የይቅርታ መድረክ (ዐቢይ ኢትዮጵያዊ ሥ/ወ)

=== ለዕምባ-ጠብታ-ዕዳዋ፤በአንዲቷ-ይቅርታ=ለትንስዔዋ-።===
         የይቅርታ ፈንጂ  ።
          ዐቢይ ኢትዮጵያዊ ሥ/ወ
 
የዕምባ-ባለዕዳዎች ኢትዮጵያ ትጣራለች፤
ትንሳዔ ጀምራ፤ይቅርታዬን እያለች።
እምዬ ነች አትሽሿት፤
አምባገነኖች ያቆሸሿት።
የእግዚአብሔር ቤት የሆነች፤
ትጣራለች-ቢያቆስሏትም በልጆቿ እየዳነች።
ከአብርኳ ግን ተከፍለው ዛሬም ሕዝቧን የሚበድሉ፤
ከጠላቶቿ እስከአሁንም ብዙ መርዞች ያገኛሉ።
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ዕምነት ለታጠቁ፤
በጉልበት በብረት አሉ እየተጠቁ
በተለይ በዚህ ወቅት የፍቅር እጃቸው፤
የአጋዚ ጥይት ገድሎ ለሚፈጃቸው፤
ከልብ በአደባባይ”በድለናል”ካሉ፤
መፍትሄ ነው”ይቅርታ”በዕውነት ከማሉ። 
እናም እንደማዲንጎ በፍቅር የተረታ፤
አሁን ለሕዝቡ ይስጥ
የፈንጂ ይቅርታ።
ለኢትዮጵያችን ትንሳዔ ለዕምባዋ ጠብታ፤
ለፈንጂ በደላችን እንበላት ይቅርታ።
ኃይሌ እና ገንዘቤ፤ኢትዮጵያን ያላችሁ፤
ለሰንደቋ በዓለም የተሟሟታችሁ፤
በአንድ ወቅት የኢትዮጵያን ሕዝብ፤
አዋረዳችሁ ነበር በአምባ-ገነን ስድብ።  
እንደው ባትሆኑም ከልደቱ ተርታ፤
እንደልጅ ማዲንጎ ሕዝብ ጠይቁ ይቅርታ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ይህን ጥሪ ስማ፤
በልብ-ፅላት ጻፈው ማን እንደሚያቅማማ።
በየጓዳው ሞልቷል ቢጠራ’ማይሰማ፤
ልጆችህ ሲደፉ በዓጋዚ ስንደማ።
እሰዬን አስተውል፣እነገብሩ አሥራትን፤
ያን ታምራት ላይኔ ያስገነጠላትን።
በየመድረኩ ላይ ዛሬም የሚዋሹ፤
በዜና አንባቢነት ህሊና ያቆሸሹ።
ሞልተዋል ድርቅ የለም ለምተናል እያሉ፤
ጉጅሌ ለበላው ጅለው የሚያጃጃሉ።
እነዚህን ሁሉ ሐቁ እንዲፈጃቸው፤
የእነ መሓሙድ ይቅርታ ወጥቶ ያፈንዳቸው።
እናም ሕዝቡን ስሙት አድምጡት ላንድአፍታ፤
እንደልጅ ማዲንጎ ጠይቁ ይቅርታ።
ለኢትዮጵያ ትንሳዔ ለዕምባዋ ጠብታ፤
ከበደላችን ታጥበን እንበላት ይቅርታ።
እንደው ስንቴ ከዱን ከመካከላችን፤
በአምባገነን ጉያ አሾፉ በሕዝባችን።
በኪነት-በስፖርቱ በፖለቲካ-ስልጣን፤
በምርጫ በትግል ስንቱን ጀግና አጣን።
ይህን የሕዝብ በደል ማዲንጎ አሸንፎ፤
አስደሰተው ሕዝቡን በይቅርታው አቅፎ።
የዶክተር ዐቢይ ፍቅርም በጅምላ ቢሆንም፤
በሕዝቡ ይጣራል ይሻላል ከምንም።
የሚያሳዝነው ግን እዚህ ይቅርታ ሲለን፤
እዚያ በተንኮሎች  አለ  የሚያስገድለን።
ሕዝቡ ትዕግስት አለው ነግቶም ይጠብቃል፤
እነማን ገዳዮች እንደሆኑም ያውቃል።
እናም የበደላችሁ ያኔ ተለጥፋችሁ፤
ዛሬውኑ ይቅርታ ጠይቁ ፈጥናችሁ።
ባንዳውን ሳይጨምር፣ስንቱ ስው ተረታ???…
በሆዱ በሥልጣን ለገንዘብ ተፈታ።
ሰለሞን ተካልኝ በቁም-ሲታይ ሞቱ፤
ያ ንዋይ ደበበም አየን ሲሆን ገልቱ።
አይ አስቴር አወቀም ባለድምጻዊቷ ፤
ኢትዮጵያን ነው የከዳች ለስንዝር ዕርስቷ።
ሠራዊት ፍቅሬማ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሲል፤
ወደገደል ሮጠ ሲያስገድል ሲሰልል።
አበበ ባልቻንም እንዳፈናጠጠ፤
ሺፈራሁን ይዞ ባንዳነት መረጠ።
ወዶ ገባ ሆነ ከጉጅሌ ጉያ፤
ሥራ-አጥ እንስቶችን አ’ርጎ መደለያ።
ሰለሞን ተካልኝ ና ሲባል ብላልኝ ፤
እንደጅብ ይጮሃል እሱስ ይጠንባልኝ።
እነ እንትናም ቢሆን ስንቱ ይቆጠራል፤
ወዲያው ካያለበት እንደነጋ  ይጠራል።
እናም እንደማዲንጎ በፍቅር የተረታ፤
አሁን ለሕዝቡ ይስጥ
የፈንጂ ይቅርታ።
ለኢትዮጵያችን ትንሳዔ ለዕምባዋ ጠብታ፤
ለፈንጂ በደላችን እንበላት ይቅርታ።
ኃይሌስ ቢሆን ስንቴ አውቆ አልታለለ፤
ጀግናው እንዳልተባለ በወቸገል-ሥም ማለ።
ፈንጂ ነው ዕውነታ ሐቅ ነው መናገር፤
ጉጅሌ ኢትዮጵያን ከፋፍሏታል በዘር።
ይኼን አትመስክሩ፤የኢትዮጵያ ሕዝብ አውቋል፤
ግና ይቅርታችሁን ለዓመታት ጠብቋል።
እናም ሕዝቡን ስሙት አድምጡት ላንድአፍታ፤
ታሪክ ሳይጠራችሁ የማታ የማታ፤
ዛሬ ቁረጡና ቆማችሁ በዕውነታ፤
ለኢትዮጵያችን ትንሳዔ ለዕምባዋ ጠብታ፤
በአደባባይ ስጧት፣ 
አንዲቷን ይቅርታ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.