ምርጫ፦ ቄሮ ‘መንግሥት’ ይሁን ‘ፅንፈኛ’? (በፍቃዱ ሃይሉ)

በቄሮ ምንነት እና “ድርጊቶች” ላይ በርካታ ውዝግቦች እየተነሱ ነው። ውዝግቦቹ የሚነሱት በሁለት ፅንፎች ነው፦ ፩ኛው ፅንፍ ያሉት ሰዎች “ቄሮ ቅዱስ ነው” ሲሉ፣ ፪ኛው ፅንፍ ያሉት ሰዎች ደግሞ “ቄሮ እርኩስ ነው” ይላሉ። እኔ ደግሞ ቄሮ እኛ ነህ የምንለውን ይሆናል ባይ ነኝ።

እንደኔ እንደኔ የውዝግቡ ሁሉ መንስዔ የቄሮን ምንነት እና የንቅናቄውን ዓይነት፣ እንዲሁም “የትግሉን” ወይም ደግሞ “የድሉን” ባለቤት ካለመረዳት የመጣ ነገር ይሆን ይሆናል በማለት ነው ይህንን ጽሑፍ ለአማራጭ አስረጅነት ያዘጋጀሁት። እግረመንገዴንም ለውዝግቡም ይሁን ለውዝግቡ መንስዔ የሆኑ ተቃርኖዎችን እዳስሳለሁ። ዓላማዬ ከፅንፉ እና ከፅንፉ ወዲህ ዓለም እንዳለ ለማሳየት እንጂ መሞከር ብቻ ሳይሆን ፍረጃችን ተፅዕኖ እንዳለው ማስታወስም ጭምር ነው።

ቄሮ – ሥያሜው ምን ይነግረናል?

‘ቄሮ’ ቃሉ ‘ያላገባ፣ ያልወለደ’ ወጣትን ይወክላል። ነገር ግን ወጣት የሚለውን ቃል የሚተኩ ሌሎች የኦሮምኛ ቃላት አሉ። እነዚህም ‘ደርደሩማ’፣ ‘ደርገጌሳ’ እና ‘ጎሮምሳ’ የሚሉት ቃላት ምሳሌ ይሆናሉ። ቄሮ የሚለው ቃል ምንጩ ‘ቄረንሳ’ ከሚለው እና ነብር የሚል ትርጉም ካለው ቃል የተቀዳ እንደሆነ ይነገራል። ስለዚህ ቄሮ ማለት እንደነብር ያለ ብርቱ ወጣት ማለት ነው፣ ማለት እንችላለን። ይሁን እንጂ አሁን በተለይ በኦሮሞ ፖለቲከኞች ዘንድ ‘ቄሮ የሚለው ቃል ፍቺ ‘አብዮተኛ ወጣት’ የሚል ትርጉም አለው።

“የቄሮ ንቅናቄ” ውልደት እና ዕድገት

ቄሮ የሚለው ቃል የፖለቲካ መድረኩ ውስጥ የገባው እ.ኤ.አ. በ2011 የአረቡ አብዮት በፈነዳበት ወቅት ነበር። መቀመጫውን ዳያስፖራ ያደረገው ንቅናቄ ከዩንቨርስቲ ተማሪዎች ጋር ግንኙነት በመመሥረት ‘ቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ’ የሚባል ኢመደበኛ ማኅበር ፈጠረ። የዚህ ማኅበር አባላት መረጃዎችን በኢሜይል እና በድረገጻቸው እየተለዋወጡ በርካታ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ቀጠሉ። ሥማቸው በይፋ የተነሳው ግን በ2006 የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላንን ተከትሎ በተነሳው እና ዩኒቨርስቲዎችን ባዳረሰው የተቃውሞ ሰልፍ ወቅት ነው።

