የወቅቱ ፖለቲካ አሰላለፍና የመደመር ፖለቲካ ፈሊጥ!!

አገራችን ኢትዮጵያ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት መውደቅ በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ በቁልቁለት መንገድ ላይ እየተጓዘች በአሁኑ ወቅት በውድቀት እና በመበታተን አፋፍ ላይ ታጣጥራለች። በመሆኑም ዛሬ የምንገኘው ይህቺን
አሳዛኝ አገር እየመተሩ ወደ ተስፋ ምድርነት ለመቀየር ሩብ ጉዳይ እንደቀራት እድለኛ አገር አድርገው በአሰልቺ የሀሰት ፕሮፓጋንዳቸው ሲያደነቁሩን የኖሩ ሁለት ነውረኛ አገዛዞች ተፈራርቀውብን ወደ ሦስተኛው የከፋ ምዕራፍ እየተሸጋገርን
ባለንበት ዘመን ላይ ሆነን ነው። አሳዛኙ ነገር የዛሬዎቹ ባለጊዜዎች የትናንትናዎቹን አስተሳሰብ ተላብሰው አንድ አይነት ድራማ እየተጫወቱ፤ ነገር ግን እኛ የትናንትናውን ስለምንረሳ በዛሬው ድራማቸው ተጠምደን የትናንትናውን ዓይነት
ትዕይንት ሲተውኑ እያየን፤ ዛሬ የታደሱ መስሎን በፈንጠዝያ መንፈስ ውስጥ ሆነን ሣሩን እንጂ ገደሉን አለማየታችን ነው።

ዛሬ ላይ በሥልጣን ላይ ያሉት የልዩ ልዩ ኃይሎች አሰላለፍ ሲመዘን፤ የምንገኝበት ሁኔታ ልክ እንደ ትናንቱ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ የ1966ቱን የመንግሥት ግልበጣ ተከትሎ በተለምዶ «የአብዮት ፍንዳታ» እየተባለ ከሚጠራውና
ከ1983ቱ ወያኔና ሻዕብያ አዲስ አበባ ሲገቡ ከነበርንበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው። እንደሚታወቀው ከ1967ቱ የመንግሥት ግልበጣ ማግሥት በሥልጣን ላይ የተሰየመውን ወታደራዊ አምባገነን ቡድን ተጠግተው የራሳቸውን ጠባብ
ፍላጎት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለመጫን በይፋ የተሰለፉ አምስት ድርጅቶች ነበሩ። እነዚህ አምስት ድርጅቶች በተለያየ ስም ይጠሩ እንጂ ሁሉም የኦነግን ጠባብ የፖለቲካ ፕሮግራም አቀንቃኞች ነበሩ።

አምስቱ በሥልጣን ላይ በነበረው ወታደራዊ አገዛዝ ዙሪያ በተለያየ መንገድ ተጠምጥመውበት «የለውጥ ኃይል» በመምሰል ጠባብ ፍላጎታቸውን ያራምዱ የነበሩ ኃይሎች ይፋዊ መጠሪያ «የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽሕፈት
ቤት» የሚል ነበር። እነዚህ ኃይሎች በወታደራዊው ቡድን ዙሪያ በመጠምጠም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተጀመረውን ተቋማዊ የለውጥ እንቅስቃሴ አጨናግፈው በጠባብ ፍላጎታቸው በመተካት በአጭር ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ
ምድር ሰማያዊው የሲዖል በር ተበርግዶ እንዲከፈት አደረጉ። የኢጭአቱ ባሮ ቱምሳ በመርማሪ ኮሚሽን፤ ሌላኛው የኢጭአት መሪ ዘገዬ አስፋውና የማሌሪዱ ዲማ ነገዖ በመሬት ይዞታ፤ የመኢሶኑ ኃይሌ ፊዳ በርዕዮተ ዓለም ቀረጻ፤
የወዝሊጉ ዶክተር ሰናይ ልኬ በብሔራዊ የአገር መከላከያና አቦማ ምትኩ በአብዮታዊ ሰደድ ድርጅቶች ውስጥ በመሰማራትና የ1967ቱን የመንግሥት ግልበጣ ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጣውን ወታደራዊ አገዛዝ በመክበብ፤

