ከታሪክ መድረክ – የሰንደቅ[1]ዓላማው ወንጀለኛ አርማ (ኀይሌ ላሬቦ)

ፕ/ር ሃይሌ ላሬቦ

ይኸንን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሣሣኝ በኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ዙርያ የተነሡት አወዛጋቢ ጥያቄዎችና ክርክሮች ሲሆኑ፣ በተለይ ደግሞ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሊቀመንበር የነበሩት፣ አሁን በጡረታ ያሉት ሊቅ (ዶር.) ነጋሦ ጊዳዳ የባሕርዳር ሕዝብ አዲስ ለተመረጠው ለኢሕአዴግ ጠቅላይ መሪ ለሊቅ ዐቢይ አሕመድ የደስታ ስሜቱን ሊገልጥ፣ ድጋፉን ሊሰጥ ሲል ይዞ በወጣው ሰንደቅ ዐላማ ላይ የሰጡት ኂሳዊ አስተያየት ነው። ሊቅ ነጋሦ የባሕርዳር ሕዝብ በነቂስ ይዞ የወጣው ምንም ምልክት ከላዩ የሌለበት ማለትም ልሙጡ የአረንጓዴ ብጫ ቀይ ቀለማት ሰንደቅዓላማ የአገሩን ሕገመንግሥት የሚፃረር ነው ብለው በመኰነን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በሳቸው እይታ ሰንደቅዓላማው ሁለት ከፍተኛ ሕጸጻት ያሉበት ሲሆን፣አንደኛው ዘውዳዊ ሥርዐትን የሚያንጸባርቅ የነአፄ ኀይለሥላሴና የነአፄ ምኒልክ ሰንደቅዓላማ፣ ሁለተኛ ደግሞ የዚህ ሥርዐት ፍሬ እንደመሆኑ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት የሚፃረር፣ እኩልነቱንም የሚያናጋ ነው ብለው ያብራራሉ። ሊቅ ነጋሦ በርሳቸው ሊቀመንበርነት ሌሎች ኻያስምንት የኢሕአደግ አባላት ተሳትፈውበት ያጸደቁትንና፣ የሕገመንግሥቱ አካል ያደረጉትን ሰንደቅዓላማ ብቸኛው ሕጋዊና “የሀገሪቱን ሕዝቦች እኩልነት የሚያረጋግጥ” ነው ብለው ያስተምሩናል። የአዲሱን ጠቅላይ መሪያቸውን “መደመር” የሚለውን መፈክረ ቃል በመጨመር፣ ሊቁ ይኸንኑ አቋማቸውን ሲያብራሩ የሰንደቅዓላማውንም አመጣጥ በመጨመር ነው። እንዲህ ነው ያሉት፤

እነዚያ [ማለትም የነገሥታቱ] ባንድራዎች አንድ ሊያደርጉን እንደማይችሉ አይተን 1987 . የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ የሚደመር፣ ሃይማኖታችንን በሙሉ የሚደምር፣የተለያዩ ግለሰቦችንንና ቡድኖችን የሚያግባባና ሁላችንም አንድ የሚያደርግ ባንድራ የቱ ነው? ብለን በሕገመንግስቱ አንቀፅ ሦስት ላይ አስቀመጥን

የዛሬ ውይይቴ የሊቅ ነጋሦ ትረካ ምን ያህል እውነተኝነት አለው ብሎ በመጠየቅ ብቻ ሳይታገት፣ የትኛው ሰንደቅዓላማ ነው ሕጋዊ በሚለው ርእስ ላይ ደግሞ መወያየት ይሻል። አባቶቻችን “ነገር ከመጀመርያው፣ እህል ከመከመርያው” እንደሚሉ፣ የ‘ልሙጡ’ን ሰንደቅዓላማ አመጣጥ ከ ‘ባለኮከቡ’ ጋር አስተያይቶ መናገሩ ሚዛናዊ ፍርድ ለመስጠት ተገቢ ይመስለኛል። ውይይቱን ከልሙጡ ልጀምር።

ሁላችንም እንደምናወቀው፣ አፄ ምኒልክ፣ በአፄ ቴዎድሮስ ዳግማዊ ተጀምሮ፣ በአፄ ተክለሃይማኖትና በአፄ ዮሐንስ ራብዓይ የቀጠለውን የኢትዮጵያን የመልሶመገንባት ሥራ፣ ከማንኛውም የቀደሟቸው ነገሥታት፣ የተሻለ ብልሃትና የበለጠ ፍቅር በመጠቀም እፍጻሜ ያመጡት መሪ ናቸው። ሕዝባቸውም በውድ እንጂ በግድ እንዳይገዛላቸው ስላልፈለጉ፣ እሳቸውን ከመውደድ የተነሣ፣ እንደንጉሥና እንደአባት ሳይሆን፣ እንደወላጅ እናት ‘እምዬ ምኒልክ” ብሏቸው በመጥራት ፍቅሩን ገልጦላቸዋል። የዘመናቸውም ሆኑ፣ ከነሱ በኋላ የመጡ የዓለም ታሪክ ጸሐፊዎችና ገዢዎች የማስተዳደር ብልሃታቸውን አይተው “የወጣለት ጥሩ መሪ ነበር” በማለት አድንቋቸዋል። በጥበባዊ አስተዳደራቸው፣ የኢትዮጵያ ክብር አደገ። የዘመናዊ አስተዳደር መሠረትም ተጣለ[2] እያሉም ይናገራሉ። ታሪካቸውን ካየን፣ ለኢትዮጵያ ዘመናዊነትን ለማስጨበጥ በአፄ ምኒልክ ዘመን ያልተነካ የአስተዳደር ዘርፍና መስክ አልነበረም ማለት ይቻላል። ሰንደቅዓላማም ከነዚህ ዘርፎች አንዱ ነው። ዛሬ የሚውለበለው የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ፣ ቀጥዬ እንደምገልጸው፣ አቀማመጡ ልዩ ቢሆንም፣ ቅርጹንና ሦስቱን የቀለማት ዐይነት ያገኘው በአፄ ምኒልክ ዘመነመንግሥት ስለሆነ፣ ሊቅ ነጋሦ “የአፄ ምኒልክ ባንዲራ” ቢሉት አይገርምም። ግን የረሱት ነገር ቢኖር፣ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚወደው ባለሦስት ቀለማት ሰንደቅዓላማ ባንድጋ ማውለብለብ በአፄ ምኒልክ ይጀምር እንጂ፣ የቀለማቱ አደራደር ንጉሠነገሥቱ ከወሰኑት ጋር አይገናኝም ብቻ ሳይሆን፣ ከአድዋ ድል ማግሥት በፊት አሁን ባለው መልክ በሕይወት መኖሩ ራሱ ያጠራጥራል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅዓላማ በይፋ ተበሠረ የተባለው በአውሮጳ አቈጣጠር [አ. አ.] በጥቅምት ፲፰፻፺፰ ዓ. ም. የነጭ ዐባይን ዙርያ ሊቃኝ በመዘጋጀት ላይ ለነበረው የፈረንሳይና የኢትዮጵያ ጓድ፣ አፄ ምኒልክ እንደአ.አ. በጥቅምት ፲፰፻፺፯ ዓ. ም.፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ብለው በሰጡት ድርጊት ላይ በመመሥረት ነው። ቀለማቱ አቀማመጣቸው አግዳሚ ሁኖ፣ ከላይ ቀይ፣ ከመኻል “ም” ፊደል የተለጠፈበት ብጫ፣ ከታች ደግሞ አረንጓዴ ነበር። “ም” የ”ምኒልክ” ምሕፃረ-ቃል ሲሆን፣ ዋናው ዓላማ በአካባቢው ለነበሩት የአውሮጳ ቅኝ ገዢዎች፣ አገሪቷ በርሳቸው ሥር መሆኗን እንዲያውቁት ሲባል ሆን ብሎ የተደረገ ይመስላል። ሰንደቅዓላማው በየምክንያቱ እንደየአስፈላጊነቱ በአፄ ምኒልክ ዘመን እጥቅም ላይ ቢውልም፣ በዐዋጅ የተነገረ ነገር ግን አልነበረም። የቀለማቱም አደራደር ግልጥ አልነበረም። አንዳንድ ጸሓፊዎች ብጫው እንዳለ በመኻል ሁኖ፣ አረንጓዴውን ከላይ፣ ቀዩን ከሥር ያዩበትም ጊዜ እንደነበረ ይናገራሉ። ንጉሠነገሥቱ ቀለሞቹንና አደራደራቸውን እንዲሁም አግዳሚ አቀማመጣቸውን በምን ላይ ተመሥርተው እንደወሰኑ ግልጥ አልነበረም። የቀለሞቹንም ዐይነት የወሰኑት፣ በጥናትና በኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ ተንተርሰው ሳይሆን፣ “የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ይዘን መጓዝ አለብን” የሚለው የነጭ ዐባይ ቃኝ ጓድ ጥያቄ እንደዱብ ዕዳ ሳይታሰብ የመጣባቸው ስለነበር፣ አሳቡን በቅርብ ከሚያውቋቸው ከፈረንሳይና ከኢጣሊያን ሰንደቅዓላማዎች ቀለማት በመዋስ ነው የሚል አስተያየት አለ[3]። ግን “ሦስቱን ቀለማት ባንድጋ የመስፋቱ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር፣ ቀለማቱ፣ ከጥንት ጀምረው በተለያዩ ነገሥታት እንደኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ለየብቻቸው ይንጠለጠሉ ስለነበር፣ የውጭ አገሮችን በማየት በድቦላ የተቀነባበሩ ናቸው የሚለው አባባል ውሃ አይቋጥርም ብል ስሕተት አይመስለኝም። በጊዜው የነጭ ዐባይ ቃኝ ጓድ አባል የነበረው ፈረንሳዊው ቻርል ሚሼል ኮቴ የሦስቱ ቀለማት ቊራጮች እንዴት እንደተሰፉ ሲያብራራ፣

