የእንግዳውን ኪሳራ ማን ይክፈለው? ማሕሌት ፋንታሁን)

እንግዳው ዋኘው ይባላል፤ ትውልዱ እና ዕድገቱ በሰሜን ጎንደር ዞን፣ ታች አርማጭሆ ወረዳ ነው። የ33 ዓመት ወጣት ሲሆን፤ ከ1997 ወዲህ (በ1997፣በ2005 እና ከ2007—2009) ሦስት ጊዜ ለእስር ተዳርጓል። ከ1996 ጀምሮ በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ገብቶ በመሳተፍ ትግል የጀመረው የቅንጅት አባል በመሆን ሲሆን አንድነት ፓርቲ በምዕራብ አርማጭሆ ሲመሠረት ደግሞ መሥራች አባል እና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ በመሆን አገልግሏል።
እንግዳው ስለራሱ ሲናገር “መልካም ሥነ ምግባር ካላቸው ቤተሰብ የተወለድኩ የአርሶ አደር ልጅ ነኝ። አባቴና እናቴ ስለ አገር እና ስለ ወገን ፍቅር ሲነግሩኝ ነው ያደግኩት። የተወለድኩበት አካባቢ አርማጭሆ ደግሞ እኔ ከመወለዴ በፊት ጀምሮ የትግል አካባቢ ስለሆነ ምን ጊዜም ለአምባገነን ገዥ መገዛት እንደሌለብን ይነግሩናል። ይህም አሁን ላለሁበት የፖለቲካ ሕይወት አስተዋፅኦ አድርጓል። በተለይ አያቴ ሕዝብንና አገሬን እንድወድ በተቻለኝ ሁሉ ሰዎችን እንድረዳ ይመክረኝ ነበር። 9ኛ ክፍል እያለሁኝ ነው ወደ ፖለቲካ የገባሁት በዚህም ምክንያት የሕዝቡን በደል ለእናቴ ስለምነግራት ለትግሉ ታበረታታኛለች። ታናሽ እህቴም በተመሳሳይ አሁንም ቢሆን መስዋት የከፈልክለትን ትግል ዳር ማድረስ እንዳለብኝ ታበረታታኛለች” ሲል ስለአስተዳደጉ፣ የፖለቲካ ተሳትፎውን እንዴት እንደጀመረ እና የቤተሰብም ድጋፍና ማበረታቻ ተለይቶት እንደማያውቅ ይገልፃል።
በ2007 ከመታሰሩ በፊት በሰሜን ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ መሬት አስተዳደር መሥሪያ ቤት ይሠራ ነበር። በመሥሪያ ቤቱ በኩል ገበሬው ላይ የሚደርሰውን በደል አይቶ ከገበሬው ጎን በመቆሙ፣ በሕገ ወጥ መንገድ መሬት ለሱዳን ሲሰጥ ዝም ባለማለቱ እና የሙስና ወንጀል የፈፀሙ ባለሙያዎች እና አመራሮችን በማጋለጡ ምክንያት በ2007 “ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት አለክ፤ አባላትም እየመለመልክ ትልካለህ” በሚል የሽብር ክስ እንደተመሠረተበት ይገልፃል። ሁለት ዓመት ከስምንት ወር በእስር ሆኖ ክሱን ሲከታተል ቆይቶም ሰኔ 9/2009 ቀን ፍርድ ቤት በሰጠው ፍርድ በነፃ ተሰናብቶ ከእስር ወጥቷል።
እንግዳው በ1997 እና 2005
እንግዳው ዋኘው በ1997 እና በ2005 ለአጫጭር ጊዜ ጎንደር ውስጥ ታስሮ ነበር። በ1997 ከምርጫ በኋላ በነበረው የፖለቲካ ተቃውሞ ታስሮ የነበረ ሲሆን፣ በ2005 የታሰረው የአንድነት ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምፅ የሚል ሕዝባዊ ሠላማዊ ሰልፍ ለመጥራት በሚቀሰቅስበት ወቅት የጎንደር መሬት ለሱዳን ተላልፎ መሰጠቱን የሚገልፅ በራሪ ወረቀት በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ፣ አብርሃጅራ ከተማ ላይ በመበተኑ ነው።
