በጎይትኦም ያይኑ ሰብአዊ መብታችን ተጥሷል ያሉ የአ/አበባ ሀ/ስብከት ካህናትና ሠራተኞች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጣልቃ ገብነት ጠየቁ

ሐራ ዘተዋሕዶ

  • ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነላቸውን፣የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ተፈጻሚ አላደረጉም
  • የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ወደ ሥራቸው አልመለሷቸውም
  • የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት፣ አቤት ባዮቹን እያነጋገረ ነው፤ ለዛሬም ቀጥሯቸዋል
  • “ጉዳዩ እየተበላሸና እየከበደ መጥቷል፤”ያሉት ፓትርያርኩ አጣሪ አካል ያቋቁማሉ
  • ቋሚ ሲኖዶስ በዛሬ ስብስባው፣ አጣሪውን አካል ሳይሠይም እንደማይቀር ተጠቆመ

†††

Pat Abune Mathias vs Goitom

በጉቦኛነትና ጎሠኝነት ላይ ባተኮረ የቅጥር፣ የዕድገትና የዝውውር አፈጻጸም ችግሮች ሳቢያ እየታመሰ በሚገኘው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አመራር ላይ በሚቀርቡ አቤቱታዎች ጫና የበዛባቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ “ጉዳዩ እየተበላሸና እየከበደ መምጣቱን” ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ረቡዕ በተካሔደው የቋሚ ሲኖዶሱ ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባ ማጠናቀቂያ ላይ፣ ሁከቱ በየቀኑ እየበዛ መኾኑን የጠቆሙት ቅዱስነታቸው፣ “አያያዙ[የሥራ አስኪያጁ ጎይትኦም ያይኑ] አላማረኝም፤” ብለዋል፡፡ መንግሥትም ከሚደርሱት አቤቱታዎች በመነሣት መፍትሔ እንዲሰጥ ማሳሰቡን አስታውቀዋል፡፡ ከሩስያ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መልስ አጣሪ አካል በማቋቋም ኹነኛ መፍትሔ እንደሚሰጡ ቢጠቁሙም እስከ አሁን ተግባራዊ ሳያደርጉት ሰንብተዋል፡፡ በዛሬ ዐርብ፣ የቋሚ ሲኖዶስ ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባ፣ የሚያቋቁሙት አጣሪ አካል ሊሠየም እንደሚችል ተነግሯል፡፡
በሌላ በኩል፣ አቤት ባዮቹ ዳኝነትና መፍትሔ ፍለጋቸውን ያላቋረጡ ሲኾን፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፖስታ ቤት በኩል የላኩት አቤቱታ ደርሶ፣ ካለፈው ሳምንት ዐርብ ጀምሮ ጽ/ቤታቸው እያነጋገራቸው እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ከባለጉዳዮቹ መካከል ከሐምሌ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ለእንባ ጠባቂ ተቋምና ለፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር አቤቱታ ሲያሰሙ የቆዩ አስተዳዳሪዎች፣ ካህናትና ሠራተኞች እንደሚገኙበት ተጠቅሷል፡፡
አቤቱታቸው ኹለት ነጥቦችን የያዘ ሲኾን፤ የመጀመሪያው፡- ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በፌዴራል ጠቅላይ ሰበር ሰሚ ፍ/ቤት በተሰጠ የሕግ ትርጉም፣ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ ቀዳሾችና አወዳሾች በመንፈሳዊ ፍ/ቤት እንጅ በመደበኛ ፍ/ቤት ጉዳያቸው እንዳይታይ(እንዳይከሡ) መዘጋቱ ነው፡፡ ይህም፣ ሰዎች ኹሉ በሕግ ፊት እኩል እንደኾኑ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 የተደነገገውን የሚጥስ በመኾኑ ገደቡ ተነሥቶላቸው መብታቸውን በመደበኛ ፍ/ቤት ከሠው ማስከበር እንዲችሉ ጠይቀዋል፡፡ ለዚህም ያነሣሣቸው፣ ቤተ ክርስቲያን በምታስተዳድራቸው ካህናትና ሠራተኞች ላይ ባላት የዳኝነት ሥልጣንና በደረሰባቸው አስተዳደራዊ በደል ላቀረቡት ቅሬታ ፍትሐዊ ውሳኔ ቢሰጣቸውም፣በአፈጻጸም መብታቸው በመጣሱ መኾኑን አስረድተዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያንን በበላይነት የሚመራት ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በቋሚ ሲኖዶስ አማካይነት ከወራት በፊት የወሰነላቸው ውሳኔ በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ማናለብኝነት እንዳልተፈጸመላቸው በማስታወስ፣ ገቢራዊነቱን መከታተል የሚጠበቅባቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተፈጻሚ ያደርጉላቸው ዘንድ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጣልቃ ገብነት ለጽ/ቤታቸው ባቀረቡት አቤቱታቸው ጠይቀዋል፡፡
 የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፥ ችግሩን እቀርፍበታለሁ ያለውን የቅጥር፣ የዕድገት፣ የዝውውርና የዲስፕሊን ደንቦችን ዝግጅት እያጠናቀቀ መኾኑ ተሰምቷል፡፡ኾኖም የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችን በተመለከተ የመወሰን ሙሉና የመጨረሻ ሥልጣን ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ እስከኾነ ድረስ፣ ከሁሉ በፊት ውሳኔውን ማስፈጸም ይኖርበታል፡፡አቤቱታ አቅራቢዎቹን ወደ ሥራ በመመለስ ረገድ(የውዝፍ ደመወዝና ጥቅማጥቅም አከፋፈሉና ምደባው)፣ ለአፈጻጸም የሚያዳግቱ ጉዳዮች ቢኖሩት እንኳ ማብራሪያ መጠየቅ እንጅ የተፈረደላቸውን ሓላፊዎች፣ ካህናትና ሠራተኞች፣ ፍትሕ በማዘግየት ወደ ሌላ አካል መግፋቱ፣ በቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ የአሠራር ነጻነትና ልዕልና ላይ ጥያቄ የሚያስነሣ በመኾኑ ስሕተቱ የከፋ ይኾናል፡፡