“[አፄ ምኒልክ] እስከዚያ ቀን ድረስ ለየብቻቸው ተይዘው ይንጠለጠሉ የነበሩትን ሦስቱን የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ቀለሞች፣

ማለትም ቀይ፣ ብጫ፣ አረንጓዴ፣ ለመጀመርያ ጊዜ ባንድጋ እንዲሰፉ ዐዘዘ፣[4]

ሲል ቀለማቱ የተውሶ አለመሆናቸውን ያሳያል።  ሁኖም በቀለማቱ አደራደር ጉዳይ ላይ ስምምነት ያልነበረ እንደነበረ ግልጥ ነበር። ስለዚህም ከንጉሠነገሥቱ ዕረፍት በኋላ፣ በቀለማቱ አሰላለፍም ሆነ፣እንዲሁም ከጥንት የኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ስላላቸው ግንኙነትና ትስስር ላይ የተጧጧፈ ክርክር መነሣቱ የግድ ሆነ። በክርክሩ ጊዜ፣ የአፄ ምኒልክ የግቢ ሚኒስቴርና የሥርዐተ መንግሥታቸው ዋና አቀናጅ የነበሩት፣ አቶ ኀይለማርያም ሠራቢዮን[5] በንጉሠነገሥቱ ወቅት የነበረውን የቀለማት ድርድር ሲደግፉ፣ ሌሎቹ አልተቀበሏቸውም። ሁኖም እኚህ የንጉሡ ባለሟል በፈለጉት ረድፍ ማለትም በቀይ፣ በአረንጓዴና በብጫ ቀለማት የተሠራው፣ በላቲን አሜሪቃ ውስጥ በሚገኝ ቦሊቪያ በተባለ አገር በቅድሚያ በመወሰዱ፣ የሰንደቅዓላማው ቀለማት አቀማመጥ አረንጓዴ፣ ብጫ፣ ቀይ ይሁን የሚለው ቡድን ክርክሩን አሸነፈ። ስለዚህ የአፄ ምኒልክ ሰንደቅዓላማ ቀለማት ድርድር አገልግሎቱን በዚሁ አበቃና፣ በ፲፱፻፱ ዓ. ም. በአረንጓዴ፣ ብጫና፣ቀይ ተተካ።

እስካሁን ባለኝ መረጃ መሠረት ከኢትዮጵያውያን ደራሲዎች ስለኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ቀለማትና ረድፋቸው በጽሑፍ ያስቀመጠልን ይኸ አሸናፊ ቡድን ብቻ ነው ማለት ይቻላል። ከመኻላቸው፣ ጐላ ያለ ሚና የተጫወቱት ራሱን “የኢትዮጵያ ልጅ” ብሎ የሚጠራ መምህር ጸጋዘአብ[6] ሲሆን፣ ሌላው ነጋድራስ ደስታ ምትኬ[7] ነው።  እንደየቅደም ተከተላቸው፣ አንደኛው ሐምሌ ፪ ቀን ፲፱፻፲፯ ዓ.ም.፣ ሁለተኛው ደግሞ ጥር ፲፫ ቀን ፲፱፻፲፰ ዓ ም በብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ላይ ባወጡት ጽሑፎቻቸው የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ዘመናትን ያስቈጠረና ከትውልድ ወደትውልድ እየተላለፈ የመጣ መሆኑን ይገልጹልናል። ለምን የቀስተደመና ቀለማት ተመረጡ ለሚለው ጥያቄ፣ መልስ ሲሰጡን፣ ጥንተመሠረታቸው በብሉይ ኪዳን በኦሪት ዘልደት ምዕራፍ ፱፣፲፪-፲፯ ታሪክ ጋር የተያያዘ መሆኑ ይነግሩናል። ይኸውም፣ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ዳግመኛ በንፍር ውሃ ላያጠፋት ከኖኅ ጋር የተዋዋለው የዘለዓለም ቃልኪዳኑ ምልክት ነው ይላሉ። ከዚህም ባሻገር፣ኢትዮጵያም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝታ ለዘላለም በባዕድ ሳትገዛ እንደምትኖር የሚያረጋግጥላት ከእግዚአብሔር የተሰጣት ምልክት እነዚህ ቀለማት ናቸው በማለት የሰንደቅ ዓላማውን ጥንተመሠረት ከብሉይ ኪዳኑ ታሪክ ጋር ያያይዛሉ።

ሌሎች ከኋላቸው የመጡት ምሁራን በበኩላቸው ሁለቱ ጸሓፊዎች ለሰንደቅዓላማው ቀለማት በሚሰጡት ምስጢር ቢስማሙም፣ በአጀማመሩ ግን የሚለዩ ይመስላል። በነዚህ አባባል፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በተመሠረተበት ወቅት፣ ነገሥታቱና ምሁራኑ ተመካክረው ሲያበቃ፣ በሰንደቅዓላማው ምሥጢር ወይንም ትርጒም ከተስማሙ በኋላ ሦስት ቀለማት እንዲሆኑ ተወሰነ። አፄ ገላውዴዎስ (1532-1551) ኢማም አሕመድን፣ አፄ ዮሐንስ (1864-1881) ግብፆችን፣ አፄ ምኒልክ (1882-1906) ኢጣሊያኖችን በአድዋ ድል የመቱት በዚህ ትእምርተ ኀይል ነው ይላሉ።

ከነዚህ ሁለቱ አቋሞች ግልጥ የሆነ ነገር ቢኖር፣ የዛሬ ሰንደቅዓላማ ቀለማት ከጥንት ሲወርዱ ሲዋረዱ የመጡ ቢሆኑም፣ በግልጥ ሕጋዊነት ያገኙት በአፄ ምኒልክ ነው።  የቀለማቱ አሰላለፍ ግን እልባት ያገኘው ከሰፊ ውይይትና ክርክር በኋላ ቁይቶ እንደተወሰነ ነው። አፄ ምኒልክም ለመላው ዓለም የሰንደቅዓላማው ባለቤት ኢትዮጵያ መሆኗን ቢያሳውቁትም፣ ውሳኔው ግን በምንም መልኩ በይፋ እንዳልታወጀ ግልጥ ነው። ንጉሠ ነገሥቱ ቀለማቱን የመረጡት በታሪክ በመተንተራስና የቀለማቱንም ምስጢር በማገናዘብ ነበር ቢባልም፣ ከኋላቸው የመጡት ምሁራን በትርጒሙ ቢስማሙም የቀለማቱን አሰላለፍ ግን አልተቀበሉትም። ቢሆንም፣ የሰንደቅዓላማውን ታሪክ ከቀለማት አንፃር ስንመለከት፣ የመላ ኢትዮጵያን ሕዝብ ያዋሐደና ያስተሳሰረ ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቷን ምድር ጠባይና እምነት ያካተተ እንጂ፣ ሊቅ ነጋሦ እንደሚሉት የአገሪቷን ሕዝብ እኩልነት የሚያናጋ፣ አንድነቱን የሚፃረር ባሕርይ በፍጹም የለበትም። እንደዚህ ካልሁ በኋላ፣ ታሪኩን ባጭሩ መመልከት የግድ ይሆናል።

የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ታሪክ በሁለት መክፈል ይኖርብናል። አንደኛው፣ ያልተጻፈና፣ በአፈታሪክ ላይ ብቻ የተመሠረተ። ሁላችንም እንደምናውቀው፣ ኢትዮጵያውያን ሁሉንም ነገር በዝርዝር የመጻፍ ባህል እምብዛም ያላዳበርን ሕዝብ ነን። እኔ ራሴ የግእዝ ተማሪ ሳለሁ፣ በብዙ የኢትዮጵያ አብያተተክርስቲያናት በዓላት ከቦታ ወደቦታ እየነገድሁ እሳተፍ ነበርና፣ እጅግ በጣም የሚገርመኝ ነገር ቢኖር፣ በየበዓላቱ የሚቀኙት የቅኔ ዐይነቶችና ብዛት ሲሆን፣ ከነዚያ አንድም ሳይጻፍ እዚያው እተቀኘበት ተቀብሮ መቅረቱ ነበር። ከቅዱስ ያሬድ ጊዜ ጀምሮ ከተቀኙት ቅኔዎች መካከል ሁሉም ባይሆኑ፣ አንድ ሦስተኛው እንኳን ቢጻፍ ኖሮ፣ ኢትዮጵያ አፈራች መባል የሚቻለው የመጻሕፍቱ ብዛትም ሆነ፣ ዐይነትና ጥራት ማንኛውንም የምዕራባዉያን ቤተመጻሕፍት (የአሜሪቃን ኮንግረስንና የብርቲሽን ቤተመጻሕፍቶች ጭምር) እጅግ በጣም ባስናቀ ነበር። ምንም ሃይማኖትን ያማከሉ ቢሆንም፣ ቅኔዎቹ በቃላት አጠቃቀም ርቀት፣ በይዘታቸው ጥልቀት፣ ባዘሉት አሳባቸው ምጥቀት፣ በምሥጢራቸው ውስብስብነትና በአጻጻፋቸው ስልት ከፍተኛ የምዕራብ ዓለም የኪነጥበብ ደራሲያን የሚባሉትን እንደጣሊያኑ ዳንቴ አሊጌሪ፣ የእንግሊዙ ዊሊያም ሼክስፔር የመሳሰሉትን ዋጋ ባሳጣቸው ነበር ብዬ አምናለሁ። ባሕሉ ባለመዳበሩ ይኸ ሊሆን አልቻለም። ሁኖም ግን፣ ጉዳዮችን በጽሑፍ የመመዝገብ ልማድ አለመዳበር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ በአብዛኛው ዓለም የነበረ ችግር ነው ማለት ይቻላል።