የእንግዳው ረዥም እስር
በሽብርተኝነት ክስ ሰበብ ታስሮ ሁለት ዓመታት ከስምንት ወራት በኋላ በነጻ ከእስር የተሰናበተው እንግዳው ዋኘው፤ ይኖርበት ከነበረው ሰሜን ጎንደር ምዕራብ አርማጭሆ፣ አብረሃ ጅራ ከተማ ሲታሰር ስለነበረው ሁኔታ እንዲህ ያስታውሳል፡- “ጥቅምት 25 ቀን 2007 ከለሊቱ 11፡00 ሰዐት ላይ ነበር የምኖርበት ቤት ሁለቱም በር በኃይል የተንኳኳው፡፡ ማንነታቸውን ስጠይቅ ፖሊስ መሆናቸውን ነገሩኝ። ልብሴን እስክለብስ እንዲጠብቁኝ ስጠይቃቸው ‹አንተ መሣሪያ እስክታነሳ ነው የምንጠብቅህ?› ብለው በሩን ገንጥለው ለመግባት ሲሞክሩ ልብሴንም ሳለብስ ከፈትኩላቸው። እንፈልግሃለን ብለው አብሬያቸው እንድሔድ ሲጠይቁኝ የዓላማ ጉዳይ ስለሆነ አላንገራገርኩም። ከቤት እንደወሰዱኝ አብረውኝ የተከሰሱ ጓደኞቼ አባይ ዘውዱ እና አንጋው ተገኝ ቤት ሔደን እነሱንም ይዘው ወደ ከተማው ውስጥ ያለ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን። ከዛ ወደ ጎንደር እንዳንወሰድ የአካባቢው ሕዝብ ሕፃን አዋቂ ሳይል አዳባባይ ወጥቶ አትወስዷቸውም ብሎ ሲቃወሙ ነበር። የአካባቢው ሕዝብ በአርማጭሆ በኩል ወደ ጎንደር የሚወስደውንም መንገድ ዘግቶት ነበር። በኋላ ላይ መከላከያ፣ ሚሊሻ እና ልዩ ፖሊስ መጥቶ በሱዳን አቅጣጫ በመተማ በኩል አድርገው፣ ጎንደር 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ አመሻሽ 12 ሰዐት ላይ ደረስን። መኪና ላይ እንደ ዕቃ እንደሚጫን ተደርድረን፣ እጃችን በካቴና ታስሮ እና ጎንበስ ጎንበስ ብለን ነበር የተጓዝነው። ደክሞን ቀና ካልን እንደበደብ ነበር። ሦስታችንም የተለያየ ክፍል እንድንገባ ተደረገን። የነበርኩበት ቤት በር አልነበረውም። የሚጠበቀው በሁለት ፌደራል ፖሊስ ነው። ኮርነር ላይ ፊቴን ለግድግዳ ሰጥቼ እንድቀመጥ ነው የተነገረኝ። ከታዘዝኩት አቀማመጥ ውልፍት ካልኩ በር ላይ የሚጠብቁኝ ፌደራሎች ይደብቡኝ ነበር።”
እንግዳው የፖሊስ ምርመራ ጎንደር 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ በገባ ማግስት መጀመሩን ይናገራል፡፡ ድብደባም በከፍተኛ ሁኔታ ተፈፅሞበታል። በፖሊስ ጣቢያው ለአራት ቀናት ከቆየ በኋላ ጥቅምት 28 ቀን 2007 ከለሊቱ 9 ሰዐት ላይ ዓይኑ በጨርቅ፣ እጁ በካቴና ታስሮ ጉዞ ወደ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ተጀመረ።
እንግዳው በማዕከላዊ
