዳዩ የሚያሳስበው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በተቻለ መጠን ደብዳቤውን በመገልበጥ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በተለይ አገር ውስጥ ያላችሁ እንድትልኩ ትብብር እንጠይቃለን፡፡ ለአመንስቲይ እንተርናሺናልም ተልኻል፡፡

 

አርበኞቻችን አንረሳም !

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.