ስለሰንደቅዓላማ ህልውናውም ሆነ ቀለማቱ መናገር አስፈላጊ ሁኖ ባለመታየቱ ይሁን፣ ወይንም በሌላ ለኛ ሥውር በሆነ ምክንያት፣ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ፣ በየዘመኑ የመጡት የኢትዮጵያ ጸሓፊዎች መዝግበው የተውልን ነገር ባይኖርም፣ መጠቀሙን ከጀመሩት አገሮች ኢትዮጵያ ከመጀመርያዎቹ፣ ማለትም በፊታውራሪነት ከመሩት አንዷ መሆን አለባት የሚሉ በርካታ ናቸው። ስለዚህ፣ሰንደቅዓላማ በአገሪቷ ውስጥ በጥቅም ከዋለ ዘመናት ያስቈጠረ መሆን አለበት ቢባልም፣ ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ ግን በርግጥ የሚታወቅ ነገር የለም።

ሰንደቅዓላማን መጀመርያ ላይ እንደአገር መለዮና መታወቂያ ብዙውን ጊዜ ይጠቀሙ የነበሩት መርከበኞች ናቸው። አክሱማውያን በዘመናቸው፣ ይልቁንም አፄ ካሌብ በስድስተኛ ዘመነምሕረት መካከል፣ የናግራንን ክርስቲያኖች ያሳድድ የነበረውን አይሁዳዊውን ድሁኔዎስን ሊወጉት ቀይባሕር አቋርጠው ወደዐረብ አገር ሲሄዱ፣ መርከቦቻቸው ብሔራዊ ሰንደቅዓላማ እያውለበለቡ እንደተጓዙ አይጠረጠርም። ሰለሰንደቅዓላማው ቀለማት ዐይነት መረጃ ባይኖረንም፣ ስለህልውናቸው ግን ቢያንስ ከዐሥራ አምስተኛ ዘመነምሕረት አንሥቶ እስከአጼ ምኒልክ ዳግማዊ ዘመነ መንግሥት አልፎ አልፎ በነገሥታቱ ታሪከነገሥት ይታወሳል። አፄ ምኒልክ ሐረርን ከአራት መቶ ዓመታት በኋላ ማለትም በ፲፰፻፸፱ ዓ. ም. መልሰው በያዙበት ወቅት፣ ከተማውንና የመንግሥትን መዛግብት የሚረከቡትን መልእክተኞቻቸውን ከሰንደቅዓላማ ጋር እንደላኩ የታሪካቸው ጸሓፊ ይገልጻል[8]

ከኢትዮጵያ ወጣ ብለን የውጭ አገር ጸሓፊዎች ካየን፣ ቢያንስ ከ፲፭ኛ ዘ. ም. አንሥቶ፣ የሰንደቅዓላማ በኢትዮጵያ መኖር በሰፊውም ባይሆን በመጠኑ ተመዝግቧል። ስለቀለማቱ ግን የተናገረ የለም። ሐተታ ላለማብዛት ሲባል ከነዚህ ጸሓፊዎች ሦስት ጠቃሚዎች ናቸው ብዬ የማምናቸውን ብቻ ላንሣ። አንዱ የኢማም አሕመድ ዜና መዋዕል ደራሲ፣ የመናዊው ሺሐብ አድ-ዲን ነው። ሌላው በወቅቱ ኢትዮጵያን የጐበኙ የፖርቱጋል ዜጎችና፣ እንዲሁም እነሱ በሰጧቸው ጥቈማ በመመሥረት የካርታ ሥራ ባለሙያዎች ጠቃሚ መረጃዎች ትተውልናል።

ኢትዮጵያን ስለማሸነፍ በሚለው መጽሐፉ ሺሐብ አድ-ዲን[9] በእስላሞቹ በኩል ስለነበሩት ሰንደቅዓላማዎች ቀለማትና ቊጥር በዝርዝር ይገልጣል። ስለክርስቲያኖቹ ሲናገር ግን ጀብዱነታቸውን በማድነቅ፣ አርማቸውን እንደለበሱ፣ ሰንደቅዓላማቸውን እያውለበለቡ እንደሞቱ፤ ወይንም መኳንንቱ የእስላሞቹ ጥቃት እጅግ ቢያይልባቸውም፣ እነሱም ሰንደቅዓላማቸውም እንደተራራ ገደል ቀጥ ብለው እንደቆሙ ነበር” ብሎ ከመናገር ውጭ ስለሰንደቅዓላማዎቹ መልክ፣ ቀለምና ቍጥር ያለው ነገር የለም። ስለኢማሙ ሰንደቅዓላማዎች ሲናገር ግን፣ ሦስት ነገሮች ግልጥ ይሆናሉ። የያንዳንዱ የጦር መሪ ሰንደቅዓላማ በኢማሙ የተሰጠ ሲሆን፣ ባለአንድ ብቻ ቀለምና፣ በሰንደቅ ላይ ሳይሆን በጦር ጫፍ ላይ የሚሰካ ነበር። ስለዚህ ሰንደቅዓላማው በወቅቱ በአጋጣሚ የተፈጠረ እንጂ ቀዋሚና የቈየ አገራዊ መለዮ እንዳልሆነ ያመለክታል። ሁለተኛው፣ ቀለማቱ “የኢትዮጵያ ቀለማት” ተብለው ከሚመደቡት የቀስተደመና ዙርያ ካሉት አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ጥቊርንና ነጭንም ይጨምራል። በደራሲው እንደተመዘገበው፣ የኢማሙ ሰንደቅዓላማ ቀለም ብጫ ነበር። የኢትዮጵያም ነገሥታት አርማቸውን ብዙውን ጊዜ የሚለጥፉት በብጫው ላይ ስለሆነ፣ የግራኝም መለዮ ይኸው ቀለም መሆኑ፣ የሁለቱ መመሳሰል የአጋጣሚ ጉዳይ ነው ብሎ ማለፉ አስቸጋሪ ነው ብዬ አምናለሁ። ቀስተደመና ዓመቱን በሙሉ፣ በክረምት ወቅት ዝናም ሲዘንም፣ በበጋ ደግሞ በበርካታ ፏፏቴዎች አካባቢ የሚከሠት ምልክት በመሆኑ፣ የሰው ልጅ እንደሰንደቅዓላማ መጠቀም የጀመረው ምናልባትም “የቀስተደመና ቀለማት” ይሆናሉ ተብሎ ይታመናል። በኢማም አሕመድ እንዳየነው፣ አብዛኞቹ በኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ራስገዝ አስተዳደሮች ይጠቀሙት የነበረው ከነዚህ ቀለማት መካከል መርጠው ነው። ከዚህም የተነሣ፣ ባንዳንድ አካባቢ “የኢትዮጵያ

በዝናም ወቅት ወይንም ከፏፏቴ አካባቢ የሚታይ ቀስተደመና

ቀለማት” በመባል እስከመታወቅ ደርሰዋል።

ከፖርቱጋሎች በኩል ስለሰንደቅዓላማ ጉዳይ የተሻለ መረጃ የሚሰጠን ማኑኤል ባራዳስ ነው ማለት ይቻላል። በአ.አ. በሺ፮፻፴፬ ዓ. ም. ስለትግራይ ታሪክና ሥነምድር በጻፈው መጽሐፍ ኢትዮጵያውያን ሰንደቅዓላማቸውን በጦርነትም በሠርግም ወቅት እንደሚጠቀሙት፣ በአሣሣል፣ በመልክ፣ በዐይነትና በቁመት ሁሉም አንድ እንደሆነ፣ በቤተሰብ ሆነ ወይንም በመኰንን ማዕርግ ደረጃ ልዩነት እንደሌለ ያወሳል[10]። ሌላው፣ ስለካህኑ ዮሐንስ ምድር የተሣሉት በርካታ ካርታዎች ናቸው። ከነዚህ መካከል በሺ፭፻፸፫ ዓ.ም. ላይ ዳቹ አብርሃም ኦርቴሊዩስ[11] በሠራው ካርታ ላይ ተንተርሶ፣ ዊልም ጃንሶን ብለው[12] በሺ፮፻፷ ዓ. ም. የሣለው ነው። ካርታው በግልጥ ኢትዮጵያ የካህኑ ዮሐንስ የግዛት አገር መሆኑን ይገልጣል። አማራ፣ ትግሬ፣ ዶባ፣ ደንከል የሚሉ የቦታ ስሞችም ተመዝግበዋል። ከውስጡ የአንድ ወንድና የአንዲት ሴት ምስል ከሁለት ጃንጥላ የያዙ ልጆች ሥዕል ጋር ተሥሏል። ሴትዮዋ የለበሰችው ልብስ፣ ከላይ አረንጓዴ ሸሚዝ፤ ከመኻል ብጫ ጒርድ፣ ከታች እስከ እግሯ የሚደርስ ቀይ ሽርጥ ሲሆን፣ በቀለማቱ የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ያንጸባርቃል። ች። ዛሬም ቢሆን በኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ቀለማት ያጌጠ ቀሚስ፣ ሸማና ብሔራዊ ልብስ ተለብሶ ማየት የተለመደ እንደሆነ እናውቃለን። የብለው ካርታ ምሥል የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ የመቶ ዓመት ታሪክ ሳይሆን፣ ቢያንስ ከአራት መቶ ዓመት በላይ ዕድሜ አለው የሚለውን አቋም ይደግፋል ማለት ይቻላል።