እንግዳው ዋኘው ከጎንደር ጥቅምት 28 ቀን 2007 ለሊት ተነስቶ በማግስቱ ጥቅምት 29 ቀን ከምሽቱ 3 ሰዐት ላይ ማዕከላዊ ደረሰ። በጎንደር 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ በቆየባቸው 4ት ቀናት ምግብ ባለመቅመሱ እና በደረሰበት ድብደባ ምክንያት ማዕከላዊ ሲደርስ እጅግ ተዳክሞ እና ተጎሳቁሎ እንደነበር ይናገራል፡፡ “‹ምንም በማያገባክ ባለሥልጣናት ሙስና ሠርተዋል እያልክ እንዲከሰሱ ታደርጋለክ›፣ ‹አንተ ተቃዋሚ ነህ፤ ባለሥልጣናት የፈለጉትን ቢያደርጉ ምን ያገባሃል?›፣ ‹ሕዝቦችን መሬት ተወስዶባችኋል እያልክ አደራጅተካል› እያሉ ነበር ምርመራ ላይ የሚሰድቡኝ፣ የሚያንጓጥጡኝ እና የሚደበድቡኝ። ቀጥለውም የማላውቃቸውን ሥሞች እየጠቀሱ አብረሃቸው ሆነህ ለግንቦት 7 መልምለህ ልከሃል እያሉ አምኜ እንድፈርምላቸው ሦስት ወር ሙሉ ቀን እና ለሊት ለምርመራ እያሉ እየጠሩ ደብድበውኛል። ምን ላርግልህ የሚባል መርማሪ ኩላሊቴ ላይ የመታኝ አሁን የኩላሊት በሽተኛ አድርጎኛል። አሁን ድረስ ምግብ ስበላ ሕመም ይሰማኛል” ይላል፡፡
እንግዳው ይደርስበት የነበረውን ጫና ተቋቁሞ እነሱ ያሉትን ሳይሆን ያመነበትን ብቻ ቃል የተናገረበት ወረቀት ላይ ከፈረመ በኋላ ከጨለማ ክፍል ወጥቶ በማዕከላዊ ምርመራ የጨረሱ ሰዎች የሚቆዩበት ክፍል ወደ ሆነው እና በእስረኞች ‹ሸራተን› የሚባለው ክፍል ተዘዋወረ። “ምንም ማስረጃ አላቀረቡብኝም ነበር። እንዲያውም አንድ መርማሪ እንደምፈታ ነግሮኛል” ይላል እንግዳው። “ነገር ግን፣” ይላል ሲቀጥል፣ “ነገር ግን ሸራተን ካገኘኋቸው ሌሎች እስረኞች ጋር በወልቃይት የማንነት ጉዳይ ላይ ውይይት ሲደረግ ወልቃይት የአማራ መሆኑን ማስረጃ እየጠቀስኩ ስከራከር የሰሙ ጆሮ የሆኑ [ለፖሊስ መረጃ የሚያቀብሉ] እስረኞች ለመርማሪዎች ስለነገሯቸው፣ ከብሔራዊ ደኅንነት እና መረጃ ቢሮ ስልክ ጠልፈናል ብለው በጽሑፍ ያቀረቡትን የሐሰት ሪፖርትን ማስረጃ ብለው የሽብር ክስ መሰረቱብኝ” ይላል። ለአራት ወር ከ15 ቀን የስቃይ እና የጭንቅ ቀናትን በማዕከላዊ ካሳለፈ በኋላ የሽብር ክስ ተመሥርቶበት ወደ ቂሊንጦ የእስረኞች ማቆያ ተላከ።
የቂሊንጦ ያልተጻፈ ሕግ
እንግዳው ቂሊንጦ እንደገባ ዞን ሦስት ነበር የተመደበው፡፡ በቂሊንጦ እንዲተኛ የተመደበበት አልጋ ጎን ካለ አልጋ የሚተኛ የሚከታተለው እስረኛ ተመድቦበት እንደ ነበር ይገልጻል። የፖለቲካ እስረኞችን እንቅስቃሴ እየተከታተሉ ለኃላፊዎች ሪፖረት የሚያደርጉ እስረኞች በቂሊንጦም ሆነ ሌሎች እስር ቤቶች ያልተጻፈ ነገር ግን የተለመደ አሠራር ነው። እንግዳው እንደሚለው፣ የተመደበበት እስረኛ ለፀብ የሚተነኩሱ በርካታ ነገሮችን በማድረግ ነው ብዙ ጊዜውን የሚያሳልፈው። እነሱ በተመደቡበት አልጋ አካባቢ የሚያድሩ እስረኞችንም እያንጓጠጠ እና እያንቋሸሸ በተደጋጋሚ ይሰድባቸው እንደነበር ይናገራል፡፡ እንግዳው ግን ፀብ ውስጥ ቢገባ ምን እንደሚከተልበት በማሰብ የሚከታተለውን ልጅ ድርጊት እያየ እንዳላየ፤ እየሰማ እንዳልሰማ ሆኖ በዝምታ ለማለፍ ይሞክር እንደነበር ያስታውሳል፡፡ “አንድ ቀን ግን ልጆቹን ሲሰድብ ‹ተው ልጆቹን