ማንም ድርጅት በሉዓላዊነታችን ላይ መደራደር አይችልም የሀገሩን ባለቤት 100 ሚሊዮን የኢትዮ}ያ ህዝብ እንጂ ስብሓት ነጋና በረከት ስምዖን አይደሉም

ከበላይ ገሰሰ

በኢትዮ}ያ የፓለቲካ ቀውሱን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ገና መልክ ሳይዝ ፣ ሁነኛ የሆነ ማዕከላዊ መንግስት ገና ሳይጠናከርና በሁለት እግሩ ሳይቆም ፣ ሁሉንም የለውጥ ባለድርሻዎች ሊያሳትፍ የሚችል ፓሊሲና ሕግ ገና ሳይወጣ ፣ ባጠቃላይ ሀገራችን  ምስቅልቅልና ድፍርስ ሁኔታ ላይ እያለች ድንገት አሁን በቀውጢ ጊዜ የኢትዮ ኤርትራን የዳር ድንበር ጉዳይ እንደ አንገብጋቢ ጉዳይ ታይቶ በአስቸኳይ እንዲወሰን የተደረገበት ዋናው ሚስጢሩ ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መነሻ እንዲሆነን የሚከተሉትን ዓበይት ነጥቦች እንመልከት ::

 1. አንደኛውና ዋናው ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በህወሓቶች ላይ የደረሰውን የፓለቲካ ሽንፈትና ውርደት ማካካሻ ለማድረግ ሲሆን በሀገራችን ላይ የተጀመረውን የለውጥ ሂደትን ከቁጥጥራቸው ውጭ እየሆነ መሄዱን በውል የተገነዘቡትን የህወሓት መሪዎች እንደለመዱት በነርሱ ላይ ያነጣጠረውን የህዝቡን አመፅ ግቡ እንዳይታ መንገዱን ለማሳሳትና ህዝቡ ዋናው የለውጥ አጀንዳውን ትቶ ወደ የዳር ድንበር ንትርክና እንካ ስላንቲያ እንዲገባ ለማድረግ ሆን ተብሎ የተቀየሰ ሴራ መሆኑን አያጠራጥርም:: ስለዚህ ህወሓቶች የለውጡን ጥያቄ መመለስ ስለማይችሉ አደናጋሪና አስደንጋጭ አጀንዳን በመፍጠር የለውጡን መንፈስና የህዝቡን ቀልብ መቀየርና ማዛባት የተለመደና የተካኑበት የአርባ ዓመት ሙያቸው ነው::

 

 1. ሁለተኛው ምክንያት የተጀመረውን የለውጥ ሂደት በዚሁ ከቀጠለ ህወሓት የአንበሳ ድርሻ ይዞ በበላይነትና በፈላጭ ቆራጭነት የሚገዛትን ኢትዮ}ያ እንደማትሆን እሙን ነው :: ስልጣኑ በህዝቡ ባለቤትነት እጅ ከገባ ደግሞ ህወሓት ከነ ግሳንግሱ እየከሰመ መሄዱን አይቀሬ ነው ብቻ ሳይሆን ላለፉት አርባ ዓመታትን ያህል በሀገርና በህዝብ ላይ የሰራቸውን ክህደቶችና ወንጀሎችንም ጭምር ውሎ አድሮ መፈተሻቸውና ዳግም መነሳታቸው አይቀርም :: በመሆኑም ህወሓቶች ከዚሁ አጣብቅኝ ሁኔታ ለመውጣት የወሰዱት አማራጭ ሉዓላዊነታችንና ብሄራዊ ጥቅማችንን አሳልፈው በመስጠት ከኤርትራ ጋራ አዲስ ወዳጅነትና የትግራይ ትግሪኚን ግንኙነት መስርተው በጥገኝነት ለመኖር እንችላለን የሚል የቆየ ስሌት ነው

 

