ራያና የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር/ ትህነግ/ ተላላኪዎች ጉዳይ (ምስጋን በላይ)

ቅድመ ኢህአዴግ ኢትዮጵያ ራያ በሁለት አስተዳደር ተከፍሎ አንደኛው ራያ፣ ራያና አዘቦ በትግራይ ክፍለ ሐገር ሌላኛው  ደግሞ ራያና ቆቦ ተብሎ በወሎ ክፍለ ሐገር ይተዳደር እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር /ትህነግ/ የተመራው ኢህአዴግ በ1982 ዓመተ ምህረት ነሐሴ ላይ የራያን አካባቢ ተቆጣጠረ። ልክ እንደሌሎች የሰሜን ወሎ አካባቢዎች የራያና ቆቦ አውራጃ ዋና መቀመጫ የነበረው የአላማጣ ወረዳና የዋግ አውራጃ አካል የነበረው የወፍላ ወረዳም (ኮረም) በታምራት ላይኔ  ይመራ በነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን) ክፍለ ህዝቦች ከ1983 – 1985 ዓመተ ምህረት ይተዳደር ነበር። የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት የነበረው አቶ ዮሴፍ ረታ የአላማጣ ክፍለ ህዝብ በመሆን አላማጣን ካስተዳደሩ ታጋዮች አንዱ ነበር።  በዚህ ወቅት በአላማጣና አካባቢዋ የመሬት ስሪት /ማከፋፈል/ እንደ አዲስ የተከናወነ ሲሆን የማከፋፈሉን ሂደት የመሩት እነ ሠናይ ገብረ መድኅንና ሲሳይ መንግስቴ የመሳሰሉ የኢህዴን ታጋዮች ነበሩ። ከ1985 ዓመተ ምህረት በኋላ ግን እንዴት እንደተወሰነ ሳይታወቅ እነዚህ ወረዳዎች ወደ ትግራይ ክልል በማካለል በትህነግ መሪር አገዛዝ ስር እንዲወድቁ ተደረገ።

እንደ ራያዎችና አንዳንድ የኢህዴን ነባር ታጋዮች ዕይታ የወሎ ክፍለ ሐገር አካል የነበሩት እነዚህ ሁለት ወረዳዎች ወደ ትግራይ በዚህ ወቅት የተካለሉት ስለራያ ጉዳይና የኢህዴን የውስጥ ድርጅት ነጻነት በተመለከተ ከትህነግና የትህነግ ተላላኪ ከነበሩ የኢህዴን ከፍተኛ አመራሮች ጋር ሽንጡን ገትሮ ይሟገት የነበረው ይርጋ አበበ (ሓው ጃኖ) ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሊገባ ልክ አንድ ወር ሲቀረው (ሚያዚያ 20 ቀን 1983 ዓመተ ምህረት) በወያኔ ሴረኝነት በታደሰ ካሳ /ጥንቅሹ /፣ ህላዌ ዮሴፍና በረከት ስምዖን አቀናባሪነት ከተገደለ በኋላ ነው። ትህነግ አዲስ አበባ እንደገባ የአላማጣ ወረዳና የወፍላ ወረዳን ወዲያዉኑ ወደ ትግራይ ያላካተተበት ምክንያት ህዝቡ በይርጋ ሞት እጅግ ያዘነበትና የተቆጣበት ጊዜ ስለነበርና በራያ አካባቢም በትህነግ ላይ ልዩ ልዩ ተቃወሞዎች ይነሱ ስለነበር እነዚህ ተቃዉሞዎች እስኪረግቡ ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው። ሆኖም ግን  በኢህአዴግ ስም ትህነግ በአካባቢው እንደ ጆፌ አሞራ ስያንዣብብ እንደነበር ይታወቅ ነበር። የትህነግ መስራች የነበረና ኋላ ላይ ከድርጅቱ የተባረረው ካህሳይ በርሄ በጻፈው መጽሐፉ እንደተገለጸው የራያ አካባቢ (ራያና አዘቦ ጨምሮ ) በትግራይ ክልል ስር መካለል የለበትም የሚል ከፍተኛ ተቃውሞ በሽግግሩ መንግሥት የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንስተው ነበር። ይሁንና በ1987 ዓመተ ምህረት ሕገ መንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት ራያዎች ሳይመክሩበትና ሳይፈቅዱ በ1985 ዓመተ ምህረት ትህነግ የራያን አካባቢ በጉልበት ወደ ትግራይ በማካተት የግዛት ማስፋፋት ህልሙን  ዕውን  እያደረገ ነበር። ምንም እንኳን  ሕገ መንግሥቱ የክልል አወቃቀር የደነገገውና ያጸደቀው  በ1987 ዓመተ ምህረት ቢሆንም ትህነግ ለራሱ ጥቅም ሲሆን ሕግና ሥርዓት ቦታ የላቸውም። ለዚህ ነው የራያ አካባቢ ወደ ትግራይ የተካለለበት መንገድ  ከመነሻው ሕገ ወጥ ነበር የሚባለው። ይህ ደግሞ የራያ መሬት በጉልበተኛው ትህነግ በወረራ የተወሰደ መሆኑ ሊሰመረበት ይገባል።