አትስደብ› ብዬ ብለው ቢሮ ሔዶ ‹እየዛተብኝ ነው› ብሎ ከሶኝ ወደ ቢሮ እንድጠራ ከተደረግኩ በኋላ ሁለት የዞኑ ኃላፊዎች ደበደቡኝ” ይላል እንግዳው፡፡ የዞን ተጠሪዎች ቢሮ ተጠርቶ በተደበደበ ማግስት ፍርድ ቤት ቀጠሮ ስለነበረው የደረሰበትን ነገር ለፍርድ ቤቱ በመግለጽ ኃላፊዎቹ እንዲጠየቁበት ማድረጉን ይገልጻል። ይሁን እንጂ በሌላ ጊዜም በተመሳሳይ ቢሮ ተጠርቶ እግሩ እስኪሰበር ድረስ በኃላፊዎች ድብደባ ተፈፅሞበታል።
የተቃጠለ አስከሬን በቂሊንጦ
የቂሊንጦ እስር ቤት ነሐሴ 28 ቀን 2008 በእሳት መያያዙ ይታወሳል፡፡ የቃጠለው ቀን በርካታ እስረኞች ወደ ዝዋይ እና ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ሲወሰዱ፣ እንግዳው ግን እዚያው ቂሊንጦ ለሁለት ሳምንታት ከቆዩ በኋላ ወደ ዝዋይ እንዲዛወሩ ከተደረጉ እስረኞች ውስጥ አንዱ ነበር ነበር። በቂሊንጦ በቆዩበት ሁለት ሳምንታት የተቃጠሉትን ቤቶች ባዶ እግራቸውን ሆነው እንዲያፀዱ ተገደው እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በሚያፀዱበት ጊዜ ቃጠሎው ከተከሰተ ከአንድ ሳምንት በኋላ ስላጋጠመው ነገር ሲናገር “አንድ ቀን ዞን 2፣ ሰባተኛ ቤትን እያፀዳን እያለ በእሳት ቃጠሎ ሞቶ የከሰለ ሰው አየን። ለኃላፊዎቹ ሔደን ያልተነሳ ሬሳ እንዳለ ስንነግራቸው፤ ገብተን እንድናፀዳ ያዘዙን እራሳቸው ቢሆኑም ‹ማን እዩ አላችሁ?!› ብለው እየደበደቡ አስወጡን። ከዛ በኋላ እኛን ደግመው የፅዳቱን ሥራ አላሠሩንም” ይላል፡፡
እንግዳው ወደ ዝዋይ ማረሚያ ቤት እንዲሔድ ከተደረገ በኋላ 280 እስረኞችን አንድ ክፍል አስቀመጧቸው። ውኃ በቀን አንድ ጊዜ ለሊት ላይ ብቻ የሚያገኙ ሲሆን በቀን አንድ የላስቲክ ቡትሌ ውኃ ብቻ ነው የሚደርሰው። የውኃ እጥረት በመኖሩም ምክንያት የሽንት ቤቱ ሽታ ይረብሻቸው ነበር። የነበረውን ነገር እንግዳው እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፡- “አንድ ክፍል ውስጥ 280 ነበርን። መውጣት የለም። መንቀሳቀስም አይቻልም። እንደ ማዕከላዊ ማለት ነው። እንታመም ነበር። በዚያ ላይ ለሊት ተንቀሳቅሳችኋል እያሉ ጠዋት እያወጡ ይደበድቡናል።”
እነ እንግዳው ቂሊንጦ ከታደሰ በኋላ ከዝዋይ ተመልሰው መጥተዋል፡፡ ወደ ቂሊንጦ ከተመለሱ በኋላም ድብደባው አልቀረላቸውም። የተመለሱ ቀን የማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች በድብደባ እንደተቀበሏቸው የሚናገረው እንግዳው፤ የዛን ቀን በፌሮ ብረት በደረሰበት ድብደባ የእጁ አጥንት ስብራት እንዳጋጠመው እና ከተፈታ በኋላም እንዳልተሻለው ይናገራል። በቀጣይ ባሉ ቀናትም ጠዋት ሊቆጥሯቸው የሚገቡ ፖሊሶች ሲመጡ ይደበድቧቸው ነበር። በዚህ ተማርረውም እስረኞቹ ተሰብስበው የግቢውን ኃላፊ አስጠርተው ከተናገሩ በኋላ “ከዚህ በኋላ እንዳትደበድቧቸው” የሚል መመሪያ እንደወጣ ይገልጻል።
