የቅማንት ክልል መመሥረትን በሶስት መንገዶች . . .  – አንዱዓለም ተፈራ

ሰኞ፣ መጋቢት ፳ ፩ ቀን፣ ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህረት

አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ

ጎንደር የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ፤ ከጓደኞቼ መካከል ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ። አንድ ላይ የዘጠነኛ፣ የአስረኛና የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪዎች ነበርን። ግንብነህ አየለና አምባቸው አየለ ይባላሉ። በተለይ እሁድ እሁድ ማታ፤ ከዚያች በዚያ ወቅት ከነበረችው አንዲቷ ሲኒማ ቤት፤ ሲኒማ ጎንደር፤ የሚታዩትን ሲኒማዎች ለማየት፤ ከግማሽ ሰዓት በፊት ከአምባቸው አየለ ጋር ቆመን፤ ( ሁለት ሜዟችንን -> አንድ ሽልንግ -> ሃምሳ ሳንቲም፤ በኪሳችን ቋጥረን ) የሲኒማውን ማስታወቂያ ስዕሎችና ፎቶግራፎች እያየን፤ ከፎቁ ላይ የሚንቆረቆረውን የሬይ ቻርልስ “ኖ ሞር ኖ ሞር ጃክ” እየሰማን ስንጠብቅ ትዝ ይለኛል። ቀን ላይ፤ ሸጋዎቹ የዞብልና ባላጋራቸው የአፍሪቃ ቡድን እያለፉ ሌሎች ሲተኩ፤ እኒሁኑ ተተኪ ቡድኖች ሲጫወቱ ለማየት፤ ፋሲለደስ የእግር ኳስ ሜዳ ስለምንሄድ፤ የቀኑን ሲኒማ እናልፈዋለን። እኒህ ወንድማማቾች የመጡት ከጭልጋ ነው። እኔ ደግሞ ከአዘዞ ነኝ። ለመጨረሻ ጊዜ ግንብነህን ያገኘሁት፤ አሜሪካ፤ የዛሬ ሃያ ሶስት ዓመት፤ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ቅንጅትን (ኢዴኃቅ) ለመመሥረት፤ እሱ ከሳንፍራንሲስኮ እኔ ደግሞ ከሳክራሜንቶ ተወክለን ዋሺንግተን ዲ. ሲ. በሄድንበት ጊዜ ነበር። በዚያ ቦታ የጎንደር ልማት ማኅበርን መሥርተን፤ በዋሺንግተን ዲ. ሲ. ማኅበሩ ሲመዘገብ፤ ከአስመዝጋቢ አስራ አንድ ሰዎች፤ ግንብነህና እኔ ሁለቱ ሆነን ፈርመናል።

የነግንብነህ አባት ፊታውራሪ አየለ አባ ጓዴ ይባላሉ። እሳቸው በኋላ የጭልጋ አውራጃ አስተዳዳሪ የሆኑ፤ ጥሩ ጀግና ነበሩ። በመጨረሻ ቀኖቻቸው፤ በስደት ታመው በነበሩበት ሥፍራ ነበርኩና፤ ተመላልሼ ጠይቄያቸው፤ በቀብር ስነ-ሥርዓታቸውም ላይ ተገኝቻለሁ። ፊታውራሪ አየለ አባ ጓዴ በአባታቸው ከቅማንት ሲወለዱ፤ በናታቸው የአማራ ተወላጅ ናቸው። ሁለቱ ጓደኞቼ ልጆቻቸው፤ አባታቸው የአማራ ሴት አግብተው፤ ከአማራ እናታቸው የተወለዱ ስለሆነ፤ የቅማንት ወገንነታቸው ወደ ሩብ ወርዷል። አሁን የቅማንትን ጉዳይ በቀንደኝነት ከሚያቀነቅኑት መካከል፤ ዘመነ ካሠኝ፤ አማራ ሚስት አግብተው ወላልደዋል። አባታቸው ካሠኝ ዓለማየሁም ከአማራ ሴት ወላልደዋል። ይኼን ያነሳሁበት ምክንያት አለኝ። ምክንያቴም፤ አሁን በአማራና በቅማንት መካከል ልዩነት በመፍጠር የሚደረገው ሩጫ፤ በታወቁ የአማራና የቅማንት ቤተሰብ ላይ ምን ያህል ችግር እንደሚፈጥር በማሳየት፤ በአካባቢው ተወላጆች የማያባራ ግጭት የሚፈጥርና መፍትሔ የለሽ ዘለዓለማዊ ቁርሾ መሆኑን ለመግለጽ ነው። በርግጥ ለኔ፤ ቅማንትን ከአማራ የሚለየው ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ የለኝም።