ከዚያ በኋላ የተጋጋለው የተቃውሞ ሰልፍ መላው ኦሮሚያን ሲያዳርስ በየአካባቢው ያሉ ወጣቶች ራሳቸውን ቄሮ ብለው መጥራት ጀመሩ። የመጀመሪያው የቄሮ አደራጅ የነበረው (qeerroo.org የተባለ) ድረአምባም ይሁን የፌስቡክ ገጹ አሁን እምብዛም ተከታታይ የላቸውም። ይልቁንም የወጣቶቹ ኅብረት መሪ ተደርጎ በዘልማድ የሚወሰደው የኦኤምኤን ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃዋር መሐመድ ነው።

ከዚያ በኋላ በኦሮሚያ ክልል፣ በየአካባቢው የሚነሱት ተቃውሞዎች ውስጥ የሚሳተፉ የተደራጁም ይሁኑ ያልተደራጁ ወጣቶች በሙሉ – ራሳቸውን ሲገልጹም ይሁን ሌሎች ሲገልጿቸው – ቄሮ በሚል ሥያሜ ሆነ። ቄሮ በዚህ አካሔድ በማንም ግለሰብ ወይም ቡድን ቁጥጥር ሥር ያልሆነ፣ ነጻ ነገር ግን በኦሮሙማ (ኦሮሞነት) የተሰባሰበ ኢመደበኛ ቡድን ሆነ። ይህ ማለት ግን ወጣቶቹ በፖለቲካ ፍልስፈፍናቸውም ይሁን ብስለታቸው፣ በኢትዮጵያ እና ኦሮሚያ ታሪክም ይሁን ፖለቲካ አረዳዳቸው ወጥ አቋም አላቸው ማለት አይደለም።

ይህ በእንዲህ እያለ በአማራ ክልል የነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ላይ የሚሳተፉትን ወጣቶች ሥም ለመስጠት ተሞከረ። ‘ፋኖ’ የሚለው ሥያሜ ‘ቄሮ’ ከሚለው ጎን ለጎን መጠቀሱ የተለመደ ነገር ሆነ። ያን ጊዜ በቄሮ ሥምም ሆነ በፋኖ ሥም የሚደረገው ነገር በሙሉ፣ ማዕከላዊ መንግሥቱን እስካስጨነቀ ድረስ “ትክክል” ነበር። ይሁን እንጂ መሬት ላይ “ቄሮ ነኝ” የሚሉትን ያክል፥ “ፋኖ ነኝ” የሚሉ ወጣቶች እምብዛም አልነበሩም። እንዲያውም ‘ፋኖ’ የግንቦት ሰባት ፈጠራ ነው የሚሉ የአማራ ብሔርተኞች ገጥመውኛል። ይሁንና የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ አሁን ለምናየው የለውጥ አዝማሚያ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ወጣቶችን ሲጠሩ “ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ…” እያሉ መጥራትን ‘ፕሮቶኮል’ አድርገውታል።

የትግሉ እንዲሁም የድሉ “ባለቤቶች”

የያኔዎቹ ኦሕዴድ እና ብአዴን ተባብሮ ትሕነግ ላይ ማበይ፥ ከወጣቶቹ አመፅ ባልተናነሰ (ወይም በበለጠ መልኩ) ኢሕአዴግን ነቀነቀው። የፓርቲዎቹ ከወጣቶቹ ጋር ያልተጻፈ መግባባት ላይ መድረስ ደግሞ የቀድሞውን ኢሕአዴግን ገድሎ፣ አዲሱን ኢሕአዴግ ወለደ። አሁን ከትሕነግ/ኢሕአዴግ ወደ ኦዴፓ/አዴፓ/ኢሕአዴግ አገዛዝ ተሸጋግረናል። ይሁንና ገና አመፁ አልሰከነም። የትግሉ ባለቤት ተቃዋሚዎች በሙሉ፣ በተለይም አደባባይ የወጡት የኢትዮጵያ ወጣት አመፀኞች ናቸው፤ የድሉ ባለቤቶች ግን የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች፣ በተለይም ኦዴፓ እና አዴፓ ናቸው። ያለእነሱ ከቀድሞ አቋማቸው መቀልበስ፣ እንዲሁም ለማበር መወሰን በኢሕአዴግ ቤት አሁን ያለው ወደ ዴሞክራሲ የመሸጋገር ዕድል ፈፅሞ አይመጣም ነበር ብዬ እገምታለሁ።