የጠበቃ ክልከላ
እንግዳው ዋኘው ወደ ማዕከላዊ ከመምጣቱ በፊት ለአራት ቀናት የቆየበት የጎንደር 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ እያለ ከቤተሰብም ሆነ ጠበቃ ጋር እንዲገናኝ አልተፈቀደለትም። ማዕከላዊ እንደገባ አንድነት ፓርቲ ጠበቃ አቁሞለት የነበረ ቢሆንም በአራት ወር ከ15 ቀን የማዕከላዊ ቆይታው አንድም ቀን ጠበቃውን እንዲያገኝ አልተፈቀደለትም ነበር፡፡ በሁለት ዓመት ከአራት ወር የቂሊንጦ ቆይታው ደግሞ ሁለት ቀን ብቻ ጠበቃ እንዳገኘ ከዛ ውጪ ጠበቃው ሊያማክረው በመጣባቸው ጊዜያቶች የለም እያሉ እንደሚመልሱበት ይናገራል።
የቤተሰብ ናፍቆት
ማዕከላዊ በነበረበት ወቅት አንድ ጊዜ፣ ቂሊንጦ በነበረበት ወቅት ደግሞ ሊፈታ አካባቢ አንድ ጊዜ፣ ባጠቃላይ በሁለት ዓመት ከስምንት ወራት የእስር ቆይታው ውስጥ ሁለት ቀን ብቻ ቤተሰብ ከጎንደር መጥተው ጠይቀውታል። ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዳ እንዲህ ይላል፡- “ቤተሰብ እንዳይጠይቀኝ የአካባቢው ካድሬዎች ‹ሽብርተኛ ስለሆነ ብትሔዱ እናንተንም ያስሯችኀል› እያሉ ያሰፈራሯቸው ነበር። በዚህም ምክንያት የአካባቢው ካድሬዎች በቤተሰቤ ላይ ተፅዕኖ ስለነበር ላለመጠየቄ ምክንያት ነበር። እንዲሁም የቦታው ርቀትም ቤተሰብ እንዳይጠይቀኝ ሌላው ምክንያት ነበር።”
ኢፍትሓዊው የፍርድ ሒደት
እንግዳው ዋኘው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋለበት ቀን ጀምሮ ባለው ጠቅላላ የእስር ቆይታው በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 19 ላይ የተጠቀሱት አብዛኛዎቹ የተያዙ ሰዎች መብቶች አልተጠበቁለትም፡፡

እንግዳው ዋኘው ለአንድ ዓመት ከ8 ወራት ያለጥፋቱ ታስሮ ቆይቶ በፍርድ ቤት ውሳኔ በነጻ ቢሰናበትም፣ የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ በሕጉ መሠረት ወደ ቀድሞ የሥራ ገበታው አልመለሰውም፡፡
ጥቅምት 25 ቀን 2007 ቀን ከሚኖርበት ቤት ሊወስዱት የመጡ ፌደራል ፖሊሶች ያሳዩት የፍርድ ቤት የማሰሪያም ሆነ፣ ቤት የመበርበሪያ ፈቃድ አልያዙም ነበር። ጎንደር 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ አራት ቀናት ሲቆይ ፍርድ ቤት አልቀረበም። ጥቅምት 29 ቀን 2007 አዲስ አበባ የሚገኘው የፌደራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ከተዘዋወረ ከ24 ቀን በኋላ፣ ኅዳር 23 ቀን 2007 ነበር ፍርድ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበው፡፡
