የሰኔ 16ቱ የቦምብ ጥቃት በብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት የቀድሞ ሀላፊ የተመራ ነው – የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ

Ethiopian Prime Minister Abiy Ahmed waves to supporters as he attends a rally in Addis Ababa, Ethiopia June 23, 2018. REUTERS/Stringer

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 3 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰኔ 16ቱ የአዲስ አበባው የቦምብ ጥቃት በብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት የቀድሞ ሀላፊ የተመራ መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎችን አስመልክተው በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ባለፉት አምስት ወራት ከሰብዓዊ መብት ጥሰትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ምርመራ መደረጉንና በዚህ ሂደትም ማስረጃ መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በመስቀል አደባባይ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት በብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት የቀድሞ ሀላፊ የተመራ መሆኑን ተናግረዋል።

የተፈጸመው ጥቃት ፖለቲካዊ አንድምታ እንዳለው ያነሱት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፥ ጥቃቱ በውጭ ሃገርና ሌላ ሃገር ውስጥ ባለ የስራ ሃላፊ ጋር በቅንጅት መፈጸሙንም ነው የተናገሩት።

መቀመጫዋን ኬንያ ያደረገችውና በጥቃቱ ተባባሪ የሆነችው ገነት ወይም ቶለሽ የተባለችው ግለሰብም፥ በሰው ምልመላና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ መሳተፏንም ጠቅሰዋል።

በወቅቱ ጥቃቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሄራቸው ኦሮሞ ስለሆነ ጥቃቱ በኦሮሞ ተወላጆች መፈጸም አለበት በሚልም ለጥቃቱ የኦሮሞ ተወላጆች መመልመላቸውን ገልጸዋል።

ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘም ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን አስታውሰዋል።

በዚህም በተለያዩ ወንጀሎች በተለይም በፖለቲካና ከሽብር ጋር በተገናኘ በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ከፍ ያለ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸም እንደነበር ነው የተናገሩት።

በዚህ ሂደትም ፖለቲከኞች ተገደው ከፖለቲካው እንዲርቁ የማድረግና ሃገር ለቀው እንዲሰደዱ የማድረግ፥ ይህን በማያደርጉት ላይ ከፍተኛ እንግልትና ድብደባ ይፈጸም እንደነበርም አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች የራሳቸው ባልሆኑ የጦር መሳሪያዎች እና ሰነዶች ላይ በግድ ፈርመው የእኔ ብለው እንዲያምኑ እንደሚደረግም ጠቅሰዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥም ሰዎች መገደላቸውንና በርካቶች መሰወራቸውንም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አውስተዋል።

ከዚህ ባለፈም በሚስጢራዊ እስር ቤቶች በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት መጣሱንም ነው ያነሱት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ።

ተጠርጣሪዎችን በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት ከማቅረብ ይልቅ ወደ ስውር እስር ቤቶች በመውሰድ የማሰቃየት ተግባር እንደሚፈጸም ያነሱት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፥ ይህም በብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እንደ ሃላፊነት ይታይ ነበርም ነው ያሉት።

በኤሌከትሪክ ሽቦ መጥበስ፣ በጀርባ አስተኝቶ በአፍና አፍንጫ ላይ ፎጣ በማድረግ በውሃ ማፈን፣ ለረጅም ጊዜ ፀሃይ እንዳያገኙ ማድረግ፣ ዛፍ ላይ ሰቅሎ መግረፍ፣ ጥፍር መንቀል፣ ጫካ ውስጥ ራቁትን ማሳደር፣ ዘቅዝቆ መስቀል፣ ሙቀት ባለባቸው አካባቢዎች በሙቀት ማሰቃየት፣ አይንን ሸፍኖ ራቁትን ጫካ ውስጥ መጣል፣ አልፎ አልፎ ደግሞ ከአውሬ ጋር ማሰርን የመሰሉ ተግባሮች ሲፈፀሙ ነበር ብለዋል።

በተጨማሪም ብልትን በፒንሳ መጎተትና መሳብ፣ ብልት ላይ ውሃ ማንጠልጠል እንዲሁም ሴቶችን እየተፈራረቁ መድፈርና ወንዶች ላይ የግብረ ሰዶም ድርጊት መፈጸም በእነዚህ እስር ቤቶች ይፈጸመ እንደነበርም ገልጸዋል።

በዚህ ሳቢያም በርካቶች ለከፍተኛ የአካል፣ የስነ ልቦና እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መዳረጋቸውን እና የተለያዩ ጉዳቶች መሰበር እና ጠባሳ የመሳሰሉ ጉዳቶችን ማስተናገዳቸውንም ጠቁመዋል።

ከዚህ ባለፈም በርካቶች ዘራቸውን ለመተካት መቸገራቸውንም ነው በመግለጫቸው ያነሱት።

እስካሁንም ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል 36 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው እና ሰባት ድብቅ እስር ቤቶች በአዲስ አበባ መገኘታቸውንም አስረድተዋል።

 

በምናለ ብርሃኑ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.