ይሁንና ወጣቶቹ የልኂቃን ተቃዋሚዎችን ጥያቄ ከማስተጋባት ባሻገር ለእንዲህ ያለ ነፍስን አሳልፎ እስከመስጠት የሚደርስ ብሶት የዳረጋቸው ሥራ አጥነት እና ‘የሪከግኒሽን’ ጥያቄ መልስ ቢሰጠው ኖሮ፥ ድሉን የጋራ ድል አድርገን መቁጠር የምንችልበት ዕድል ይኖር ነበር።

አሁን ባለው ሁኔታ ብዙኃን ሥራ አጦች በየአደባባዩ በከፈሉት መስዋዕትነት፥ ‘እነዚህ ሥራ ፈቶች ደግሞ መረበሽ ጀመሩ’ እያሉ ይበሳጩባቸው የነበሩ ልኂቃን በአንድ በኩል፣ እንዲሁም በሌላ በኩል ደግሞ ‘እስከመቼ እንዲህ ተዋርዳችሁ ትኖራላችሁ፣ ታግላችሁ ነጻ ውጡ እንጂ’ እያሉ ሲቆሰቁሷቸው የነበሩ ልኂቃን ሥልጣን እየተቆጣጠሩ ሲመጡ ወጣቶቹ ችላ መባላቸው ሐቅ ነው።

ይህ ነገር ምናልባትም የትግሉ “ባለቤቶች” እና የድሉ “ባለቤቶች” ወይም “ተጠቃሚዎች” መካከል መቃቃር ሳያስከትል አይቀርም። ይህ ጉዳይ አዲስ ብሶት የሚወልድ መሆኑም የጊዜ ጉዳይ ነው።

“ጀግኖች” የነበሩ “ፅንፈኞች”
(የውክልና ጦርነት መሣሪያዎች)

በየአካባቢው በሥራ አጥነታቸው ምክንያት ዋጋ አጥተው፣ በአደገኛ ቦዘኔነት ተፈርጀው ከፊሉ ስደት እየበላቸው፣ ከፊሉ ሱስ እየዋጣቸው የነበሩ ወጣቶች ድንገት የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመፅ ማገዶ ነበሩ። ያኔ “ጀግኖች” ተብለዋል። ምክንያቱም ለልኂቃኑ ፖለቲካ ሁነኛ መሣሪያ ነበሩ። ወጣቶቹ ምናልባትም አእምሮ ከሚያላሽቅ የሥራ አጥነት ስሜት ወጥተው፥ ለራሳቸው ያላቸው ዋጋ እና ግምት የጨመረው በዚህ አመፅ ባደረጉት ተሳትፎ ይሆናል። ሕዝባዊ አመፁ ቆሞ ድንገት አገር መረጋጋት ሲጀምር ግን ወደ “መንደር ያሰለቹ አደገኛ ቦዘኔነት” መመለሳቸው ሆነ። ከተሰጣቸው ሥም መውረድ ከባድ ነው። ስለሆነም የአብዮታቸው ጠባቂ ሆኑ – ከሳሽ፣ ፈራጅ እና ቀጪ። የደቦ ፍርድ፤ በዚህ ወቅት ነው በፅንፈኝነት መፈረጅ የጀመሩት።

በዕውቁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የምትመራው ‘ኢትዮጲስ’ ጋዜጣ (በጥቅምት 24, 2011 እትሟ) በርዕሰ አንቀፅዋ ቄሮዎችን ለዘብተኛ እና ፅንፈኛ በሚል ከለያየቻቸው በኋላ ፅንፈኞቹን የማስቆም ሥራ መሠራት እንደሚገባ ጠቁማለች። የኢትዮጲስ ስህተት ምናልባት (አንድም) በአገሪቱ የደቦ ፍርዶች እና ወደ ስርዓት አልበኝነት የሚወስዱ እንቅስቃሴዎችን ለቄሮ ብቻ ለይታ መስጠቷ ነው። መቼም በድንጋይ ወግሮ መግደል እና በእንጨት ላይ ዘቅዝቆ መስቀልን የመሳሰሉ የደቦ ፍርዶች አንዱ ከሌላው የሚሻሉበት መንገድ አለ ተብሎ አይታመንም። በዚህ ረገድ ጉዳዩ ‘ወጣት ፅንፈኞች’ በሚል ሊጠቃለል ይችል ነበር ብዬ አምናለሁ። (ሁለትም) ቄሮ የተጻፈ ፕሮግራም የሌለው፣ አባላቱ በዝርዝር የማይታወቁ፣ አንድ ስትራቴጂ እና ግብ የሌለው የግፉአን ማኅበር መሆኑን ከግምት ውስጥ ያላስገባ መደምደሚያ መሆኑ ስህተት ያደርገዋል። ይህም ማለት ማንም ተነስቶ ቄሮ ነኝ ብሎ ማወጅ እና በዚያ ሥም ወንጀልም ይሁን መልካም ጀብዱ መፈፀም ያስችለዋል ማለት ነው። ብዙኃን መገናኛዎች ግን ቡድኑን ግልጽ ቅርፅ እና መዋቅር እንዳለው እንዲሁም “ተግባሩን” አቅዶ እንደፈፀመ ማኅበር ተመልክቶ “እንዲህ ነው” ወይም “እንዲያ ነው” ማለት የተሳሳተ ትርጉም ይሰጣል። (ሦስትም) የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች – ለምሳሌ የጃዋር “የቄሮ መንግሥት” እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ “ፀጉረ ልውጦችን መቆጣጠር” የመሳሰሉ – ንግግሮች ወጣቶቹን የውክልና ጦርነት ውስጥ እንደከተታቸው ከግንዛቤ ያላስገባ መደምደሚያ መሆኑ ነው።

ፍረጃ እና ተፅዕኖው፤
እስመ ሥሙ ይመርሖ ሀበ ግብሩ
(nomen est omen)

ቄሮንም ይሁን ፋኖን ወይም ሌላ የፖለቲካ ቡድኖችን በተመለከተ ለምናደርጋቸው ፍረጃዎች ማድረግ የሚገባን ጥንቃቄ አለ። ፍረጃ (labeling) በሥነ-ልቦና ግንባታ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንዳለ በርካታ ጥናቶች ያሳያሉ። «እነ እከሌ ይህን አያደርጉም»፣ «እንትን ሆኜ እንዲህ አላደርግም» የሚሉ አባባሎች የሚያስረዱን ቁምነገር ቢኖር የሆኑ ሰዎች ስብስብን የሚገልጽ ማንነትን የምንበይንበት (labeling/defining) መንገድ መልሶ የአባላቱን ድርጊት እንደሚወስን መረዳት እንደሚያሻን ነው። “ቄሮ አብዮተኛ ወጣት ነው” በተባለ ጊዜ አደባባዮችን በተቃውሞ ሰልፎች ንጧል። የለውጥ ጀምበር ሲከፈት “ለውጡን ጠብቁ” ሲባል እንደዚያው ለማድረግ እየሞከረ ነው። ወጣቶቹ በልኂቃኑ የሚሰጣቸውን ሥያሜ ለመመጠን እየተፍጨረጨሩ ነው። “ቄሮ መንግሥት ነው” ብለን ከአቅሙ በላይ ሥራ ከምናሸክመው፣ “ቄሮ የዴሞክራሲ እና የሥልጡን ፖለቲካ ጠበቃ ነው” ብለን በዚህ አቅጣጫ እንዲተጋ ብናደርገው ይመረጣል። “ቄሮ ፅንፈኛ ነው” እያልን ወደዚያ ከምንገፋው “ቄሮ ይህንን አያደርግም” ብለን ብንገስፀው ይሻላል።

ቺርስ ለጥንቃቄ!