ጠባቡን የኦነግ አላማ ጊዜያዊውን የወታደራዊ መንግሥት ሥልጣን [mandate] ተጠቅመው ኢትዮጵያን ወደ መቀመቅ የሚያወርድና የሕዝብን ሉዓላዊነት ለዘለቄታው የሚያናጋ ቋሚ ለውጥ በአገራችን ላይ እንዲካሄድ አድርገዋል።
ከፍ ሲል የቀረቡት የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ ድርጅቶችና ተከታዮቻቸው የደርግ አገዛዝ ተወግዶ ወያኔ ሻዕብያን ተከትሎ አዲስ አበባ ከገባ በኋላም በአንድ የኦነግ ጥላ ሥር ተጠቃለው በመሰባሰብ በደርግ ዘመን በ1967 ዓ.ም.
ጊዜያዊውን የመንግሥት ሥልጣን ተጠቅመው ያደረጉትን አይነት ቋሚ ጉዳት ያስከተለ የውድመት ተግባራቸውን ቀጥለዋል።

በ1983 ዓ.ም. ወያኔንም ተጠግተው የሽግግር መንግሥቱን ሥልጣን ተገን በማድረግ ቋሚ ጉዳት የሚያስከትሉትን ዘረኛነትን ሕጋዊ ማድረግን፣ ኢትዮጵያን በጎሳ ክልሎች መሸንሸንንና የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊትን መበተንን በግንባር ቀደምትነት የፈጸሟቸው አገራዊ ጉዳቶች ናቸው። በ1983 ዓ.ም. በአንድ ኦነግ ጥላ ሥር ተሰባስበው የነበሩት ኦነጋውያን፤ ከሽግግሩ ወቅት በኋላ ወደ ብዙ ግንባሮች ተበታትነው የቆዩ ቢሆንም፤ ዛሬ ላይ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ የሚመስል ነገር መከሰቱን ስላዩ፤ የኦነግን ፕሮግራም
የሚያቀነቅኑ ሌሎች ድርጅቶችን ጭምር በማቀፍ አምስት ሆነው በመሰባሰብ «ሽግግር» የሚመስልን ጊዜ እየጠበቁ ሥልጣን በመጠምጠም የተካኑበትን ያንኑ ጠባብ ፍላጎታቸውን ወደ ቋሚ ለውጥ እንዲሸጋገር እያደረጉ ነው። ባለፈው
ሳምንት መግለጫ ያወጡት አምስቱ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች አሁንም «የለውጥ ኃይል» እየተባለ የሚጠራውን የተጠጉት በ1967 ዓ.ም. «የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት» ሆነው፤ በ1983 ዓ.ም. ደግሞ «የሽግግር
መንግሥት» አካል ሆነው ያደረጉትን ከጠባብ ፍላጎታቸው የሚመነጨውን አገራዊ ጉዳት ቋሚ ለማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ከዘመን መገጣጠም ባሻገር በግልጽ የተካኑበትን ስልታቸውን ተግባራዊ ስለማድረጋቸውም ምልክቶች እየታዩ
ነው። የአዲስ አበባ ሕዝብ በሚከፍለው ግብር ኦሕዴድ/የአሁኑ ኦዴፓ አዲስ ሕግ አውጥቶ የሾመው ጊዜያዊ ምክትል ከንተባ ማንም ሳይጠይቀው የአዲስ አበባ ግብር ከፋይ ሕዝብ የአፍ መፍቻ ቋንቋው ኦሮምኛ የሆነ ይመስል በነበረው የትምህርት
ሥርዓት ላይ «የራሴ» የሚለውን ቋንቋ በመደረብ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ኦሮምኛ የአዲስ አበባ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የትምህርት መስጫ ቋንቋ እንዲሆን አድርጓል። የአዲስ አበባ ጊዜያዊ ከንቲባው በ2011 ዓ.ም. ጊዜያዊ ሥልጣኑን
ተጠቅሞ የአዲስ አበባን የትምህርት ሥርዓት የለወጠው ልክ ኢብሳ ጉተማ በ1983 ዓ.ም. የሽግግር መንግሥቱን ጊዜያዊ የትምህርት ሚንስትርነት ሥልጣኑን ተጠቅሞ የኢትዮጵያን የትምህርት ሥርዓት ለመለወጥ በገባበት በር ገብቶ ነው።
እንግዲህ! ዛሬ ላይ የደረስንበት «የለውጥ ሂደት» እየተባለ የሚጠራው ወቅት፤ ከ1967ቱ የደርግ ጊዜያዊ መታደራዊ አገዛዝ ዘመን ጅማሮና ከ1983ቱ የወያኔ ዘመን የሽግግር መንግሥት ጊዜ የተለየ የሚያደርገው አንዳች ነገር የለም።
በ1967 ዓ.ም. በጊዜያዊው ወታደራዊ መንግሥት ደርግ ላይ ተጠምጥመው ጠባብ ፍላጎታቸውን ወደ ቋሚ ለውጥ የቀየሩ ቡድኖች፤ በ1983ቱ የሽግግር ወቅት ተጠቅመው የአገርን መገነጣጠል ሕጋዊ የሚያደርገውን የፖለቲካ
ፕሮግራማቸውን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እንዲሆን ያስደረጉ ቡድኖች፤ ዛሬም እንደ አለፉት ጊዜያት ሁሉ «የለውጥ ሂደት» የሚባለውን ተጠግተው ጠባብ ፍላጎታቸውን ወደ ቋሚ ለውጥ እያስቀየሩ ናቸው።