ግንብነህ ከቅማንትነቱ ይልቅ አማራነቱ በሶስት እጅ ያደላል። አባቱ፤ ምንም እንኳ የቅማንት ትውልዳቸውና የአማራ ትውልዳቸው እኩል ቢሆንም፤ ለቅማንት ተወላጆች መኩሪያ ናቸው። ጀግንነታቸውን ማንኛችንም ብንሆን ልንጠይቀው የምንችል አይደለም። አማራ ናቸው ወይንስ ቅማንት? ስንል ደግሞ ጥያቄው ይከብዳል። ግንብነህ አብሮኝ የጎንደር ልማት ማኅበርን ለማቋቋም ይሯሯጥ እንደነበር፤ የጎንደር ልማት የመመዝገቢያ ሰንዱን በማገላበጥ ማግኘት ይቻላል። አሁንም በቅማንትና በአማራ መካከል የሚደረገውን የመከፋፈል አባዜ በመቃወም የቆሙ ብዙ፣ እጅግ ብዙ የቅማንትና የአማራ ተወላጆች አሉ። ወደ ጽሑፌ ይዘት ልመለስና፤ ለምንድን ነው የቅማንት ክልልን ለመመሥረት ያስፈለገው? ይኼን እንግዲህ በሶስት መንገዶች ማየት አለብን፤ ከሕገ – መንግሥቱ፣ ከትግራይ መስፋፋትና አማራውን አዳክሞ ከማጥፋት።

፩ኛ.    ከሕገ-መንግሥቱ አንጻር፤

አሁን ኢትዮጵያ እየተስተዳደረች ያለችው፤ ሀገሪቱ የብሔሮችና የብሔረሰቦች ናት ከሚለው ቅምር በተመነዘረ ሸርፍ ነው። ስለዚህ፤ በሀገሪቱ ማንኛውም የፖለቲካ ክንውን ለመሳተፍ፤ የአንድ ብሔር ወይንም ብሔረሰብ አባል ሆኖ መገኘት ግድ ነው። በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት፤ ኢትዮጵያዊያን ሳይሆኑ፤ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ናቸው ስለተባለ፤ “እኔ አንድ ኢትዮጵያዊ ነኝ” የሚለው አባባል፤ ትርጉም የለውም። ይህ ደግሞ በሕገ-መንግሥቱ የተደነገገና የሀገሪቱ መተዳደሪያ ደንብ ነው። ስለዚህ፤ ለአንድ የቅማንት ተወላጅ፤ ቅማንት ነኝ ማለቱ እንጂ፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለቱ ዋጋ የለውም ማለት ነው። በርግጥ አማራ ነኝ በማለት መቀጠል ይቻላል። ግልጹ ጉዳይ ግን፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለውን መሰረዙ ላይ ነው። ስለዚህ ሕገ – መንግሥቱ የቅማንት ክልልን ማበጀቱን ይፈቅደዋል፤ ገዥው ክፍልም ይፈልገዋል። በርግጥ ይህ ከትግራይ በስተቀር በሌሎች ክፍሎች ገና በመስፋፋት የሚተገበር ጉዳይ ነው። በትግራይ ክልል፤ ሳሆ ነኝ፣ ራያ ነኝ፣ ወይንም ሌላ ማለት አይፈቀድም። በጎንደር ግን ዛሬ ቅማንት፣ ነገ ደግሞ ጋፋት፣ ወይጦ፣ ሽናሻ፣ ሌላም ይከተላል። እንግዲህ ማጠንጠኛው ሕገ – መንግሥቱ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ከሕገ – መንግሥቱ አንጻር፤ የቅማንት ክልል መቋቋሙ ትክክል ነው። የዚህ ተቃውሞ የሚነሳው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ የብሔርና የብሔሮች ሳትሆን፤ የኢትዮጵያዊያን ናት ሲባል ብቻ ነው። አለበለዚያ ደግሞ፤ ቅማንት ነኝ የሚለውን፤ የለም አማራ ነኝ በል፤ ማለታችን ነው። ይህ ደግሞ ዴሞክራሲያዊነት ሆነ ኢትዮጵያዊነት አይደለም። ሁሉም የትውልድ ማንነቱን ራሱ እንጂ ሌላ ሊወስንለት አይገባም።