ሰሞኑን በራያ አላማጣና በራያ አዘቦ ከተሞች የሚኖሩ ራያውያን “የራያ ማንነት መወሰን ያለበት በራያዎች ነው” በማለታቸው ብቻ ለትግራይ ልዩ ኃይል ስናይፐርና መትረየስ ጭፍጨፋ መጋለጣቸው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ዘዴዎች የዘገቡት ጉዳይ ነው። የትግራይ መንግሥት ለራያ ህዝብ ስለማንነትህ እኔ አውቅልሃለሁ፤ እኔ ያልኩህን ካልሆንክ ወይም እኔን መስለህ ካላደርክ መልሴ ጥይት ነው እያለ መሆኑ ሰሞኑን የተወሰዱ ኢሰብአዊ ዕርምጃዎች ማሳያዎች ናቸው።እርምጃዎቹ ግድያን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ከአላማጣ ታፍሰው የት እንደገቡ እስካሁን ድረስ አይታወቅም። ከዚህ በተጨማሪ የራያ ተወላጅ የሆኑ በርካታ ባለሃብቶች፣ ምሁራንና የአገር ሽማግሌዎች ስነ ልቦናቸውና ሞራላቸው ለመጉዳት በማሰብ በገዛ ህዝባቸውና ወገናቸው ፊት በሰንሰለት ታስረው እየተደበደቡ መቀሌ ውስጥ መከራና ስቃይ እየተቀበሉ ይገኛሉ።

