መቀነስ እማይችል አስመሳይ ካድሬ ነው! (በላይነህ አባተ)

አቤቱ ጌታዬ ዘንድሮስ ለጉድ ነው፣
ተደረጃ ወጥቶ ደምር ሲል ሰባኪው፣
“አሜን! አሜን!” ይላል ተታች ተሰባኪው፡፡

ለደማሪ ስብከት “አሜን! አሜን!” ያለው፣
ጨርቁን ጥሎ እስቲሄድ ጨርሶ ያበደው፣
ምስጢርና ጥቅሙን ሳያጣጥመው ነው፡፡

ምልክቱን እንኳ ብንመለከተው፣
መደመር እሚያልፈው በመቀነስ ላይ ነው፡፡

መቀነስ ወደ ጎን ባይፈጠር ኖሮ፣
መደመር ባልኖረ ወደ ታች ተሰምሮ፡፡

የክርስቶስ እጆች መቀነስ ባይሆኑ፣
ራሱና እግሮቹ መስቀልን ባልሰሩ፡፡

በመደመር ስብከት ጨርቅህን የጣልከው፣
እንደ ጅል ፍቅረኛ ቦዘህ የፈዘዝከው፣
የመቀነስን ጣም እባክህ ቅመሰው፡፡

ቆሻሻን ከንፁህ ብትቀላቅለው፣
እንደ ከበት አዛባ መጨመላለቅ ነው፡፡

ተራራ ዘራፊን ከሕዝብ ብትደንበው፣
ጉበት ኩላሊትም ወጥቶ ማለቁ ነው፡፡

ህፃናት ጨፍጫፊን አቅፈህ ብትስመው፣
እንደ ይሁድ ታንቀህ ሲኦል መግባትህ ነው፡፡

ተኮናኙን ተፃድቅ ብትቀላቅለው፣
ተማትችለው አምላክ ጦርነት መግጠም ነው፡፡

መለኮት ከሰማይ ሁለት ቤት የሰራው፣
ይኸንን ተገነት ያን ሲኦል የዶለው፣
መቀነስ ማካፈል ስላስፈለጉ ነው፡፡

እና ተደማሪ ተጌታ ልቀህ ነው፣
እርጉምና ብሩክ የምትቀላቅለው?

እንደ ድምር ፓስተር እንደ ኮለኔሉ፣
አስመሳይ ካህናት ሆዳም ጳጳሳቱ፣
ደመራን ተድምር እያደናበሩ፣
ያላመነን ታማኝ አቀላቅለው ፈቱ፡፡

ለገሰ ዜናዊ ፋኖ ጥግ ተቀብሮ፣
አቦይ ገረመድን ተሀዲስ ጎን አርፎ፣
እርክስ አላለም ወይ መቃብሩስ ደምሮ?

ሌባ ከጨዋ ጋር አብሮ ተደምሮ፣
ነፍስ አጥፊ ታዋላጅ አብሮ ተቀላቅሎ፣
ከሀዲ ተታማኝ ድብልቅልቅ ብሎ፣
እንዴት ይራመዳል አገር በእግሩ ቆሞ?

ያርባ ዓመቱ ታሪክ እንደሚያስተምረው፣
አማራ ተህወሀት አብሮ እሚደመረው፣
የእየሱስን ስቅለት ይሁዳ ሲፍቀው፣
እሳትም ተውሀ አብሮ ሲተኛ ነው፡፡

ነቀዝና ምስር አብረው የሚኖሩት፣
ነቀዝ ወደ ምስር የተቀየር እለት፣
አለዚያ ምስሩ ነቀዝ ሆኖ ሲያነክት፡፡

ሰፍቶ ለመጠገን የተቀደደን ጨርቅ፣
በመቀስ ዝተቱን መጀመርያ ቀንጥስ፡፡

ቀንሰህ ቀንሰህ ደህና ደህናው ሲቀር፣
በመርፌ እያያዝክ እየቀጠልክ ደምር፡፡

የሱሪን ቀዳዳ በመጣፊያ ልደፍን፣
ባሮጌ ካኪ ላይ አዲስ ጨርቅ ብትደምር፣
ብዙም ሳትራመድ እሬብህ ቦግ ይላል፡፡

እንኳንስ ሕዝብ ቀርቶ እራፊም ሲደመር፣
መቀስ ብድግ አርጎ መቀነስ ይቀድማል፡፡

መቀነስን ትቶ መደመር ሰባኪው፣
እድፉን ሳይታጠብ አዲስ ልብስ አምሮት ነው፡፡

በቆሸሸ ገላ ንፁሕ ልብስ ቢለብስም፣
በአካላቱ ቢረጭ አንድ ጠርሙስ ሽቶም፣
ሐጥያቱ ሲያልበው መከርፋቱ አይቀርም፡፡

ስለዚህ ከስብከት ንስሐ ይቀድማል፣
ተመደመር በፊት መቀነስም ያሻል፡፡

ድምር በቅነሳ ታልተረጋገጠች፣
እንደ አቢይ አህመድ ውሸታም ስሌት ነች፡፡

መርዙንም ጀርሙንም ድምር አርገህ ውጠህ፣
ሽቅብ ቁልቁል ብሎ እንዳያጣድፍህ፡፡

ለድለላ ስብከት ለወሬ እንዲመቸው፣
ፍቅርና ይቅርታን በከንቱ እሚያነሳው፣
በሙታን ላይ ፈርዶ ፍትህ ለመግደል ነው፡፡

ቀጥቅጦና ሰልቦ ትውልድ ያመከነው፣
በልጇ እሬሳ ላይ እናት ያስቀመጠው፣
ከተማ ገጠሩን በሰው ደም ያጠበው፣
አብሮ እሚደመረው ምን አምላክ ፈቅዶ ነው?

ሕዝብን ታራጁ ጋር ተደመር እሚለው፣
የሰማእት ሕልፈት ደንታ የማይሰጠው፣
መቀነስ እማይችል አስመሳይ ካድሬ ነው፡፡

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ህዳር ሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.