3 COMMENTS

 1. Few ethink leaders should not disturb our pease ….we Ethiopians are so hybrid and homogeneous peope … All human being blood s are the same when you go to laboratory …… 4 types

 2. Dear Befekadu,

  I agree with some of your points. But you are an irrational when you say that Qerroo has struggled because of unemployment problems. You tried to describe them all as jobless and wthout political objectives. What about you and the stupid and racist Eskinder Nega. Were you jobless and without political objectives that you struggled against the TPLF? You can answer for yourself.

  Eskinder Nega ist a disrespectful modern Debitera who tries to sell his backward ideas as a journalistic works and views. He has no merits as journalist. His recognition was just a political drama which was organized by some of his peers. No more!

  This ugly guy, Eskinder Nega, is one of the worst and mentally bankrupt human beings in Ethiopia today. His mission is just distracting. He writes here and there nonsense which may promote division and enmity among different peoples of Ethiopia. But it is futile.

  The main problems with the offsprings of the ex-neftengas like Eskinder are their greediness and selfishness. They are still dreaming for the “golden” time of the their forefathers. Even they had only conflicts of interest with the TPLF. They don’t care for true unity, democratic rights and justices.
  The Menilik of Eskinder Nega is the Hitler of Africa. Down with all his hegemony mentalities and plans! Anti-unity and toxic are those like Eslinger Nega, the arogant Berhanu Nega and their disciples in crimes against humanity. They don’t believe in unity with diversity.

  No more business as usual. Even his radical statements make the Oromo nation and other subjugated nations in Ethiopia more strong and determined to fight his backward and uncivilized mentalities. He will see soon the uprooting and eradication of his bankrupt ideology.

  The politics of one language, one culture and a single nation cannot be accepted any more in Ethiopia. Don’t forget that such demands have no room in today’s Ethiopian politics. But now temporally you can make noise here and there. That is all what you can do right now.
  De-Amharanisation of the whole Ethiopian politics is indispensable and absolutely necessary in order to reform and reshape Ethiopia as a country of multinational state. The politics of one language, one culture and a single nation cannot be accepted any more. Also there is no Ethiopian identity as some idiotic individuals try preach us those like the chameleon Ermias Legesse. It is a fake identity and ridiculous.

  Disassociating Ethiopia from the politics of Menilik is indispensable for emancipation of all the nations. The creation a new national flag is crucially important in order to build a national consensus. The new flag should have reflect a true multinationality of that country.

 3. በግሌ አስተያተያት “ለውጥ” የተገኘው በቄሮ፣ በፋኖ እየተባለ የሚዘባረቀውን ቱልቱላ አልስማማበትም፡፡ ዐብይ እንዴት ስልጣን ላይ እንደመጣና በሱ በኩል የተገኙ የማንክዳቸው እድሎች ተፈጥሮልናል፡፡ እሰየው!!! አንድ ማመን ያለብን ነገር ወያኔ ነገሩ አላምር ስሊው ስልጣኑን ጥሎ እኮ መቀሌ ዋሻ ነው የገባው፡፡ በስላም ፈርቶ መፈርጠጥም እኮ ትልቅ ነገር ነው ጦር አንስተው እንዋጋ ብለው ህዝብ አለማስረጨሳቸው፡፡ እንዲያውም የወያኔ በሰላም መፈርጠጥ እና የእንዳርጋቸው ጽጌ፣ የእስክንድር ነጋ መታሰር በዓለም ድረጃ የኢትዮጵያን ፓለቲካ አጉሊ መነጽር ውስጥ ማስገባቱ ለመጣው “ለውጥ” አሳማኝነት አለው ቄሮ ፋኖ እያልን በባዶ ሜዳ ክምንቀባጥር ፡፡ የመታሰራቸው ሁኔታም ለለውጥ ትልቅ አስተዋጻኦ አድርጓል ብል ሊያከራክረን ይችላል ባይ ነኝ፡፡ ቄሮ ለእስክንድር ሲጮህ አንድም ቦታ አላየንም፡፡ ፋኖ በግንቦት 7 አርበኞች ምክንያት ለታሰሩት ሁሉ ለበቀለ ገርባ ሳይቀር ጠዋት ማታ ጮዃል፡፡ ጽሁፍህ ፈራ ተባ እያልክ የጻፍከው ስለሆነ ምን ለማለት እንደፈለክ እና ያለን አቋም በትክክል ልረዳ አልቻልኩም፡፡

