ፍትህ በወረራ ለተያዙ ራያ፣ ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ወገኖቻችን!!

የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ድርጅታዊ መግለጫ

ወያኔ የሽግግር መንግስት ከሚባለው በፊት ጀምሮ በወረራ በያዛቸው ወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት፣ እንዳ መሓሪ፣ በራያ አዘቦ፣ ወፍላ፣ አላማጣና እንዲሁም በሂደት መተከልን ጨምሮ በወገኖቻችን ላይ ዛሬም ድረስ ተባብሶ የቀጠለው ግድያ፣ አፈና፣ ማፈናቀልና ዐይን ያወጣ ሕገወጥ ድርጊቶች እንዲቆሙ የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት ያለምንም ቅድመ  ሁኔታ  የመከላከያ ሰራዊት በአስቸኳይ በመላክ ወገኖቻችንን ከባሰ ጥቃትና ግድያ እንዲታደግ ጥቅምት ፭ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ) ልሳን በሆነው መቅደላ ልዩ
ዕትም ቁጥር ፴ ና ከዚያም በፊት በተከታታይ በወጡ ልዩ ዕትሞች ቁጥር ፳፰ና ፳፱ ጥሪ ተደርጎ ነበር።

ይሁን እንጅ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ቅድሚያ ለሚሰጠው አሳሳቢ ጉዳዩች ትኩረት ሰጥተው ለቀረበላቸው አስቸኳይ ጥሪ ተገቢውን እርምጃ ባለመውሰዳቸው…. ይሄውና ሳምንቱን ሙሉ በራያና አካባቢው ባሉ የዐማራ ወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግድያ፣ አፈናና ማፈናቀል ሙሉ በሙሉ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ችሏል። የትግራይ ልዩ ኃይል የሚባለውና ስውር ታጣቂዎች ያላቸውን ኃይል በሰላማዊ ወገኖቻችን ላይ እየተጠቀሙ ነው!!

ብዙ ወጣቶች በአደባባይ እየተገደሉ ከመሆኑ ባሻገር እስካሁን ድረስ በሽዎቹ የሚቆጠሩ የራያና አካባቢው ወጣቶችን የትግራይ ልዩ ኃይል ከመንገድና ከየቤታቸው አፍሶ የት እንደ አደረሳቸው አይታወቅም!! በተመሳሳይ ሁኔታ በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ያለው ሁኔታ አሁን ራያ ካለው አሰቃቂ ሁኔታ የተለየ አይደለም። ግደያው፣ አፈናውና ማፈናቀሉ አሁንም በፈረቃ ተፋፍሞ ቀጥሏል።!   በመሆኑም የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ) በራያና አካባቢው ባሉ ወገናችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ሁለንተናዊ ጥቃት በጽኑ ከማውገዝ ባሻገር የቱንም ያህል ትግሉ አስቸጋሪና ውጣ ውረድ የበዛበት ይሁን እንጅ የወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት፣ እንዳ መሓሪ፤ በራያ አዘቦ፣ ወፍላና አላማጣ እንዲሁም መተከል
በወገኖቻችን የተነሳው ሕጋዊ ጥያቄ ተገቢው ሕጋዊ መልስ ሳያገኝ ለአፍታም እንኳ ቢሆን ቸል የማይለው ከመሆኑ ባሻገር የሚከተሉት ጉዳዮች ዛሬም በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆኑ በድጋሜ (ዐኅኢአድ) ይጠይቃል፦

፩ኛ/ የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት አሁንም የጉዳዩን አሳሳቢነት ክፍተኛ ግምት በመስጠት
የመከላካያ ሰራዊትና ሁኔታውን በአካል ተገኝቶ የሚቆጣጠር መንግስታዊ አካል ወደ ቦታው በመላክ
የሰላማዊ ወገኖቻችንን ሕይወት በአስቸኳይ እንዲታደግ፣

፪ኛ/ የወያኔ ልዩ ኃይል ከላይ ከተጠቀሱት ሁሉም አካባቢዎች በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ እንዲደረግ፣

፫ኛ/ መላው የዐማራ ነገድ ተወላጅ የሆነና የጉዳዩን አሳሳቢነት በአዘን እየተመለከተ ያለው የኢትዮጵያ
ሰላም ወዳድ ሕዝብ በሰላማዊ ወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግድያ፣ አፈናና ማፈናቀል በጽኑ
እንዲያወግዘውና ከራያና አካባቢው ወገኖቻችን ጋር በአስቸኳይ አብሮ እንዲቆም በአክብሮት
እንጠይቃለን፣

፬ኛ/ ኢሕአዴግ በአዋሳ በ11ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባዔ እና ብአዴን (አዴፓ) በ12ኛ የምክር ቤት ስብሰባ
ያስተላለፉትን ውሳኔ ተግባራዊ በማድረግ ችግሩ በተፈጠረባቸው ወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት፣ እንዳ
መሓሪ፣ በራያ አዘቦ፣ ወፍላ፣ አላማጣና እንዲሁም በሂደት መተከልን ጨምሮ እየተፈጸመ ያለውን የሕዝብ
እልቂት በአስቸኳይ በሕግ እንዲያስቆሙ እንጠይቃለን፣

የዐማራ ኅልውና መጠበቅ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው!!                                                                               

  የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.