 1. ህወሓቶችም ሆነ ሻዕቢያውያን ድብቅ አጀንዳቸውንና ህልማቸውን እውን ለማድረግ የመረጡት ምቹ ጊዜ አሁን ነው:: ላለፉት ግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል በሀገራችን ምድር የተተከለውንና የተዘራውን የከፋፍለህ ግዛ መርዝ ውጤቱ ለሀገሩ ለክብሩ ለመብቱ ለነፃነቱ ለሉዓላዊነቱና ለአንድነቱ ጥብቅና የሚቆም ትውልድ የለም ” የኢትዮ}ያ ህዝብ በዘር በሀይማኖት ተከፋፍሏል ” ኢትዮ}ያ ገና ሳትረጋጋና ሳትጠነክር የዳር ድንበሩን ጉዳይ አሁን ካልወሰነው ሌላ ጊዜ ዕድል አይኖረንም ” ስለዚህ ሳይቀድሙን ቶሎ ብለን አሁን መጨረስ አለብን ከሚል ስሌት የተነሳ ነው::

 

 1. የኢትዮ ኤርትራ ዳር ድንበር ጉዳይ ከውጭ ሐይል እጅ የፀዳ አይደለም:: ከልምዳችን እንዳየነው በአካባቢው ስላለው ችግር ለመፍታት ሁሉ ጊዜ ታሳቢ ተደርጎ የሚወሰደው የኢትዮ}ያ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ሳይሆን የሚቀድመው የውጭ ሐያላን መንግስታትን ያስደስታል? እርዳታ ያስገኝልናል? በስልጣን ላይ ያቆየናል? ወዘተ የሚሉትን ጥያቄዎች ነው መነሻ የሚደረገው:: በዚህ ምክንያት የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ሁሉ ጊዜ ከኢትዮያውያን እይታና ቁጥጥር ውጭ ሚስጢራዊ በሆነ መንገድ የውጭ ሐይል ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ እንዲወሰን ይደረጋል::

 

 1. የዳር ድንበሩን ወሳኔ እንዲፋጠን ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ሻዕቢያ ራሱ በሚገባ ስራውን ስለሰራ ነው:: በአንድ በኩል ከሻዕቢያ በስተጀርባ ካሉት ሐይሎች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን በማጠንከር በቀይ ባህር ቀጠና ያለውን ሁኔታ የመደራደር ዓቅሙንና ተፈላጊነቱን ከፍ እንዲል አድርጎታል:: በሌላ በኩል ደግሞ በሀገራችን ጉዳይ የተፈጠረውን ፓለቲካዊ ቀውስ በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር ሲቆጣጠረው ስለቆየ የህወሓት መሪዎችን እጅ ጠምዝዞ እንዲወስኑ ለማድረግ ምቹ ሁኔታና አጋጣሚ ተፈጥሮለታል:: በአንፃሩ በአስር ሽዎች ጀግኖች የወደቁበትን ጥያቄ መና ሆኖ እንዲቀር በማድረግ በተለይም ለትግራይ ህዝብ ዳግም ሞት፣ ዳግም መርዶ፣ ዳግም ውርደትና ዳግም ሐፍረት የሚያከናንብ ውሳኔ ነው::

 

 1. ሌላው የውሳኔው እንድምታ የአዲሱን የጠቅላይ ሚኒስትር ስራ ለማጉደፍና ከህዝቡ ጋር ለማጋጨት ሆን ተብሎ የተሸረበ ሴራ ይመስለኛል እንጂ ዶክተር ዓቢይ የመለስን ታሪክ ይደግማል ብዬ አላምንም::

ይሁን እንጂ የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ጉዳይ ስንት የደምና የህይወት ዋጋ የተከፈለበት ያልተቋጨ ጥያቄ ስለሆነ ዛሬ በሆይ ሆይታ መሬትን ቆርሶ በመስጠት ብቻ ስር የሰደደውን ችግር የሚፈታ ጉዳይ አይደለም :: ችግሩ ከባድመ በላይ ነው:: እሱም የመቶ ሚሊዮን ህዝብ ሉዓላዊነትን ፣ ብሄራዊ ጥቅምንና ጂኦ ፓለቲካዊ ድህንነትን ሳይረጋገጡ የህዝቡን አፈ በመዝጋት  በሻዕቢያና በህወሓት መሪዎች መካከል በጓሮ በሚደረገው የፓለቲካ ቁማር ጨዋትና ሽኩት ዘላቂ መፍትሄ ይመጣል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው:: ጭስና ሐቅ መውጫ አያጣም እንደሚባለው ሁሉ የኢትዮ}ያ ህዝብን በመናቅና ምንም ማድረግ እንደማይችል እንደጉንዳን በመመልከት የሚደረገውን ውሳኔ በሰው ቁስል ላይ እንጨት እንደ መስደድ ያህል ይቆጠራል::

 ታዲያ ሐቁ ምንድን ነው?  

 • የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ጉዳይ ቀደም ሲል ቅኝ ገዚዎች ራሳቸው ያፈረሱት ውል ሲሆን ከአልጀርስ ውል በሗላም ሻዕቢያ ራሱ ሕግ ወጥ በሆነ መንገድ በመጣስ ያፈረሰው ስለሆነ ካሁን በፊት የተደረጉ ውሎች ሁሉ በአሁኑ ግዜ ተፈፃሚነት የላቸውም::

 

 • በአሁኑ ግዜ የሀገራችን ሁኔታ ጨርሶ ሳይረጋጋና በሀገራችን ጉዳይ ላይ ያገባናል የሚሉትን የፓለቲካ ሐይሎችና ሌሎች ማሕበረሰባዊና የእምነት ተቋማት እንዲሁም የሀገሩን ባለቤት የሆነውን ሰፊው ህዝብ በማግለል መሬትን የመሸንሸን እሽቅድድም በሀገርና በህዝብ ላይ ተጨማሪ ክሕደትና ወንጀል መፈፀም ነው::

 

 • ስንት ደም ያፋሰሰ ውስብስብ የሆነውን የሀገራችን ሉዓላዊነት ጉዳይ በአንድ ፓለቲካዊ ድርጅት በጓዳ የሚወሰን አይደለም :: ጉዳዩ ከፓለቲካ ድርጅቶች እጅ ወጥቶ አግባብ ባላቸው የመንግስት አካላት አማካኝነት ለፓርላማ ቀርቦ ይፋ የሆነ ውይይት ሳይደረግበት በነ በረከት ስምዖንና በነ ስብሓት ነጋ አጃቢነት የሚወሰን አይደለም::

ከዶክተር ዓቢይ አህመድ መመረጥ በሗላ ከዳር ድንበሩ ጉዳይ ጋር

                  ተያይዞ በትግራይ አካባቢ እየታየ ያለው ክስተት ምንድን ነው?

 

ህወሓቶች ባላሰቡበትና ባልገመቱት ሁኔታ ከቁጥጥራቸው ውጭ በሆነ መልኩ ዶክተር ዓቢይ አሕመድን ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኖ ከተመረጠ ማግስት ወደ ትግራይ ከፈረጠጡበት ቀን ጀምሮ ያልለመዱትን ድብ ዕዳ ስለሆነባቸው ወደ ትልቅ ትርምስና መደናገር የገቡ መሆናቸውን ከሚናገሩትና ከሚሰሩት ስራ በግልፅ እየታየ ነው:: ከዚህ ፍራቻና ድንጋጤ በመነሳትም ከወትረው ለየት ባለ ሁኔታ ካድሬዎቻቸውን ብቻ እየሰበሰቡ ከሚናገሩዋቸውና በተለያየ መድረክ ከሚሰጧቸው መግለጫዎች ውስጥ በከፊል የተወሰዱ አንኳር አንኳር ነጥቦቹን እንመልከት::

 • የዶክተር ዓቢይን አካሄድ በዓይነ ቁራኛ እንጂ በበጎነት አልተመለከቱትም:: እነሱ ያላደረጉትን በማድረጉና በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ በእንጀራቸውና በህልውናቸው ላይ የመጣባቸው አስመስለው ነው ለህዝቡ እያቀረቡት ያሉት:: በተለይም የወጣቱን ዓመፅና የህዝቡን የለውጥ መነሳሳት በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ስጋትና ጥቃት አድርገው ነው አሁንም እየተናገሩ የሚገኙት::

 

 • የአማራ የኦሮሞና የደቡብ ህዝብ መቀራረብና የትግል አንድነትን መፈጠር ለስርዓታቸው ህልውና እንደ ትልቅ አደጋ አድርገው የሚመለከቱት መሆኑን በተለያዩ ህዝባዊ ስብሰባዎች በተደጋጋሚ ተናገሯል:: ከዚህ መደናገር በመነሳትም ኢሕአዴግ እንደ ድርጅት ይቀጥላል? ወይስ ይከስማል? የሚለውን መስቀለኛ ጥያቄ በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንዲቆሙ አድርጎቿል::

 

