በእግዜር እና በኮንዶሚኒየም ተስፋ ላልቆረጠው የአዲስ አበባ ነዋሪ (ከላጡኝ ጉመዡ)

እንደምን ከረማችሁ ፤ ጥቅምት 29 2011 ዓ.ም የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር በሮ ጥቅምት 30 2011 ዓ.ም ላይ ሊያወጣ እቅድ የያዘለትን የኮንዶሚኒየም እጣ አወጣጥ ስነ ሥርዓት የመገናኛ ብዙሐን ባሉበት እጣው የማይወጣበትን ምክንያት በምክትል ቢሮ ኃላፊው አማካኝነት ሲያሳውቅ ሚዲያ ላይ ሰማሁ፡፡ እኔም የማውቀውን ጥቂት ለማለት ወደድኩኝ፡፡

አንደኛ፡-

የአዲስ አበባ ነዋሪ በ1997 ዓ.ም ለኮንዶሚኒየም ቤት እጣ ተመዝግቦ ይህው እጣውን ሲጠብቅ ድፍን 14 ዓመት ሞላው ፤ ይህ የሆነበት ምክንያት እስከ አሁን የተሰሩት ቤቶች ለተመዝጋቢው መድረስ አቅቷቸው ሳይሆን በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ ለምሳሌ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌደሬሽን ምክር ቤት የመሰሉ ግዙፍ የሀገሪቱ ተቋማት ለተመራጮቻቸው የቤት ፍላጎት ለማሳካት የቤት ጥያቄዎችን የሚጠይቁት አዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደርን ነው፡፡ ይህም ተቋም እነዚህን ተቋማት እምቢ የማለት አቅሙ ስለሌለው የጠየቁት ቤቶች መቶም ሆነ ሦስት መቶ አንስቶ ከመስጠት ውጪ አማራጭ የለውም፡፡ በተጨማሪ የልደታ መልሶ ማልማት ሥራ በሚሰራበት ወቅት 2500 ቤቶች  ነበሩ ፤ ነገር ግን ቤቶቹ ተሰርተው ለነዋሪ የተላለፉት 1800 የሚያንሱን ብቻ መሆናቸውን ያወቅነው በስተመጨረሻ ነበር፡፡ ይህም የሆነበተ ምክንያት ከልደታ ሳይት ብቻ 700 ቤቶች ለባለስልጣኖች ሕግን መሰረት ያላደረገ እደላ ቀድሞ በመከናወኑ ነበር፡፡ ይህ ማስረጃም/መረጃም ስላለው የአሁኑ የከተማው አስተዳደር በምን ሁኔታ ቤቶቹ እንደተላለፉ በነካ እጁ ቢመለከተው የሚል አስተያየት አለኝ፡፡

ከ6 ዓመት በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጎፋ ሳይት የተሰጡትን ከ50 በላይ ባለ ሁለተ መኝታ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለተመራጮች ባስተላለፈበት ጊዜ ቤቶቹ እኛን የሚመጥኑ አይደሉም ተብለው በፓርላማ ለሰራተኞች በእጣ የተላለፈበት ጊዜም ነበር፡፡ ይህ ፓርላማ ዛሬ ላይ ይህን ቢል ጥሩ ነበር፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቦሌ ማተሚያ ፊት ለፊት እና CMC በወር 150 የመብራትና የውሃ ብቻ እየከፈሉ የሚኖሩበት አካባቢ ነው፡፡