«መጤ» እየተባለ እየተካሄደ ያለውን ሕዝብ የማፈናቀል የዘር ማጽዳት ድርጊት አዲስ ነገር አይደለም። የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች በ1967 ዓ.ም. ምስኪኑን የአማራ ገበሬ በጦር እየወጉ፤ በመሬት ከበርቴ ስም ከመሬቱ
አፈናቅለውታል። የ1967ቱ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ መንግሥት ዘመን፤ የ1983ቱ የሽግግር ዘመንና ከ2011 «የለውጥ ሂደት» የሚለየው፤ ሕቡዕ የነበሩ እንደ ሻዕብያ አይነት ድርጅቶች በግልጽ ወጥተው ወደ ጠረጴዛው በመቅረብ ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው የኦነግና የወያኔ ፕሮግራም አቀንቃኞች ጋር መቀላቀላቸው ነው። የ1983ቱ የሽግግር ዘመን ከ2011ዱ «የለውጥ ሂደት» እና «የመደመር እሳቤ» የሚለየው ደግሞ ወያኔ እጅግ መጎልመሱ፣ ኦነግ ከነትጥቁ
አገር ቤን እንዲንቀሳቀስ ተፈቅዶለት ጦር ጭምር የሚሰብቅ ጎረምሳ መሆኑና ሻዕብያ አርጅቶ «የለውጥ ሂደት» ዘዋሪዎች ነን የሚሉትን ከአኮረፉት የፕሮግራም ተጋሪዎቻቸው ጋር አስታራቂና አንጋሽ መሆኑ ብቻ ነው።
መደመር የሚለው አዲሱ የፖለቲካ ትርክት በውስጡ አዎንታዊ የሆኑ አስተሳሰቦች ቢኖሩትም አገዛዙ የተዋቀረበት ጸረሕዝብ ርዕዮተ ዓለም እሳቤውና የቆመበት የፖለቲካ መሠረት ግን ከመደመር ጋር ፊት ለፊት የሚላተም ነው። በመሆኑም
በዘመነ-መደመር የእርስ በእርስ ግጭትና መተላለቅ መገለጫችን ሆኖ ተቆርቋሪ የሌላቸው ደሃዎች፣ ሴቶችና ልጆች በማንነታቸው ምክንያት በገጀራ እየተቆራረጡ ሜዳ ላይ እየተጣሉ ነው። የተረፉት ደግሞ በአገራቸው ውስጥ ስደተኛ
ሆነው ከአንዱ መጠለያ ወደሌላ መጠለያ እየተባረሩ የቁም ስቅላቸውን እያዩ ይገኛሉ። በዘመነ-መደመር ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በአገር ውስጥ በተካሄደ የሕዝብ መፈናቀል አንደኛ ሆናለች። ኦሮምያ ክልል በሚባለው አካባቢ ታጥቆ
በስፋት እየተንቀሳቀሰ ያለው ኦነግ፤ ኦሮሞ ያልሆነውን፤ በተለይም ደግሞ ዐማራውን ለይቶ የማጥፋትና የማፈናቀል ዘመቻውን እንደ አዲስ በቅርቡ እንደሚጀምር ውስጥ ውስጡን እየተላለፉ ያሉ መልእክቶች ይጠቁማሉ። በመንግሥትነት
