በሶማሌና ኦሮሚያ አዋሳኝ የጅምላ መቃብር ተገኘ

በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ወሰን ላይ የጅምላ መቃብር መገኘቱ ተገለጸ። ፖሊስ እንዳስታወቀው የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ ታማኝ በሆነው የልዩ ሃይል ተፈጸሟል በተባለ ግድያ የ200 ሰዎች አስክሬን በአንድ ጉድጓድ የተቀበረበት የጅምላ መቃብር ተገኝቷል።

ግድያው የተፈጸመው በሁለቱ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ወቅት እንደሆነ የገለጸው ፖሊስ ተጨማሪ የጅምላ መቃብር ለማግኘት ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

አቶ አብዲ ዒሌ በስልጣን ዘመናቸው ፈጽሟቸዋል ለተባሉት ወንጀሎች በህግ ተይዘው በእስር ላይ የሚገኙ መሆኑ ታውቋል።

የጅምላ መቃብሩ መገኘቱ የተመለከተው መረጃ የወጣው ትላንት በነበረው የአብዲ ዒሌ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ ነው።

በእስር ላይ የሚገኙት የሶማሌ ክልል የቀድሞ ፕሬዝዳንት አብዲ መሀመድ ዑመር፡ አብዲ ዒሌ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ 4ኛ የወንጀል ችሎት በቀረቡ ጊዜ መርማሪ ፖሊስ ካቀረባቸው ማስረጃዎች አንዱ 200 ሰዎች በአንድ ላይ የተቀበሩበት የጅምላ መቃብር መገኘቱ ነበር።

ፖሊስ በጅምላ መቃብሩ የተገኘው የ200 ሰዎች አስክሬን መለየትና የድርጊቱን መፈጸም የሚያረጋግጡ ምስክሮችን ቃል በመቀበል ላይ በመሆኑ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ አስፈልጎኛል በማለት ለችሎት ገልጿል።

በተጠርጣሪው የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ ላይ እየቀረቡ ካሉ ማስረጃዎች የጅምላ መቃብሩ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ትኩረት ስቧል።

ሲ ኤን ኤንን ጨምሮ የአሜሪካኖቹ ትልልቆቹ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን የሰጡበት ጉዳይ ሆኗል።

ከተለያዩ ማስረጃዎች ጋር የቀረበው የጅምላ መቃብሩ ጉዳይ በአብዲ ዒሌ በቀጥታ ትዕዛዝ በሚቀበለው የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል የተፈጸመ መሆኑን የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ላይ ተመልክቷል።

በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ወሰን አካባቢ እንደተገኘ የሚገለጸው የጅምላ መቃብር ውስጥ የተገኘው የ200 ሰዎች አስክሬን የማን እንደሆነ የመለየት ስራ ባይጠናቀቅም በሁለቱ ክልሎች መካከል ለአንድ ዓመት በዘለቀው ግጭት ወቅት የተፈጸመ እንደሆነ ግምቶች አሉ።

ትላንት አብዲ ዒሌ ፍርድ ቤት በቀረቡ ጊዜ የጅምላ መቃብሩ ጉዳይን በተመለከተ ጠበቆቻቸው ተቃውሞ አንስተዋል።

በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ ተገኘ የተባለው የጅምላ መቃብር አዲስ ምርመራ በመሆኑ ተነጥሎ እንዲታይ የአብዲ ዒሌ ጠበቆች መከራከሪያ አቅርበዋል።

ፖሊስ ግን የ200 ሰዎቹ ግድያ በተጀመረው የክስ ሂደት በተደረገ የምርመራ ስራ ወቅት የተገኘ በመሆኑ አንድ ላይ ሊካተት ይገባል ብሏል።

ወንጀሉ ከባድና ውስብስብ መሆኑን በመጥቀስም ፖሊስ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም የፖሊስን ጥያቄ ተገቢነት ያለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ በሚል የተጠየቀውን የምርመራ ጊዜ መራዘም ፍቃድ ተቀብሎታል።

ኢሳት ያነጋገራቸው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ ዑመር የ200 ሰዎች አስክሬን የተገኘበት የጅምላ መቃብር ጉዳይ በፌደራል መንግስቱ በምርመራ ላይ የሚገኝ ነው፡

እኛ በክልላችን በርካታ የጅምላ መቃብሮች እንዳሉ በደረሰን መረጃ ላይ ምርመራ እያደረግን ነው ብለዋል።

አቶ ሙስጠፋ በአቶ አብዲ ዒሌ የስልጣን ዘመን የተገደሉ የሶማሌ ተወላጆች የሚገኙበት የጅምላ መቃብሮችን በተመለከተ የሀገር ሽማግሌዎች በተሳተፉበት ምርመራው እየተጠናቀቀ በመሆኑ በቅርቡ ይገለጻል ብለዋል።

ኢሳት ዲሲ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.