የአረመኔው ቡድን በዚህች አገር ያመጣብንን ሁሉ ከነሰንኮፉ እንጣል! (ሰርፀ ደስታ)

እኔን ሰሞኑን እየሆነ ያለው ነገር የፈጠረብንን ስሜት ከራሴ ጀምሮ የተወሰኑ ጓደኞቼን ስጠይቅ ተመሳሳይነት አለው፡፡ ይሄንኑ የእኛን ስሜት ጀነራል ባጫ ደበሌ በኦኤም ኤን ከደጀኔ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ ሲናገሩት ሰምቼ ገርሞኛል፡፡ እንደገባኝ ብዙ ሰው የተሰማው የተቀላቀለ ስሜት ነው፡፡ ያ ጊዜ አልፎ ከሰበዓዊ ፍጡር ያልተፈጠሩ የሚመስሉ አረመኔዎች ባደረጉት ድርጊት እየተለቀሙና እየታደኑ መሆኑ ደስታ ይሁን ሀዘን ብዙዎቻችን የተሰማን ስሜት ግልጽ አልሆነልንም፡፡ በተለይ የተፈጸሙ እጅግ የሚዘገንኑ አረመኔያዊ ብሎ ብቻ ማለፍም የሚከብዱ ድርጊቶችን ስንሰማና ስናይ በጣም ስሜታችንን ጎድቶታል፡፡ እንደ አገርም ሁሉንም አንገት የሚያስደፋ ነው የትንም ያህል ፈጻሚዎቹ የአረመኔው ቡድንና አጋሮቹ ቢሆኑም፡፡ ለመሆኑ ይሄ ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሆን ምክነያቱ ምን ነበር ብለን ስንጠይቅ መልሱ እንዲህ እንደዋዛ የወያኔ አገዛዝ ብቻ ተብሎ ሊታለፍ የሚችል ሆኖ አላየሁትም፡፡ ለአረመኔው ቡድን አረመኔያዊ ድርጊቶች ትልቅ ጉልበት የሆኑት ብዙ ሌሎች ግብዓቶች ነበሩት፡፡ ጥቂት የማይባሉትም ከራሱ የአውሬዎቹ ሰለባ ከሆነው ሕዝብ የሚመጣ ችግር ነው፡፡

የአረመኔው ቡድንና አጋሮቹ የዛሬ ከ27 ዓመት በፊት አገርን ሲወሩ ሁሉንም የአገር መሠረት የነበሩትን እሴቶች አፍርሰው ለራሳቸው አሁን ለምናየው አረመኔያዊና አውሬያዊ ድርጊታቸው እንዲመቻቸው ሰርተውና አዋቅረው ነው እዚህ የደረሱት፡፡ ዛሬ ለውጥ የተባለው ከመጣ 8 ወር ሆነው፡፡ የ27 ዓመቱን የአውሬያዊ ድርጊቶችን ለማስቆም ግን ገና ብዙ የሚቀር ይመስላል፡፡ በአንዳንዶች ቦታ አሁንም የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት አለ፡፡ አንዳንዶች ቦታ አሁንም በአሉ አመራር ነን የሚሉ እየደረሱ ያሉ ግፎች አሉ፡፡ ቀላል የማይባሉት አውሬዎች እየተለቀሙ ቢሆንም አሁንም በጣም ዋነኞቹ አልተያዙም፡፡ ያም ሆኖ የአውሬያዊ ድርጊቶችን ለመፈጸም የተዘረጉ መሠረቶችን አንዱም ገና አልተነካም፡፡

ሰሞኑን እኔ ከምሰማቸው እንደማስታወሻ ልጠቁም፡
የመስቃንና ማረቆን ሕዝብ ግጭት በማህበራዊ ሚዲያዎች ብዙ ከተሰራጩት አንዱ ነው፡፡ ይህ ግጭት ሰሞኑን እንደ አዲስ አገርሽቶ ይሁን የቀጠለ ባይገባኝም ግን ግጭቱ ከወራት በፊት ጀምሮ ተሰምቷል፡፡ ለምን ማስቆም እንዳልተቻለ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ወልቃይት ራያ ለዘመናት እልባት ሳያገኝ አሁንም መፍትሄ ሳይበጅለት እያየለ ነው ያለው፡፡ ሲዳማ ክልል ከአልሆንሁ እያለ ነው፡፡ የማንነትና ክልልን ጉዳይ በይደርና በተረጋጋ ጊዜ መወሰን ቢቻልም ግጭቶችን ግን ማስቆምና ሕዝብን የተረጋጋ ሕይወት እንዲቀጥል ማድረግ 8 ወር ብዙ ነው፡፡ ስምንት ወር ቀጠለ ማለት እየተለመደ ይሄድና እንዲሁ በስርዓተ አልበኝነት ነገሮች ይቀጥላሉ የሚል ትልቅ ስጋት አለኝ፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በአጭር ጊዜ መፍታት ግድ ነው፡፡