 

የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ቀለማት በለበሱ ምስሎች አስጊጦ ዊልም ጃንሶን ብለው በ፲፮፻፷ ዓ. ም. የሠራ የኢትዮጵያ ካርታ

ስለልሙጡ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ብዙ የሚባል ነገር አለ። ግን የኢሕአዴግ መሪዎች እንደገለጹት ጨርቅም ቀለምም፣ እንጨትም እንዳይደለ መረጋገጥ አለበት። ባጭሩ፣ ያንድ ሕዝብ የመሬቱ ባለቤትነት፣ የነፃነቱ ርግጠኝነት፣ (የጥሩም ሆነ የመጥፎ) ታሪኩና ርእዮተ ዓለሙ መግለጫ ነው ብሎ ማጠቃለሉ ይበቃል። ኢትዮጵያ ከዐምስት ዓመት ትግል በኋላ፣ፋሽስቶች ድል ሁነው አገሯን ጥለው እንደወጡ፣ ነፃ አገርና የመሬቱ ባለቤት መሆኗን ለመላው ዓለም ያስታወቀችው፣ በጭቈናቸውም ሥር ለዐምስት ዓመት ይሠቃይ ለነበረው ሕዝቧም ድሉን ያበሠረችው፣ በመጀመርያ ይኸንን ልሙጡን ሰንደቅዓላማዋን በመሬቷ ላይ በመትከል ነው።

በቀስተደመና ምስል የተሣለው ይኸ የኢትዮጵያ ባለሦስት ቀለም ሰንደቅዓላማ፣ እንዳየነው፣ በጥንታዊነቱም ሆነ ባዘለው ምሥጢር የሚያስደምም ነው ቢባል ውሸት አይደለም። አረንጓዴ፣ ብጫ፣ ቀይ ቀለማት፣ ትርጒማቸው የአገሪቷን ጥንተንጥሮች ማለትም የ “ምድር፣የመንግሥትና የሕዝብ” ፍጹም ውሕደት ሲያንጸባርቅ፣ ባሕርያቸው ደግሞ አንድም ሦስትም መሆኑን ያመለክታል። ምድር በአረንጓዴ ቀለም ስትመሰል፣ በልምላሜዋ የሁሉም የሕይወት ምንጭና ፍሬ ሰጪ መሆኗን ያሳያል፤ ቀዩ ደግሞ ዜጐችዋ ላገርና ለወገን ፍቅር ሲሉ ያፈሰሱትን ደምና የከፈሉትን መሥዋዕት፣ ካስፈለገም ለዚሁ ቅዱስ ዓላማ ወደፊት ሕይወታቸውን በጀግንነት ሊሠዉ ዝግጁ መሆናቸውን ያረጋግጣል። በብጫ የተመሰለው መንግሥት፣ የምድርና የሕዝብ ጠባቂ፣ የሁለታቸውም የአንድነት ማተብና ሐረግ ሲሆን፣ ሕዝቡን አገር ለመከላከልም ሆነ ለልማት በኅብረት ማሰለፍ ግዴታውና አላፊነቱ እንደሆነ ይነግረናል። በአገራችን፣ ሦስት ቊጥር የፍጽምና ምልክት ነው። የቀለማቱ ሦስትነት ባንድ በኩል የአገሪቷን ልዩ ልዩ የአየር ጠባይ፣ የመሬት አቀማመጥ፣ ሀብትና ፍሬያማነት ሲመሰክር፣ በሌላው ደግሞ በሕዝቧም መኻል ያለውን የእምነት፣ የቋንቋና የባህል ልዩነት ያመለክታል። የቀለማቱ ጨርቆች ባንድጋ መሰፋታቸውና ከሰንደቁ ጋር መያያዛቸው፣ መሬት፣ መንግሥትና ሕዝብ በዓላማ፣ በአቋምና በግብር ያላቸውን ውሕደትንና እኩልነትን ብቻ ሳይሆን, ሕዝቡም በታሪክና በባህል፣ በደምና በኑሮ እንዲሁም በማንኛውም ማኅበራዊ ዘርፍ ርስበርሱ የተሳሰረና የተዋሐደ፣ ላንድ ዓላማ የቆመ እንደሆነ ያስረዳል።

ይኸ በ፲፱፻፱ ዓ. ም. ብሔራዊ መግለጫ እንዲሆን በሕግ የተደነገገው ሰንደቅዓላማና ቀለማቱ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድነቱና የነፃነቱ ምልክት ከመሆን አልፎ፣ ተመሳሳይ አገልግሎቱን ለሌላውም ለሰፊው ዓለም በማበርከት በታሪኩ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል። በምዕራባውያን ጭቈና ይማቅቅ የነበረው ጥቍር ሕዝብ በፈታኝና እልህ አስጨራሽ ትግሉ ወቅት፣ በኢትዮጵያዊነት ዙርያ በመሰለፍ ብቻ አልነበረም ለአርነቱ የታገለው። ሰንደቅዓላማዋንም የትግሉ መከታ፣ የነፃነቱ ፋና፣ የድሉ ዋስትና አድርጎ ነበር የተመለከተው። ይልቁንም ዓለምን ካስደነቀው ከአድዋ ድል በኋላ፣ጥቊር ሕዝብ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ እንደትእምርተ ኀይልና ትእምርተ መዊዕ አድርጎት ለማየት ተገደደ። የአሳቡ ጠንሳሽ የመላውን ዓለም ጥቊር ሕዝብ፣ ለዚህ ዓላማ ባንድጋ ያሰባሰበው፣ ስመጥሩው የጃማይካው ተወላጅ ማርኩስ ጋርቬይ[13] ነው። አቶ ጋርቬይ፣ በአ. አ. በ፲፱፻፳ ዓ.ም. “ተመልከት ዓላማህን፣ ተከተል አለቃህን” ሲል የጥቊር ሕዝብ ማንነት መግለጫና፣ የትግሉ ተስፋ እንዲሆንለት የመረጠው የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማን ቀለማት ነው[14]። ወደሠላሳ ዓመታት ቈይተው፣ ነፃነታቸውን የተጐናፀፉት አብዛኞቹ የአፍሪቃ መንግሥታትም፣ የአገራቸው ክቡርና አኩሪ ታሪክ፣ የነፃነታቸው ማረጋገጫ፣ የመሬታቸው ባለቤትነት ማስመሰከርያ እንዲሆን የመረጡት፣ እነኚሁኑን የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ሦስቱን ቀለማት በመዋስና፣ መሠረት በማድረግ ስለነበር፣ ዛሬ “የመላዋ አፍሪቃ ቀለማት” በመባል ይታወቃሉ።

የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ከፍተኛ አድናቆት በዚህ ብቻ አላበቃም። የአድዋ ድል፣ የጥቁር ሕዝብ ተጋድሎ ደጋፊ የነበረውንና በዘመናዊ ፈጠራው የታወቀውን፣ ጋሬት አውጉስቱስ ሞርጋን[15]ን ከኢትዮጵያ ጋር ሊያተሳስር በቅቷል። የመኪናና የተለያየ ተሽከርካሪ በዓለም ላይ ብቅ ማለት፣ መጓጓዣ መንገዶቹን እጅግ በጣም አጨናንቆ፣ ብዙ ሕዝብ ለአደጋ ሲያጋርጥ፣ ለሞት ሲዳርግ፣ ብዙ ቢሞከርም ፍቱን መፍትሔ ሊገኝ አልተቻለም። የተቻለው፣ በአ. አ. በ፲፱፻፳፪ ዓ. ም. ላይ፣ አቶ ሞርጋን የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ቀለሞች ለትራፊክ መብራት አገልግሎት በማዋሉ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ፣ ሦስቱ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ቀለማት፣ ማንኛውም ዘመናዊ ተሽከርካሪ በሚጓዝበት መንገዶች፣ በመላው ዓለም ከዳር እስከ ዳር፣ የሰውን ልጅ መመላለሻ ጠባይ ተቈጣጣሪ ሁነዋል። ሦስትዬው ቀለማት የትራፊክ መብራት በያለበት፣ የሕግ አስጠባቂና አስከባሪ ኀይል ብቻ ሳይሆን፣ አገልግሎቱን ከጀመረበት ወቅት ጀምሮ፣ የብዙውን ሰው ሕይወት ከሞት አድነዋል፤ ትርምስምስና ጭንንቅ ከየመገናኛ መንገዱ አስወግደው ዘርና አካባቢ፣ ቋንቋና ባህል፣ እምነትና የትምህርት ደረጃ፣ መደብና ማዕርግ፣ ዳራና ፆታ ሳይለዩ፣ ሁሉንም በእኩልነትና በትክክል፣ በሥነሥርዐትና በመከባበር እያስተናገዱ ይገኛሉ።