የተሰየሙት የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች፤ ኦሮሞ ላልሆነው በአደባባይ እየጻፉት ያለው ማስጠንቀቂያ ከዚህ ጋር አብሮ የሚታይ ነው። እነዚህ ወገኖች ወደ አገር ቤት የገቡት፤ በተለይም ደግሞ አዲስ አበባ ላይ አንጻራዊ ድጋፍ ይኖራቸዋል
የሚባሉትን በአንድነት ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች እንደ ሥጋት ስላዩዋቸው፤ ከወዲሁ ለማጥፋት የቆረጡ ይመስላል። ቡራዩ ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ በማን ታቅዶ በእነማን እንደተካሄደ ሰለባዎቹ ራሳቸው እየተናገሩ፤ በመንግሥትነት
የተሰየሙት የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች ግን አጋጣሚውን በመጠቀም ሌሎችን በደረቁ በመወንጀል የአዲስ አበባ ወጣቶችን «የግንቦት ሰባት አባላት» እያሉ በማፍስ ወደ ወታደራዊ ጣቢያዎች እያጋዙ የሌላውን ጩኸት በመቀማት
ኦነግን ከደሙ ንጹሕ አድርገው ለመከላከል እየተረባረቡ ይገኛሉ።
የአገዛዙ መዋቅር የተዘረጋው የጎሳ ግጭት እየተፈጠረ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ እየተከሳከሱ ሞትን ሲያነግሱ በአልጋው በየጊዜ የሚቀመጡቱ ለእድሜ ይፍታሽ እየተፈራረቁ እንዲገዙ ተደርጎ ስለሆነ፤ ወደፊትም እስካሁን ያየነው አይነት ዘግናኝ
የጎሳ ግጭት መቀጠሉ አይቀሬ ነው። በፋሽስት ወያኔ ተስፋፊነት አማካኝነት በተነጠቁት የአባቶቻቸው ርስት የተነሳና እየተካሄደ ባለው የዘር ማጥፋት ምክንያት በወሎና በጎንደር ያሉት ዐማሮች ውስጥ ያለው ንዴት ቀላል አይደለም።
ኦነግ «ኦሮሚያ» በሚለው አካባቢ ኦሮሞ ብቻ የሚኖርበት አገር ለመገንባት እየተዋጋ ነው። ኦብነግ በሰላማዊ መንገድ ይሁን እንጂ ለመገንጠል ትችላለህ የሚል ማደፋፈሪያ ተሰጥቶታል። ሌላውም በየጎራው እያብላላው ነው። የጎሳ
ግጭት አንዴ ከተነሳ ግጭቱ እየፈጠረው ያለው ትርምስና መተላለቅ በራሱ ኃይል እየተቀጣጠለ ስለሚስፋፋ ለማቆም አስቸጋሪ ነው።