የመርከብ ስያሜ ከመቀሌ ወደ ፊንፊኔ፡ ሰሞኑን መቀሌ የነበረች መርከብ ሥሟ ተቀይሮ ፊንፊኔ ተብላለች በሚል ከአየኋቸው አተካራዎች አንዱ ነው፡፡ የወሮበላውና አረመኔው ቡድን ፍጹም የተሳካለት ነገር ቢኖር ጥላቻና ዘረኝነት የተመረዙ የቀበሌ አስተሳሰብን በሥፋት ማሰራጨት ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ተናግሯል የተባለው ግለሰብ የባሕር ትራንዚት ኃላፊ ነው የተባለ ነው፡፡ ሰውዬው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንዲህ ያለ ጉዳይ አንስቶ ተናግሮ ከሆነ መጀመሪያ በተናገረው ነገር ሊጠየቅ ይገባል፡፡ ከመቀሌ ወደ ፊንፊኔ ሥም መቀየር ላይ አደለም ቁም ነገሩ፡፡ ከጅምሩ መቀሌና ፊንፊኔ ብሎ ለመርከቦች ሥያሜ መስጠቱ የቀበሌ እሳቤ እንጂ ተገቢም አልነበረም፡፡ አገሪቱ፣ በተለይ የፌደራል ንብረት የሆኑ ነገሮች እንዲህ በጠባብ ዘረኝነት ኪስ ውስጥ ከቶ ሕዝብንም በዚሁ እንዲያስብ ለማድረግ ታስቦ ነው እንዲህ ያሉ ስያሜዎች የሚሰጡት፡፡ አንዳንዶች ሁሉም የክልል ከተሞች ስም ለመረከቦች ተሰጥቷል ችግር የለውም ይላሉ፡፡ ችግሩ እኮ እዚህ ጋር ነው፡፡ አረመኔው ቡድን ሁሉንም ነገር የራሱን መሠረት የሆነውን የጠባብ ዘረኝነትን ተከለበትን የዘር ፌደራሊዚሙን ለማስተዋወቅ ሊጠቀምበት አስቦ እንጂ የከተሞቹ ሥም በትክክል እንዲተዋወቅ አደለም፡፡ ከሆነስ ሆነና ፊንፊኔ የሚባል መርከብ ከአለ አዲስ አበባ የሚል መርከብ አለወ ወይ ቢባል መልስ አለወ ወይ የሚለውም ሌላ ነገር ነው፡፡ ዛሬ የወሮበላው ቡድን አባል በብዛት ከትግራይ ስለሆኑ መቀሌ የሚባል መርከብ ሥም ለመቀየር ምክነያት ከሆነ ደግሞ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ይሄ ጉዳይ እንዴና ለምን ተነሳ? መቀሌን ፊንፊኔ አሉ ተብሎ ይሄን ያህል ለምን ተናፈሰ? ሆኖስ ከሆነ ለምን መቀየር አስፈለገ? ሥያሜዎቹ የአረመኔውን ሥርዓት ለማስተዋወቅ ነው ከተባለ ታስቦበት ሁሉም መቀየር በአለበት ሁኔታ መቀየር አለበት፡፡ እንደእኔ ደግሞ የፌደራል ንብረት የሆኑ ነገሮች መጠራት ከአለባቸው አገር አቀፋዊ ይዘት በአላቸው ስሞች እንጂ የዘረኝነትን አስተሳሰብ ለማስፋፋትና ለማስተዋወቅ በሚያገለግሉ ሥያሜዎች አደለም፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ታላላቅ ወንዞች አሏት፡፡ የአሉን መርከቦች አገራትን የሚያቋርጡትን ትልልቅ ወንዞቻችንን ያህል እንኳን እንዳልሆኑ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ከዛ የእነዚህ ገባሮች ወደሆኑት እንኳን ብንቀጥል ብዙዎቹ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ናቸው፡፡ ለመርከባቱም ሥያሜ ወንዞች የተሻለ ይቀርባሉ፣ ሐይቆችም አሉ፡፡ እንግዲህ መቀሌና ፊንፊኔ የሚል ስያሜ ከጅምሩ ለምን እንደመጣ እያስተዋልን አሁን ሆነ ተብሎ የሚወራው ነገር ደግሞ ሌላ የባሰ ችግር ነው፡፡