ውዝፍ ደመወዛችን ተከፍሎን ወደ ሥራችን እንድንመለስ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንም ማስጠንቀቂያ የሰጠ ቢኾንም፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ውሳኔውን ተፈጻሚ ባለማድረጋቸው ሰብአዊ መብታችን እየተጣሰ ነው፤ ያሉ ስድስት የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናትና ሠራተኞች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጣልቃ ገብነት ጠየቁ፡፡
Copy of plea to pm office
በተለያዩ አድባራት የሚሠሩ ሦስት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ሦስት ካህናትና ሠራተኞች፣ ባለፈው ሰኞ ግንቦት 23 ቀን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ባቀረቡት አቤቱታ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛው ወሳኝና ሕግ አውጭ አካል የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ውዝፍ ደመወዛቸው ተከፍሏቸው ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ ያሳለፈው ውሳኔ በቅዱስ ፓትርያርኩ በኩል እንዲፈጸምላቸው ይደረግ ዘንድ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ድጋፍ ጠይቀዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔውን የሰጠው፣ ከአንድ ወር በፊት፣ ሚያዝያ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ባደረገው የቋሚ ሲኖዶስ ስብሰባ እንደኾነ የገለጹት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መ/ር ጎይትኦም ያይኑ ግን፣ “ውሳኔውን ወደ ጎን በመተውና ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም ተፈጻሚ ባለማድረጋቸው” ከነቤተ ሰዎቻቸው ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው እንዳለ ተናግረዋል፡፡

የጉዳዩ መነሻ፣ ሀገረ ስብከቱ በአቤቱታ አቅራቢዎቹ ላይ ያሳለፈውን ከሥራና ደመወዝ የማገድ፣ የማሰናበትና የማዛወር ውሳኔ በመቃወም በመንፈሳዊ ፍ/ቤት የቀረበ አቤቱታ መኾኑ ተገልጿል፡፡ መንፈሳዊ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ፣ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ውዝፍ ደመወዛቸው ተከፍሏቸው ወደየሥራቸው እንዲመለሱ፣ በአስተዳዳሪነት ሓላፊነት ያሉትንም ለፓትርያርኩ አስቀርቦ እንዲያስመድብ ወስኖላቸዋል፡፡ ሀገረ ስብከቱ በውሳኔው ላይ ይግባኝ ቢጠይቅም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት የሀገረ ስብከቱን መንፈሳዊ ፍ/ቤት ውሳኔ አጽንቶታል፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት፣ ከፍተኛው መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ሕግ አውጭና ወሳኝ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ እንደመኾኑ፣ ሀገረ ስብከቱ የይግባኝ አቤቱታውን የቅዱስ ሲኖዶሱ አስፈጻሚ አካል ለኾነው ቋሚ ሲኖዶስ አቅርቧል፡፡