የራያ ህዝብ ጥያቄ አሁን ለምን የበለጠ ተጋጋለ? ብለው ለጉዳይ ሩቅ የሆኑ ሰዎች ሊጠይቁ ስለሚችሉ ማብራራቱ ጠቃሚ ይሆናል። የራያ ህዝብ ያለፍላጎቱ ወደ ትግራይ ክልል መካለሉ ከላይ ተጠቅሷል።  በዋነኛነት ግን የራያ ህዝብ የበይ ተመልካችኔት ይቁም ፣ ማንንቴና ባህሌ ይከበር፣ የራሴን አካባቢ በራሴ ላልማና ተጠቃሚ ልሁን ነው እያለ ያለው። እዚህ ላይ መታወቅ የሚገባው ነገር ላለፉት 27 ዓመታት ራያን የሚያስተዳድሩት ከአድዋ አካባቢ የሚመደቡ የትግራይ ሰዎች ሲሆኑ ትምህርታቸውም ከአራተኛ ክፍል ያልዘለሉ የፊደል ሽፍታዎች ናቸው። ከመሬት ጋር በተያያዘ እጅግ በርካታ ቁጥር ያለው ወጣት የገበሬ ልጅ መሬት አጥቶ ስራ ፍለጋ ወደ አረብ አገር እየተሰደደ ባለበት ሁኔታ ከገበሬው ባልተሻለ ባህላዊ የአመራረት ዘዴ የሚጠቀሙ እንቨስተር የሚል ታፔላ የተሰጣቸው የትግራይ ተወላጆች መሬቱን ተቆጣጥረዉት ይገኛሉ። የራያ ገበሬም መልሶ የእነሱ ወዛደር በመሆን ራሱ አርሶ መጠቀም ሲችል ለእነሱ እያመረተ ይሰጣል። የከተማ ቦታም ግልጽ የሆነ አድልዎ በማድረግ  በሊዝ የሚሰጡት አካባቢዉን ለማያውቁ የትግራይ ሰዎች ብቻ መሆኑ ራያዎች በየጊዜው ሲታዘቡ ኑረዋል።ይህም ዘዴ የአካባቢውን ዲሞግራፊ ለውጥ እያመጣ እንደሆነ ግልጽ እየሆነ ሄደ።በየጊዜው ወደ ራያ የሚመደቡ የትግራይ አስተዳዳሪዎች ሁሉ እንደ ኗሪ ሰው ሰፊ የከተማ ቦታ ይመሩና ወደሌላ አካባቢ ሲመደቡ የተመሩትን የከተማ ቦታ በብዙ ሺህ ብር በመሸጥ በሙስና ከሚያገኙት በተጨማሪ የከተማ ቦታ ሽያጭ አንዱ የገቢ ምንጫቸው ነው። በአላማጣም ሆነ በሌላ የራያ ከተሞች የሚመደብ አስተዳዳሪ ቦታ ሳይመራና ሳይሸጥ የተመለሰ ካድሬ የለም ቢባል ሰው ላያምን ይችላል። ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመት እየሆነ የነበረው/ ያለው/ ዕውነታ ግን ይሄው ነው። ምክንያቱም መሬቱን የሚያከፋፍሉት መሃንዲስ ተብዬዎችም የሚመደቡት ከአድዋ አካባቢ ስለሆኑ ለምን ብሎ የሚጠይቅ ሳይሆን  ይልቅ የወንዜ ልጅ ተያይዘን እንዝረፍ የሚል እንጂ።

ሌላው አሳዛኝ ጉዳይ ትህነግ በዚህ ሳይወሰን የራያ ማንነት መገለጫ የሆኑ ነባር የቦታ ስሞችና ተቋማት ለራያ ህዝብ ባህልና ዕሴት  ጠቀሜታና ተያያዥነት በሌላቸው ስሞች የመተካቱ ጉዳይ የራያ ህዝብ “ትህነግ ፍላጎቱ ምንድን ነው?” ብሎ እንዲጠይቅ አድርጎታል። ይህ አልበቃ ብሎት እንደ ትምህርት ቤት የመሳሰሉ ተቋማት ለራያ ህዝብ ምንም አስተዋጽኦ ባላደረጉ የትግራይ ታጋዮች መሰየሙ ራያ ያፈራቻቸው ስንት ጀግኖች እያሉ በትግራይ ሰዎች ስም መሰየሙ የራያ ህዝብ የራሱ ጀግና የለውም ማለታቸው ይሆን? ብሎ እንዲጠይቅ አድርጎታል። ሌላው ማሳያ በተማሪዎቹ ውጤታማነት በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ  ስምና ዝና የነበረው የ“ታዳጊዋ ኢትዮጵያ አጠቃላይ 2ኛ ትምህርት ቤት” ይዞታ በመውረር የትግራይ ሰዎችን  ብቻ በመምረጥ ማከፋፈላቸው ሰዉን  በአንድ ወቅት ያስገረመው ጉዳይ ነበር። ይህ ሳያንሳቸው ትምህርት ቤቱን ለማዳከም ሲሉ በታዳጊዋ ኢትዮጵያ ይሰጥ የነበረውን  የመሰናዶ ትምህርት በራሳቸው ታጋይ ስም ወደሰየሙት “ኢያሱ በርሄ  ትምህርት ቤት” አዛውረዉታል። መቼም የትህነግ ጸብ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነት ጋር ስለሆነ በአንድ ወቅት “ታዳጊዋ ኢትዮጵያ ትምህርት ቤት”ን መለስ ዜናዊ ብለን ካልሰየምነው ሙተን እንገኛለን ብለው ቢነሱም የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና ወላጆች ባደረጉት ከፍተኛ ተቃውሞ ሌላ ትምህርት ቤት “ዝክረ መለስ” ብለው ከሰየሙ በኋላ “ታዳጊዋ ኢትዮጵያ” ይባል የነበረውን ትምህርት ቤት አውጥተው አውርደው “አላማጣ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ” ብንለው የአላማጣ ህዝብ አይቃወምም በማለት ትምሀርት ቤቱ ከተመሰረተበት ዘመን ጀምሮ ይጠራበት የነበረው “ታዳጊዋ ኢትዮጵያ” የሚለዉን ስም ማስወገድ ችለዋል።