፪ኛ.    ትግራይን ከማስፋፋት አንጻር፤

አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ነው። በሀገሪቱ ያለው መንግሥት፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ነው። የዚህ መንግሥት የሕልውናው መሠረትና የቆመለት ዓላማ፤ የ“ትግራይን ክልል” ማስፋፋት፣ የ“ትግሬዎች”ን ጥቅም መጠበቅ፣ ባጠቃላይ በማንኛውም መንገድ “ትግራይን ማስቀደም” ነው። በርግጥ ይህ በተግባር ሲተረጎም፤ “ትግራይ”ን ወይንስ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አባላትንና ደጋፊዎችን የሚለውን መመልከት ይጠይቃል። በመሠረቱ ግን አገላለጹ የግድ “ትግሬዎች”ን እና “ትግራይ”ን ይመለከታል። ስለዚህ መንግሥቱና የመንግሥቱ ማንኛውም አካል ሁሉ፤ የዚህ የ“ትግራይ”ን የማስፋፋት ፍላጎት ማከናወኛ ነው። በመንግሥቱ ዙሪያ የተቋቋመ ማንኛውም የኅበረተሰብ ስብስብ፤ የዚህ ዓላማ ተገዥ እና አገልጋይ ነው።

ከዚህ ስንነሳ፤ ትናንት የወልቃይትን፣ የጠለምትን፣ የከፊል ጠገዴን፣ የብራ ዋስያን ክልሎች ከጎንደር፤ የዋግን ደግሞ ከወሎ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ወደ ትግራይ ማጠቃለሉ፤ የተነሳበትን ዓላማ ከግቡ ከማድረስ አኳያ መታየት አለበት። ቀጥሎ የላሄንና ሻግኔንና ቀሬውን የጠገዴ ክፍል በነካ እጁ ከጎንደር፤ የራያና አዘቦን ደግሞ ከወሎ በማን አለብኝነት ገሸለጠው። የተከዜን ግድብ ሠራ። የበለሳን ለም መሬት አጉረጠረጠበት። የስሜንና ተራሮች አንጓጠጠበት። በትምህርት ቤቶች እኒህን ሁሉ፤ ከደባርቅ፣ ከዳባትና ከአምባ ጊዎርጊስ አልፎ የጎንደር ከተማ ተራሮችንም የትግራይ ናቸው እያለ ወጣቶቹን አስተማራቸው። ለትግራይ የባህር በር ባቡር መንገድ መሠራቱ፤ የሀገሪቱ ወታደራዊ ክፍሎች ማዕከላዊ አውታሮቻቸው በትግራይ መከተማቸው፤ የትምህርት ዕድሉና የሀገሪቱ ሀብት ስምሪት ለትግራይ ማድላቱ፤ ከዚሁ የተያያዘ ነው።

ይሄ አልበቃው ብሎት፤ ዓይኑን ወደ ትልቁ የአባይ ግድብ ያጉረጠረጠው የኼው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ ወደዚያ ለመድረስ በሚያደርገው ግስገሳ፤ በመንገዱ ያሉትን ሁሉ ወደ ትግራይ ማጠቃለል አለበት። ስለዚህ አንድም ከታች በሶስተኛው ቁጥር በተገለጸው ምክንያት፤ ሌላም በዚህ ቁጥር በተዘረዘረው ጉዳይ፤ የቅማንት ክልልን መፍጠር ጠቃሚ መንገድ ሆኖ አገኘው። በዚህ ስሌት፤ በአርማጨሆና በጠገዴ መካከል ያሉትን የዳንሻን አካባቢዎች የወታደራዊ መናኸሪያ ካደረገ በኋላ፤ ቀድሞ የተያያዘውን ማፈናቀሉን ቢገፋ፤ ያካባቢው ነዋሪ እንደማይመቸው ተገነዘበ። ስለዚህ፤ ጠቡን ከትግሬዋች ነፃ አውጪ ግንባር ይልቅ፤ በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ለማድረግ፤ የቅማንት ክልልን መፍጠር፤ ዓይነተኛ መንገድ ሆኖ አገኘው። እናም ሆድ አደር የቅማንት ተወላጆችን ማስባሰቡን ቀጠለበት። በአማራው በኩል እንደ አለምነውና ጓዴ ዓይነት ለሆዳቸው ያደሩ አስተዳደሩን እንደያዙት ሁሉ፤ በጎንደርም እንዲሁ ሆድ አደሮችን ይዞ፤ የቅማንት ክልልን ጉዳይ አነሳ። በዚህ ወቅት የጎንደር ተወላጆች በአንድነት ቆመው አይሆንም አሉ። የተለመደ የጊዜያዊ ማፈግፈጉን አስቀደመ። ነገር ግን፤ በመሠረቱ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ ስሌቱን በምንም ዓይነት መንገድ ስለማይቀይር፤ አድብቶ፣ አሰልሶ፤ መጣ። ይሄን ጊዜ፤ ጠቡ በቅማንት ክልል ፈላጊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል ሆነ። ጠቡ በወንድማማቾች መካከል ሆነ።

