ሜቴክ ያለ ህጋዊ የጨረታ ሂደት የ37 ቢሊየን ብር የውጭ ሃገር ግዢ ፈጽሟል

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 3 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ያለ ህጋዊ የጨረታ ሂደት የ37 ቢሊየን ብር የውጭ ሃገር ግዢ መፈጸሙን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገለጸ።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎችንና በፍትህ ስርዓቱ እየተሰሩ ስላሉ ስራዎች   መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከ2004 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ባከናወናቸው ግዢዎችና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ምርመራ በማድረግ መረጃ መሰብሰብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በዚህም ተቋሙ በሃገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ በንብረት ግዢ እና ፋይናንስ ጋር በተያያዙ የግዢ ሂደቶች ላይ ከፍ ያለ የህግ ጥሰት መፈጸሙን አስረድተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የ37 ቢሊየን ብር የውጭ ግዢን ያለ ጨረታ ሂደት ማከናወኑን ተናግረዋል።

ግዢዎቹ በተቋሙ የበላይ ሃላፊዎች፣ በሃላፊዎቹ የስጋ ዘመድ፣ በጥቅም በተሳሰሩ ግለሰቦችና ተቋማት መካከል እንዲሁም በደላላዎች የተፈጸሙ መሆናቸውንም ነው ጠቅላይ አቃቤ ህጉ የተናገሩት።

ከሃላፊዎቹ ጋር የስጋ ዝምድና ያላቸው ግለሰቦችም እንደ ደላላ በመሆንና ተቋሙን ከተለያዩ አለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በማገናኘት ግዢው እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ጠቅሰው፥ በዚህም በቢሊየን የሚቆጠር የሃገር ሃብትና ንብረት መመዝበሩን አንስተዋል።

የንብረት ግዢው ከአንድ ኩባንያ በድግግሞሽ እንደሚፈጸም ያነሱት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፥ በዚህ ሂደት ግዢው ላይ እስከ 400% የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ግዢው ይፈጸም ነበርም ነው ያሉት።

በዋናነትም ቻይና እና ሲንጋፖር ከሚገኙ ኩባንያዎች ግዢው የሚፈጸም ሲሆን፥ የስጋ ዝምድና ያላቸው ደላሎችም በዚህ ሂደት ከፍተኛ ገንዘብ ያገኙ ነበር ነው የተባለው።

ከዚህ ባለፈም ተቋሙ የሃገር ውስጥ ግዥን ሙሉ በሙሉ ያለምንም ጨረታ ሂደት መፈጸሙንም አስረድተዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.