እንግዴህ ሊቅ ነጋሦ የሚያጥላሉት ሰንደቅዓላማ በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክና ጥልቅ ምሥጢር ያለው ብርቅ ቅርስ ብቻ ሳይሆን፣ ለብዙ የዓለም ክፍሎችም የነፃነታቸውና ያገራቸው ባለቤትነት ምልክት ሁኖ ያገለገለ ነው። ከኢትዮጵያ ገጸምድር አላንዳች ማመንታት መጥፋት ያለበት ሰንደቅዓላማ ቢኖር ባለኮከቡ እንጂ ልሙጡ መሆን የለበትም። ባለኮከቡ ሰንደቅዓላማ እጅግ በጣም አስከፊ የሆነ ታሪክ ውጤት መሆኑ አይካድም። ይኸንንም ለመረዳት ከፈለግን የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ሕወሓት)ን ታሪክ መመልከት ግድ ይሆንብናል።

በየካቲት ወር በ፲፱፻፷፰ ዓ. ም. ባወጣው በመጀመርያ እትም መግለጫው፣ ሕወሓት የትግራይ ሕዝብ የተፈጥሯዊና ማኅበራዊ ችግሮች መሠረታዊ ምክንያት ሦስት ናቸው ካለ በኋላ፣ እነሱም ኢምፔርያሊዝም፣ ባላባታዊ ሥርዐትና የአማራብሔረሰብ  መሆናቸውን እንደዚህ ሲል ይገልጣል።

የትግራይ ሕዝብ ለረጅም ዘመን ሰብኣዊና ፖለቲካዊ መብቱ ተነፍጎ ሲጠላና ሲናቅየኖረበት ምክንያትጨቋኝዋ የአማራ ብሔር ሆነ ብላ እንደመንግሥት መመሪያዋ አድርጋስለሠራችበት ነው። እንዲሁም ደግሞ በትግራይ ሥራ ታጥቶሕዝቡ በሽርሙጥናና በስደት እንዲሁምበረኀብ፣ በድንቊርናና በበሽታ እየተሠቃየያለበትመሠረታዊ ምክንያት ኢምፐርያሊዝምና ባላባታዊ ሥርዓት.…ጨቋኝዋ የአማራ ብሔር የምታደርገው የኤኮኖሚ ብዝበዛና የፖለቲካ ጭቈናነው። ስለዚህጨቋኝዋ የአማራ ብሔር ጭቈናዋ እስካላቆመች ድረስ ኅብረተሰቧ ዕረፍት አታገኝም።

ይኸ የሕወሓት መግለጫ ያስቃል ብቻ ሳይሆን፣ ያሳዝናልም። በሐሰትና የተዛባ ርእዮተ ዓለም የተመሠረተ ስለሆነ። ልክ ሒትለር የጀርመኖችን ችግር በአይሁዶች፣ እንዲሁም የግራዘመም ርእዮተዓለም ባላቸው ግንባሮችና ግለሰቦች ትከሻ ላይ እንደጣለ ሁሉ፣ ሕወሓትም የትግሬ ሕዝብ ጠላቶች እያለ ይጮህ የነበረው፣ በገዛ ጭንቅላቱ እንጂ በትግራይ ውስጥ በውን ህልውና በሌላቸው ምክንያቶች ላይ ነበር ማለት ይቻላል። እስኪ ሦስቱንም ዐጠር ባለ መልካቸው እናገናዝባቸው።

ኢምፐርያሊዝም፣ ጥቅማጥቅም ሊገኝባቸው ይቻላል በተባሉት አገሮች በቅኝ ግዛት፣ ወይንም በጦር ኀይል፣ ወይንም ሌላውንም ዐይነት ስልት በመጠቀም አንዱን አገር በግልጥ፣ ካልተቻለም በሥውር መቈጣጠር ይገባል በሚል ርእዮተ ዓለም የተገነባ የፓለቲካ ሥርዐት ነው። ሁላችንም እንደምናውቀው፣ ብዙውን ጊዜ ይኸ አስተሳሰብ ከምዕራባውያን መንግሥታት ጋር ተቈራኝቶ ይገኛል። ምን ሊያገኙ ሲሉ ነው ምዕራባውያን ትግራይን ለመቈጣጠር ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን የሚያጠፉት ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ይኸንን ያህል ደደቦች ስላልነበሩ አላደረጉትም፤ ሊያደርትጉም አልሞከሩም። ኢምፐርያሊዝም ሌላው ቀርቶ፣ ትግራይ የምትባል አገር መኖሯን እንኳ እንደሚያውቅ ማስረጃ ያለ አይመስለኝም።

የባላባታዊ ሥርዐትስ። ባላባታዊ ሥርዐት በአብዛኞቹ የአውሮጳ አገሮች በመካከለኛ ዘመነምሕረት ላይ የተከሠተ በመሬት ሽግሽግ ላይ የተመሠረተ የሥልጣን አደላደል ነው። በዚህ ሥርዐት መሠረት፣ ንጉሡ ለመሳፍንቱ መሬት ያድላል፤ እነሱም በለውጡ የውትድርና አገልግሎት ይሰጡታል፤ ከነሱ ሥር ያሉት ደግሞ በተራቸው ጢሰኞቻቸው ሲሆኑ፣ አራሹ ክፍል ለይስሙላም ቢሆን ከጌቶቹ ለሚለገሥለት የጥበቃና የጸጥታ አገልግሎት ውለታ ለመመለስ ሲል በመሬታቸው ላይ ለመኖር፣ እጅመንሻ ለመስጠትና ከምርቱ የተመደበለትን ሊከፍል ይገደዳል። ታዲያ ይኸ ዐይነት ሥርዐት በትግራይ ነበር ወይ ቢባል ስለመኖሩ ምንም ዐይነት ማስረጃ የለም። በትግራይ ቀርቶ በማንኛውም የኢትዮጵያም ሆነ የአፍሪቃ ክፍል መኖሩን የሚያረጋግጥ ሰነድ እስካሁን አልተገኘም። ድርጅቱ ሽፍትነቱን በጀመረበት ወቅት ይታዩት በነበሩት አንዳንድ ነገሮች ላይ ከተመሠረትንና፣ በአፄ ኀይለሥላሴ ዘመነመንግሥት ለነበረው የምጣኔሀብት ሥርዐት፣ ባሕርያቱን በሚያንፀባርቅ መልኩ የግዴታ ስም ይሰጠው ከተባለ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ፣ የሕወሓት መግለጫ በወጣበት ወቅት እየተጠናከረ ይሄድ የነበረው የድልብ ገንዘብ ማለትም የካፒታሊስም እንጂ ባላባታዊ ሥርዐት አልነበረም።

አማራስ። ለመሆኑ አማራ ምንድር ነው። ስለአማራ ብዙ ተጽፏል፣ ብዙም ተነግሯል። እኔም በተለያዩ ወቅቶችና መድረኮች በጉዳዩ በመጠኑ ጽፌአለሁ፤ ተናግሬምአለሁም። ሰፋ ያለ ማብራርያ የፈለገ፣ እነዚያን ጽሑፎቼን እንዲያነብብ፣ ቃለምልልሶቼንም አንዲሰማ ይጋበዛል[16]። እንዲያው ለነገሩ ያህል፣ ዐጠር ያለ ገለጣ ልስጥና ልቋጭ። ሕወሓት ሥልጣን እስከያዘበት ዘመን ድረስ፣ አማራ የሚለው ቃል መቼም ጊዜ ከአንድ ብሔረሰብ ጋር ተቈራኝቶ አይታወቅም። ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የውጭ አገር ደራሲዎች አማራ ሲሉ የሚያመለክቱት፣ አሁን ወሎ በመባል የሚታወቀውን ክፍለአገር፣ ወይንም አሁንም ቢሆን እዚያው ጠቅላይ ግዛት ውስጥ የሚገኘውን የአማራሳይንትን ምድር ነው፤ አለበለዚያም ኢትዮጵያዊ የሆነውን በሙሉ ነው። በአማራ ምድር ይኖር የነበረው ሕዝብ የመጣው ደግሞ ከአክሱም ነው ተብሎ ይነገራል።

ሕወሓት አማራ ሲል ነገሥታቱን ወይንም የገዢውን ከፍል ይሆን የሚያመለክተው ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው። ነገሥታቱም ሆኑ፣ የገዢው ክፍል አማርኛ ይናገሩ እንጂ፣ የመጡት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ መሆኑ ግልጽ ነው። ትግራይ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ይተዳደር የነበረው ከማንኛውም የኢትዮጵያ ግዛቶች ይበልጥና በተሻለ ሁናቴ በገዛ ራሱ ምድር ተወላጆች እንጂ ከሌላ አካባቢ በመጡት ሹሞች አልነበረም።

ሕወሓት አማራ የሚለው አማርኛ ተናጋሪውን ከሆነ፣ አማርኛ ቋንቋ እንጂ ብሔረሰብ አይደለም። ሕወሓት ሥልጣን ይዞ አገሪቷን በብሔር እስካወቃቀረ ድረስ፣ አማርኛ ተናጋሪው የጠባብ ብሔረሰብነት አመለካከት ስላልነበረው፣ ራሱን እንደጐሣ ቈጥሮ አያውቅም። አማርኛ ይልቅስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ርስበርሱ ሊግባባ የፈጠረው የመላ ኢትዮጵያውያን የጋርዮሽ ቋንቋ ነው። የኢትዮጵያን ብሔረሰቦች በሙሉ ለማንኛዉም ሳያዳላ የሚወክል፣ ከማንኛውም ጋር የማይተሳሰር፣ ሲናገሩት ጉሮሮ የማይከረክር፣ ምላስ የማያዶለዱም፣ ገለልተኛ፣ ግልጽና ጥርት ያለ ቋንቋ ነው።