 • የተቃዋሚ ጎራውን ከዶክተር ዓቢይ ጋር መቀራረብና የፓለቲካ እስረኞችን የመፈታት ጅምር በበጎ ሳይሆን እንደ ስጋት ነው የሚመለከቱት:: ይህንን የሚገድብ ሕግ ለማውጣትም እየተንቀሳቀሱ ናቸው::

 

 • ዛሬ በትግራይ ተወላጆች ዘንድ የዓረና ትግራይ ለሉዓላዊነት ዴሞክራሲ ፓርቲ እንደ አንድ አማራጭ ሐይል እየተጠናከረ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን ሌሎች በሀገር ውስጥና በዲያስፓራ ለፍትሕና ለዴሞክራሲ የቆሙ አዳዲስ ሲቢክ ማሕበራት መፈጠር ጀምሯል:: ይህም ለህወሓት መሪዎች ትልቅ ስጋትና ራስ ምታት እየሆነባቸው ይገኛል:: ይህን አደጋ ለመግታት ሲባልም በአንፃሩ በስብሓት ነጋ በቴድሮስ ሐጎስና በበረከት ስምዖን በእጅ አዙር የሚደራጁና የሚደጎሙ አግዓዚያን በሚል ስም የትግራይ ትግርኚን አጀንዳ አንግበው የተነሱ ስብስቦች በሀገር ውስጥና በውጭ ዓለም እየተበራከቱ መጥቷል ::

 

 • የውጭ ግንኙነትን በሚመለከት ደግሞ ሁለት ዓይነት ስጋቶች እንዳላቸው በየስብሰባቸው ተንፀባርቋል:: አንደኛ ሊበራል ዴሞክራሲ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ላይ ተፅዕኖ እንዳይኖረው ይፈራሉ:: ሁለተኛ የውጭ ዲፕሎማሲው በተለይም የኤርትራን ጉዳይ በሚመለከት ከነርሱ እይታና ቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ ይሰጋሉ::

በጥቅልሉ ሲታይ ከዚሁ ፍርሃትና ጭንቀት በመነሳት በተለይም ዶክተር ዓቢይን ስልጣን ላይ ከመጣ ጀምሮ በትግራይ በሚካሄዱ ስብሰባዎች በካድሬዎቻቸው አማካኝነት ተደጋግመው እየተነሱ ካሉት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ውስጥ አንደኛ ከመገንጠል አዝማሚያ ጋር ተያይዞ “ ገፋ ቢል ጎሙጎፋ” የሚል ስሜት ነው:: ይህ ተግባራዊ ለማድረግም በቅድሚያ ሁሉንም ነገር ትተን በልማትም በኢኮኖሚም ሆነ በፓለቲካ በትግራይ ላይ በመረባረብ የመከላከል ዓቅማችንን እንገንባ የሚል ነው:: ሁለተኛ ህወሓትን ከውድቀትና ከመሞት እናድን የሚል ነው:: ሶስተኛ የሀገር ውስጥ ጠላቶቻችን ሳይበራከቱና ሳይቀድሙን በአስቸኳይ ከኤርትራ እርቅ በማድረግ አማራጭ በር ይኑረን የሚሉት ሀሳቦች ናቸው እየተሰራጩና እየተንፀባረቁ የሚገኙት::

 

ስለሆነም ከዚሁ ጭፍን አመለካከት በመነሳት የኢትዮ ኤርትራን የድንበር ጉዳይ በሚመለከት አሁን በአስቸኳይ ውሳኔ እንዲያገኝ የተደረገበት ዋናው ምክንያትም ለሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች በጎ በማሰብና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ተብሎ ሳይሆን መነሻው በአንድ በኩል ህወሓት አሁን በኢትዮ}ያ ውስጥ በደረሰበት የፓለቲካ ኪሳራና ቀውስ ጋር በተያያዘ የመጣ የጭንቀት እርምጃ መሆኑን አያጠራጥርም:: በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮያውያን መካከል አንድነት እንዳይፈጥርና የለውጡን ሂደት ለመቀልበስ ሲባል ሆን ተብሎ አዲስ አጀንዳ በመስጠት የያዝነውን ጉዳይ ትተን ወደ እንካ ስላንቲያ እንድንገባ የተጠነሰሰ ደባ መሆኑን እሙን ነው::

 

እግዚአብሄር የሀገራችንን ሰላምና አንድነት ይጠብቅ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.