በድርጅታዊ ጉባዔው አብዮታዊ ዴሞክራሲን ለመተካት አቅጣጫ አልተቀመጠም- ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ግንባሩ የሚመራበትን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራም
ለማጎልበት አቅጣጫ ማስቀመጡን የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር ገለጹ።

ግንባሩ ላለፉት 27 ዓመታት ሲመራበት የነበረውን አብዮታዊ ዴሞክራሲን የሚተካ ርዕዮተ ዓለም ተጠንቶ ለመጪው ጉባኤ እንዲቀርብ ጉባኤው ውሳኔ አሳልፏል ተብሎ በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የተሰራጨው መረጃ ስህተት መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ፥ አንዳንድ የግንባሩ ብሄራዊ ድርጅቶች አባላት በጉባኤው ግንባሩ የሚመራበት አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፕሮግራም መለወጥ አለበት የሚል ሀሳብ አንስተው ነበር።

አባላቱ ባነሱት ጥያቄ ዙሪያ በጉባኤተኛው አስተያየት ከሰጠበትና ውይይት ከተደረገበት በኋላ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራምን ይዞ ለመቀጠል ከስምምነት መደረሱን ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገልፀዋል።

ግንባሩ በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ በመጓዝ ለውጥ ማምጣት እንደሚችልም በሁሉም ዘንድ መግባባት መፈጠሩንም ተናግረዋል።

የፕሮግራም ለውጥ ለማድረግ ማሰብ ክልክል እንዳልሆነ ያነሱት ወይዘሮ ፈትለወርቅ፥ በተለያዩ ጊዜያትም ግንባሩ የፕሮግራም ለውጦችን ሲያደርግ እንደነበር አውስተዋል።

የፕሮግራም ማሻሻያዎችን ለማድረግና የሚተካ ርዕዮተ ዓለም እንዲጠና የሚወሰነው ግን በኢህአዴግ ጉባኤ ላይ አለመሆኑን ተናግረዋል።

የፕሮግራም ለውጥ ለማድረግ በስሜት ሳይሆን ጥናቶች ሊካሄዱ እንደሚገባም አንስተዋል።

እንደ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ማብራሪያ፥ ከዚህ ቀደም ግንባሩ የፕሮግራም ለውጦችን ሲያደርግ ነበር፤

ማሻሻያዎች ሲደረጉ የነበሩት ጥናት ከተካሄደና መላው የድርጅቱ አባላት እንዲሁም ህዝብ እንዲወያይበት ከተደረገ በኋላ ነው፤

በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎችና ኮንፍረንሶችም ከተካሄዱና መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ ማሻሻያዎች ሲደረግ ነበር።

ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.