አሳዛኙ የአማራ ህዝብ የጤና አገልግሎት ተቋማት ሁኔታ፣ ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል እነደማሳያ!! (መልካሙ ተሾመ)

በቀደም ለታ ሃኪም ቤት ነበርኩ፤ ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል፡፡ ሌላ ጊዜ እንዲህ ያለ ከደረጃ ግርጌ የሆነ አገልግሎትና አስተዳደር ሲገጥመኝ እበሽቅ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ብግነቴን ጨርሸ አፈርኩ፡፡ እውነት እዚህ አገር መንግስት አለ ወይ? ብዬ ጠይቄያለሁ፡፡ ያላዬ ሰው ውሸት ይመስለዋል፡፡

ምን ዓይነት በደል ነው ባካችሁ? እዚህ ቦታ አኪም ሆነህም ታካሚ ሆነህም ወይም እንደ እኔ ጠያቂ ሆነህ ብትገኝ ትታመማለህ፡፡ አዕምሮህም አካልህም ይቃወሳል፡፡ እንዲህ ባለ አስጠሊታ የስራ ቦታ ላይ ተገኝተው ፍዳቸውን የሚያዩ ሃኪሞችን እመለከታለሁ፡፡ ሁሉም ወጣቶች ናቸው፡፡ ጥቂቶችን አውቃቸዋለሁ፡፡ ቡና እየጠጣን ስለ ጉዳዩ አወራን፡፡ ነገርዬውን በለቱልኝ፤ ለችግሩ ያላቸው ግድና መብከንከንም ከፍ ያለ መሆኑን ተገነዘብኩ፡፡

ዋና ችግሩ ምንድነው? አልኩ የማላውቀው ይመስል? ችግሩን አወራን፡፡ ሁሌም እንደማደርገው እና መፍትሄውስ ምንድነው? ስል ጠየቅሁ፡፡ ብዙ አማራጭ አነሳን፡፡ ቆይ እናንተ ግን አይደብራችሁም ወይ? ለምን የሆነ ነገር አታደርጉም? አልኩት፡፡

ሃኪሙ ቀጠለ:- አሁን ችግር ማውራት ሰልችቶናል፡፡ ሰሚ አለመኖሩንም አረጋግጠናል ወይም አጯጯሁን አልቻልንበትም ይሆናል፡፡ ስራ ይበዛብናል፡፡ የእኛ ስራ መብዛት እንደ ሌላው ስራ መብዛት ያለ አይደለም፡፡ ከመደበኛው የህክምና ስራችን ውጭ ያለውን የአስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ፣ መብቶቻችን ለማስከበር መንቀሳቀስ አልቻልንም፡፡ እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ ድሃ ሆነህ ድሃ ህዝብ እንደማከም ያለ ስሜትን የሚነካ ስራ የለም፡፡ አንዳንዴ አገር ጥዬ መጥፋት ያምረኛል፡፡ ግን ደግሞ ችግሩን በመሸሽ አናመልጠውም፡፡ ክህደትም ይሆንብኛል፡፡

(በመሃል ስልኩ ጮኸ ፤ በደንብ ያልሰማኋቸውን የሙያ ቃላት እየጠራ ትዕዛዝና ምክር ይሰጣል ፤ ለጁኔየሮቹ)::

የሆነው ሆኖ በህክምናው ዘርፍ ያሉትን ችግሮች በመቅረፍ የህክምናውን ደረጃ በማሻሻል የህዝባችን ጤና ለመጠበቅ በማሰብ ማህበር ለማቋቋም/ለማጠናከርና እንደገና ለማደራጀት እየተንቀሳቀስን ነው አግዙን አለኝ፡፡
በሃኪሙ አነጋገርና ነገር እየተደመምኩ ፤ ምን እናግዛችሁ? አልኩት፡፡

የአማራ ሃኪሞች ማህበርን ለማደራጀት ቀጠሮ ይዘናል፤ ለጥቅምት 03 ቀን 2011 ዓ.ም፤ ባህር ዳር፡፡ ለዚህች ስብሰባ የሚሆን የአዳራሽ፣ የገንዘብ ድጋፍ ብዙ ቢሮ ዞረን ሁሉም እምቢ አሉን፡፡ ይገረምህና ጤና ቢሮ እንኳን እምቢ አለን፡፡

ማመን አልቻልኩም፡፡ ህጋዊ ማህበሩ በህጋዊ ደብዳቤ ስፖንሰር ጠይቃችሁ ነው አዳራሽና የሁለት ቀን የስብሰባ ማስኬጃ ያጣችሁት? ጠየቅሁት፡፡
አዎ አለኝ፡፡ ቀጠለና ፦
እናንተ የምታወሩትን አይተን ዶር ጋሹን ያሰረው ስርዓት የተለወጠ መስሎን ነበር፡፡ በየቢሮዎቹ በዞርን ጊዜ ያየነው ግን ያው የድሮው ነው አለኝ፡፡
—————————————————-
የአማራ ጉዳይ የሚያገባችሁ ሁሉ ተባበሩ፡፡

ሀ) ስለ ማህበራቸው ጻፉላቸው፤ አስተዋውቁላቸው፡፡
ለ) የሀሳብ፣ የሙያ፣ የገንዘብ፣ የማቴሪያል ድጋፍ አድርጉላቸው፡፡

————————————–
ይታያችሁ የአማራ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው በባህር ዳር ከተማ የሚገኘው ብቸኛው የፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል ይህን ያክል ውስብስብ ችግር ላይ ከወደቀና አገልግሎት መስጠት ወደማይችልበት ደረጃ ከደረሰ በክልሉ በሚገኞ ዞኖች እና ወረዳዎች ውስጥ ያሉ ሆፒታሎች እና ሃኪም ቤቶች ሁሉ ከፈለገ ህይወት ቢብሱ እንጅ እንደማይሻሉ ይናገራሉ የሚያውቋቸው፡፡

የበደላችን ብዛቱ ዓይነቱና መጠኑ፡፡
የአማራ ፖለቲካ መፍትሄ የመስራት ፖለቲካ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.