ይህ የቅማንት ክልል መመሥረት ለማን ይጠቅማል? የቅማንት ክልል የትኛው ነው? የጎንደሬ አማራውስ ክልል የትኛው ነው? የኅብረተሰብ የዕድገት ሂደት፤ በሰዎች ፍላጎትና ዕቅድ የሚጓዝ አይደለም። የቅማንትና የአማራው ውርርስና መዋሃድ፤ በዕቅድ የተሠራ አይደለም። የታሪክ ሂደት ነው። ምንም ወደ ኋላ ሂደን ለመቀየር የምንችለው የታሪክ ክስተት የለም። ትናንት የተበላሽን፤ የዛሬዎቹ፤ ለዛሬና ለወደፊቱ እንዲያምር፤ ዛሬ ማስተካከል እንችላለን። ትናንት የነበረን ሀቅ ግን፤ የዛሬዎቹ፤ ዛሬ፤ ትናንት እንዳልነበረ ማድረግ አንችልም። ያለፈ፣ የተፈጸመ ሀቅ ነው። አቡነ ዘበሰማያት ተደግሞበታል። አርቆ ያሰላው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ዛሬ እያከናወነ ያለው ተግባር፤ በመሠሪ እኩዩ እምነት፤ ቋሚ እንዲሆንለት ነው። ችግሩ ግን ሕዝቡ እምቢ እያለ እየታገለ ያለበት ሀቅ ስለሆነ፤ በምንም መንገድ ሊፍቀው አለመቻሉ ነው። ትናንት ስንል፤ በታሪክ ሂደት አኳያ፤ ሆን ተብሎ በዕቅድ የሚተገበረውን ሳይሆን፤ በኅብረተሰቡ ዕድገት ምክንያትና በጊዜ ሂደት ስሌት፤ ከግንዛቤያችን ውጪ ሆኖ የተከሰተን የኅብረተሰቡ እንቅስቃሴ ሀቅ ነው። የወልቃይትና የጠለምት ወገናችን መፈናቀልና መባረር፤ የትናንት ሊሆን አይችልም። ገና የሰቀቀን ስቃይ መብራቱ እየተንቀለቀለ ነው። አይጠፋም። ያልጠፋን መብራት ደግሞ ነበር ማለት አይቻልም፤ አሁንም አለና!

የቅማንት ክልል መመሥረት፤ ዋና ምክንያቱ፤ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር የፖለቲካ ቅመራ ነው። በርግጥ ይህ ኢትዮጵያን ለማጥፋት፤ ጣሊያን፣ ቱርክ፣ እንግሊዝ ተጠቅመውበታል። ግን አልቻሉም። አሁን ደግሞ በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የቅማንት ክልል ሲፈጠር፤ ምን ጊዜም የማያባራ ንትርክ ከጎንደሬ አማራው ክልል ጋር ይኖራል። በዚህ ምክንያት፤ አነስተኛና ደካማ የሆነው የቅማንት ክልል፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርን መከታ አድርጎ፤ ከአማራው እንዲያስጥለው፤በትግሬዎች ክልል ጥላ ሥር መጠቃለል አለበት። ከዚያም በራሱ ክልል ሆኖ፤ ለትግሬዎች ገብሮ፤ በሁለተኛ ዜግነት የጊዜያዊ ሕልውና ያገኝና፤ በመጨረሻም ተደምስሶ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሥር ያለ፤ የትግሬዎች ቦታ ይሆናል። ቅማንቶችም ከምድረ ገጽ ይጠፋሉ። ድሮውንም የትግራይን ክልል ለማስፈት እንጂ ለቅማንቶች ከማዘን የተቀየሰ ስላልሆነ፤ ተቆርቋሪ አጥቶ፤ ቅማንት ይጠፋል። ይሄን ከሩቁ የተገነዘቡ አሁን በአንድነት ተሰልፈው ቆመዋል። ጋፋት ሆነ ሽናሻ፣ ወይጦ፣ ሻንቅላም ሆነ አገው፤ ጎረቤት ሲታማ የኔ ብለህ ስማ ነው! ነገ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አዲስ አበባ ላይ ተቀምጦ የደቡብ ኢትዮጵያዊያን ቢጠናከሩ፤ ወላይታ፣ ሲዳማ፣ ሃድያ፣ ከምባታ፣ ጉጂ፣ እያለ በሕገ-መንግሥቱ ደንብ፤ ክልሉን መከፋፈሉ አይቀሬ ነው። ኦሮሞም እንዲሁ ይጠብቀዋል። ይህ ሁሉ፤ ኢትዮጵያን ለማዳከምና የትግራይን ክልል ለማጎልበት ከታቀደው የመጀመሪያው መነሻ የመነጨ ስሌት ነው። እናም የቅማንት ክልል መመሥረት፤ ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የትግራይን ክልል የማስፋፋት ፍላጎት የመነጨ የፖለቲካ ስሌት ነው። ቁልፉም ሕገ-መንግሥቱ ነው።

