በአዲስ አበባ ዙሪያ የህገ-ወጥ ግንባታ መስፋፋት እንዳለ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በፊንፊኔ ዙሪያ  በኦሮሚያ ልዩ ዞን በሚገኙ ከተሞች የህገ ወጥ  ግንባታ መስፋፋት  እንዳለ በጥናት ማረጋገጡን የኦሮሚያ ክልል  የከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲ  አስታወቀ።

ኤጀንሲው  በዞኑ ያካሄደውን ጥናት አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

በዚህ ወቅት መንግስት ለተለያዩ ልማቶች ያዘጋጃቸው መሬቶች ለህገ ወጥ ግንባታ መጋለጣቸውን ጥናቱ አመልክቷል።

ለህገ ወጥ ግንባታው የፓለቲካ አለመረጋጋት፣ የከተማ ይዞታ እየተስፋፋ መምጣትና  በአጭር ጊዜ ለመክበር በሚንቀሳቀሱ አካላት የሚደረግ የመሬት ወረራ ምክንያት  እንደሆነ ጥናቱ አሳይቷል።

የህገ ወጥ ግንባታው በ2010 እና 2009 ዓመተ ምህረቶች  በከፍተኛ ሁኔታ  የተስፋፋበት ወቅት እንደነበረ የተጠቆመ ሲሆን፥ በተለይ የ2010 ዓመተ ምህረቱ ከፍ እንደሚል ተጠቁሟል።

ህገ ወጥ ግንባታው ከፍ ካለባቸው ከተሞች  ለገጣፎ፣ለገዳዲ እና ሱሉልታ መሆናቸውን ጥናቱ ያመለከተ ሲሆን፥ህገ ወጥ ግንባታውን የተለያዩ አካላት እንደሚያካሄዱት የኤጀንሲው ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ደረጀ ተናግረዋል።

ከዚህ  ባለፈ ቤተ እምነቶች፣ እድሮችና የተለያዩ ማህበራዊ ተቋማትን  ምክንያት በማድረግ ህገ ወጥ ግንባታ እንደተስፋፋ ነው ጥናቱ  ያመለከተው።

ቅንጅታዊ አሰራር አለመፈጠር፣ በፓሊስ አካላት የሚፈፀሙ ህገ ወጥ ተግባራት፣ አመራሮች እርምጃ ለመውሰድ ወደ ኋላ ማለት እና   መለዋወጥ  ለህገ ወጥ ግንባታው በተጨማሪነት የተጠቀሱ  ምክንያቶች ናቸው።

ጥናቱ  የአጭርና ረጅም ጊዜ መፍትሄዎችን ያስቀመጠ ሲሆን፥ በአጭር ጊዜ ከተያዙት መፍትሄዎች መካከል   ህገወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ የተፈፀመባቸውን አካባቢዎች የሚለይ ኮማንድ ፓስት ማቋቋም ና ከህብረተሰቡ ጋር ሰፊ ውይይት ማድረግ እንደሆነ ተገልጿል።

የረጅም ጊዜ መፍትሄ በመሆን  በጥናቱ የተገለፀው  በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋውን  ህገ ወጥ የመሬት ግንባታና ወረራን ማስቆም ነው ተብሏል።

በሰርካለም ጌታቸው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.