ባሳለፍነው ሳምንትም የኦነግ ታጣቂዎች በምዕራብ ወለጋ በጉሙዝ የጸጥታ ኃይሎች ላይ የፈጸሙትን ግድያ ተከትሎ በተቀሰቀሰው የጎሳ ጥቃት ከ80 ሺህ በላይ ዐማራና ኦሮሞ በሁለት ቀናት ውስጥ «ቤንሻንጉል ጉሙዝ»
ከሚባለው ክልል ውስጥ ሲፈናቀሉ፤ ከሰባ በላይ ንጹሐን ዜጎች ደግሞ በግፍ ተገድለዋል። በዚህም የተነሳ በዘመነ መደመር ሰላም የለም። ወደፊትም ድኅነት፣ ችጋርና ዘረኛነት ጭካኔን እየወለደ፤ ጎሰኛነት እሳር እያርከፈከፈ፤ በጥላቻና
በቂም ታውረን በአገራችን የተከፈተው የሲዖል በር መገርገዱ አይቀሬ ነው።

በመደመር ስም ተደራጅተውበት በመንግሥትነት በተሰየሙት አካላት እያደረጉት ባለውም ሂደት፤ ወደፊት ካለፈው የባሰ እንጂ የሚሻል ነገር እንደማይመጣ ከአሁኑ ግልጽ የሆነ ይመስላል። የወደፊቱን የከፋ የሚያደርገው ዛሬ ላይ
መንግሥታዊ መዋቅሩን ተጠቅመው ኦነግ የሚፈጽመውን ግድያ ለመደበቅ ያላቸውን ልዩ ችሎታ ከመጠቀም የማይሳሱት በመንግሥትነት ተሰይመው ኃላፊነት ግን የማይሰማቸው የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃቃኝ የሆኑ ባለሥልጣናት በመደመር
ስም ቁጥራቸው እያደረ እየጨመረ በመሄድ ላይ ስለሆነ ነው።
ይህ ሁሉ ምስቅልቅል ሕጋዊ የሆነው የወያኔ ጎሰኛነት የወለደው ደዌ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው የኃይል አሰላለፍም የወያኔና የኦነግን ፕሮግራም የሀሳብ መስመር መሠረት ያደረገ ነው። የወያኔን ፕሮግራም በመቃወም ዙሪያ
ጠንካራ የኃይል አሰላለፍ ተፈጥሮ ጸረ-ሕዝብ፣ ጸረ-ሀገርና ሕገ ወጥ የሆነው አገዛዙ የተዋቀረበት ርዕዮተ ዓለምና ርዕዮተ ዓለሙ የወለደው ሕገ አራዊት ዋጋ እንዲያጣ ሆኖ እስካልተወገደ ድረስ ግን፤ ኢትዮጵያውያንን እያጫረሰ ያለው የወያኔ
ሕገ መንግሥት የወለደው ግፍና ጭካኔ የጊዜ ጉዳይ እንጂ በየተራ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ላይ መፈጸሙ የማይቀር ነው።

ከመደመር ሒሳብ አቀንቃኙ ከዓቢይ አሕመድ አፍ ማር ቢዘንብ እንኳ ተፈጻሚ የሚደረገው ጸረ-ሕዝብ፣ ጸረ-ሀገርና ሕገ ወጥ የሆነው ርዕዮተ ዓለምንና ታሪክን እየደገምን፤ የነበረንን እያጣን፤ በጎሰኛነት ሞተር እየተነዳን፤ በመከሳከስ ሞትን
እያነገሥን እንተላለቃለን እንጂ ሌላ የተሻለ ነገር አይመጣልንም። ጸረ-ሕዝብ፣ ጸረ-ሀገርና ሕገ ወጥ የሆነው የወያኔ ሕገ አራዊት እስካለ ድረስ የሕግ የበላይነት፣ ንብረት የማፍራት፣ ዜጋ የመሆን፣ የሕይወት ጥበቃ፣ ወዘተርፈ የሚባሉትና
ለሰው ልጅ ኅልውና የሚያስፈልጉት ሁኔታዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጠሩ አይችሉም። «ፌዴራሊዝሙን ሊያፈርሱ፤ ቋንቋና ማንነት ሊደፈጥጡ፤ የድሮ ሥርዓት ሊመልሱ፣ ወዘተርፈ» የሚለውን የኦነግና የወያኔ ፕሮግራም አቀንቃኞች
የሐሰት ክስ ያለ ርኅራሔ መጋፈጥ ያሻል። ስለሆነም ዛሬ ላይ ኢትዮጵያውያንን እያፋጀ ያለው የወያኔ ሕገ አራዊት ሲዘጋጅ ያልተወከሉና እንዲገለሉ የተደረጉ ዜጎች ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሕገ-ወጡን የወያኔ ፕሮግራም በማፍረስ ዙሪያ
የጋራ ግንባር ፈጥረው «ሕገ መንግሥት» ተብዮው ተወግዶ በሕዝበ ውሳኔ የሚጸድቅ ሕገ መንግሥት እንዲዘጋጅ ወደ ተግባር የሚለወጥ [workable] መርሐ ግብር አውጥተው በቋሚነት ሊታገሉ ይገባል። ሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅትም
የዜጎችን መብት፣ ሰላምና አንድነት ለሚያመጣ ሕገመንግስት አውን መሆን የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁነቱን ያረጋግጣል።

ኢትዮጵያ በቆራጥና ጀግኖች ልጆቿ መስዋዕትነት ለዘለዓለም ጸንታ ትኖራለች!
ፈለገ አሥራት የትውልድ ቃል ኪዳናችን ነው!

የዐማራው ሕልውና መጠበቅ ለትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው!
ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.