የቡና ታሪክ ባለቤትነትና የከፋ ሕዝብ ተቃውሞ፡ ሰሞኑን በደቡብ ከፋም ተቃውሞ አለ፡፡ እንደሰማሁት ተቃውሞው ደግሞ የቡና መገኛ እኔ ነኝ እኔ ነኝ በሚል ነው አሉ፡፡ አሁንም ችግሩ ያለው ሕዝብ ጋር ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ችግሩ በቀጥታ የፌደራል መንግስቱን ጨምሮ የኦሮሚያንና የደቡብን በተለይም የከፋን ዞን አስተዳደር የሚመለከት ነው፡፡ ከሁሉም ግን የፌደራል መንግስቱ ችግር ሆኖ ነው ይህን ጉዳይ ያየሁት፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ነው፡፡ የቡና መገኛ በሚል አንድ ትልቅ ዝግጅት ቦታው ላይ ሊዘጋጅ ታስቦ ጂማ ይሁን ወይስ ቦንጋ በሚል ነው ችግሩ የተነሳው፡፡ እንደገባኝ ጂማ እንዲሆን የኦሮሚያ መንግስት ሲፈልግ ቦንጋ እንዲሆን ደግሞ የከፋ ዞን ሕዝቡን ጨምሮ ይፈልጋል፡፡ ቦታው ላል ከተባለ ምንም የሚያምታታ ነገር ያለው አይመስለኝም፡፡ በዩኔስኮ ሳይቀር ተመዝግቦ ያለው የቡና መገኛ ከፋ ነው፡፡ ከተማው ደግሞ ቦንጋ ነው፡፡ የዚህን ጉዳይ በዚህ መልኩ ከአየንው የዚህን ያህል ውሳኔው ያጠረና ግልጽ የሆነ ነው፡፡ ጅማ ይሁን ከተባለ ደግሞ በቂ ምክነያት ኖሮ ሁሉም ሊስማማበት የሚችል ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ታሪካዊ እውነታዎችን ለማዛባትና ነገሮችን ወደራስ የመሳብ ያው 27ዓመት ያደለብነው የቀበሌ አስተሳሰብ ነው፡፡ ምን አልባት ቦንጋ ይህን ዝግጅት ለማስተናገድ አቅም የላትም ከተባለ አንድ ምክነያት ነው፡፡ ያም ሆኖ ይሄ አሳማኝ ምክነያት አደለም፡፡ የዝግጅቱ ዓላማ የቡናን መገኛ ለማስተዋቅ ታስቦ ከሆነ በቀጥታ በድንኳንም ቢሆን ሲሆን ሲሆን በዚሁ ተመዝግበው በአሉ የተፈጥሮ ጫካዎች ማዘጋጀት ነው፡፡ ከተማ ከተፈለገ ደግሞ ቦንጋ ከጂማ ይቀርባል፡፡ ይህ የከፋ ሕዝብ ጥያቄ በጣም መሠረታዊና በትክክልም ተገቢ ነው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ በዚህ ምክነያት እንኳንስ ችግር መፈጠር ቀርቶ የዚያ አካባቢ ሕዝብ በልዩ ሁኔታ የቡና መገኛ ባለቤትነቱን ክብር ለመጠበቅ ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ልዩ ሥጦታ በተገባው ነበር፡፡ ሥጦታው ማሕበረሰቡ በሚያስፈልጉት የጋራ ተቋማት ለምሳሌ፣ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት የመሳሰሉት ቢሆንና የዚሁም ሥያሜ ከዚሁ ታሪክ ጋር ለወደፊትም መዘከሪያ እንዲሆን መሆን ነበረበት፡፡ ይሄ እንግዲህ በዋናነት በፌደራል ደረጃ ያሉ ባለስልጣናን ጨምሮ የአካባቢው አስተዳደሮች የሚፈጥሩት ችግር ነው

ከዚህ ሌላ አሁን ብዙ አረመኔያዊ ደርጊት የፈጸሙ ፍጡሮችን በሕግ ቁጥጥር ሥር ያልዋሉ አሉ፡፡ እሰካሁንም ሴራቸውን በየቦታው እየፈጸሙ ነው፡፡ አሁንም ሌላ ማምታታት ላለመኖሩ እርግጠኞች አደለንም፡፡ አሁን ለውጥ ምጪዎቹ ቁርጠኛ ከአልሆኑ ችግር አለ፡፡ የዚህን ጉዳይ ዝርዝር አሁን መናገር አልፈልግም፡፡ በድፍኑ ቁርጠኝነትና ፍጥነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚጠይቅ ነው፡፡ ማንም ይሁን ማን፡፡ ብዙዎች እንደተባለው ነው ዘር ውስጥ ተከልለው አሁንም በነጻነት ይኖራሉ፡፡
በመጨረሻም ለዘለቄታው ይህ የወሮበላ አረመኔ ቡደን የዘረጋውን ሁሉ አፍርሰን አገሪቱ ከምንም በፊት ወደነበረችበት አስተሳሰብ መመለስ ግድ ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ እርምጃ ሊወሰድ ግድ ነው