የራያ ህዝብ (ወልቃይትን ጨምሮ) እየደረሰበት ላለው ስቃይና መከራ ከትህነግ ቀጥሎ መጠየቅ ያለበት የራያን ህዝብ ለዚህ ክፉ አውሬ አሳልፎ የሰጠው የቀድሞው ኢህዴን/ ብአዴን ከፍተኛ አመራር ነው። በራያ ተወላጅነታቸው የሚታወቁት የኢህዴን/ ብአዴን ከፍተኛ አመራር የነበሩት ከበደ ጫኔ  እና  ታደሰ ካሳ / ጥንቅሹ/ በቅርቡ ከአዴፓ ሥራ አስፈጻሚነት ተወግደዋል። የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በራያ ህዝብና በወልቃይት ህዝብ ለሚነሱ የማንነት ጥያቄዎች በትህነግ የሚመራው መንግሥት በሠላማዊ መንገድ ሊፈታው ይገባል። የትግራይ ክልል ጸጥታ መደፍረስ ለአማራ ክልልም ጠንቅ ነውና በማለቱ ከትህነግ በኩል የተሰጠው ምላሽ በጣም አሳፋሪና አንድ ሃላፊነት ከሚሰማው አካል የማይጠበቅ እንደሆነ ግልጽ ነው። ወግ አሳመርኩኝ ብሎ የትህነግ ተላላኪው ጌታቸው ረዳ ስለአዴፓ መግለጫ ሲጠየቅ “ትግሬዎች ናችሁ ብለህ ከድርጅትህ አመራርነት አባርህ  ስታበቃ እነሱ የተወለዱበት ቦታ ግን የኛ ነው ማለት አይቻልም፤ አንዱን መምረጥ አለብህ!” ይላል። እዚህ ላይ ጌታቸው ሊያወራ የፈለገው የአላማጣ ተወላጅ ስለሆነው ከበደ ጫኔና ሰለየወፍላው ተወላጅ ታደሰ ካሳ መሆኑ ግልጽ ነው። ጌታቸውም ሆነ ሌሎች የትህነግ አመራር አባላት እንደሚያውቁት ከበደም ሆነ ታደሰ የተባረሩት በማንነታቸው ምክንያት ሳይሆን ዕድሜ ልካቸው የውያኔ ቡችሎች/ አገልጋዮች/ ሆነው ያለፉ ሰዎች ስለሆኑ ነው። ከበደና ታደሰ በትግሬነታቸው የሚያምኑ ከነበሩ በ1985 ዓመተ ምህረት የትህነግ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ የነበረው ወንድወሰን ከበደ ከትህነግ ወደ ብአዴን ሲሄድ ለምን እነሱስ ወደ ትህነግ አልሄዱም? ታደሰም ሆነ ከበደ ለአማራ ቀርቶ ለራያም የሚሆኑ ሰዎች አይደሉም። ከበደ ይሰጣቸው የነበሩ ቃለ መጠይቆች ውግንናው ታግዬለትአለሁ ለሚለው ድርጅትና ህዝብ ሳይሆን ለትህነግ እንደነበር በግልጽ አሳይቷል። ታደሰ በይርጋ አበበ ላይ የሰራውን ደባ እንኳን ጌታቸው የራያ አርሶ አደርም አሳምሮ ያውቀዋል።ታደሰ በኢህዴን/ ብአዴን የመሸገ የትህነግ ተላላኪና አስፈጻሚ እንደነበር የቀድሞው የኢህዴን ከፍተኛ አመራር ያሬድ ጥበቡ የትግል ጓዱን ስብዕና እንደሚከተለው ይገልጸዋል፤ “ እግረ መንገዴን ወዲ ዜናዊ የነበረበት ወርኢ ቤዝ-አምባ ስደርስ ሊጣላኝ ነገር የሚፈልግ መለስን አገኘሁት ። ከታደሰ የሬዲዮ መልዕክት ስለደረሰው ነው ብዬ አልጠረጠርኩም ነበር። ከዓመታት በኋላ ነው ታደሰና ታምራት ከወዲ ዜናዊ ጋር በድብቅ የሚገናኙበት የሬዲዮ ኮድ እንደነበራቸው ያወቅነው። ” (ወጥቼ አልወጣሁም ገጽ 256)። እነዚህ ወንጀለኞች ነበሩ እንግዲህ ከአማራው ጋር ተሰልፈው ዕድሜ ልካቸውን ለትህነግ ሲሰሩ የኖሩት። ፍትህ ቢኖር ኖሮማ መጠየቅ የሚገባቸው በሃገር ደረጃ ነበር!

