ሰሚ ያጣው የአማራ ገበሬዎች መፈናቀል (ያሬድ ሓይለማሪያም)

የአገዛዝ ሥርዓቱ ሥልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ከአገሪቱ ክፍሎች በተለይም ከኦሮሚያ እና ከቤኒሻንጉል ጉምዝ የተፈናቀሉ አማራ አርሷደሮች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው። በዚህ ዙሪያ ዝርዝር ምረጃ ለማግኘት ኢሰመጉ ያወጣቸውን በርካታ መግለጫዎች ማገላበጥ ይቻላል። ይህ ችግር መፍትሔ ሳያገኝ አሥርት አመታቶች ተቆጠሩ። ኢሰመጉ ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ በየጊዜው ካወጣቸው መግለጫዎች ጥቂቱን ማየት ይቻላል፤

http://www.ethiopians.com/rep03.html 
https://www.ehrco.org/wp-conte…/uploads/2000/…/special32.pdf
https://www.ehrco.org/wp-conte…/uploads/2016/…/special34.pdf
https://ahrethio.org/…/HRCO-136th-Special-Report-English.pdf

ይህ ዘርን መሰረት ያደረገ ዜጎችን የማፈናቀል ተግባር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚታይ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ በሌሎች ሥፍራዎች የሚከሰቱት የጎሳ ግጭቶችን ተከትሎ ነው። በቅርቡ በኢትዮ-ሱማሌ እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ድንበሮች አካባቢ የተከሰቱት የእርስ በርስ ግጭቶች በአገሩት ከታዩት መፈናቀሎች ትልቁን ቁጥር የያዘና የብዙ ሰዎችም ህይወት ያለፈበት አሳዛኝ ክስተት ነው።

በአማራ ተወላጆች ላይ ላለፉት 27 ዓመታት በተለያዩ ክልሎች የሚፈጸሙት የማፈናቀልና የማዋከብ እርምጃዎች ግን ከሞላ ጎደል አብዛኛዎቹ ከጎሣ ግጭቶች ጋር የተያያዙ ሳይሆን በአካባቢው ባሉ የመንግሥት ተሿሚዎች ትዕዛዝ እና መሪነት የሚፈጸሙ ናቸው። ለዚህም ይህን የኢሰመጉን መግለጫ ማየት ጥሩ ማሳያ ነው፤ https://ehrco.org/…/34th-special-report-serious-destructio…/

በ1992 ዓ.ም. በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ ኪራዎ ወረዳ ውስጥ በአካባቢው የመንግስት ባለሥልጣናት ትዕዛዝ የክልሉ ልዩ የፖሊስ ኃይል እና ሚሊሽያዎች በአማራ ተወላጆች ላይ ክልላችንን ለቃችው ውጡ በሚል በሰነዘሩት እርምጃ ብዙዎች ተገድለዋል፣ ቁጥራቸው ከ10ሺ በላይ የሆኑ ተሰደዋል፣ መኖሪያ በቶቻቸው በከፍተኛ መሳሪያ እየጋየ እንዲወድም ተደርጓል፣ የእምነት ሥፍራዎች ተዘርፈው ተቃጥለዋል።

ለነገሩ በሌሎች ክልሎች ያሉ የመንግስት ባለሥልጣናት ብቻ ሳይሆኑ በአማራ ተወካይነት ስም ባህርዳር የተቀመጠው በአዴን ለህውሃት አሽከርነቱን ለማሳየት ሲል በክልሉ የሚገኙ የአማራ ገበሬዎችን የመሬት ሽንሸና በሚል ሰበብ ብዙ ሺዎችን ማፈናቀሉ ይታወሳል። ይህ ችግሩ ዛሬም መቀጠሉ የሚያሳየው ነገር ይህ የአማራ ገበሬዎችን የማዋከብና የማፈናቀል ድርጊት የሥርዓቱ የተበላሸ የጎሳ ፖሊሲ ውጤ መሆኑ ነው። ይህን ችግር የጠ/ሚንስትር አብይ አስተዳደር ቅድሚያና ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የማያዳግም እርምጃ ሊወስድ ይገባዋል። ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት የሚፈናቀሉባት፣ የሚሳደዱባት፣ የሚታሰሩባት እና የሚገደሉባት ኢትዮጵያ ታሪክ ሆና መቅረት አለባት።

ሌላው አሳዛኙ ነገር አለም አቀፍ ማህበረሰቡም በአገዛዝ ሥርዓቱ የጎሳ ትርክት ታውሮ ይሁን ወይም በሌሎች ምክንያቶች በአማራ ክልል ውስጥ ለሚፈጸሙ የመብት እረገጣዎች እና በአማራ ተወላጆች ላይ ለሚፈጸሙ በደሎች ተገቢውን እና በቂ ትኩረት አለመስጠቱ እጅግ አሳፋሪ እና አሳዛኝም ነው። ኢሰመጉ ያወጣቸውን መግለጫዎች ለእነዚህ አካላት ይደርሳሉ። ይሁንና የዚህን ሕዝብ በደል በአግባቡ ለመመርመር የሚንቀሳቀስ አለም አቀፍ ተቋም አለመኖሩ ያሳዝናል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.