እነመጋቤ ሃይማኖት መንግሥቱ ድረስ በሚል ማኅደር፣ በሀገረ ስብከቱ መንፈሳዊ ፍ/ቤት የቀረበውን የስድስት ካህናትና ሠራተኞች ክሥ እንዲሁም የሀገረ ስብከቱን የይግባኝ አቤቱታ፣ ባለፈው ጥር ወር በሠየመው ኮሚቴ አማካይነት ሲያጠና የቆየው ቋሚ ሲኖዶስ፣ ሚያዝያ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ፣ በፓትርያርኩ ማስታወሻ ተደግፎ የቀረበለትን የኮሚቴውን የሕግ አስተያየትና የውሳኔ ሐሳብ በመመርመር ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በዚህም መሠረት፦ መጋቤ ሃይማኖት መንግሥቱ ድረስ፣ መልአከ ገነት አባ ሀብተ ማርያም ቦጋለ እና መልአከ መዊዕ አባ ኃይለ ሥላሴ ገብረ ጊዮርጊስ የተባሉት ሦስቱ የአድባራት አለቆች፣ ውዝፍ ደመወዛቸው ተከፍሎ ወደ አስተዳዳሪነት ሥራቸው እንዲመለሱ ወስኖላቸዋል፡፡
በተመሳሳይ ኹኔታ፥ ከሥራና ከደመወዝ የታገዱበት ምክንያት በፍ/ቤት ታይቶ በነጻ የተሰናበቱት ዲያቆን ዘውገ ገብረ ሥላሴ እና አላግባብ እንዲሰናበቱ የተደረጉት መሪጌታ ዳንኤል አድጎ እንዲሁም ወደ ሌላ ደብር መዛወራቸውን የተቃወሙት መ/ር መሣፍንት ተሾመ በዲቁና ሲያገለግሉበት ወደነበረው ካቴድራል ውዝፍ ደመወዛቸው፣ የበዓል ቦነሳቸውና ወጪና ኪሳራቸው ተከፍሏቸው እንዲመለሱ የሀገረ ስብከቱ መንፈሳዊ ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ እንዲፈጸምላቸው ቋሚ ሲኖዶሱ ወስኖላቸዋል፡፡
Copy of Holy Synod on A.A dio1
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የውሳኔውን ቃለ ጉባኤ በማያያዝ፣ ሀገረ ስብከቱ እንደ ውሳኔው አግባብ እንዲስፈጽም ሚያዝያ 18 ቀን በጻፈው ደብዳቤ ትእዛዝ መስጠቱንና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንም ውሳኔው ተግባራዊ እንዲኾን ማስጠንቀቁን የጠቆሙት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ ሥራ አስኪያጁ ግን፣“በማናለብኝነት ተፈጻሚ አለማድረጋቸውን”ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ባቀረቡት አቤቱታ አስታውቀዋል፡፡ “በእኛም ኾነ በሥራችን በምናስተዳድራቸው ቤተሰዎቻችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱብን ነው፤” በማለት ምሬታቸው የገለጹ ሲኾን፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳለፈው ውሳኔ በፓትርያርኩ እንዲፈጸም ጽ/ቤቱ ጣልቃ ገብቶ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡
አቤቱታው በፖስታ ቤት በኩል የደረሰው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት፣ ባለፈው ሰኞ ግንቦት 27 ቀን ጠርቶ እንዳነጋገራቸውና ማብራሪያም እንደጠየቃቸው የጠቀሱት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ ለዛሬ ዐርብ እንደቀጠራቸውና ስለጉዳዩ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ ሊመክርበት እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ “የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ በማስፈጸም አልያም በሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ ማስጠንቀቂያ መሠረት ሀገረ ስብከቱን በሕግ ተጠያቂ በማድረግ ለከፋ እንግልት የተጋለጠንበት ችግር እልባት ያገኛል ብለን እንጠብቃለን፤” በማለት ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡
ቋሚ ሲኖዶሱ የይግባኝ አቤቱታውን እየመረመረ በነበረበት ወቅት ስለጉዳዩ በአዲስ አድማስ የተጠየቁት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መ/ር ጎይትኦም ያይኑ በሰጡት ምላሽ፣ “ደረጃውን ጠብቀን ነው የምንሔደው፤ መንፈሳዊ ፍ/ቤቱ ወስኖልን ተግባራዊ አልኾነልንም የሚሉ ሰዎች፣ ቋሚ ሲኖዶሱ ይመለሱ ብሎ ከወሰነ የማይመለሱበት ምክንያት የለም፤” ብለው ነበር፡፡ በመታየት ላይ ያሉ ጉዳዮች ውጤት ሳይታወቅ ምደባዎች ተደርበው ስለሚሰጡበት ኹኔታም፣ “ይኼ ሊኾን የማይችል ነው፤ እኛ ሕጋዊ መሥመሩን ተከትለን፣ የስንብት ደብዳቤ ጽፈን ከለቀቁ በኋላ ነው ሠራተኛ የምንመድበው፤” የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት፡፡
ሥራ አስኪያጁ ይህን ይበሉ እንጅ፣ ከአቤቱታ አቅራቢዎቹ መካከል፣ መጋቤ ሃይማኖት መንግሥቱ ድረስ ከቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ በኋላ ቀደም ሲል በነበሩበትና ጥፋታቸው በማስረጃ ሳይረጋገጥ ከተነሡነበት ደብር ውጭ በእልቅና ቢመደቡም፣ ደብሩ ሙሉ ደመወዛቸውን ለመክፈል እንደማይችል አስታውቋቸዋል፤ በተመሳሳይ ኹኔታ መልአከ ገነት አባ ኃይለ ማርያም ቦጋለ፣ እገዳቸው ታይቶ ቢነሣላቸውም፣ በቦታቸው ላይ ሌላ አስተዳዳሪ በመመደቡ እየተጉላሉ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
Advertisements

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.