ከዚያ በኋላም ምርመራው አላለቀም እየተባለ ሦስት ወር ከሦስት ሳምንት በላይ በጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ቆይቶ መጋቢት 15 ቀን 2007 ከሌሎች፣ ከጎጃም እና ከጎንደር በተመሳሳይ ወቅት እና ሁኔታ እንደርሱው ታስረው ከነበሩ የሰማያዊ፣ የአንድነት እና የመኢአድ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር በአንድ መዝገብ ተካቶ ክስ ተመሥርቶበታል። የቀረበበት ክስም በፀረ-ሽብርተኝነቱ ዐዋጅ መሠረት ዋስትና የማያሰጥ በመሆኑ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሆኖ ክሱን እንዲከታተል ተደርጓል።
እንግዳው የቀረበበት ክስ ‹ቀኑና ወሩ በትክክል ተለይቶ ባልታወቀበት 2005፣ ለግንቦት 7 የሽብርተኛ ድርጅት በድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች አማካኝነት ተመልምሎ አባል በመሆንና ሲሳተፍ ቆይቶ በኋላ ላይም ሌሎችንም እየመለመለ ወደ ኤርትራ በመላክ እና መረጃ በማስተላለፍ ተግባር ላይ ሲሳተፍ› እንደነበር ይገልጽና ‹በ2001 የወጣውን የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 7(1) ሥር የተመለከተውን በመተላለፉ የተመሠረተ ክስ› መሆኑን ያትታል። እንግዳው ይህንን የቀረበበትን ክስ ያስረዳል በሚል በፌዴራል ዐቃቤ ሕግ የቀረበበት ማስረጃ የብሔራዊ የመረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት የላከው “የስልክ ልውውጥ ጠለፋ በጽሑፍ የቀረበ ሪፖርት” ነው። ጉዳዩን የተመለከተው የልደታ ምድብ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት ብይን በሰጠበት ሰኔ 21 ቀን 2008 ይህንን ማስረጃም ተከላክሎ ነጻ እንዲወጣ ብይን አስተላልፏል።
ክሱን በመከላከል ሒደት እንግዳው ከ1997 ጀምሮ የቅንጅት አባል ሆኖ ሲሠራ እንደቆየ፣ በ2001 አንድነት ፓርቲ ሲመሠረት ከመሥራቾች አንዱ እንደነበረ እና እጁ እስከተያዘበት ቀን ድረስም በአንድነት ፓርቲ አባልነት ሲያገለግል እንደነበረ፣ የግንቦት 7 አባል አለመሆኑን፣ ከመረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት የቀረበበት የተጠለፈ የስልክ ልውውጥ ሪፖርት ስልክ ቁጥር እንኳን ያልተጠቀሰበት ከመሆኑም ባሻገር ተከላከል የሚያስብል ማስረጃ አለመሆኑን፣ ሌላ ምንም ማስረጃ እንዳልቀረበበት እና የተቃዋሚ ድርጅት አባል በመሆኑ ብቻ ለእስር መዳረጉን በመግለፅ የራሱን ቃል በመከላከያ ማስረጃነት አቅርቧል። በተጨማሪም በጎንደር ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል መሆኑን እና ከመሬት ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ሙስናዎችን ይታገል የነበረ ሰው መሆኑን ለፍርድ ቤት የገለፁ ሁለት የሰው ምስክሮችን አስደምጧል፡፡
