የብአዴን አባላት የህውሃትን አገዛዝ አወገዙ

የብአዴን አባላት የህውሃትን አገዛዝ አወገዙ፡፡ ሰሞኑን በሁለት የተለያዩ ቀናት በተደረገው የባህር ዳር ከተማ አጠቃላይ የብአዴን አባላት ስብሰባ፣ “የህውሃት አገዛዝ በአማራው ላይ ማለቂያ የለሽ ስቃይና ሰቆቃ ለዓመታት ሲያደርስ ቢቆይም፣ክልሉን በሚያስተዳድሩ አድር ባዮች ምክንያት እንዳንናገር ታፍነን ነበር” በማለት አባላቱ የህውሃትን አገዛዝ በድፍረት ሲቃወሙ ተሰምተዋል፡፡

በባህር ዳር ሙሉዓለም አዳራሽ በተደረገው ስብሰባ የክልሉ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ስብሰባውን በመጀመሪያው ቀን የመሩ ሲሆን፣በሁለተኛው የስብሰባ ቀን የአማራ ብዙሃን መገናኛ ስራ አስኪያጅ አቶ አለባቸው ስብሰባውን ከሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር አብረው መርተዋል፡፡
“ብአዴን ለአማራው ህዝብ ምን ፈየደ?” የሚለው ጥያቄ በአብዛኛው አባላት የተነሳ ሲሆን ከፍተኛ የብአዴን አመራሮች የህውሃትን ዓላማ ለማስፈጸም የቆሙ እንደነበር በመድረኩ ተሳታፊዎች በስፋት ተነግሯል፡፡
የሚዲያ አካላት እንዳይሳተፉ በተከለከለበት በዚህ ዝግ ስብሰባ፣ አቶ አለምነው መኮንንም እንደ አንድ አጀንዳ በመሆን ተነስቷል፡፡የቀድሞው ብአዴን ጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን የአማራውን ህዝብ በንቀት አንደበቱ በመሳደብ የሚታወቀውና አሁን የመለስ አካዳሚ ዳይሬክተር በመሆን በመስራት ላይ ያለው አለምነው መኮንን “የህውሃት ተላላኪ ነው!”በሚል በመድረኩ ተሳታፊዎች በስፋት ተኮንኗል፡፡ አቶ አለምነው በተለይ የወልቃይትን አማራ ማንነት ጉዳይ ለማዳፈን የህውሃት መንግስት በክልሉ ውስጥ የሚያደርጋቸውን እንቅሰቃሴዎች በመደገፍ ሲሰራ እንደነበር በማስረጃ በተደገፈ መልኩ በተሳታፊዎች ቀርቧል፡፡ ሌሎችም አመራሮች የህውሃትን ዓላማ ለማስፈጸም የማያንገራግሩ ፍጹም የህውሃትን የበላይነት አክብረው ስልጣናቸውን የሙጥኝ በማለት ህዝቡን የረሱ እንደነበሩ በመድረኩ ተሳታፊዎች በስፋት ተነግሯል፡፡
“የአማራ ክልል ህዝብ በሚከፍለው ግብር ልክ የልማቱ ተጠቃሚ አልነበረም” የሚል ቅሬታ በተነሳበት በዚህ ስብሰባ በክልሉ ህዝብ ቁጥር ልክ የሚበጀት በጀት እንዳልነበርና አብዛኛው የክልሉ ገቢ ወደ ትግራይ ክልል በመሄድ ክልሉን የመቀዬር ስራ እንደተሰራበት በግልጽ የታዬ ጉዳይ መሆኑን በድፍረት ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በነበረው አለመረጋጋት የመኖሪያ አካባቢያቸውን በፍርሃት በመልቀቅ ወደ ትግራይ ለሄዱ ተወላጆች “ተፈናቀሉ” በሚል ሰበብ የትግራይ ክልል መንግስት መኖሪያ ቤት የመስሪያ ቦታና መቋቋሚያ ገንዘብ መስጠቱን ያስታዎሱት የብአዴን አባላት፤ “ዛሬ ከቤሻንጉልና ኦሮሚያ ክልሎች በኃይል እየተፈናቀሉ ነፍሳቸውን ለማዳን የተሰደዱ ዜጎችን ቤተክርስቲያን እንዲጠለሉና ለምነው እንዲያድሩ መጣላቸው አግባብ ነዎይ?” በማለት ለአመራሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡”ሃገሪቱ ሁለት ዓይነት ዜጋ እንዲኖራት የፈቀዳችሁ አሁን በስልጣን ላይ ያላችሁና ቀደም ብለው የአማራውን ህዝብ እንወክላለን በማለት አመራር ሲሰጡ የነበሩ ባለስልጣናት የስራ ውጤት ነው” በማለት ተቃውሟቸውን ያሰሙት አባላቱ ተፈናቃዮች፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳይጠለሉ ከፍተኛ ውክቢያ በህውሃት ደጋፊና ተላላኪዎች ሲፈጸምባቸው እንደነበር አጋልጠዋል፡፡
መድረኩን ሲመሩ የነበሩ የብአዴን ከፍተኛ ባለስልጣናት በሰጡት መልስ “ህውሃት የአገዛዙን የበላይነት ወስዶ ነበር” የሚለውን የህዝብ ትችት እስከዛሬ ሲቃዎሙ ቢቆዩም ፣ትክክል እንደሆነ ማረጋገጣቸውን ለተሰብሳቢው አምነዋል፡፡
ህውሃት በትግራይ ክልል የተለዬ ስራ በመስራት የክልሉን በጀት በመዝረፍ ብቸኛ ተጠቃሚ እደነበረ ዘግይተው ማዎቃቸውንም ገልጸዋል፡፡ በሃገር አቀፍ ደረጃ ክልሎች በህዝብ ብዛታቸው ልክ ድርሻቸውን እንዳላገኙ የቀረበው ቅሬታ እምነታቸው መሆኑን የተናገሩት አመራር ፤ክልሎች ትክክለኛውን ድርሻ መውሰድ አለመውሰዳቸውን የሚያረጋግጥ አስራ ሶስት አባላት ያሉት ገለልተኛ ኮሚቴ ተቋቁሞ በምርመራ ላይ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

(ኢሳት ዜና ግንቦት 29 ቀን 2010 ዓ/ም)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.