ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሰጠን ተስፋና ጥርስ አልባው አንቀጽ 39 (ጌታቸው ኃይሌ)

ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሰጠን ተስፋና ጥርስ አልባው አንቀጽ 39  (ጌታቸው ኃይሌ) 1ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከታየ ጀምሮ ሰፊ ትችት ስለተካሄደ፥ ያልተባለ፥ ለኔ የተረፈ ነገር የለም። “ለመሆኑ ከየትኛው የሐሳብ ወገን ነህ?” እንደተባልኩ ተረድቼ፥ ውገናየን ትንሽ ለየት ባለ መንገድ ልመልስ እሞክራለሁ። ቀጥሎ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ያወዛገበን የኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 አቅም ኖሮት ሳይሆን በጥላው ብቻ እንደሆነም አሳያለሁ። ጥላ ስለማልፈራ፥ አንቀጽ 39ን መፍራት አቁሜያለሁ። ለዚች አጭር ድርሰት መነሻ የሆኑኝ አቶ ካሣሁን ነገዎ በአውስትራሊያ የአማርኛ ራዲዎ ጣቢያ በቅርብ ቀን  የጠየቀኝ  ጥያቄዎች ናቸው።

እንደ መቅድም፤

የኢትዮጵያ ሀገርነትና መንግሥት የቤተ ሰቦች ስጦታዎች ናቸው። የአክሱም፥ የዛጔ፥ የአምሐራ፥ የጐንደር፥ የሸዋ። ዘመነ መሳፍንትም ቢሆን የቤተ ሰብ አስተዳደር ነበር። ሕዝብ ሲነቃ፥ ወይም ተመኘ። ምኞቱ ካንዴም ሁለቴ አላዋቂዎች እጅ ገባ፤ መጀመሪያ ደርግ ላይ፥   በኋላ ደግሞ ኢሕአዴግ ላይ። ምኞቱ ቀጥሏል።

የኢሕአዴግ የሙከራ ዘመን። ወይም ቀዳማዊ ኢሕአዴግ

የነፈሰውን የዐውሎ ነፋስ ለውጥ ሳይቆረቁረን ለመቀበል እንዲመቸን፥ ኢሕአዴግ የዛሬ ሃያ ሰባት ዓመት ሥልጣን ከያዘበት ጀምሮ እስከዛሬ ያለውን አገዛዝ ወይም   እንድንለው የዶክተር ዐቢይ አሕመድ ንግግሮች ይጋብዙናል። በዚህ ዘመን ብዙ ስሕተቶች ተሠርተዋል። ስሕተቶቹን የማያውቅ ስለሌለ ከዝርዝሩ አልገባም። የኢጣልያን የፋሺስት ዘመን የሚያስመሰግን ነበር ብሎ ማለፉ ይሻላል። ዘመኑን የሙከራ ዘመን ብለን ከወሰድነው፥ በሙከራው (በመከራው) ዘመን የተደረገን ስሕተት እንዳይደገም ማድረግ እንጂ ወደኋላ ተመልሶ ማረም ወይም  ጥፋተኛውን መቅጣት ተገቢ አይሆንም። የዶክተር ዐቢይ አሕመድ አቋም “በዚህ እንለፈው” የሚል ነው።

ዳግማዊ ኢሕአዴግ።

ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በጠቅላይ ሚኒስተርነት በነገሠ ጊዜ የተጀመረውን የኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመን ልንለው እንችላለን። በዚህ ዘመን በቀዳማዊ ኢሕአዴግ ዘመን የተደረጉ ስሕተቶች ይታረማሉ፤ የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ። ከሕዝቡ ጋር አብሮ የተጨቆነው ኢትዮጵያዊነት ተፈቶ ያለመልማል። የሚያኮራን ታሪካችን እንደዱሮው እንዲያኮራን እሱም ከእስረኞቹ ጋር አብሮ ይፈታል። የወያኔ ትግሬዎች የፈለጉትን የሚገድሉበት ዕድል ይሰረዛል። የጎሳ መለዮ ካርድ ይቃጠላል። ሕገ መንግሥቱ ይከበራል።

