እንኳንስ ያልተመረጠ የተመረጠ መንግሥት የሚወስነውን ጎጂ ውሳኔ መቃወም ተገቢ ነው!

አገሬ አዲስ
ግንቦት 30ቀን 2010ዓም(o7-06-2018)

አገር  የሕዝብ ንብረት ነው።በአገር ጉዳይ ላይ ወሳኙም ባለቤት የሆነው ሕዝቡ ነው።የአገርን ጥቅም በሚመለከት ጉዳይ ላይ ሕዝቡ ይወስን ሲባል ደግሞ ሁለት አይነት መንገዶች አሉ።አንደኛው በቀጥታ ሕዝቡ ድምጽ እንዲሰጥበት ሪፈረንደም የሚባለው  ሂደት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሕዝቡ ይወክለኛል ብሎ በመረጠውና አላፊነት በሰጠው መንግሥትና ፓርላማ የሚወሰን ይሆናል።ከዚህ ውጭ ሕዝብ ያልመረጠው መንግሥት ነኝ ባይ ቡድን ወይም ፓርላማ የሚል ጭንብል ያጠለቀ ስብስብ በምንም አይነት የአገር ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት መብት የለውም።ውሳኔ ቢሰጥም የጠና አይሆንም ።በማንኛውም ጊዜ ሊቀለበስ ይችላል።

በሰለጠኑትና በዴሞክራቲክ ስርዓት የሚመሩ አገሮች ይህንን አሠራር እንደ ባህል ይዘው ይሠሩበታል።እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የዴሞክራሲ ባህልና አሠራር የሌለባቸው አገሮች ደግሞ በጉልበትና በማጭበርበር ሥልጣኑን የያዙ ግለሰቦችና ቡድኖች የፈለጋቸውን ውሳኔ ሲሰጡ ማዬት የተለመደ ነው።ሕዝብ የሚያሳልፉትን ውሳኔ አድማጭ እንጂ ተካፋይ አይሆንም።ሊቃወምም የሚችልበት መንገድና መብት የለውም።ለመቃወም ቢነሳ በሃይል ይደፈጠጣል።

ሌላውን ትተን ባለፉት አርባ አምስት ዓመታት በአገር ጉዳዬች ላይ ሲወስኑ የኖሩት በሕዝቡ የተመረጡ ባለሥልጣኖች  ሳይሆኑ ሥልጣኑን በጉልበት ነጥቀው የአምባገነንነት ስርዓትን ያሰፈኑ ወንበዴዎች ነበሩ ፤አሁንም ናቸው። ይህንን አይነት ስርዓት በመቃወም ሕዝቡ ያላሰለሰ ትግል በማካሄድ ብዙ መስዋእት ከፍሏል።ለከፈለው መስዋእትነት ግን  አሁንም ያገኘው መልስ የሚመጥነው አይደለም።በብዙ መልኩም ከሳቱ ወደረመጡ ሆኖበታል።

አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሥልጣን ላይ የወጣው ቡድን ላለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት የቆየው የኢህአዴግ ስርዓት ሲውሸለሸል ለማጠናከር  የተፈጠረ ስልታዊ እርምጃ  እንጂ በዓላማ የተለዬና በሕዝብ ምርጫና ፍላጎት አላፊነት የተሰጠው ሕጋዊ አይደለም። እራሱ ጠ/ምኒስትሩ ለውጡ ከአንዳንድ የአሠራሮች የተሻገረ እንዳልሆነ በአደባባይ ገልጾታል።እሱ ለውጥ የለም ሲል ለውጥ አለ ብለው ላንቃቸው እስኪነቃ ድረስ የሚጮኹ፣ይህንን ቡድን እንደ ለውጥ ሃዋርያና ለተሻለ ስርዓት ፋና ወጊ አድርገው የሚቆጥሩ ግን  ጥቂቶች አይደሉም።