ሁለተኛ ፡-

ላለፉት በርካታ  ዓመታት ፤ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ፤ ከመከላለከያ ፤ ጡረታ የወጡ የጦር ጉዳተኞች ምናምን እየተባለ በየሳምንቱ ከቀበሌ ፤ ከወረዳ እና ከክፍለከተማ በተጨማሪ ከከፍተኛ የመንግሥት ተቋማት የድጋፍ ደብዳቤ እየያዙ እስከ ቅርብ ወራት ድረስ የኮንዶሚኒየም ምዝገባ ሲካሄድ ነበር፡፡ ይህም ቢያንስ በሳምንት ከ 200 በላይ ተመሳሳይ ጉዳይ ያላቸው ግለሰቦች በ1997 ዓ.ም የመረጃ ቋት ውስጥ የሚገቡበት አካሄድ ይመቻችላቸው ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ተመዝጋቢዎች አሳማኝ መረጃ ይዘው ቢመጡም ብዙዎቹ ግን የሚሰሩበትን ተቋም ተገን በማድረግ በመስሪያቤታቸው ጡንቻ በመተማመን ሙሉ የሙያ ልብሳቸውን ማዕረጋቸውን ጨምሮ ከአጋዥ ደብዳቤ ጋር የሚመጡበት አኳሃን በመኖሩ ምዝገባው እስከ 2010 ዓ.ም የመጨረሻዎቹ ወራት ሲከናወን ነበር፡፡ አሁን ያለው የከተማ አስተዳደር እነዚህ ከሕግ ውጪ ከ14 ዓመት በፊት የተከናወነን ምዝገባ ቋት ውስጥ የገቡ ሰዎችን የሚመረምርበት መንገድ ቢያዘጋጅ እና ኦዲት ቢያደርግ መልካም ነው፡፡

ሦስተኛ ፡-

ይህን የቤት ፈላጊዎች ሲስተም ያበለጸገው INSA ሲሆን ጠቅላላ የሶፍትዌሩ መረጃ በኢንሳ እጅ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ለበርካታ ጊዜያት  INSA ያበለጸገውን ሶፍትዌር ለተቋሙ እንዲያስረክብ ፤ ባለቤትነቱም በቤቶች አስተዳደር ስር እንዲሆን ደብዳቤ ቢጻፍለትም እስከ መጨረሻው ዙር የቤቶች እጣ አወጣጥ ስነ ስርዓት ድረስ መረጃው በ INSA ስር ይተዳደር ነበር፡፡ ይህ ማለት በባህር መዝገብ የተመዘገቡ የቤት ፈላጊዎች ባሕር መዝገብ ላይ በወቅቱ እንደተመዘገቡ ተጣርቶ ፤ ሲስተም ውስጥ እንደገቡ ተረጋግጦ ፤ ከዚህ በፊት ቤት ያልወጣላቸው መሆናቸውን በባለሙያ ተፈትሾ ሌሎችም ውስጣዊ ሂደቶችን አልፈው የእጣ ማውጣት ስነ-ስርአት ውስጥ መግባት ሲገባቸው የሆነው ግን ሕግና መመሪያን ያልጠበቁ በመሆናቸው ሶፍትዌሩን ያበለጸገው አካል በሚሰጠው መረጃ መሰረት ቤቶች እጣ እንዲወጣ በመደረጉ ምክንያት ይህ ነው የማይባል ጉዳት በሕዝብና በመንግስት ላይ ደርሷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የመረጃ ቋቱ ብዙ ችግሮች እንዳሉበት እየታወቀ INSA ችግሮቹን ተቀብሎ አፋጣኝ ማስተካከያ መስጠት ባለመቻሉ ፤ ሶፍትዌሩ በሚሰራበት ጊዜ ሦስተኛ ወገን ተቆጣጣሪ ባለመኖሩ በርካታ ችግሮች ሲያጋጥሙ እንደነበር ፤ ይህ የቤቶች መረጃን በሦስተኛ ወገን አስቀምጦ እጣ ማውጣት ስርዓት ማከናወን ሕጋዊ ጥያቄ ማስነሳቱ ይታወቃል፡፡