፫ኛ.    አማራውን ከማዳከምና ከማጥፋት አንጻር፤

የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሲቋቋም፤ ከመጀመሪያዎቹ አራቱ ግቦቹ አንዱ፤ “በአማራው መቃብር ላይ የትግራይን ሪፑብሊክ እንመሠርታለን!” የሚል ነው። ስለዚህ የማያባራው አማራን የማጥፋት ዘዬው፤ አሁንም እዚህ ላይ በውል እየተተገበረ ነው። የቅማንት ክልልን መመሥረቱ፤ ለቅማንት ተወላጆች ካለው ተቆርቋሪነት የመነጨ አለመሆኑ ግልጽ ነው። ተጨማሪ ቁም ነገሩ፤ የቅማንት ክልል መቋቋሙ፤ በውስጡ ያዘለው ጉዳይ ነው። ከላይ በቁጥር ሁለት፤ ይህ የቅማንት ክልል መመሥረት፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ትግራይን የማስፋፋት ዓላማው እንደሆነ አሳይቻለሁ። እዚህ ላይ ደግሞ፤ አባሪ የሆነውን፤ አማራውን የማጥፋት ዓላማው፤ ሌላው ክፍል እንደሆነ አሳያለሁ።

በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አእምሮ፤ ደርግ ጊዜያዊ ጠላቱ፤ አማራው ደግሞ ዘለቄታዊ ጠላቱ ነበር። ስለዚህ፤ ለማንኛውም በተግባር ላይ የሚያውለው ዕቅድ፤ መነሻውና መዘወሪያው ይሄው ነው። ሌሊት ከእንቅልፉ የሚያባንነው፣ ቀን ከጥላው የሚያስበረግገው ነገር ቢኖር፤ የአማራው በሕልውናው መኖር ነው። ጭንቅላቱን የወጠረው አማራውን ለማጥፋት መሯሯጥ ነው። ስለዚህ የቅማንት ክልል መፈጠር፤ የዚህ ስሌት ሂደት ነው። አማራውን ማጥፋት የሚችለው፤ ብቻውን ሳይሆን፤ ሌሎችን በአማራው ላይ እንዲነሱ በማድረግ ነው። የኦሮሞዎችን ነፃ አውጪ ግንባር በመጠቀምና ስማቸውን በመያዝ ራሱ ተነስቶ፤ በደቡብ፣ በደቡብ ምሥራቅና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፤ አማራውን በኢሰብዓዊ መንገድ፤ አረመኔና አውሬነት በሞላው ጭካኔ፤ ቃላት በውል በማይገልጹት ሁኔታ፤ ጨፈጨፈ። ለስሙ የአማራ ክልልን ከፈጠረ በኋላ ደግሞ፤ ክልልሉን በማጥበብ፤ ቆይቶም የክልሉን ነዋሪ ቁጥር በማሳነስና ሆን ብሎ በመጨፍጨፍ፤ የማጥፋት ዘመቻውን መራው። አሁን ደግሞ በአማራው ክልል ውስጥ ሌሎች ክልሎችን መፍጠሩን ተያያዘው። የኒህ ክልሎች መፈጠር በሁለት መንገድ ይጠቅመዋል። አንደኛ አማራውን፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለውን እምነቱን ጥሎ፤ አማራው ተጠቃ በሚለው ጉዳይ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ያደርገዋል። ሁለተኛ ደግሞ አማራው ብቸኛ ሆኖ “አማራው ተጠቃ!” በሚለው ወጥመድ መተበተቡና እየተዳከመ መሄዱ ነው። ይህ ደግሞ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርን፤ ወደ አቀደው ግቡ፤ ፍጥነትን ባጎለበተ ግስግሳ፤ እንዲሮጥ ያመችለታል። እናም የቅማንት ክልል መፈጠር ለዚህ ተግባር መሆኑ ግልጽ ነው።

በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ፍላጎት የቅማንት ክልል ተፈጥሯል። ይኼን እንዴት መቃወም ይቻላል? ይኼን ሀገር አፍራሽ ተግባር መቃወም ግዴታ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ አግባብነት ያለን ወገኖቻችን ተደራጅተን ለመቃወም መነሳታችን ትክክል ነው። ቁም ነገሩ ግን፤ ይህ ተቃውሞ ግቡን እንዲመታ፤ በምን መንገድ ቢኬድ የበለጠ አስተማማኝ ይሆናል? ነው። ተቃውሞው ለምን የቅማንት ክልል ተፈጠረ? አይደለም። ተቃውሞው ይህ የቅማንት ክልል መፈጠር ጉዳይ፤ ከሀገራችን ሕልውናና ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጥማታችን አንጻር፤ ምን አስተዋፅዖ አለው? የሚለው ነው። ሀገራችን፤ በዚህ በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የቅመራ ሂደት፤ የትናንትናዋ ዩጎዝላቪያ በዛሬዋ ሶማሊያ የፖለቲካዊ ሀቅ ድሪቶ ተሸብሻቢ ትሆናለች።