1. በብሔር የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ እንዲፈርሱ፡፡ ይህ ከሁሉም በላይ የሕዝብ ነቀርሳ የሆነ አደገኛ አስተሳሰብን የፈጠረ ነው፡፡ በግልጽ በአንድ ክልል ይቅርና በአንድ ቀበሌ እንኳን ከዚህ ዘር ብቻ የሚባል ሕዝብ በማይኖርባት አገር በዘር ተደራጅቶ የአንድን ዘር ብቻ እውክላለሁ እያለ ሊመራው የሚችል አንድም አስተዳደራዊ ወሰን ለወሮበላ ቡድኖች ሊሰጥ አይገባም፡፡ የኖራችሁበት አስተሳሰብ ስለሆነ አልገባ ከአላላችሁ በቀር ለምሳሌ ኦዴፓ በምን ሂሳብ ዛሬ ኦሮሚያን የተባለውን አዴፓ በሚን ኢሳብ አማራ የተባለውን ይመራል፡፡ በግልጽ በስያሜያቸው ሌላውን በክልሉ የሚኖረውን እንደማይወክሉ ይናገራሉ፡፡ በስያሜ ብቻም ሳይሆን እስከሁን በድርጊትና ክሌሎቹ ሕገ መንግስት ብለው በአጸደቁት ሰነድ ሳይቀር ነው፡፡ እንዲህ በአለ ቁማር ብሔር ብሔረሰብ በሚል ማምታታት ሊቆም ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ወሳኝ እርመጃ ማንም ይሁን ማን በኢትዮጵያ ውስጥ ዘርን ተኮር ያደረገ ስያሜ ያለው የፖለቲካ ቡድንን በሕግ ማገድ ነው፡፡ ይህ በታሪካችን ጠባሳ የሆነ ትልቅ ስብራት ያደረሰብን ነው፡፡ ለመቼውም ይሔው ተጽፎ ለትለውልድ ሊተላለፍ ይገባል፡፡

2. ዛሬ ክልል የተባሉት ፈርሰው በአዲስ መልክ በሚሆን የፌደራል አከላለል ሊወሰን ግድ ይላል፡፡ ያኔ የእከሌ ዘር የተባለ ሳይሆን ለአስታዳርና ምቹነትና የሕዝብን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ይሆናል፡፡ አሁን ያለው የአውሬው ቡድን ክልል ሌላው እስካሁንም ያልቆመው የብዙዎች እልቂት ምክነያት ነው፡፡ ዜጎች በክልል አስተሳሰብ ታጥረው ዘረኝነትን በደንብ እንዲከተሉ ተደርጎ ሆን ተብሎ የተሠራ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ዜጎችን የገደለም የለም፡፡ በአዲስ መልክ የሚዋቀረው የአስተዳደር ወሰን በተለይ በሚጎራበቱ ማህበረሰቦች አካባቢ ሁሉንም ማሕበረሰብ በአንድ የሚያቅፉ ልዩ አስተዳደራዊ ወሰኖችን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ ከቦረናና ከሱማሌ ክልል የተውጣጣ ልዩ የሁለቱም ሕዝብ በአንድነት የሚኖርበት አስተዳደራዊ ግዛት፡፡ የሁለቱንም ቋንቋ ባሕል በመስተጋብር የሚያራምዱ፡፡

3. ሌሎች ብዙ ጎዳዮች ቀድመው ወደነበሩበት ሊመለሱ ይገባል፡፡ በቀላሉ ሁሌም የሚገርመኝ ታሪካዊው የሆለታ ገነት ጦር ትምሀርት ቤት ኃያሎም አርዓያ ጦር አካዳሚ መባሉ ነው፡፡ ይሄ የኢትዮጵያን ሕዝብ በጨካኝ አረመኔዎች እንዲያልቅ ለአደረገ ቡድን የሰራን ሰው ሥም ዛሬም የኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ተቋም የሆነውን ይህን ጦር ትምህርት ቤት ለመሰየም መዋሉ ብቻም ሳይሆን ጥሩ ለሰራ እንኳን ቢሆን የዚህ ጦር ትምህርት ቤት ሥም የማይገባው መሆኑ ነው፡፡ የጦር ትምህርት ቤት ብዙ መታሰቢያ ሊሆንላቸው የሚገቡ ተማሪዎችም መሥራቾችም አሉትና፡፡

4. ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለይ በአማራ ክልል ብዙ ነገሮች በግንቦት 20 በሚል ሥም ሲጠሩ ይደመጣል፡፡ ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቁር ቀን ሆኖ እንዲከበር መሆን ያለበት ቀን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ እንዲህ ያለ አረመኔ ቡድን ገጥሟት አያቀምና፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች እርመጃ እየተወሰደ ቢሆንም አሁንም የሚቀሩ አሉ፡፡ አንዳንዶቹም ሕዝቡ በጉልበት ስማቸውን አነሳ እንጂ አስተዳደሮቹ ምንም እርምጃ አልወሰዱም፡፡ ከእዚህ አረመኔ ቡድን ጋር የተያያዙ ማናቸውም ሥሞች ከኢትዮጵያ ተቋማት ላይ እንዲጠፉ፡፡ ከዚሁ ተመሳሳይ ብዙ የቦታ ሥያሜዎችም ለውጥ እንዲደረግባቸው ተደርጓል፡፡ ታሪካዊ እውነቶች ያሉባቸው ይሁኑ፡፡ ያም ሆኖ ስያሜ ማህበረሰቡ እየቀየረው የሚሆን እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሆኖም ሆን ተብሎ ታሪክን ለማውደም የተቀየሩም አሉና እንዲታሰብባቸው፡፡ ሁሌም እንደምሳሌ የምጠቅሰው ዝዋን ባቱ ብሎ መቀየር ታሪክን ለማውደም የተሴረ እንጂ እውነቱ ዝዋይ ከዜይ ሕዝብ ጋር ለዘመናት የኖረ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በተመሳሳይ ከጂግጂጋ የደጅ አዝማች አፈወርቅ አፈወርቅ ወልደሰማያትን መታሰቢያ ከጂገጂጋ ማጥፋት ታሪካዊ ስህትት ነው፡፡ ደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት ደጃዝማች የተባሉት ከሞቱ በኋላ ሲሆን እኚህ ሰው በጣሊያን ውጊያ ከፍተኛ የተባለ ጀብዱ በቆራሄ ኦጋዴን የፈጸሙ ናቸው፡፡ አብረዋቸው ደግሞ የተዋጉት የዚሁ አካባቢ ሕዝብና ከዋናው ሱማሌ ጭምር በሚተባበሯቸው ተዋጊዎች ነው፡፡ እኚህ ሰው ታሪካቸው ብዙም አይታወቅም፡፡ በመጨረሻም እዛው ሲዋጉ የሞቱ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ የእኚህ ሰው ታሪክ የዚሁ አካባቢ ነዋሪዎች ታሪክ እንጂ ገና ለገና ሱማሌ ከሚባለው ጎሳ አልተወለዱም በሚል እሳቤ መሆን ባልተገባው፡፡

5. ሌሎችም የአረመኔው ቡድን ያመጣብንን ከነሰንኮፉ አውጥተን እንጣል፡፡ እርም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ አውጡ!!!
አመሰግናለሁ!
ቅዱስ አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ! አሜን!

3 COMMENTS

  1. ይቅርታ ይደረግልኝና ኦሮሞ ስም የመቀየር በሽታ ነው የተጠናወታቸው:: የ600 አፈታሪክ ይዘህ ደብረ ብርሃንን ይቀየር እንዳትለኝ ብቻ::
    ወይኔ እፍረት የሌለው የተጨማለቀ አገር የሚያቀል አዋራጅ ነው::

    ሥም መቀየር በህግ ላይ ተጽፎ መቆም አልበት:: በኦሮምኛ ትርጉም እየተባለን እታች እራሳችንን አውርደን እንደ ህጻን ሥም እየተነስን መቀየር ማቆም አለብን!

    የሄ ሥም የመቀየር የዲያቢሎስ በሽታ ክልሌ :እኔ እኔ ከማለት ተለይቶ አይታይም::

    ወያኔ ገና ብዙ አሳፋሪ ድርጊቱን ብዙ የሚመልስው አለ:: የእዲስ አበባን ዩኒቨርሲቲ ንብረት አንዱ ነው:

  2. What a commentary! It is a blessing to have Ethiopians like you who stand for the truth. Yes, all ethnic political parties must be abolished. No civilized nation in the world allow such parties to exist. Yet, Abiy and his buddies do not seem to want this abolished. Why? It is a mystery to me.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.