ይህ ሕልሜ ነው ወይስ እውነት? ብዙዎቹ ጉዳዮች በአለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ተፈጽመዋል። ይህን ካላደረገ ብለን ሳንጨርስ የምንመኘውን ያደርጋል። ከዚህ የበለጠ ፍጠን ማለት፥ ሲሮጥ ተሰናክቶ ባፍ ጢሙ እንዲደፋ ማድረግ ይሆናል። በቀዳማዊ ኢሕአዴግና በዳግማዊ ኢሕአዴግ መካከል ያለው ትልቅ ወንዝ በተራቡ አዞዎች የተሞላ ነው። ዶክተር ዐቢይ ተጠንቅቆ እያደባ፥ ምናልባትም ለአዞዎቹ ምናምን እየጣለላቸው ካልዋኘ፥ ሊበሉት ይችላሉ። “በሰላም እንዲሻገር ሕዝብ ይደግፈው፤ አበጀህ እያልን እንጩህ” የምንለው፥ አዞዎች ጩኸት እንደሚፈሩ ስለምናውቅ ነው። ድፍረቱንና ጀግንነቱን ማድነቅ ግዴታችን ነው።

የዶክተር ዐቢይ አሕመድ እርምጃ

የዶክተር ዐቢይ አሕመድ አመጣጥ እግዚአብሔር “የሕዝቤን ዋይታ ሰምቻለሁ” ብሎ ሙሴን ያስነሣውን ይመስላል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ዱሮም ራብተኛ ነበር። በዘመነ ኢሕአዴግ ግን የደረሰበት ረኀብ አምሳያ የለውም። ሕዝቡ ምናምን ቀምሶ ለማደር የሚያደርገውን ለመስማት ይከብዳል። ለምሳሌ፥ ደርግ ቤታቸውን ለወሰደባቸው ሰዎች በወር 250 ብር መድቦላቸው ነበር። ዛሬም፥ ከሠላሳ አምስ ዓመት በኋላ፥ የሚከፈላቸው ያንኑ በአሁኑ ገበያ አንድ ቁና ጤፍ የማይገዛ 250 ብር  ነው። ቢያንስ  ቢያንስ 2300 ብር መሆን ነበረበት።

ዶክተር ዐቢይ አሕመድን የኢትዮጵያ አምላክ የላከው ለመሆኑ አራት ነገሮች አሳምነውኛል፤ ፥ በደስታ እንድንኖር ተስፋ የሰጠን የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ ነው። ሁለተኛ፥ በሞት የተፈረደባቸውን እስረኞች ሳይቀር አስፈታ፤ ሦስተኛ፥ በሚሠራው ሥራ የሚጠሉት ሰዎች የሚጽፉበትን አያለሁ። ፥ ከአቶ ይልማ መገርሳ ጋር ያለው መልካም ግንኙነት ነው። የእግር ኳስ ጨዋታ ስለምወድ፥ ይኸንን ከዚያ ምሳሌ በማምጣት ላስረዳ፤ አንድ ቡድን የሚያሸንፈው ብዙ አይጥ (ግብ) ሲያስቆጥር ነው። አስቆጣሪውን ተጫዋች ጓደኞቹ ያቅፉታል፥ ክብር ይሰጡታል። ጥሩ ተጫዋች እሱ ቢያገባ ክብር እንደሚያገኝ እያወቀ፥ የራሱን ዕድል ከተጠራጠረ፥ ኳሷን ለሌላው ተጫዋች ያቀብላታል። አቶ ለማ መገርሳ ለሥልጣን ሳይጓጓ ለኢትዮጵያ ስላሰበ፥ ዶክተር ዐቢይ አሕመድን አስቀደመ።

ዶክተር ዐቢይ በመነሣቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእግዚአብሔር ምስጋና እያቀረበ ነው። የበለጠ ድጋፍ የሚያገኘው፥  ማንም ኢትዮጵያዊ  በመረጠው ቦታ የመኖር መብት አለው የሚለውን የሕገ መንግሥት አንቀጽ ሲያስከብር ነው። በአሁኑ ሰዓት ይህ አንቀጽ የሚጣሰው ከባለ ሥልጣን በጽሑፍ በተሰጠ ትእዛዝ መሆኑን ዶክተር ዐቢይ ያውቃል። በደል የሚደርሰው በኦሮሞዎች ላይ ጭምር ነው። ይኸንን እንዲያስቆም እያሳሰብን፥ ለማቆም የተቸገረበት ነገር ቢኖር ነው ብሎ ማሰብም ተገቢ ነው።