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የግለ ሰብን ሀገራዊ የፖለቲካ ተሳትፎ በመጠበቅ ላይ የተመሠረተ ነው። በግለ ሰብና በቡድን መብት አኳያ፤ ያልሆነ ንትርክ በመካከላችን አለ። የዚህ ሁሉ ምንጭ የትግሬዎች ነፃ አውጪ የፖለቲካ ስሌት ነው። የግለሰብን መብት መጠበቅና መከበር የተቀበለ ሰው፤ የቡድን መብት ለሚባለው ሞሰብ፤ ፊቱን አያዞርም። የቡድን ስንል፤ የየቡድኑ ትልቅነትና ትንሽነት ሊያስከትል የሚችለውን መበላለጥ አላገናዘብንም። ምን ዓይነት ቡድኖች ሊፈጠሩ ይችላሉ የሚለውን አልተመለክትን። አንድን ኢትዮጵያዊ በማንነቱ ወይንም በእምነቱ የሚያገሉ ብድኖች ሊፈጥእሩ እንደሚችሉ አላጤንንም።በአባላት ብዛትም፣ በጥራትም፣ በመብትም እኩል የሆኑ ቡድኖች አይፈጠሩም። ለዚህ በሀገራችን ያለው ሀቅ ቦታ አይለግስም። መበላለጥ ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ቦታ የለውም። የትልቁ ስብስብ ቡድን አባል፤ የትልቁ ስብስብ ቡድን አባል በመሆኑ ብቻ፤ የትንሹ ስብስብ ቡድን አባል ከሆነው የሚለይና የተለየ መብት የሚያገኝ ከሆነ፤ እኩልነት ገደል ገባ! ተሽቀንጥሮ ተጣለ። ይኼን ነው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በተግባር ላይ እያዋለ ያለው። በአሁኑ ሰዓት፤ ከአራቱ “ነፃ” ትልልቅ ድርጅቶች አባል ውጪ፤ አንድ ኢትዮጵያዊ የመንግሥቱን ሥልጣን መጨበጥ አይችልም። ይህ ማለት፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፣ የ“ብሔራዊ የአማራ ዴሞክራሲያው ንቅናቄ”፣ የ“ኦሮሞዎች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት” ወይም የ“ደቡብ ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ድርጅት” አባል ያልሆነ ኢትዮጵያዊ፤ በትረ መንግሥቱን ሊጨብጥ አይችልም። አባልነት ደግሞ ከነዚህ አራቱ “ብሔሮች” ካንዱ መወለድን ግድ ይላል። በርግጥ እየየም ሲደላ! ነውና፤ ይሄ ራሱ መተግበሩ ሌላ ጉዳይ ነው። ነው እንበልና፤ በዚህ ሂደት፤ አንድ የአኝዋክ ወይንም የቅማንት ተወላጅ፤ በምንም መንገድ ሀገሪቱን የማስተዳደር ቦታ ቀርቶ፤ ምኞት እንኳ እንዲኖረው ቀዳዳ የለውም። ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያዊነት መብት ገደል ገባ!

