በሰኔ 16 ቦምብ ፍንዳታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ለመግደል በመሞከር የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ቀጠሮ ተጠየቀ

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ድጋፍ ለመግለጽ አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደ ሰልፍ ላይ ቦምብ በማፈንዳት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ለመግደል በመሞከር በተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች ላይ ቀጠሮ ተጠየቀ።

አምስቱ ተጠርጣሪዎች አቶ ጌቱ ግርማ፣ አቶ ብርሃኑ ጃፋር፣ አቶ ጥላሁን ጌታቸው፣ አቶ ባህሩ ቶሎሳና አቶ ደሳለኝ ተስፋዬ ዛሬ ጥዋት ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስራ ዘጠነኛ ወንጀል ችሎት ቤት ቀርበው የነበረ ሲሆን ጠበቃ የለንም በማለታቸው ቀጠሯቸው ወደ ከሰዓት ተዛውሯል።

“ለወታደራዊ ደኅንነቱ የማንቂያ ደወል ነው”

የዓለምፀሐይ፣ የፍስሃ እና የካሳሁን አዲስ ተስፋ

“ትጥቅ መፍታት ለድርድር አይቀርብም”፡ መንግሥት

ፍርድ ቤቱም ጠበቃቸውን ይዘው ከሰዓት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ በወሰነው መሰረት ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳን ይዘው ቀርበዋል።

ዐቃቤ ህግ በባለፈው ወቅት የነበረውን ክስ እንደገና ያቀረበ ሲሆን በዚህም መሰረት በኬንያ ናይሮቢ ተቀማጭነቷን ያደረገችው ገነት ታምሩ (ቶለሺ ታምሩ) አቀነባባሪነት ሀገሪቷ መመራት ያለበት በዶ/ር ዐብይ አህመድ ሳይሆን ቀድሞ በተመሰረተው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የሚል ዓላማ ይዘው ጥቃቱን እንዳደረሱ ክሱ አትቷል።

ክሱ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ ስም የራሳቸውን ዓላማ የሚያራምዱና የኦሮሞን ህዝብ ፍላጎት የማስያፈፅሙና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም በማለት ጥቃቱን ለመፈፀም እንደተነሳሱም ገልጿል።

በምላሹም ጠበቃ ወንድሙ ከደንበኞቻቸው ጋር በዛሬው ዕለት በመገናኘታቸው የፅሁፍ መቃወሚያ ለማቅረብ ዕድል እንዳላገኙ ጠቅሰው ፍርድ ቤቱ ቀነ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው በጠየቁት መሰረት ለጥቅምት 16 2010 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል።

ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳ

ክሱንም ከሰሙ በኋላ ጠበቃ ወንድሙ ክሱና ደንበኞቹ የሰጡት ቃል እንዳልተጣጣመ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በዋነኝነትም የሚያነሱት ተጠርጣሪዎቹ በተለያየ ቀን መያዛቸው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ለምሳሌ አንደኛ ተከሳሽ ጌቱ ግርማ በነጉርሜሳ አያና መዝገብ ከነበቀለ ገርባ ጋር በሽብርተኝነት ከሁለት ዓመት በላይ ታስሮ ክሳቸው ተቋርጦ ነፃ ከወጡት አንዱ መሆኑ ምክንያት እንደሌለው ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

“በዶ/ር ዐብይ መምጣትም ተጠቃሚ ከሆኑት አንዱ ነው” ብለዋል።

• በሰልፉ ላይ የታየው ክፍተት ምን ነበር?

ሶስት ወር ሳይቆይ እንደታሰረና ሌላኛው ተከሳሽ ብርሃኑ ጅፋር ስጋ ነጋዴ ሲሆን የተያዘውም ስጋ ሲያመላልስ እንደተያዘ ገልፀዋል።

ሌላኛው ተከሳሽ አቶ ጥላሁን ጌታቸው አባታቸው አቶ ጌታቸው ጎንፋ ከአንድ አመት በላይ በሽብር ተከሰው በዶ/ር ዐብይ አህመድ አማካኝነት በምህረት ክሳቸው ከተቋረጡት አንዱ ናቸው።

በአባቱ ዕስር ምክንያት ጫካ ለመዋጋት ወስኖ የነበረና በአባቱ መለቀቅ ምክንያትም ምስጋናን ለማቅረብ መስቀል አደባባይ በነበረው ሰልፍም እንደተገኘም ጠበቃው ጨምረው ገልፀዋል።

“ተጠርጣሪዎቹ በቦታው ላይ የተገኙት ለዶ/ር ዐብይ አህመድ ምስጋናቸውን ለማቅረብ ነው” ብለዋል።

ከዚህ በፊት ከነበሩት የሽብር ክስ ጋር እንደሚመሳሰሉም አቶ ወንድሙ ያስረዳሉ።

“ጌቱ፣ ብርሃኑ፣ ጥላሁን ምስክር ሁኑ ተብለው ምስክር አንሆንም በማለታቸው ክስ እንደተመሰረተባቸው ነግረውኛል” በማለት ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ሌላኛው የክሱ አስገራሚ ጉዳይ ብለው ጠበቃ ወንድሙ ያነሱት ዶ/ር ዐብይ “በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የተጠላ በመሆኑ” የሚለው ነው።

“ዶ/ር ዐብይ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ተወዳጅ ነው። ብዙ ሺ እስረኞችን ከእስር ቤት አውጥቷል፤ ለአስርት ዓመታት በስደት የነበሩ የተለያዩ ፓርቲዎችን ወደ አገራቸው መልሷል” ያሉት አቶ ወንድሙ ክሱ እንደሚጣረስና በቀጣዩ ቀጠሮም በዝርዝር እንደሚያቀርቡ አስረድተዋል።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመለክተው አንደኛ ተከሳሽ ጌቱ ግርማ ከሁለተኛ ተከሳሽ ጋር ሱሉልታ ላይ በመገናኘት ሰልፉን የጠራው ገለልተኛ ወገን ሳይሆን ኢህአዴግ ነው ኤችአር 128 የተባለውን በአሜሪካ ኮንግረስ የተላለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ እንዳይሆን ያደርጋል የሚል ምክንያቶችን በመግለጽ ቦምቡን በመወርወር እንዲበተን እናድርግ በማለት እንዲዘጋጁ አድርጓል።

ለሦስተኛ ተከሳሽ ደውሎም ቦምብ የሚወረውር ሰው አንዲፈልግ ተልዕኮ መስጠቱ በክሱ ተገልጿል፡፡

ሌሎችም ተከሳሾች በቡድን በመደራጀት ለጊዜው በቁጥጥር ስር ባልዋሉ ግለሰቦች ጋር በመተባበር በተለያየ መንገድ ቦምቡን ለመወርወር ሰዎችን በመመልመልና በሌሎችም ጉዳዮች ተሳታፊ እንደሆኑ ክሱ አትቶ በሽብርተኝነት ድርጊትም ወንጅሏቸዋል።

በሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በተፈፀመው ጥቃት የሙሳ ጋዲሳና ዮሴፍ አያሌው የተባሉ ግለሰቦች ህይወታቸው ማለፉንና ከ163 በላይ ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱ የሚታወስ ነው።

BBC Amharic

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.