ፍርድ ቤቱም ከክሱ ጋር የተያያዘውን ማስረጃ እና እንግዳው ያቀረባቸው መከላከያ ማስረጃዎቹን መርምሮ፣ ከብሔራዊ የመረጃ እና ደኅንነት ቢሮ የቀረበው ማስረጃ “ከሌሎች ማስረጃዎች ጋር ተደማምሮ ስላልቀረበ እና ለመመዘን አስቸጋሪ ስለሆነ” በማለት ሰኔ 9 ቀን 2009 በነፃ አሰናብቶታል። ነገር ግን የቀድሞ ሕይወቱን መልሶ ማግኘት አልተቻለውም፡፡
“ነፃ” ነገር ግን “ሥራ አጥ”
እንግዳው ዋኘው በእስር ሆኖ የቀረበበትን የሽብር ክስ ሲከራከር ቆይቶ፣ ከሁለት ዓመት ከስምንት ወር በኋላ ሰኔ 9 ቀን 2009 ነፃ መሆኑ ተፈርዶለት ከእስር ሲወጣ “እናቴ ከታሰርኩ ጀምሮ መሬት ላይ ነበር የምትተኛው። በመፆም ነው በእስር የነበርኩበትን ጊዜ ያሳለፈችው። እንደተፈታሁ ከሰማች በድንጋጤ ትሞትብኛለች ብዬ፣ ወንድሜ ቀስ ብሎ አረጋግቶ እንዲነግራት ካደረግኩ በኋላ ነው ወደ ቤት የሔድኩት” ይላል፡፡ ወደ ቀድሞው ሥራው ለመመለስ በማሰብም ፍርድ ቤት የሰጠውን ነፃ መውጣቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ይዞ ቀድሞ ይሠራበት ወደ ነበረው የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ መሬት አስተዳደር ቢሮ ይሔዳል። መሥሪያ ቤቱም ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ስለቆየ ወደ ሥራ ገበታው መመለስ እንደማይችል ደብዳቤ ጽፈው ይሰጡታል።
ወንጀል ሠርቶ ሳይሆን በፖለቲካ ሴራ በመታሠሩ፣ ኋላም ያውም ፍትሐዊ ባልነበረ ፍርድ ሒደት በነጻ የተሰናበተው እንግዳው ይህንን እሺ ብሎ መቀበል አልሆነለትም፡፡ በዚያ ላይ ሌሎች እንደሱ በተመሳሳይ መንገድ ከሁለት ዓመት በላይ ታስረው የነበሩ ነገር ግን ወደ ሥራቸው የተመለሱ ሰዎች እንደሚያውቅ የሚናገረው እንግዳው፣ በዚህ ተስፋ ሳይቆርጥ ወደ አማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ መሥሪያ ቤት በማምራት ወደ ሥራ እንዲመልሱት ጥያቄውን ሲያቀርብ “በኛው ገንዘብ እኛን ስትዋጋ ቆይተህ እንዴት ወደ ሥራዬ መልሱኝ ትላለክ? ስለፈታንክ ነው ወይ?” የሚል ምላሽ እንደተሰጠው ይገልጻል።
“ቀጥዬ ደግሞ የክልሉ እንባ ጠባቂ ተቋም የሚባል አለ። እዛ ገባሁኝ። ‹በሽብር የተከሰስክ ስለሆነ ወረዳው የወሰነው ውሳኔ ትክክል ነው› ተባልኩ። የርዕሰ መስተዳድሩ ቢሮ ለመግባት በተደጋጋሚ ሞከርኩ፤ ነገር ግን ላገኛቸው አልቻልኩም። የቀድሞ መሥሪያ ቤቴ፣ የመሬት አስተዳደር የክልል ቢሮ ሔጄ አናገርኳቸው፤ እነሱ ደግሞ ‹ሲቪል ሰርቪስ ሲጽፍ ብቻ ነው የምንመልስህ፡፡ እኛ መመለስ አንችልም› አሉኝ። ተመልሼ ሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳዳሪውን ሔጄ ስጠይቅ ምላሹ ያው ነው። እንዲያውም እዛ ያሉ ሰዎች ‹መሬት ለጄነራሎች ተሰጥቷል፣ ለኮሎኔሎች ተሰጥቷል እያልክ ስትቀሰቅስ አልነበረ?