እንግዲህ በዚህ እውነታ ላይ ነው ያለነው። ታዲያ ለኔ የቅማንት ክልልን መመሥረት መሠረታዊ ተቃውሞዬ፤ አንድም የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር የፖለቲካ ፍልስፍናን ካለመቀበል ይነሳል። ይህ ማለት፤ የዚህ ገዥ ክፍል የፖለቲካ ፍልስፍና ትክክል አይደልም ነው። የዚህ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መሠረቱ፤ በኢትዮጵያ የነበረውን ሀቅ፤ “በገዥዎችና በተገዥዎች መካከል ሳይሆን፤ በ”ተገዥ ብሔሮች” እና በ”ገዥው የአማራ ብሔር” መካከል ነው።” የሚለው ነው።  ይህ ለኔ በወቅቱ የነበረውን የትግል መሽከርከሪያ ያጣመመ ነው እላለሁ። ያኔም አሁንም የራመድኩትና የማራምደው አቋሜ ነው። በወቅቱ የነበረው የአፄው ግዛት፤ የሥልጣን ወንበሩን ለማደላደል፤ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ባገኘው መንገድ አሰግዷል። በዚህ ኋላቀር አገዛዙ፤ ሁሉንም የሀገሪቱ ክፍሎች፤ የግል በረቱ አድርጓል። በርግጥ አንዱን ክፍል ከሌላው ክፍል የበለጠ አጥቅቷል። ይህ ማለት ግን፤ አንዱን ክፍል ጎድቶ ሌላውን ክፍል ጠቅሟል ማለት አይደለም። ማንኛውንም የሀገሪቱ ክፍል አልጠቀመም። ራሱን የገዥውን ክፍል ብቻ ጠቅሟል። ታሪካዊ ውስንነቱ አግዶታል። ሆኖም ግን፤ ከራሱ ውጪ የጠቀመው አንድም ክፍል አልነበረም። ስለዚህ በወቅቱ መደረግ የነበረበት ትግል፤ በገዥው መንግሥትና በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ነበር። ለትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ግን፤ ትግሉ በ“ገዥው የአማራ ብሔር” እና በ“ተገዥ ሌሎች ብሔሮች” መካከል ነበር።

ሁለተኛው የቅማንት ክልልን መመሥረት መሠረታዊ ተቃውሞዬ፤ የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባርን የአስተዳደር መመሪያ ካለመቀበል ይነሳል። የዚህ ገዥ ክፍል የአስተዳደር መመሪያ ከፖለቲካ ፍልስፍናው ይመነጫል። ከፖለቲካ ፍልስፍናው የመነጨው የአስተዳደር መመሪያው፤ የፖለቲካ ፍልስናውን በተግባር የሚያውል ነው። ሀገሪቱ ውስጥ የነበረው በደል፤ በ“ገዥው ብሔር” እና በ“ተገዥ ብሔሮች” ነው ካለ፤ የሚቀጥለው የአስተዳደር መመሪያ፤ በ“ብሔሮች” ነፃነት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ግልጽ ነው። እናም የየ“ብሔሮች” ክልሎች ተመሠረቱ። የዚህ ክልል አመሠራረት፤ ከገዥው ክፍል የፖለቲካ ፍልስፍና እምነት አኳያው የመነጨ ቢሆንም፤ በትክክል ግን ሊተገበር አይቻልም። ምክንያቱም ራሱ የፖለቲካ ፍልስፍናው የ“ተገዥ ብሔሮች” አሉ እስካለ ድረስ፤ “ገዥውን ብሔር” ማጥቃቱ ግድ ይሆናልና! “ገዥ ብሔር” የተባለውን አማራ ማጥቃት፤ ለዚህ አጠቃላይ እምነቱ ገዥ ነው። ታዲያ አማራን ማጥቃት የሚለውን ስቃወም፤ መነሻዪ ይሄው የገዥው ክፍል የተሳሳተ እምነት ነው። አማራውን ማጥቃቱን ስቃወም፤ የቅማንት ክልል መመሥረቱን እቃወማለሁ። የምነሳው ግን፤ ለምን ቅማንት የራሱን ክልል አገኘ ወይንም ለምን የአማራው ክልል ተቆረሰ ከሚለው አይደለም።

ቀጥሎም የ“ትግራይ ክልል” በማለት ከ“አማራ ክልል” እየጎመደለ የተወሰደውን እቃወማለሁ። የምቃወመው፤ መካለሉንና የመካለሉን ትክክለኝነት ወይም ጉድለት ለመቋቋም ሳይሆን፤ በኔ እምነት፤ ይህ ክለላ፤ ውሎ አድሮ፤ “ኢትዮጵያን ለመቆራረስና የትግራይን ሪፑብሊክ ለመመሥረት!” ካለው ዕቅድ ጋር አብሮ የተቀመረ ነው፤ ከሚል ፍራቻዬ ተነስቼ ነው።

ተቃውሞዬ፤ ይህ ክስተት፤ በቅማንትና አማራ መካከል የማያባራ መጨፋጨፍን ስለሚያስከትል ነው። አሁንም ቢሆን፤ አንተ ከክልልህ እየተባባለ፤ በወንድማማቾች መካከል እየተፈጠረ ያለው “ይኼ የኔ! ያ ያንተ!” ንትርክ፤ በግድያና በመጠፋፋት ይከተላል ባይ ነኝ። እናም እቃወማለሁ። የትኛው ቦታ ነው የቅማንቶች? የትኛው ቦታ ነው የቅማንቶች ያልሆነ? የትኛው ቦታ ነው የጎንደር አማሮች? የትኛው ቦታ ነው የጎንደር አማሮች ያልሆነ? ከየት ነው የጎንደር አማራው ተባሮ ቅማንቱ የሚሰፍረው? ከየትኛው ከተማስ ነው ቅማንቱ ተባሮ የጎንደር አማራው የሚከትመው? ቅማንት በራሱ ክልል በምን ቋንቋ ሊናገር ነው? ምን የተለየ ባህል ሊኖረው ነው? ምን የተለየ ሃይማኖት ሊኖረው ነው? ይሄ ያስፈራኛል።