አራተኛ ፡-

እጅግ ለቁጥር የሚያዳግቱ ተደጋጋሚ የሰዎች ምዝገባ በመረጃ ቋት ውስጥ መገኝት ሌላኛው ችግር ነው፡፡ ይህ ማለት አንድ ሰው እጣ ወጥቶለት ሲያበቃ ሲስተም ውስጥ በስህተት ወይም ሆን ተብሎ እንዲቆይ ስለሚደረግ በርካታ የቤት ፈላጊዎች ስም መደጋገም ሲያጋጥም ተመልክቻለው ፤ ሦስተኛ ዙር ላይ የወጣለት ሰው 7ኛ ዙር ላይ ደግሞ ይወጣለታል፡፡ የበለጸገው ሶፍትዌር ላይ System Higher privilege ያለው ሰው በሚቀያይረው ጊዜ ሌላ ሦስተኛ ተቆጣጣሪ አካል አለመኖር ሌላኛው ችግር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የቤት እጣ ወጥቶላቸው ከባንክ ጋር ስምምነት የማይፈጽሙ ሰዎች ሥም ዝርዝር በሚታይበት ጊዜ ሁለቴ ወይም ሦስቴ ቤት የወጣላቸው ሆነው የተገኙበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡ የሲስተሙ ቋት በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ውስጥ ይገኛል፡፡ 14 ዓመት ጠብቆ ቤት የሚወጣለት ባለዕድለኛ እንዳለ ሁላ 14 ቀን ሲቀረው ተመዝግቦ የወጣለት ሰው ስላለ አሁንም ይህን የመሰሉ ጥልቅ ምርመራ የሚፈልጉ ጉዳዮችን ኦዲት ቢደረጉ መልካም ነው፡፡ በተጨማሪ ከ1997 ምዝገባ በኋላ ምን ያህ ሰዎች በሕጋዊ/ሕገወጥ መንገድ እንደተመዘገቡ ቢጣራ፡፡

አምስት ፡-

አሁን ያለችው የቤቶች አስተደደር ኃላፊ ኢንጅነር ሰናይት ትባላለች፡፡ ከሷ በፊት ያለው ደግ አቶ ይድነቃቸው(ከኢሕአዴግ በላይ ኢሕአዴግ የሆነ ሰው ነው ይሉታል) ይባላል፡፡ በአቶ ይድነቃቸው ጊዜ የቤት ኦዲት እንዲደረግ መመሪያ በመስጠት ኦዲት ተደርጎ ነበር ፤ ይህ ኦዲት ካልተሳሳትኩ ከዓመት በፊት የተደረገ ነበር፡፡ አንድ የቤት ኦዲት በሚደረግበት ጊዜ ኮሚቴ ከማዋቀር በኋላ የመጀመሪያ ስራው የቤት ኦዲት የሚያደርግበትን መስፈርት ማውጣት/ማዘጋጀት ነበር፡፡ ይህ መስፈርት ደግሞ ማዘጋጀት ያለበት ኮሚቴው እንጂ ከላይ የወረደ መሆን መቻል የለበትም፡፡ መስፈርቱ ከላይ ከወረደ በርካታ ቤቶች በኦዲት ሪፖርት እንዳይገኙ ከለላ ይሰጣቸዋል፡፡ ኦዲት የሚደረግበት መስፈርት(Criteria) ከኮሚቴው በፊት በመቅደሙ ኦዲቱ የታሰበለትን አላማ ሊመታ አልቻለም፡፡ ኦዲት ሲደረግም የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ብቻ በመደረጉ ውጤቱ ሙሉ ሊሆን አልቻለም፡፡ ይህ እንዲህ እያለ በሕገ ወጥ መንገድ የተላለፉ ፤ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ውል የገቡ ፤ የተዘጉ ቤቶች ፤ ባለቤት የሌለባቸው ፤ የተላለፈው ቤትና ውሉ የማይጣጣም ፤ ውል ሳይገቡ ቤቱ የተላለፈላቸው ፤ ባሕር መዝገብ ውስጥ የሌሉ ፤ ወ ዘ ተ… ቤቶች እየበዙ ሲሄዱ የቤት ኦዲቱ ሊቆም ችሏል፡፡ በጣም የሚያሳዝነው መንግሥት ይህን ያህል ቤቶች በሕገወጥ መንገድ የተላለፉ ተገኝተዋል ብሎ መግለጫ ሲያወጣ ፤ ቤቶቹ የተገኙበት መንገድ እና የኦዲት ሂደቱን የሚጠይቅ ጋዜጠኛ አለማየታችን ነው፡፡

ጋዜጠኛው 500 ቤት በኦዲት በሕገ ወጥ መልኩ ተገኝቷል የሚለውን ሪፖርት ለመቀበል ብቻ ሳይሆን (ጊዜውን ፤ ሳይቶቹን ፤ የተገኙበትን መስፈርት ፤ የተወሰደውን ሕጋዊ ርምጃውን ፤ ኮሚቴው የተዋቀረበትን አግባብ ፤ ወደፊት ምን መደረግ አለበት ፤ ቤት እጣው ደርሷቸው ያልተዋዋሉ ቤቶች ስንቱ በምን ? ለቀጣይ ባለበት  ተላለፉ ፤  … ማንሳትና ማፋጠጥ አለበት፡፡)