በመሠረቱ ጌታቸው ምንም እንኳን ከተከበሩና ከፍተኛ ስነ ምግባር ካላቸው የራያ ሰዎች የተወለደ ቢሆንም ስለ ራያ ለማውራት ስብዕና የለውም። ትህነግ ለዓላማዋ ስትል ወደ ፖለቲካው ከመመልመልዋ በፊት ያስተምርበት ከነበረው መቀሌ ዩኒቨርሲቲ የተባረረው በስነ ምግባር ጉድለት ምክንያት መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን በመልካም ሥነ ምግባር ያደጉ የራያ ልጆች የራያ ማንነት ይከበር ስላሉ ብቻ “በረንዳ አዳሪዎችና ተላላኪዎች” በማለት ስም ያጠፋል። ለነገሩ ጌታቸው ስም በማጥፋትና እንዳገኘው በመዘባረቅ በኩል ተወዳዳሪ የለዉም። የኮሚዩንኬሽን ጉዳዮች ተጠሪ ሚኒስትር በነበረበት ወቅት የተከበረዉን የኦሮሚያ ህዝብ የገለጸበት መንገድ የሚታወቅ ስለሆነ እዚህ ማንሳት አያስፈልግም ። ይቅርታም አልጠየቀም። ትንታጎቹ የኦሮሞያ ወጣቶች አንድ ቀን “ከበው እንደሚያነጋግሩት” ጥርጥር የለኝም። ልብ ካለው ግን አስቀድሞ ይቅርታ እንዲጠይቅ እመክራለሁ።