  እስክንድር ነጋ የሰው መብት ተሟጋች ነው ፣ ለቆመበት ዓላማም ከነቤተስቡ ብዙ መክራ የጠቀበለ ቁርጠኛ የኢትዮጵያ ወርቅ ልጅ ነው!!! እስክንድር ያስቀመጣቸው የአገራችንን የወቅቱን ቀውሶች ሁላችንም ስላም ፈላጊ ኢትዮጵያውያኖች ውስጥ ያለውን ስጋትና ፍራቻን ነው ግልጽ አድርጎ ያስቀመጠው፡፡ ጃዋር “ለውጥ” የመጣው ቂሮና ፋኖ እያለ በተለይ ስለ ቄሮ እያጋነነም ነው የሚናገረው፡፡ የጃዋር የፌስቡክ ተከታይ ሁሉ በሱ ቤት ቄሮ ነው፡፡ ቁመነገሩ ግን ማን “ለውጥ” አመጣ የሚለው የህጻን ጥያቄ አይደለም ሁላችንን ሊያሳስበን የሚገባው፡፡ ቄሮ ነው ለውጥ ያመጣው ካልክም ይሁንልህ፡፡

  ቄሮ “ለወጥ ” አምጥቼያለሁ ብሎ የሚነግረን ከሆነ በአገሪቱ ንጹሃን ወገኖቻችንን እናቶች፣ ህጻናቶች ከየቦታው እየተፈናቀሉ ልብ በሚሰብር ሁኔታ ጠዋት ማታ እምናየው እውነታ ስለሆነ ለዛም ሃላፊነት የመውሰድ ግዴታ አለበት፡፡ ለውጥ አመጣሁ እያሉ መደንፋትና መጨፈር እና ሰው ዘቅዝቆ ሲሰቅሉ ደግሞ እኔ አይደለሁም ማለት ከሃላፊነት የጎደለ እራሱን የቻለ ወንጀለኛነት ነው;፡፡

  በየጊዜው ወገኖቻችንን መጤ እየተባሉ እየተሰደዱ ፣ ቤታቸው በእሳት እየጋየ እምንመለከተው ህጻናት ሳይቀር ልብ በሚሰብር ሁኔታ የምንመለከትው መነሻው ቄሮ በለው ኦነግ በኦሮሞ ድርጅት እየተፈጠረ ያለ የህብረተሰብ ቀውስ ነው፡፡

  ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሆነ ዜጋ ወገኖቻችንን በገዛ አገራቸው እንደመጤ እየተቆጠሩ ከሚኖሩበት አገር እየተፈናቀሉ መሰደድ መመልከት ሊያሳስበውና ሊያስቆጣው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ግዴታ ከአንድ ዘር መወገን የለብህም፡፡ የሰብአዊ መብት እንዲከበር መጠየቅ እንዲኖር ግዴታ እስክንድር ነጋ መሆን የለብንም፡፡ እንደ እስክንድር ነጋ ማንኛውም ሰው አገራችን እያየን ያለውን የሰው መፈናቀል ሁኔታ ሊያስቆጣንና ፣ ሊያሳስበን ለሁላችንም ይገባል፡፡ ይሄ ክልሌ እያለ ህዝብን የሚከፋፈል ቅዥታም ህገ መንግሥት የዐብይ መንግሥት ለውጥ ማድረግ ፈቃደኛ ካልሆነና የፓለቲካ ትርፍ እያከማቸበት ክሆነ በአስቸኳይ አስተዳደሩ ውስጣዊ መፍትሄ የመፈለግ የህዝብን ደህንነትና ህልውና የማስጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡

  ፍትህ ለኢትዮጵያ ወገኖቻችንን!!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.