ስድስት ፡-

ኢንጅነር ሰናይት (ኃላፊ) ተሹማ ለጋዜጠኞች መግለጫ ለመስጠት ደብዳቤ ለሁሉም ሀገር ውስጥ ላሉ የመገናኛ ብዙሀን ተልኮ ነበር አሉ፡፡ ከዚያ በፊት ኢንጅነር ሰናይት ተቋሙ ላለፉት 14 ዓመታት ምን ያህል 20/80(አንድ ፤ ሁለት እና ሦስት መኝታ)  ፤ 10/90 (ስቱዲዮ) ቤቶች እንደገነባ ፤ ለመምህራን ፤ ለመንግስት ባለስልጣናት ምን ያህል እደተላለፉ እና ለባለ እድለኞች ምን ያህል እንደወጣ ፤ ቤቱን ለሚሰራው አካል የሰራውን የቤት መጠን በየሳይቱ ፤ ቤቱን ያስተላለፈው ክፍል ደግሞ ለምን ያህል እድለኞች ቤቱን እንዳስተላለፈ መረጃ ፈልጋ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በላከችው የውስጥ ደብዳቤ ያገኝችው መረጃ የሰማይና የምድር የተራራቀ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ ፤ የአዲስ አበባ ቤቶች ፕሮጀክት ፤ 40/60 እና የሚመለከታቸው አካላት ይህ ነው የሚባል ግልጽ ያለ መረጃ ያለመኖር ትልቁ ችግር ነው፡፡ አሁንም ለጋዜጠኞች ተቋሙ ጋር ሄዳችሁ ምን ያህል ቤቶች ተሰርተው ለባለእድለኞች? ለመንግስት ባለስልጣናት?   ለልማት ተነሺዎች? ለመምህራን ? ለድሃ ድሃዎች(10/90) ? በሽያጭ የተላለፉ ? ብላቹ ተቋሙን ብትጠይቁ እጃቸው ላይ ወደ ኋላ ሄደው ዓመተ ምህረት እያጣቀሱ በተጠየቁት መሰረት፤ የሚያመሳክሩትና የሚሞግቱበት ምንም መረጃ እንደሌላቸው ላሳውቃችሁ እወዳለሁ፡፡

ሰባት ፡-

ቤቶቹ እጣ ውስጥ ገብተው እጣውን የሚያወጣው ሶፍትዌር አዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ቢሮ አያስተዳድረውም፡፡ የተመዝጋቢዎች መረጃ የሚይዘው ኢንሳ ያበለጸገው ሲሆን ከሱ በተጨማሪመረ እጣ ማውጫ ሲስተሙን ኢንሳ የሰራው በመሆኑ ቤቶች አስተዳደር እጣው በሚወጣበት ጊዜ ከመመልከት ፤ ጋዜጠኞችንና የከተማ አስተዳደሩን ሆቴል ተከራይቶ ከመመልከት ውጪ ምንም ቦታ ያለው ተቋም አይደለም፡፡ ይህ ማለት የተሰራው የእጣ ማውጫ ሲስተም ለፍተሻ ፍተሻ ባለሙያ ባልሆኑ የበላይ አመራሮች የሚታየው እጣው ከመውጣቱ 3 ቀናት በፊት ነው፡፡ በጣም የሚያስቀው ነገር እጣው ሲወጣ ባለሙያዎች ከኤጀንሲ ፤ ከፕሮጀክት ፤ ከ20/80 እና ከተለያዩ ክፍሎች ይዋቀሩና እጣው ከወጣ በኋላ  ‹ትክክለኛነቱን› ይፈራረሙበታል፡፡ ዋናው ጉዳይ መሆን ያለበት እጣ የሚወጣበት ሶፍትዌር ተዓማኒነቱን ከማረጋገጥ በተጨማሪ በተቆጣጣሪ የሶፍትዌር ተቋማት ተረጋግጦ ማረጋገጫ ቢሰጠው ፤ አዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ቢሮች ሶፍትዌሩን ተረክቦ ራሱ ማውጣት ቢችል መልካም ነበር፡፡ አሁን ላይ ከ175 ሺህ በላይ እጣዎች በዚህ ሲስተም ተስተናግዶ ካበቃ በኋላ ሶፍትዌሩ ላይ እምነት የለኝም ማለት የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ተቋሙም በማያስተዳድረው ሲስተም ኃፊነት መውሰድ አይገባውም ነበር ፡፡ የሚያወጣው ኢንሳ እውቅናውን የሚሰጠው የሚፈርመውና አመሰግናለው የሚለው ቤቶች አስተዳደር!!! አያስኬድም….