አማራም ሆነ፣ ትውልዱ ትግራይ ያልሆነ አማርኛ ተናጋሪ፣ ወደትግራይ ሄደ ቢባል፣ እጅግ በጣት የሚቈጠር መሆን ይኖርበታል። ከሄደም በተሰጠው የሥራ አላፊነት ተገድዶ እንጂ፣ በፈቃዱ ወዶ ነው ማለቱ ይከብዳል። በተለይም ከአፄ ምኒልክ ዘመነመንግሥት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍልሰት የነበረው ከሰሜን ወደደቡብ እንጂ ፣ከደቡብ ወደሰሜን አልነበረም። ይበልጥ ደግሞ፣ የትግራይ ተወላጆች በተለያዩ ምክንያቶችና ጊዜ፣ የመላዋን የኢትዮጵያ መሬት ከጫፍ እስከጫፍ አዳርሰዋታል፤ በተቀረው የኢትዮጵያ ምድርም እነሱ ያልረገጡት መንደር፣ ያልተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ የለም ቢባል በጭራሽ ማጋነን አይሆንም። ታዲያ እውነቱ እንደዚህ ከሆነ፣ አማራ የተባለ ብሔረሰብ አለ እንኳን ከተባለ የትኛው ነው ትግራይን የበዘበዘው፤ እንዴትስ ብሎ ነው ወደትግራይ የደረሰው፣ ምንስ ፈልጎ ነው የሄደው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። እዚያ ካልሄደ፣ የሚበዘበዝ ነገር ባገሩ ከሌለ፣ ሕወሓት ከባዶ ምድር ተነሥቶ ነው ወይ የአማራ ብሔረሰብ ነው ብሎ የሰየመውን ሕዝብ ደመኛ ጠላቱ ሊያደርግ የበቃው። የሕወሓት መግለጫ ያነበበ ድርጅቱን አዙሮ የማያይ የጥራዘነጠቆች ስብስብ፣ ወይንም የአእምሮ ቀውስ ያጠቃቸው ሰዎች ጥርቅም ነው ቢል የተሳሳተ አስተያየት ነው ብሎ ለመኰነን በጣም ይከብዳል። ትክክል አይደለም ብሎ ለመሟገትም ያዳግታል። እውነቱንም ለመረዳት ብዙም ርቆ መሄድ አያስፈልግም። የድርጅቱን መግለጫ ማንበቡ ብቻ ይበቃል።

ሕወሓት ከመነሻው አማራ ብሎ የፈረጀው ብሔረሰብ ዋና ጠላቱ መሆኑን ለይቶ ከወሰነ በኋላ ነው እንግዴህ አገሩንም ሕጉንም ያወቃቀረው። አወቃቀሩም ይኸንኑ አማራ ብሔረሰብ የሚለውን ክፍል ለማጥቃትና ለማጥፋት በሚያመቻችልለት መንገድ ነበር ቢባል ስሐተት አይመስለኝም። ሐቁ ይኸ እንደሆነ ለማሳየት ሩቅም መሄድ አያስፈልግም፤ በተከታታይ የፈጸማቸው ሥራዎች በእማኝነት ሊጠሩ ይችላሉ።

በመጀመርያ ደረጃ፣ በትግራይ የበላይነቱን ካረጋገጠ ወዲያ፣ የተዛባ ርእዮተ ዓለሙን በግብር ላይ ለማዋል የሚረዱትን አቋሞች ለማደላደል ሲል፣ ሕወሓት ሁለት ግንባር ከፈተ። ባንድ በኩል፣ አጋር ድርጅቶችን በአምሳሉ ጠፍጥፏቸው ሊፈጥር አስቦ፣ አባላት የመመልመል ዘመቻውን ተያያዘበት። ለዚህም ሲል፣ ባላንጣው ከነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ(ኢሕአፓ)ና፣ እሱን ከመሰሉ ግራዘመም ድርጅቶች፣ መርሃግብሩን ለማሳመን የቻላቸውን ግለሰቦች ከራሱ ጋር ቀላቀለ። እምቢ ያሉትን ደግሞ በመደምሰስና ከአካባቢው በማባረር አስወገዳቸው። ከዚሁ ጋር በማያያዝ ድርጅታዊ መዋቅር ለሌላቸው ብሔረሰቦች፣ በእጁ የነበሩትን የጦርሠራዊት ምርኮኞችንና፣ በብሔረሰብ ልሂቃን ስም ከየቦታው ያጠራቀማቸውን ጥቅምፈላጊ ግለሰቦችን፣ የየብሔረሰቦቻቸው ተወካዮች እንደሆኑ በማሰብ ድርጅታዊ ዕውቅና ሰጣቸው። እነዚህን ሕወሓት የመርሀግብሩ አስፈጻሚ አካል ይሆናሉ ብሎ ያቋቋማቸውን አጋር ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የሚል ጉራማይሌ ስም ሰጣቸው።

በዚህ መልክ የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወካይ እንዲሆን፣ ሕወሓት ከፈጠራቸው የኢሕአዴግ ድርጅቶች አንዱ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲአዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ነው። ሊቅ ነጋሦም ለኢሕአዴግ አባልነት ሊበቁ የቻሉት በዚህ ድርጅት ጥላ ሥር ተገኝተው በመሾማቸው እንደሆነ መታወቅ ይገባል። እንግዴህ ሊቁ ገና ከጥንስሱ አንድ የተለየ ብሔረሰብን ነጥሎ ለማጥፋት የተቋቋመው ሕወሓት ዋና አዋላጅ ከሆኑት አንዱ መሆናቸው አይካድም።

ኢሕአዴግን ያወቃቅር በነበረበት ወቅት፣ ሕወሓት ሌላም ሥራ ይሠራ ነበር። ከመሰል የትግል ጓዶቹ፣ ማለትም በአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ በሚመራው የኤርትራ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ሊቀመንበርነት፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አጋፋርነት፣ ድርጅቱ በ፲ሺ፱፻፹፫ ዓ.ም. በጋ ላይ በኤርትራ ውስጥ ተሰነይ በተባለ ከተማ በተካሄደው ስብሰባ ኢትዮጵያን በጐሣ በሚሸነሽን ሕገመንግሥት ተስማማ። የሕገመንግሥቱን ቊልፍ ነጥቦች አርቅቆ፣ ለሕወሓት መሪ ለአቶ መለስ ዜናዊ ሰጠው የሚባለው ግለሰብ፣ ከኦነግ ዋኖች አንዱ የሆነው አቶ ሌንጮ ለታ እንደነበር ተነግሯል።

የነዚህ ሁለቱ ርምጃዎች መጨረሻው ውጤታቸው የክልሎች መንግሥታት መፈጠርና፣ የ፲፱፻፹፮ ዓ. ም. ሕገመንግሥት መጽደቅ ነው። ሁለቱም ድርጊቶች ሕወሓት አማራ ብሎ የወሰነውን ብሔረሰብ ነጥሎ በማነጣጠር የመምታት ዓላማውን ለማሳካት ከመርሀግብሩ አስፈጻሚ ቡድን ከሆነው ከኢሕአዴግ ጋር ሁኖ የገነባው የአስተዳደር መዋቅር አካላት ናቸው። እስኪ ዐጠር ባለ መልክ በዝርዝር እንይ።

መጀመርያ ደረጃ፣ ሕወሓት ከኢሕአዴግ ጋር ሁኖ ክልል በመባል የሚታወቀውን የአስተዳደር መዋቅር ገነባ። የኢትዮጵያን ሕዝብ በሰማንያ ያህል የትውልድ ዝርያ ከፋፍሎ አንዱን ብሔር፣ ሌላውን ብሔረሰብ፣ የቀረውን ሕዝብ በማለት በትርጒምየለሽ ቃላት አማትቶ ሲያበቃ፣ አገሪቷን ሸንሽኖ ዘጠኝ ክልሎች ፈጠረ። በየክልሉ የሚኖረውን የሕዝብ አንድነትና እኩልነት ያረጋግጣል በማለት፣ ኮከብ ያለበትን አርማ በሰንደቅዓላማው ላይ ለጠፈበት።