› በማለት እንደሚያሳስረኝ ዝቶብኝ ነበር” በማለት ወደ ሥራው ለመመለስ ያየውን ውጣ ውረድ ይገልፃል። አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ምንም ያክል ጊዜ ታስሮ ቢሆን “ነፃ” ሲባል ወደ ሥራው መመለስ እና በእስር ወቅት ያልተከፈለው ደመወዝም እንዲከፈለው ሕግ ስለሚያዝ፣ ይህ ሕግ ተፈፃሚ እንደሚሆንለት ጠብቆ የነበረው እንግዳው “ይባስ ብሎ መፈታቴን እንደ ልግስና ቆጥረው ወደ ሥራ መመለስ መብት እንደሌለኝ ነግረውኛል” ይላል።
አዲስ ሥራ በጀማሪ ቦታ
በ2010 መጨረሻ ላይ (ከተፈታ ከዓመት በኋላ) መንግሥት በምሕረት እና ክሳቸውን አቋርጦ የፈታቸው ሌሎች እስረኞች ወደ አካባቢያቸው በተመለሱበት ወቅት፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ከእስር የተፈቱ የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ነበሩበት የሥራ ገበታ እንዲመለሱ መመሪያ ያወርዳል። ይህንም ተከትሎ እንግዳው ዋኘው ይሠራበት የነበረው የምዕራብ አርማጭሆ የመሬት አስተዳደር መሥሪያ ቤት ከመስከረም 2011 ጀምሮ ሥራ እንዲጀምር ጥሪ ቢደርሰውም “የነበርኩበት ቦታ ሰው ገብቶበታል። መመሪያው የሚለው ‹ወደ ነበሩበት የሥራ ቦታ ይመለሱ› ቢሆንም እኔ ግን የማይገናኝ የሥራ ዘርፍ እና ምንም ልምድ የሌለው ሰው የሚመደብበት ቦታ አዲስ ሥራ ሰጡኝ። ከሦስት ዓመት በላይ በቦታው ላይ ልምድ ነበረኝ።” በማለት ቀድሞ ይሠራበት የነበረው ቦታ ግን እንዳልመለሱት በዚህም ደስተኛ እንዳልሆነ ይናገራል።
እንግዳው ሁለት ዓመት ከስምንት ወር በእስር ቆይቶ፣ ፍርድ ቤት በነጻ ቢያሰናብተውም የሚመለከተው የመንግሥት አካል ሕጉ በሚያዘው መሠረት ባይታሰር ኖሮ ያገኝ የነበረውን ጥቅም ወይም ደሞዙን ወይም ኪሳራውን አልከፈለውም። የቀድሞ መሥሪያ ቤቱም ወደ ሥራ ገበታው አልመለሰውም፡፡ ከእስር ከተፈታ ከአንድ ዓመት ወደ ሥራ ሲመለስ የተሰጠው የሥራ ቦታ ልምዱን የማይመጥን፣ የጀማሪ ነበር፡፡
እንግዳው ዋኘው በእስር ወቅት ለደረሰበት ኪሳራ ካሣ ባያገኝም፣ ከእስር ከተፈታ በኋላ በፖለቲካ ተሳትፎው መቀጠሉን ይናገራል፡፡ “ከተፈታሁ አንድ ወር ጀምሮ የምታገልበትን ነገር ነው ስፈልግ የነበረው። ነገር ግን ምንም ነገር ማግኘት አልቻልኩም። በሰላማዊ ትግሉ ለመቀጠል ፍላጎቱ አለኝ። በሚዲያ ላይ የሚሰማው ነገር መሬት ላይ ጠብ የሚል ነገር አይደለም፡፡ መሬት የረገጠ ነገር መሠራት አለበት” የሚል እምነት እንዳለው የሚናገረው እንግዳው በአሁኑ ወቅት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲን ተቀላቅሎ ትግሉን የቀጠለ ሲሆን በፓርቲው ውስጥ የማዕከላዊ ጎንደር አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ አባል በመሆን እያገለገለ ይገኛል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.