የታዬው  ለውጥ መሰረታዊ የሕዝብን ጥያቄ የሚመልስ ሳይሆን አሳሳችና እንዳለፉት ሁሉ የአገርን ጉዳይ በራሱ ፍላጎት የሚወስን የነባሩ ስርዓት አካል የሆነ ቡድን  መምጣቱ ነው።ስለሆነም አሁን በሥልጣን ላይ የወጣው ቡድን  በአገሪቱ ከፍተኛ ጉዳይ ላይ ምንም አይነት ውሳኔ የመስጠት መብት የለውም።በሚወስነው ውሳኔ ተጠያቂ ይሆናል።እንኳንስ ያልተመረጠ መንግሥት የተመረጠም መንግሥት ቢሆን አገር የሚጎዳ ውሳኔ ላሳልፍ ካለ ከጥያቄ ውስጥ ይገባል፤ከሥልጣኑም እስከመወገድ ይደርሳል።ምንም እንኳን በሕዝብ ቢመረጥም እንዳሻው ሊፈነጭ የማይችልበት ሕግ ስላለ ከተጠያቂነት አያመልጥም። ለሚወስደው እርምጃ በቅድሚያ የሕዝቡን በተለይም የፓርላማውን ይሁንታ ይጠይቃል እንጂ ብቻውን አገር ነክ ጉዳይ ላይ ሊወስን አይችልም።ያም ፓርላማ አሁን በኢሕአዴግ የተሰበሰበው የጎሳ ስብስብ ሳይሆን በሕዝቡ ነጻ ተሳትፎና ምርጫ፣ ችሎታና ራዕይ ያላቸው ግለሰቦች ወይም የድርጅት ተወካዮች ተመርጠው አላፊነቱን የተረከቡበት ሕጋዊነት ያለው አካል ብቻ ነው።

ኢሕአዴግ የተባለው የጎሳ ስብስብ በቅርቡ የመሰረተው በኦሕዴድ ድርጅት መሪ በዶር አብይ አህመድ የሚመራው መንግሥት ተብዬው ቡድን ለሕዝብ ጆሮ የሚጥሙ ዲስኩሮችንና አንዳንድ እርምጃዎችን በመውሰድ ካማለለ በዃላ አሁን ወደ ተፈጥሮ ባህርዩ በመመለስ ኢትዮጵያን የሚጎዳና የሚያፈራርስ ሥራ በመሥራት ላይ ተሰማርቷል።  የኢትዮጵያ ሕዝብ በደምና በአጥንቱ  ያስከበረውን የኤርትራን ክፍለሃገር ከሃያ አምስት ዓመት በፊት እንደ ነጻ አገር እውቅና ሰጥቶ  ማስገንጠሉ ሳያንሰው  አሁን ደግሞ ፣ከሃያ ዓመት በፊት ከሰባ ሽህ በላይ ህይወት የተገበረበትን ባድመ የተባለውን ያገራችንን ክፍል  ለሻእብያ ወንበዴ መንግሥት አሳልፎ ለመስጠት ወስኗል።ከዚህ የመሬት አሳልፎ መስጠት ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችለው ችግር እብሪተኛው ኢሳያስ አፈወርቂ ከዚህ በፊት አቅርቦት የነበረው የካሳ ይከፈለኝ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን እንደወራሪ የሚያደርግ የይቅርታ ትበል ጥያቄም መነሳቱ  እንደማይቀር ነው።ያ ደግሞ ከሆነ ኢትዮጵያ ከማትወጣው የካሳ ክፍያ ግዴታ ከመግባቷም በተጨማሪ  በወራሪነት በእራሷ ምስክርነት በታሪኳ ላይ ጥቁር ነጥብ የሚያስቀምጥባት ውሳኔ ይሆናል።ይህንን የመሰለ ውሳኔ የአገር ክህደት ብቻ ሳይሆን ኤርትራን ማስገንጠሉና እውቅና መስጠቱ በኢትዮጵያ ሕዝብና በኤርትራ ተወላጆች ነጻ ውሳኔ የተደመደመ ጥያቄ ያስመስለዋል።የኢትዮጵያ ሕዝብም ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምነው የኤርትራ ተወላጅ ፍላጎቱን በነጻ እንዳይገልጽና ድምጽ እንዳይሰጥበት በማፈን የተደረገውን ደባ የሚክድ  ነው።ምንም እንኳን የወያኔ ኢሕአዴግ መንግሥት ከሁሉም አገሮች ቀድሞ እውቅና ቢሰጥም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እውቅና አለመስጠት ብቻ ሳይሆን የይገባኛል ጥያቄ የማንሳትም መብት አለው።