የክልል ዓላማ፣ ሕዝቡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ነው። እውነቱ ግን ከላይ እንደገለጽሁት ለሕወሓት ክልሎች የመግለጫውን ዓላማ ማለትም መርሀግብሩን የሚያሳካባቸው ረጃጅም ቀኝ እጆቹ ናቸው። ስለዚህ ክልሎች እስከዛሬ ድረስ ሥራችን ነው ብለው የተያያዙት፣ አማርኛ ተናጋሪውን በስመ “ነፍጠኛ”፣ “የምኒልክ ሰፋሪ”፣ “ጨቋኝ” ወይንም “የጨቋኝ ቡድን” እያሉ በማሳበብ፣ ልሕቅና ደቂቅ፣ ወንድና ሴት፣ ሕፃንና ሽማግሌ፣ ነፍሰጡርና አሮጊት ሳይለዩ በጅምላ ልዩልዩ ስልትና መሣርያ እየተጠቀሙ መግደል፣ መጨፍጨፍ፣ ሀብቱንና ንብረቱን መዝረፍ፣ ከቤቱና ከቀዬው ማፈናቀል ነው። ልክ በአውሮጳ ከጀርመን ቊጥጥር ሥር የነበሩ ግዛቶች፣ በናዚዎች የተዛባና የሐሰት ስብከት ተመርተው፣ በአይሁዶች ላይ የፈጸሙትን ግፍ፣ ክልሎችም የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ በሆነው በኢሕአዴግና በመሪዎቹ ቅስቀሳ፣ በአማርኛ ተናጋሪው ሕዝብ ላይ ከዚያ የማይተናነስ ኢሰብኣዊ ጭካኔና የዘር ማጽዳት ተግባር እንደፈጸሙ መታወቅ ይገባል። በዚህ ኅብረተሰብ ላይ ተፈጸሙ የተባሉት ኢሰብኣዊ ድርጊቶች፣ አብዛኞቹ በሥዕል የተቀረጹ፣ ለሰው መብት በቆሙ ባስተማማኝ ብሔራዊና ዓለም-ዐቀፍ ድርጅቶች ከነማስረጃቸው የተጠናቀሩ፣ እሙን በሆኑ ያይን ምስክሮች የተደገፉ ስለሆኑ፣ ማስተባበሉ ከመደናቈርና የአተካራ ግብግብ ከመግጠም ውጭ ሌላ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም።

ሕወሓት አማርኛ ተናጋሪውን ያሳደደው በመግደል፣ ንብረቱን በማውደም፣ ወይንም በማፈናቀል ብቻ አይደለም። ባንድ በኩል፣ ክልሉ በገዛ ራሱ አካባቢ ተወላጆች ይተዳደራል ብሎ የዋሁን ተመልካች ሊሸነግል ሲል፣ የክልሉን አስተዳደር መስፈርቱን በማያሟሉ ግለሰቦች ሞላ። አስተዳዳሪዎቹ አማርኛ ቢናገሩም፣ ወይንም በአማራ ክልል ቢወለዱም፣ በትውልድ ሐረጋቸው ግን ከሌላ አካባቢ የመጡ፣ ወይንም ሕወሓት የአማራ ብሔረሰብ ነው ብሎ የሠየመውን ሕዝብ ጥቅምና መብት ከማስጠበቅ ይልቅ ራሳቸው አሳዳጆቹ ከመሆን መቼም ቢሆን ተቈጥበው የማያውቁ የግለሰቦች ጥርቅም ናቸው ማለት ይቻላል። በሌላ በኩል፣ ሕወሓት ራሱ፣ የአማራ ብሔረሰብ ክልል ነው ብሎ በወሰነው ክፍለግዛት ያሉትንና፣ በታሪክ መሠረት መቼም ቢሆን የትግራይ አካል ሁነው የማያውቁትን ሰፋፊ መሬቶች እየሸረሸረ በጉልበቱ ወደትግራይ አስገብቷል። ከዚያ ባሻገር፣ በብዙ ሚሊዮን የሚቈጠሩ አማርኛ ተናጋሪዎች፣ በቀሩት ስምንቱ ክልሎች መኖራቸው እየታወቀ፣ ዜግነታዊ መብታቸውን አስገፍፎባቸዋል። በያሉበት ክልሎች ምንም መንግሥታዊ ውክልና እንዳይኖራቸው አድርጓል። በቋንቋቸው ሊማሩና ሊያስተምሩ አይችሉም፤ የመምረጥና የመመረጥ መብት ተነፍጎባቸው እንደመጤዎች ሁነው እንዲኖሩ አስገድዷቸዋል። ስለዚህ በማንኛውም ጊዜ አስተዳደሩ ከፈለገ ከክልሉ ቢያባረር ፣በሕግ የሚጠይቀው የለም ማለት ይቻላል። ወደዋናው ርእሳችን እንመለስና፣ ባለኮከቡ የኢሕአዴግ ሰንደቅዓላማ መታየት ያለበት በዚህ መነፅርና አንፃር ነው።

ባለኮከቡ ሰንደቅዓላማ እንደተባለው የእኩልነትና የአንድነት ምልክት መሆኑ ቀርቶ፣ ልክ እንደናዚ ጀርመን እስዋስቲካ የጥላቻ፣ የስደትና የግድያ ምንጭ ሆኗል። ሊቅ ነጋሦ ግን የኢሕአዴግ አባል ድርጅት አካል የሆኑት የኢትዮጵያን ታሪክ በተንሻፈፈና በተዛባ የሕወሓት ጠማማ መነጽር ብቻ ለማየት ዝግጁ በመሆናቸው ይኸንን እውነት ሊረዱ የቻሉ አይመስልም። የታሪክ ምሁር ቢሆኑም፣ ዕውቀቱ የላቸውም ብቻ ሳይሆን፣ የማሰላሰል ችሎታቸው ምን ያህል ዝቅተኛ መሆኑን አንድ ወቅት በድርጅታቸው ርእዮተ ዓለም ላይ ከመሪያቸው አቶ መለስ ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ ሊቁን ሁለትና ሁለት አራት መሆኑን የማያውቅ መሃይምን መሆናቸውን በማሽሟጠጥ እንደነገራቸው፣ ራሳቸው “የነጋሦ መንገድ” በሚለው መጽሐፋቸው ያጫወታሉ። እኔም በበኩሌ ስለሳቸው ያለኝ አስተያየት፣ ከዚሁ የማይለይ መሆኑን በጽሑፌም፣ በንግግሬም ገልጫለሁና[17] እዚህ መድገሙና መለፍለፉ አስፈላጊ መስሎ አይታየኝም።

ሊቅ ነጋሦ እጅግ አድርገው የሚያጣጥሏቸው አፄ ምኒልክም ሆኑ አፄ ኀይለሥላሴ በአስተዳደር ብቃትም ሆነ፣ በሕዝብ ዘንድ ባላቸው ተቀባይነት፣ እንዲሁም የሥልጣናቸው መሠረት ከድርጅታቸው እጅግ በጣም የተለየ መሆኑን ግን የተረዱ አይመስሉም። በዚህ ረገድ፣ ስለአፄ ምኒልክ ታላቅነት ከዚህ በላይ በቂ ስላልሁ፣ ሌላ መጨመሩ አስፈላጊ ሁኖ አይታየኝም። ስለሳቸው ታላቅነት ያለኝን ግንዛቤና ዕይታ ማወቅ ለሚፈልግ ምኒልክን ብትወቅሱ ማንነታችሁን ትረሱ በሚል ርእስ የጻፍሁትን ንኡስ መጽሔት እንዲያነብ እጋብዛለሁ። አሁን ግን ብዙም ያልሁት ስለሌለ ወደአፄ ኀይለሥላሴ ልግባ።

አፄ ኀይለሥላሴ ወደኢትዮጵያ ዙፋን የወጡት የሰው ደም ሳይፈስ፣ ንብረት ሳይነካ፣ በዘመኑ በነበረው በምርጫ ሥርዐት በታላቅ ክብርና ማዕርግ በሕዝብ በጎ ፈቃድ ነው። መኳንንቱና ቤተክህነቱ፣ ሕዝቡም ከሊቅ እስከደቂቅ ባንድ ላይ ሁኖ ባንድ ድምፅ በእልልታና በደስታ መርጧቸዋል። ይኸም ማለት፣ እንደደርግ ሰላማዊ ሕዝብ እየጨፈጨፉ፣ ንብረት እያጠፉ፣ ሥልጣን አልያዙም። እንደ ሕወሓት ደግሞ ዐሥራሰባት ዓመት በጫካ ተዋግተው፣ ንብረት አውድመው፣ ደም አፍስሰው አለውድ በግድ በጠመንጃ ኀይል በሕዝብ ጫንቃ ላይ አልተጫኑም። በዚህ የታሪክ መነጽር ካየን፣ የኮከቡ ሰንደቅዓላማው ሕጋዊነት ዋጋ-ቢስ ይሆናል። በሕወሓትና በሥራ አስፈጻሚው መልክ ወደሥልጣን የመጣ መንግሥት የደነገገውን ሰንደቅዓላማ መቀበል ማለት ደግሞ በግፍ በጠመንጃ ኀይል በሕዝብ ላይ ተጭኖ በጡንቻው ለሚገዛው መንግሥት ሕጋዊ ዕውቅናን መስጠት ይሆናል።

ብዙ ጊዜ አንዳንድ ጸሓፊዎች በሕወሓት የሚመራውን የኢሕአዴግን መንግሥት ከጀርመኑ ናዚና ከኢጣሊያኑ ፋሺዝም ሲያመሳስሉ አነብባለሁ። እኔ ራሴ ከላይ እንዳልሁት ንጽጽሩ ተገቢ ነው። ግን የሦስቱም ዐመፃቸውና ግፋቸው እንዳለ ሁኖ፣ ኢሕአዴግ በብዙ መልኩ ከሁለቱም የከፋ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ የተገነዘቡ አይመስልም። ናዚዎችም ሆኑ ፋሺስቶች ሥልጣን የጨበጡት በወቅቱ በአገራቸው በነበረው ሕግ ደንብ መሠረት በምርጫ ተወዳድረው በማሸነፍና የሕዝብን ውክልና በማግኘት ነው። ኢሕአዴግ ግን፣ ኋላ የምዕራባውያንን የገንዘብና የሞራል ድጋፍ ለማግኘት ሲል ምርጫ ቢያካሄድም፣ ዙፋኑን የተቈናጠጠው ግን በጠመንጃ ኀይል ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት። በሌላው በኩል፣ ናዚዎች እሥልጣን ላይ ሲወጡ፣ ከጀርመን ሕዝብ ወደአርባ ዐምስት ከመቶው ሥራ ፈት ነበር። ሥልጣን ከጨበጡ ሦስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግን አንድም ሥራፈት ጀርመናዊ አልነበረም ማለት ይቻላል። የኢሕአዴግ መንግሥት ግን የተሰማራው ሥራ በመፍጠር ሳይሆን፣ ያገሩን ሀብት በመበዝበዝና በመግፈፍ እንደሆነ፣ እውነተኝነታቸው የማይጠረጠር ሰፊ ማስረጃዎች በየጊዜው ወጥተዋል።