ጌታቸው የራያን ህዝብ አዋርዶ ለአዋራጅ የሚሰጥ መሆኑ ከሁለት ሳምንት በፊት አላማጣ ከተማ ተድርጎ የነበረው የትግሬዎች ስብሰባ ጥሩ ማሳያ ነው። በዚህ ስብሰባ ራያዎች ትግሬ ነን እንዲሉ የእንደርታ ተወላጅ የሆነ የታሪክ አጥማቂ ተልኮ ነበር። የታሪክ አጥማቂውና ከላሹ አቶ አድሃና ኃይሌ ይባላል። አድሃና በመጀመሪያ የተሀህት አባል በመሆን እነ ገብሩ አስራት የመሳሰሉትን መልምሎ ወደ በረሃ እንዲገቡ ያደረገ ስለመሆኑ ገብሩ የጻፈዉን መጽሃፍ ማየት ነው። አድሃና ግን ፈሪ ስለሆነ ከጓደኞቹ ጋር በረሃ ለመግባት ቃል ከገባ በኋላ መቀሌ ለነበረው የደርግ መስተዳድር ራሱን በማጋለጥ በዕርዳታ ማስተባበሪያ ድርጅት ተቀጣሪ ሆነ።በኋላም የኢሠፓ አባል በመሆን እስከ ደርግ ዉድቀት ድረስ ያገለገለ ሰው ነው። ከደርግ ውድቀት በኋላ እንደ ፍስሃ ደስታ የመሳሰሉ የትግራይ ሰዎች በኢሠፓነታቸው ምክንያት ለረጅም ዓመታት በወህኒ ቤት ሲማቅቁ ኢሠፓው አድሃና ኃይሌ ግን ምንም ሳይቀጣ በአዲስ አበባ ዩኒቭርሲቲ የታሪክ ሌክቼረር ሆኖ ተቀጠረ። የዶክትሬት ትምህርቱም እንዲቀጥል ሆነ። ሰውየው የስልጣን ጥም ያለው በመሆኑ ትምህርቱን እንደ ጨረሰ በትምህርት ክፍሉ ውስጥ ማስተማር ሲገባው ለስልጣን ሲል ወደ ትግራይ በመሄድ የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ተድርጎ ተሾመ። መቼም ትህነግ ቂሟን ስለማትረሳ እሱ የትግራይ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሆኖ ሲሾም የሰጠችው ቢሮ ድሮ የኢሠፓ ቢሮ የነበረውን ነው። በወቅቱ መቀሌ የነበሩ ሰዎች በሁኔታው ይገረሙና ይቀልዱ ነበር። ትህነግ “አንተ ኢሠፓ የማናውቅህ እንዳይመስልህ!” እያለች በተዘዋዋሪ ማሸማቀቋ ነው ይሉ ነበር። ለነገሩ በስራዉም ቢሆን  ትህነግ ደስተኛ አልነበረችም። ቢሮው ውስጥ ሲጋራዉን እያቦለለ እንቅልፉን ነበር የሚለጥጠው። በኋላም መጣያ ስታጣ ወደ አዲስ አበባ በመላክ የትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ አድርጋ አባረረችው። እዚያም ውጤታማ ስላልሆነ ለፓርላማ አባልነት እንዲወዳደር ከእንደርታ በስደት መጥቶ ወዳደገበት ራያ አዘቦ ስሙ ተልኮ ያለምንም ተወዳዳሪ የራያ አዘቦ (መሆኒ) ህዝብ ተወካይ ተብሎ የእንቅልፋሞች መነሃሪያ ወደነበረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለእንቅልፍና ለጭብጨባ ተቀላቀለ።  ከሁለት ሳምንት በፊት አላማጣ ተገኝቶ የራያን ህዝብ በውሸት ታሪክ ለማጥመቅ ሲታትር ሰንብቶ ትህነግንና ራሱን ያዋረደበት ራያ ማለት “የከብት ስብስብ ነው” ነው በማለት እሱም  እንደ ጌታቸው ረዳ ህዝብን ሲሳደብ ሰንብቶ ራያዎች አጸፋዉን በሰላማዊ ሰልፍ “ራያ የኩሩ ህዝብ  ስም መጠሪያ እንጂ እንዳንተ ዓይነት እንከፍ ራያን ሊገልጸው አይችልም። ራያ ራያ እንጂ ትግሬ አይደለም” ብሎ ትህነግ ወደማትወጣው ጣጣ እንድትዳክርና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ  በራያ እየተፈጸመ ያለዉን ዘር ተኮር ጥቃት በንቃት እንዲከታተለው በር ከፍቷል።

#አፋር_አሳዛኝ_ውሎ የአፋር ወገኖቻችን በዚህ መልክ ሲንገላኑ ውለዋል ይሄን ግፍ ሁሉም ይመልከተው ?

Posted by Tilaye ZE on Saturday, October 27, 2018

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.