ይህን ካስቀመጥኩ በኋላ፤ የዚህ ጽሑፍ አንባቢ፤ ከማንበብ አልፈው አብረው እንዲቃወሙ እፈልጋለሁ። ሀገራችን ውስጥ አንድ ወይንም አንዲት ግለሰብ፤ በኢትዮጵያዊነቱ ወይንም በኢትዮጵያዊነቷ ላይ ብቻ በተመሠረተ የሀገራችን ፖለቲካ መሳተፍ አለባቸው እላለሁ። የኅብረተሰቡን ብወዳ ( ሶሻል ኢንጅነሪንግ ) እቃወማለሁ። ማለትም፤ አንተ ትግሬ ነህ፤ አንቺ ቅማንት ነሽ እያሉ ኢትዮጵያዊያንን መፈረጅና በዚሁ አጓጉል በተፈረጀ አጥር የፖለቲካ ተሳትፏቸውን እንዲያደርጉ መወሰኑን እቃወማለሁ። ይህን ስቃወም፤ በዚህ ስሌት የተጠመደውን የክለላ ዘይቤ በደንብ አጢኜ ነው።

በመጨረሻም እንደኔ ከዚሁ ክፍለ ሀገር ተወልደው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ለሠጡት ወገኖቼ መልዕክት አለኝ። ይህ ጉዳይ እኛን በቀጥታ ስለሚመለከተን የግድ መነጋገር አለብን። በዚህ ጉዳይ ላይ ከማንም የበለጠ ቀጥተኛ ተቆርቋሪነት ሊኖረን ይገባል። በርግጥ የተለያዩ ድርጅት አባላት በመካከላችን አሉ። እናም በአንድነት የሚደረገው ሩጫ በየዘርፉ መጓተት ያጋጥመዋል። መረዳት ያለብን ግን፤ ወገኖቻችን፤ የዚህ ወይንም የዚያ ድርጅት አባል ስለሆኑ ወይንም ስላልሆኑ ሳይሆን፤ በባድማቸው ላይ በመቆማቸው፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በፈጠረውና በሚቆሰቁሰው ችግር፤ አማራ ወይንም ቅማንት እየተባሉ እየተገደሉ ነው። ይህ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። “ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶች አንቃወምም፣ እኛ የፖለቲካ ድርጅቶችን አንነካም።” የሚለው አያስኬድም። የያዝነው የፖለቲካ ጥያቄና የፖለቲካ መፍትሔ የሚሻ ሀገራዊ ጉዳይ ነው። ለዚህ የሚሠጠው መፍትሔ ወሳኝ ነው።

ስለዚህ ስብስባችን የፖለቲካ እንጂ የጠላ ማኅበር አይደለም። ሊሆንም አይችልም። የፖለቲካ ስብስብ እንደመሆኑ ደግሞ አብረው ሊታዩ የሚገባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ስብስቡ ሌሎች ድርጅቶችን እባካችሁ የሚል፣ ወይንም የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር ልመና ማመልከቻ አቅራቢ አይደለም። በግልጽ ደግሞ ምን ማድረግ ይችላል? የሚለውን ማጤን አለብን። እንዲያው ችግሩ ስለተፈጠረ ብቻ፤ መነሳት አለብን የሚለው ብዙ አያስኬድም። ስብስቡ ብዙዎቻችንን ሊያጠራቅም እንደሚችል ጥያቄ የለኝም። ስብስቡ እንዲያየው የምፈልገው፤ ይህ ጉዳይ ሀገራዊ መሆኑን፤ መፍትሔውም ሀገራዊ መሆኑን፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ዋና ጠላታችን መሆኑንና ይህ ወገንተኛ አምባገነን ገዢ ቡድን ካልጠፋ፤ ጉዳያችን መልስ እንደማያገኝ ነው። እናም መፍትሔው ሀገራዊ እስከሆነ ድረስ፤ ሀገራዊ የሆነ ስብስብ መፈጠሩ ወይንም ካሉት መርምሮና መርጦ እኛ ዋና ተጫዋቾች መሆን እንዳለብን ማሳወቅ እፈልጋለሁ። አጀንዳውን ኢትዮጵያዊ ማድረግና በግልጽ ማስቀመጡ ብቻ ነው ትክክለኛ መፍትሔ ሊያስከትል የሚችለው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.