የሌሎች አገሮችን ተመሳሳይ ጥያቄ ብንመለከትና የቻይናዎቹን እንደምሳሌ ብንጠቅስ፣

በቻይና በ1948-49 በማኦ ሴዱንግ የሚመራው የኮሚኒስት ፓርቲው ትግል ድል በማድረጉ የተነሳ ጸረ ኮሚኒስት የነበረው በጄነራል ሻንጋይሸክ የሚመራው የኮሚንታንግ ፓርቲ ከመሃል ቻይና አስተዳደር ገንጥሎ የታይዋንን ደሴታማ ግዛት በመያዝ  እራሱን የነጻ አገር መንግሥት አድርጎ ሰየመ።የዚያ አፈንጋጭ ሃይል እርዝራዥ የሆነው እስከአሁን ድረስ ከውጭ ጸረ ኮሚኒስት ከሆኑት ሃይሎች በሚያገኘው ድጋፍና እርዳታ ድንበሩን ዘግቶ ይኖራል።በቻይና መንግሥትና ሕዝብ ዘንድ ግን እውቅና አላገኘም።የጠፋችው በግ ወይም ግዛት በሚል ስያሜ የማቀላቀሉ ዘመቻ ሲካሄድ ኖሯል።አሁን የመደበኛዋ ቻይና እድገት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበረና ወሳኝ ሲሆን  ታይዋን ከውጭ ታገኝ የነበረው ድጋፍና ትኩረት እየቀነሰ ፤ ሕዝቡም ወደ እናት አገሩ ለመመለስ እየዳዳው መጥቷል።የጊዜ ጉዳይ እንጂ መቀላቀላቸው አይቀርም።ምንም ጊዜ ቢሆን ሕዝብ የጠንካራና የሃብታም አገር ዜጋ መሆንን ይመርጣል እንጂ የደሃና የትንሽ አገር ዜግነትን አይመርጥም።እንኳንስ ለዜግነት ለስደትም የተሻለ አገር ይመረጣል። ጠንካራ ሕዝብና መሪ ያለው አገር እንኳንስ የራሱን የሌላውንም ለማግኘት የሚያግደው የለም።የእስራኤሎቹንና በቅርቡም የራሽያ በኡክሬን ወደብ በክሪም ላይ የወሰዱት እርምጃ ከጥንካሬ ጋር ለተያያዘ ውጤት ማስረጃ ነው።በዓለም ፖለቲካ ወሳኙ ፍትሕ ሳይሆን ሃይል ነው። በተለይም የኤኮኖሚ አቅም ያለው አገር የጦር ሃይል ያለውን አገር ለማንበርከክ እንደሚችል አንዳንድ የአረብ ባለጸጋ አገሮችን በምሳሌ ማስቀመጥ ይቻላል።ወርቅ የተጫነች አህያ የማታስከፍተው ወይም የማትሰብረው ምሽግ አይኖርምና።እኛ ግን ሃይላችን የሚፈቅድልንን ሳይሆን ታሪካችን የሚመሰክርልንን መብታችንን የመጠዬቅ መብት እንዳለን ልንረዳ ይገባል።እኛም አንድነታችንን ካጠናከርን፣የዴሞክራቲክ ስርዓት ለማስፈን ከቻልን የማንደርስበት ደረጃ አይኖርም። ሰላም ሲሰፍን እድገታችን ይፋጠናል፣የሕዝቡ ኑሮም ይሻሻላል።ያ ሲሆን ደግሞ ከውርደት ተላቀን የተከበርን እንሆናለን።እንኳንስ የነበረንን ያልነበረንንም በሃይል ሳይሆን በመልካም አስተዳደር ለመሳብ እንችላለን።የራቁን ይቀርቡናል።

