የወልቃይት ጠገዴ አማራ ተወላጆች ከትግራይ ክልል ፖሊስ እየለቀቁ ነው (ጌታቸው ሽፈራው)

~”በማንነታችን ምክንያት የሚደርስብን ወከባና ተፅዕኖ ከአቅማችን በላይ ሲሆን ከትግራይ ክልል ፖሊስ ለቅቀን ወደአማራ ክልል መጥተናል”

በማንነታቸው ምክንያት በደል የሚደርስባቸው የወልቃይት ጠገዴ አማራ ተወላጆች ከትግራይ ፖሊስ እየለቀቁ ነው። በትናንትናው ዕለት በሚደርስባቸው በደል ከትግራይ ክልል ፖሊስ የለቀቁ 7 ፖሊሶች ወደ አማራ ክልል መጥተዋል። ከትግራይ ክልል ፖሊስ ከለቀቁት መካከል 6ቱ አድዋ፣ እንዲሁም 1 ዳንሻ ተመድበው ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸው ታውቋል።

ፖሊሶቹ አማርኛ ሲናገሩ ወከባ እንደሚደርስባቸው፣ ሞባይላቸው ላይ የአማርኛ ሙዚቃ ሲገኝ ወይንም ሲያዳምጡ ከተገኙ እንደሚገመገሙ፣ ሰብሰብ ብለው ሲያወሩ እንደሚጠራጠሯቸውና ወከባ እንደሚደርስባቸው፣ “ሮንድ” በሚወጡበት ወቅትም ባልደረቦቻቸው “እናንተ አማራ ነን ትላላችሁ፣ ምንም አታመጡም” እያሉ በመተንኮስ ለመክሰሻ ሰበብ እንደሚፈልጉላቸው ገልፀዋል። በማንነታቸው በመተንኮስ ለማሰር ሰበብ ሲፈለግላቸው ከትግራይ ክልል ፖሊስ ለመልቀቅ እንደወሰኑ ተናግረዋል። “በማንነታችን ምክንያት የሚደርስብን ወከባና ተፅዕኖ ከአቅማችን በላይ ሲሆን ከትግራይ ክልል ፖሊስ ለቅቀን ወደአማራ ክልል መጥተናል” ብለዋል።

ከአሁን ቀደምም በወልቃይትና ጠገዴ የሚገኙ የትግራይ ሚሊሻ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ተወላጆች ከእነ መሳርያቸው ወደጠገዴና አርማጭሆ መምጣታቸው ይታወሳል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.