የዶክተር ዐቢይ አሕመድ እርምጃ  የቅኔ መምህራን ኅብር የሚሉት ዓይነት ነው። ለኅብር ብዙ ጊዜ የሚሰጠው ምሳሌ አልቃሿ፥ “ዓምና ነበር እንጂ ዘንድሮስ ያለችው ነው። የሚናገረውና የሚሠራው አብዛኛውን ጊዜ፥  ማንኛውም ቡድን “ዐቢይ ወገኔ ነው” እንዲል አድርገውታል። አንድነቶች

ሚዛኑ ወደነሱ እንዲያጋድል ከፈለጉ፥ “ከናዝሬት ደግ ሰው አይወጣም” ማለታችንን ማቆም፥ በርታ ማለት፥ ዘዴ መስጠት አለባቸው።

ሆኖም፥ ወያኔዎች የራሳቸውን ሕገ መንግሥት ከተቃወሙ፥ የሁለት ኀይሎች ፍጥጫ ይፈጠራል። ሁለቱ ኃይሎች የምላቸው በአንድ ወገን የኢትዮጵያ ሕዝብ፥ በሌላ ወገን ወያኔዎች ራሳቸው እየደለቡ በፍርፋሪ የቀጠሩት የጦር ኃይላቸው ናቸው። በዚህ ፍጥጫ ጊዜ ወያኔዎች በዘረፉት ገንዘብ ለመጠቀም ሲሉ የሚያፈገፍጉ ይመስለኛል። ዱሮውንም አነሣሣቸው የተሳሳተ ነበር። የትግራይን ሕዝብ ድጋፍ ያገኙት የትግራይን የበላይነት፥ የትግሬዎችን ገዢነት ለማረጋገጥ ነው እያሉ ነበር። እውነትም ለጊዜው ጌቶች አድርገዋቸዋል። ማንኛውም ትግሬ ከአቶ አሰፋ ማሩ ጀምሮ የፈለገውን ትግሬ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ መግደል ይችል ነበር። ግን ለትግራይ ልጆች ለወዲያኛው ያተረፉላቸው ነገር ቢኖር፥ በኢትዮጵያ ሕዝብ መጠላትን ነው። ኢትዮጵያ ላይ የፋሽስት ጣልያኖች የዛሬዎቹን ትግራዮች ያህል አልተጠሉም። አንዲት የትግራይ ሴት  “በኢትዮጵያ  ሕዝብ  ፊት  ሹሩባችንን እያሳየን መራመድ አልቻልንም” እያለች ዋይታዋን ስታሰማ ሰምቻለሁ። በምን ምክንያት እንደሆነ ግን አላወቀችውም።

ባዶ አንቀጽ 39

ኢሕአዴጎችን ያልተቀበልናቸው፥ በሁለት ምክንያት ነው፤ አንደኛ፥ በሕገ መንግሥታቸው ስለከፋፈሉን፤ ሁለተኛ፥ በሕገ መንግሥታቸው በወረቀት ያጸደቁልንን መብት በሥራ ስለነፈጉን ነው። ሕገ መንግሥታቸው ውስጥ የምንወዳቸውና የምንጠላቸው አንቀጾች አሉ። ዶክተር ዐቢይ የምንወዳቸውን አንቀጾች ካስከበረልን ትልቅ ውለታ ነው። ምናልባትም ከዚያ የበለጠ ምኞት ላይኖረን ይችላል። የአንድነት ወገኖች የማንወደው ሕግ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 39 ነው።

ዶክተር ዐቢይን ማድረግ የማይችለውን፥ “እኛ የማንወደወዳቸውን አንቀጾች ከሕገ መንግሥቱ ሰርዝልን” ከማለት፥ ማድረግ የሚችለውን “ሕገ መንግሥቱን አስከብር” ብንል ይሻላል። ግን ሕገ መንግሥቱ ከተከበረ፥ በተለየ አንቀጽ 39 በራሱ ተገርስሶ ይወድቃል። ምክንያቱም አንቀጽ 39ን ጠጋ ብሎ ላየው ድቡሽት ላይ የተሠራ ባዶ ቤት ሆኖ ያገኘዋል። ምን ማለቴ እንደሆነ ላስረዳ።

