ራስህን ውቀረው (በላይነህ አባተ)

ሰይጣን ተሆኑ አይቀር እንደ አቢይ ሰባኪው፣
ስንቱን አስደፍቆ ተእግሩ ሥር ላስደፋው፡፡

ብልቷን አውጥቶ ተሚበላት አገር፣
ሱስ ያዘኝ እያለ አሞኘው ስንቱን ጅል፡፡

በዱላ ደቁኖ በመለስ ቀስሶ፣
ሊበር ይችላል ወይ እባብ እርግብ ሆኖ?

ይሁዳን ተሙሴ እያመሳሰሉ፣
እነ ፕሮፌሰር ስንቱን መንጋ አስካዱ፡፡

አምልኩ ቢባሉ አንድ አምላክ አንድ እግዜር፣
ጥሪ ተቀብለው ተጆሮ ጠቢ ዛር፣
እጅ ወደ ላይ አርገው ገቡ እንደ ምርኮ ጦር፡፡

በእንብልብልህ ተጓዝ ሲል የረገመውን፣
እንዴት ሰው ያመልካል ያሳተውን ሄዋን?

አምላክ ቀናተኛው እውነትን የሚወድ፣
ምነው አይቆጣ ምነው አይናደድ፣
ከሙሴ ወንበር ላይ ይሁዳን ስትጎልት፡፡

እየዬን ተውና መውቀስ የከዳህን፣
ራስህን ውቀር ያንዘላዘለህን፡፡

ልትቆርጥ ስትማልል ተጊንጥ ሰንኮፍ ማር፣
ነድፎ ቢዘርርህ ቢደፍቅህ ተካብ ሥር፣
ባንተ በጅሉ እንጅ በጊንጥ ማን ይፈርዳል፡፡

ዘንዶ ሰው ይሆናል ብሎ ያመነን ሰው፣
እንኳንስ እባቡ አምላክም አይምረው፡፡

ከሃያ ዓመት በላይ የጨፈጨፋቸው፣
መንበር መወጣጫ እርካብ ያረጋቸው፣
ከምድር ሥጋቸው ከሰማይ ነፍሳቸው፣
ከችሎት ገትሮ ፍርድ ቅጣት ያሰጠው፡፡

እስከዚያው ድረስ ግን ፍርዱን እስቲያገኘው፣
ትሰማኝ ተሆነ ጅልና ዘልዛላው፣
ተእባብ ሥር እንደ አፈር ወድቀህ የሰገድከው፣
ዳግም እንዳታመልክ በዛሩ በቆሌው፣
ይሰላ እንደሆነ ራስህን ውቀረው፡፡

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ሐምሌ ፲፱ ሁለት ሺ አሥር ዓ.ም.

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.