አሁን በሥልጣን ላይ የተቀመጠው ቡድን ብዙ ሕዝብ ያለቀበትን የባድመን መሬት ለመስጠት ያሳለፈው ውሳኔ በኢሳያስ አፈወርቂ ተቀባይ አልሆነም፤በሱ አባባል መቀሌንም ቢሰጡን ወያኔን የማሶገዱን  አቋማችችን አንለውጥም ብሏል።ከዚያም አልፎ በኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝባዊ መንግሥት እንዲመረጥ ያለውን ፍላጎት ገልጿል።በዚህ አባባሉ ለኢትዮጵያ ያሰበ መስሎ ለእሱና ለእሱ መንግሥት እውቅና የሰጡትና በሥሩ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ነን ባይ ቡድኖች ሥልጣኑን ቢይዙና የሚፈልገውን ጥቅም ቢያስከብሩለት መምረጡን የሚያመላክት ነው።እስከአሁን ድረስ አጥቶት ላልጎዳው የባድሜ ደረቅ መሬት ወይም ምንም ከሌላት ትግራይ ጋር ከመወዳጀት ሰፊና ብዙ ሃብት ያላትን ኢትዮጵያን የሚበዘብዝበት ዕድል ካገኘ ይመርጣል።ወትሮም ከወያኔ ጋር ግብግብ ያስገባው ኢትዮጵያን የመዝረፉ ፉክክርና የድርሻ ክፍፍሉ ነበር።

የዶር አህመድ ቡድን በተጨማሪ  ኢትዮጵያ በኤኮኖሚውም ዘርፍ የምትዳከምበትና ጥገኛ የምትሆንበትን መንገድ በመጥረግ ላይ ነው። የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት በሚል ሽፋን፣እንዲሁም በቴክኒዎሎጂ ተቋማትን ማሳደግ በሚል ሰበብ፣ በአገሪቱ ቅርስና በሕዝቡ ድካም የተገነቡትን ተቋማት በተለይም አትራፊና አገራዊ  አኩሪ ምልክት የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባቡር መስመር፣የማሪታይምና የመሳሰሉትን ብሔራዊ ንብረቶች ለውጭና ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች ለመሸጥ ሕዝብና ፓርላማ ያልወሰነበትን ውሳኔ አስተላልፏል።በዚህ ውሳኔ አገርና ሕዝብ የሚጠቀም ሳይሆን የበለጠ ጉዳት ይደርስበታል።በቅድሚያ የዚህ ውሳኔ ዓላማ አገሪቱን ለማራቆትና የቀራትን ሻሽጦ ጠራርጎ ለመውሰድ ወያኔዎቹ ያቀዱት ነው።በመሸጥና በባለቤትነት ተጠቃሚ የሚሆኑት እነዚሁ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በዘረፋ ሃብት ያከማቹት የወያኔ ቡድን አባላት ናቸው።በሽርክናው የውጭ አገር ባለሃብቶችና ኩባንያዎችም ቢሳተፉበት የሚያገኙትን ጥቅምና ትርፍ ወደ አገራቸው የማስኮብለል እንጂ መልሰው በአገር ውስጥ እንቅስቃሴ አያውሉትም።በተለይም የአየር መንገዱና ከፍተኛ የቴክኒክ ሙያ የሚጠይቅባቸው ስራዎች ለተመሳሳይ የውጭ አገር ኩባንያዎች ከተሸጡ  በኢትዮጵያ ሊሰራ የሚችለውን ሥራ ወደ አገራቸው በመውሰድ ተጨማሪ ገቢ ከማግኘታቸውም በላይ ለአገራቸው ሕዝብ ሥራ ሲፈጥሩ አገራችን የእውቀትና የባለሙያ ደሃ እንድትሆን ያደርጓታል።የኢትዮጵያ አየር መንገድን ሙሉ ለሙሉም ሆነ በከፊል ለመግዛት ሙከራ ያደረጉ አገሮች እንዳሉ አይካድም።አሁንም የዚህ ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑ መጠርጠር አያቅትም።ባለሃብቶች ትርፍ ለማግበስበስ ሲሉ ሠራተኛ ይቀንሳሉ፣ዋጋ ይጨምራሉ።በዚህም እርምጃ አገር በድሃና በሥራ አጥ ትጥለቀለቃለች።ያ ደግሞ ለሰላሟና ላንድነቷ አደጋ ነው።የውጭ ባለሃብቶች የሚፈልጉትን ያህል ትርፍ ካላገኙ ከተወሰነ ጊዜ በዃላ የሚይዙትን ይዘው ተቋሙን አሽመድምደውት ወደመጡበት ይመለሳሉ።በዚህ  አንድ ተፎካካሪ አየር መንገድ ከጨዋታው ውጭ ይሆናል ማለት ነው።ያንን የተሽመደመደ ተቋም መልሶ ለማቋቋም ደግሞ ከባድ ይሆናል።ከሃብታም አገሮች ከስዊስ ፣ከቤልጅዬም፣ከጣልያን…ወዘተ አየር መንገዶች ውድቀት መማር ይቻላል።የሆላንዱም ኬ ኤል ኤም ከፈረንሳይ አየር መንገድ ኤርፍራንስ ጋር ያደረገው ሽርክና በመኖርና ባለመኖር ዥዋዥዌ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።

እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት ቁም ነገር የአገር ባለሃብቶች ተብለው የሚቆጠሩት አብዛኛዎቹ አሁንም የስልጣኑ ባለቤት በሆነው ኢሕአዴግ በተባለው ጃንጥላ ስር ሆነው ሲዘርፉ የኖሩት ግለሰቦች መሆናቸው ነው።እነሱም ቢሆኑ አገራቸው ኪሳቸው እንጂ ኢትዮጵያ አይደለችም።ለአገር የሚያስብ መንግሥት የተዘረፉትን የአገር ሃብቶች ያስመልሳል እንጂ ለተጨማሪ ዘረፋ በር አይከፍትም።ይህ የግል ባለቤትነት (Private ownership) ዘራፊዎች እስከዛሬ ድረስ በሕገወጥ መንገድ የሰበሰቡትን ገንዘብ ሕጋዊ ከማድረጉም በላይ ወደ ውጭ በድብቅ የሚያሻግሩትን ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ እንዲያደርጉት ይፈቅድላቸዋል።

ነገ ደግሞ የቤት ሠራተኛና የጉልት ተዳዳሪ ሳይቀሩ በግዳጅ ባዋጡት ፣በሕዝቡና ባገሪቱ ስም በተገኘ ብድርና እርዳታ የተገነባው የህዳሴ ግድብና ውጤቱ ለአገር ውስጥ ጥቅም ሳይውል ለሱዳንና ለግብጽ መሸጡ በይፋ ሳይነገረን አይቀርም።ኢትዮጵያን  የማፈራረሱ ሂደት ከቀጠለ  የኦጋዴ መሬት ለሶማሊያ ፣የቦረና ነገሌ መሬት ለኬንያ፣የአፋር መሬት ለጅቡቲ፣የጋምቤላ መሬት ለደቡብ ሱዳን አሳልፎ መስጠቱ አይቀርምና ይህንን በራሱ ወሳኝ የሆነ የወያኔ/ኢሕአዴግ ተወካይ መንግሥት በቃህ!ባገራችን ህልውና ላይ የመወሰን መብት የለህም ልንለው፣ የሥልጣን ገደቡን(ወሰኑን) አያውቅምና ልናሰምርለት ይገባል።