ሕገ መንግሥቱ  አንደኛ፥ እመግቢያው ላይ ኢትዮጵያ  የብሔሮች፡ ብሔረሰቦች፡ ሕዝቦች አገር መሆኗን በይፋ ያውቃል፤ በእንግሊዝኛው nations, nationalities, and peoples ይላቸዋል። ጎሳዎቹንና ነገዶቹን ነው። ሁለተኛ፥ አገሪቱን በአንቀጽ 47 ከዘጠኝ የፌዴራል ክልል (States) ይከፍላታል ። አንቀጽ 39 የመገንጠል መብት የሚሰጠው ለእነዚህ በክልሎቹ ውስጥ ለሰፈሩት ጎሳዎችና ነገዶች እንጂ፥ በጠቅላላው ለክልሎቹ አይደለም። ሕገ መንግሥቱን ልጥቀስ፤

“1. ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፡ ብሔረሰብ፡ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው። 4. የብሔር፡

ብሔረሰቦች፡ ሕዝቦች የራሱን ዕድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል  መብት ከሥራ ላይ የሚውለው (ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው።)

ሀ) የመገንጠል ጥያቄ በብሔር፡ በብሔረ ሰቡ ወይም በሕዝቡ የሕግ አውጪ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ የድምፅ ድጋፍ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥ፡”

አንደኛ፥ እነዚህ ጎሳዎች ስንት እንደሆኑ አይታወቅም። ጎሳዎች የሌሉበት ክልል ስለሌለ፥ በየክልሉ ተፈልገው ቢቆጠሩ ወደ ሰማንያ ይደርሳሉ ይባላል። ሁለተኛ፥ ከሰማንያዎቹ ጎሳዎችና ነገዶች አንዳቸውም በሁለት ሦስተኛ ውሳኔ የሚያሳልፍ  “የሕግ አውጪ ምክር ቤት” ያለው የለም።

በመጨረሻ፥ አንቀጽ 41.1. እንዲህ ይላል፤

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው። (እንግሊዝኛው የበለጠ ግልጽ ነው፤ “Every Ethiopian citizen has the right to engage freely in economic activity and to pursue a livelihood anywhere in the national territory.”)

በሕገ መንግሥቱና በሕዝብ መካከል አለ መግባባት የተፈጠረው የስያሜ ቃላት ባለመስተካከላቸው ነው። ዋናው መደንቅፍ “ክልል” የሚለው ስያሜ ነው። “ክልል” ሲባል  አንድ ክልል አጥር ሆኖ በውስጡ የሚኖሩ ዜጋዎች የግል ንብረት ያስመስላል። ልክ ማዘጋጃ ቤት የከተማ ቦታ ዳር ድምበር ከልሎ፥ ካርታ አውጥጦ ለአንድ ሰው እንደሚያስከብር። ሐሳቡ ይኼ እንዳልሆነ ሁለት ነጥቦች ይመሰክራሉ፤ አንደኛ፥ እንግሊዝኛው “States” ማለቱ፣ ሁለተኛ፥ በያንዳንዱ ክልል ውስጥ “ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች” መኖራቸውን ማወቁ። ስማቸውን መልአክ ሳወጣው ቀርቶ ነው እንጂ፥ ክልሎች ብሔራዊ የአስተዳደር ክፍሎች፥ ራስ-ገዝ ግዛቶች ናቸው። ሁኔታው ይህ ከሆነ፥ ጥያቄያችንን እናስተካልክ፤ “ወደጥንቱ ወደታሪካዊው አከፋፈል እንመለስ። ይኸም ካልሆነ፥ “አንድ ክልል ከፈለገ ሊገነጠል ይችላል” የማይለው ሕገ መንግሥት ይከበር። “አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው” እንዳይሆን፥ ኢሕአዴግ ያወጣውን ሕግ አይጣስ።

አንድ አውቶቡስ ብዙ ሰዎች ተሳፍረዋት ከአዲስ አበባ ወደደቡብ ስትበር ትታየኛለች። መንገደኞቹ የተሳፈሯት ወደሚፈልጉት ከተማ እንደምትወሰዳቸው በመተማመን እንጂ ወዴትኛው ከተማ እንደምትሄድ ከነጂው የሰሙት ነገር የለም። ወደ ደቡብ የምትሄድ መሆኗን አይተው፥ የሻሸመኔና የናዝሬት መንገደኞች ሰፍተውባታል። ቁርጡን የሚያውቁት ሞጆ ላይ ሲደርሱ ነው። አውቶቡሷ እዚያ ስትደርስ ነጂው ሁሉንም መንገደኞች ይዞ እሱ ለመሄድ ወደሚፈልግበት የሚያደርሰውን መንገድ ይዞ ይበራል። የኢትዮጵያ አምላክ እመሪው ላይ እጁን እንዲያርፍበት እንጸልይ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.