ስምንት ፡- ከኮንዶሚኒየም ጨረታ ጋር የተያያዘ

ኮንዶሚኒየም ቤቶች ከተሰሩ በኋላ ከታች ያሉት ቤቶች በሽያጭ እንደሚተላለፉ ይታወቃል፡፡ እዚህ ላይ አሁንም እየተሰራበት ያለ አሳፋሪ ነገር ለመናገር እወዳለሁ፡፡ ይህም አንድ ተቋም ማንኛውንም ሶፍትዌር ማበልጸግ ያለበት የመንግስትን የግዥ ሕግና መመሪያ ጠብቆ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እዚህ ተቋም ውስጥ ግን ብዙ ጨረታዎች እየተወዳደሩ አሸናፊው እየተገለጸ ያለበት አንድ ግለሰብ በሰራው ሶፍትዌር አማካኝነት ነው፡፡ግለሰቡ ከተቋሙ አቶ ይድነቃቸው በነበረበት ጊዜም ሆነ ከዛ በፊት ደስ ያለውን ብር እየተቀበለ የጨረታ ሂደቱን ያከናውንላቸው ነበር፡፡ ይህን የሰራው ባለሙያ በሙያው ጥሩ አቅም ያለው ቢሆንም እስከ አሁን ተቋሙ የበለጸገውን ሶፍትዌር ያልተረከበበት ፤ የሚሸጡ ቤቶች ሲኖሩ ብቻ ከልጁ ጋር የሚደራደርበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ጨረታ የምትጫረቱ ሰዎችም ይህን በዚህ አጋጣሚ እወቁት ፤ አዲስ አበባ መስተዳደር ቀኑን ሙሉ ተወዘወፋችሁ ከአሁን አሁን ባሸንፍ ይህን ስራ እሰራበታለሁ የምትሉት የጨረታ ሂደት የሚብላላው/ የሚከናወነው በትክክለኛው መንገድ ያልተሰራ ፤ የጨረታ ሂደቱን ያልጠበቀ ፤ ከመሆኑም በተጨማሪ ሦስተኛ ወገን ያልፈተሸ ፤ ተቋሙም ያልተረከበው ማወዳደሪያ ነው፡፡ ይህን ለማወቅ ጋዜጠኞች ዛሬም መሄድ ትችላላችሁ፡፡( ሶፍትዌሩ በለጸገበትን ፤ ያወዳደሩበትን ፤ የተፈተሸበትን መንገድ አስረዱን በሏቸው)፡፡ በመጨረሻው ዙር የኮንዶሚኒየም የቤቶች ሽያጭ የጨረታ ውድድር 27ሺ ተወዳደሪዎች ነበሩ፡፡

ዘጠኝ፡-

በሉ ለዛሬ ይችን ያህል ካልኩ ይበቃል ፤ ደከመኝ … ሌላ ጊዜ ይህን ራሱ በአግባቡ ሳይደራጅና የራሱን ችግር ያልፈታ ተቋም የሕዝብ ችግር ለመፍታት የተቋቋመ መስሪያ ቤት አይነት ብዙ ስለሆኑ በሌሎች ልመለስ…  40/60 ሌላ ጊዜ…. አሁን ባለው ነባራዊ ሁናቴ አዲስ ተመዝጋቢቹ አይደለም ቤቶች አስተዳደር ተስፋ የሚያደርጉት እግዜር ይድረስላቸው ነው የሚባለው፡፡

ተስተካከሉ. . .  ራሳችሁን ለውጡ … . . ሕዝብም ተስፋ ያድርግ ነገር ግን ብዙም አያድርግ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.