በዶር አብይ አህመድ የሚመራው የኢሕአዴግ መንግሥት አላፊነት የሚሰማው ከሆነ በሕዝብ በተመረጠ መንግሥት እስኪተካ ድረስ ለዚያ መዳረሻ የሚሆነውን ዝግጅት የማመቻቸትና ያለውን ያገሪቱን ሃብትና ንብረት እንዳይባክን፣ዳር ድንበር እንዳይደፈርና ሕዝቡም በኖረበት ቦታ ሳይፈናቀል የመኖር መብቱ እንዲከበር ከማድረግ ውጭ ሌላ ተልእኮና ሥልጣን ሊኖረው አይገባም።

ይህ መንግሥትና መሪው ለአገሪቱ አንድነት፣ ለሕዝቡም ሰላም የሚያስብ ከሆነ ስለ ፍቅር ባዶ ዲስኩር ከማሰማት ይልቅ ፤የጎሰኞችን የክልል መስፋፋት፣የሕዝቡን መፈናቀል በሕግና በሃይል በማስቆም ሥራ ላይ ቢያተኩር ይመረጣል፤የሕዝቡንም አመኔታ ሊያገኝ ይችላል።ከፋፋይና ጸረ አንድነት የሆነ የጎሳን የበላይነት የሚያስከብር ሕገመንግሥት ይዞ፣በዚያም ሕግ በሕዝብ ላይ ግፍ እየተሠራ እያዩ  ስለ ኢትዮጵያ አንድነት፣ሰለ ሰላምና እድገት ማውራት ቀርቶ ማሰብ አይቻልም። ሕዝብ እየተፈናቀለና እየተገደለ ፣ያገር ውስጥ የክፍላተሃገር ወሰን እየተናደ፣ጎሳ ተኮር የድንበር መስፋፋትና ግጭት በሚካሄድበት ሁኔታ ድምጽን አጥፍቶ ለኤርትራ ድንበር ቅድሚያ መስጠት ከፈረሱ በፊት ካሮሳውን እንደማስቀደም ይቆጠራል።ለቤት ቀጋ ለውጭ አልጋ እንደሚሉት የታይታ ሥራ ነው።

ኢትዮጵያ የታመቀ ሃይል፣የሰው ጉልበት፣ገንዘብና እውቀት ያለው ዜጋ  አላጣችም ።ያጣችው እነዚህ እሴቶች በነጻነትና በዕቅድ ሊንቀሳቀሱበት የሚያስችል አገር ወዳድ  ስርዓት ነው። አሁን ያለው ሕዝብን በጎሳና በክልል ከፋፍሎ ሃይልን የሚያመናምን፣አገርን ለማፈራረስ ዓላማ ያለው ስርዓት ሲወገድ፣ በሁሉም መስክ ችሎታና አቅም ያለው ኢትዮጵያዊ አገር ወዳድ አገሩን ለመገንባት በሚደረገው እርብርቦሽ ለመሳተፍ አያቅማማም።ሳይጠየቅ በራሱ አነሳሽነት ሆ ብሎ ይመጣል።ያን ጊዜ ዘላቂ እድገትና ሰላም እውን ይሆናል።

በኢትዮጵያ ጉዳይና ንብረት ላይ ሕዝብ እንጂ ያልተመረጠ መንግሥት አይወስንም!

ለመጣ ለሄደው ማጨብጨቡን ትተን የኢትዮጵያ ሕዝብ የመብቱና ያገሩ  ባለቤት ለሚሆንበት ትግል እንነሳ!!

ኢትዮጵያ በአንድነትና በነጻነት ለዘላለም ትኑር!!!

አገሬ አዲስ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.