የባለኮከቡን ሰንደቅዓላማ ሕጋዊነት ለመረዳት ሕጉን ራሱን መመርመር የግድ ይሆንብናል። ሕግ በተደገነነለት ሕዝብ መካከል አድልዎና ልዩነት ሳያሳይ፣ ለሁሉም እኩል አገልግሎት መስጠት ይኖርበታል። ሕግ የማንም የአገሪቷ ዜጋ የመጨቈኛ መሣርያ ሁኖ መገኘትም መታየትም የለበትም። አለበለዚያ ሕግነቱ ዋጋ ስለሌለው፣ ተጨቋኙ ብቻ ሳይሆን የቀረው የአገሪቷ ሕዝብ የተቻለውን ጉልበትና መሣርያ በመጠቀም መዋጋት ይኖርበታል። የኢሕአዴግ ሕገመንግሥት፣ ሕወሓት አማራ ብሎ የፈረጀውን ብሔረሰብ ለማጥፋት የተቀናጀ መሣርያ መሆኑን ዐይተናል። ሊቅ ነጋሦ የነፃነት፣ የእኩልነትና የአንድነት አርማ ነው ብለው የሚገልጹልን ባለኮከቡ ሰንደቅዓላማ፣ በዚህ ሥርዐት ደንብ የጸደቀ መሆኑን የረሱ ቢመስልም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተገነዘበው ግን እሳቸው በሚሉት መልክ አይደለም። ለዚህ ሕዝብ፣ ባለኮከቡ ሰንደቅ ዓላም፣ ለኻያ ሰባት ዓመት የተጋረጠው የግፍና የሰቈቃ፣ የእስራትና የግድያ ምልክት አርማ ነው። ስለዚህ አማራ የተባለው ብሔረሰብ ብቻ ሳይሆን፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪካዊውንና ከአያቶቹ የወረሰውን፣ ከትውልድ አገሩ አልፎ የዓለም ግርማና ሞገስ የሆነውን ክቡር ሰንደቅዓላማ በየከተማው በነቂስ ይዞ እየወጣ ኢሕአዴግን እየተቃወመው እንዳለ እያየን ነው።

ሕወሓት የፈጸመው ግፍ ብቻውን እንዳላደረገው ተደጋግሞ ተነግሯል። በዚህ እኩይ ተግባሩ ዋና ጀሌውና ቀኝ እጁ ሕገመንግሥቱን አብሮ አርቃቂው ኦነግ እንደነበረ፣ ዓለም ያወቀው ፀሓይ የሞቀው ጉዳይ ነው። ኦነግ ልክ እንደሕወሓት፣ ኢትዮጵያን ማፍረስና የአማራ ብሔረሰብ ነው ብሎ የፈረጀውን ሕዝብ መፍጀት እንደዋና ዓላማው አድርጎ ይንቀሳቀስ የነበረ ድርጅት ነው። በቅርቡ አማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ በተጋፈጠው ግፍ፣ ኦነግን ከደሙ ንጹሕ አስመስሎ ለማቅረብ በየቦታው ዘመቻ ተሞክሯል። እውነቱ ግን በኢትዮጵያና በማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለደረሰው ታላቅ እልቂት፣ ሕወሓትም ሆነ፣ ኦነግ ከነመሪዎቻቸው (አሁን በአዲስ ድርጅት ስም የሚጠሩትን እነአቶ ሌንጮ ለታ የመሳሰሉትን የዱሮ የኦነግ መሪዎችን ጭምር) በትክክል ተጠያቂ መሆናቸው መረሳት ያለበት አይመስለኝም። ሕወሓት እሥልጣን ላይ ሲወጣ፣ ኦነግ በጊዜው የነበረውን የፖለቲካ ቀውስ በመጠቀም፣ ክልሌ ነው በሚልበት አካባቢ፣ በኤርትራዊው ሻቢያ ችሮታ እየተንቀሳቀሰ፣ ይዞታውን ለማስፋፋት ይሯሯጥ በነበረበት ወቅት፣ አማርኛ ተናጋሪውን ብቻ ሳይሆን፣ መጤ ብሎ የፈረጀውን ኢትዮጵያዊ በሙሉ፣ ያባርርና በሰው አንደበት መግለጥ በማይቻል ጭካኔ ይገድል እንደነበር በሰፊው ተመዝግቧል። ሕወሓትም በአምሳሉ በጠፈጠፈው በኢሕአዴግ አማካይነት፣ ሥልጣኑንም ሆነ ጭፍጨፋውን የተቋደሰው ከኦነግ ጋር መሆኑ የማይካድ የዐይንና የጽሑፍ ተጨባጭ ማስረጃ ይመሰክራል። ሊቅ ነጋሦ የባሕርዳር ሕዝብ እንደአራጁ የሚገምተውን የኢሕአዴግን ሳይሆን፣ ልሙጡን የአባቶቹን ታሪካዊ ሰንደቅዓላማ ብቻ ይዞ ቢወጣ፣ ሳይዘገዩ የዜና አውታሮችን ጠርተው፣ ተቃዉሟቸውን አሰምቷል። ይሁንና፣ ኦነግ ኢትዮጵያን አፍርሶ ነፃ አገር ለማቆም ያዘጋጀውን ሰንደቅዓላማ አንግቦ ሰልፍ እንደወጣ አልሰሙም ማለት ያዳግታል። ከሰሙ ለምን አንዲትም የተቃዉሞ ቃል አልተነፈሱም ብሎ መጠየቁ አስፈላጊ መሰለኝ። ሰምተው ዝም ብለው ከሆነ ደግሞ፣ ከርካሽ ስብከትና ፍርደገምደልነት ውጭ ሌላ ምክንያት ካለ ሊነግሩን ይገባል። አለበለዚያ ድርጊታቸው ካንድ ምሁር ቀርቶ ከማንም አላፊነት ከሚሰማው ተራ ዜጋ የሚጠበቅ አይመስለኝም።

ንግግሬን በጥቂት ቃላት ልደምድመው። እኔ እንደምረዳውና ከዚህም በላይ በተጨባጭ እንደተገለጸው፣ የኢሕአዴግ ክልልና ሕገመንግሥት ለመስማት የሚቀፍ፣ ለማሰብ የሚሰቀጥጥ፣ ለማየት የሚያስበረግግ፣ ለመጻፍ የሚያስደነግጥ በሰው ኅሊና የማይታሰብ ግፍ ሠርተዋል። ባለኮከቡ ሰንደቅዓላማ እንድናስብ የሚያስገድደን ይኸንን የማይካድ እውነታ ነው። የኢሕአዴግ ሰንደቅዓላማ ከናዚዎቹ እስዋስቲካ የሚለይበት ምክንያት አይታየኝም። ሁለቱም የክፋት ዐዘቅት ምልክት ናቸውና። የዚህ ዐይነት ኢሰብኣዊ ጭካኔ ማስታወሻ የሆነውን ባለኮከቡን ሰንደቅዓላማ በእጁ እንዲይዝ ከአንድ ኢትዮጵያዊ መጠበቅ ማለት፣ ልክ አንድ አይሁዳዊ የናዚን እስዋስቲካ በደስታ እያውለበለበ ለሠርግ እንዲሄድ እንደማስገደድ ይሆናል ቢባል ትክክል ይመስለኛል። በምንም አይለይም። ፍትሕና ርትዕ፣ አንድነትና እኩልነት፣ ሰላምና ፍቅር የሚመኝ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ የአገሩ የመለዮና የኩራት ምልክት ነው ብሎ በማመን ይኸንን ሰንደቅዓላማ  በእጁ ከቶዉኑ ሊይዘው አይገባውም ብል የሚያስወቅስ አቋም መሆን የለበትም። ሌላው ይቅርና፣ ማንም ኅሊና ያለውና ግፍ የሚጠላ ባለሥልጣን ደግሞ፣ ሳይውል ሳያድር፣ ለሕዝቡ ፍቅር ሲል ይኸንን ዐይነት ሰንደቅዓላማ አላንዳች ማመንታት እስከነአካቴው ሊያጠፋው ይገደዳል ብዬ አምናለሁ። ከዚያ ባሻገር፣ የኢሕአዴግ ክልልም ሆነ፣ ሕገመንግሥት ዕጣ ፋንታቸው ይኸው መሆን ይጠበቅባቸዋል። ሦስቱም፣ ማለትም ባለኮከቡ ሰንደቅ ዓላማ፣ ክልልና ሕገመንግሥት፣ ሕወሓት ለዘር ማጽጃ ዓላማው ማስፈጸሚያ እንዲረዱት የሸረባቸው የወንጀል መሣርያዎቹ ናቸው። ልክ የናዚ ተቋማትና ሥርዐት ከነአካቴአቸው እንደተደመሰሱ ሁሉ፣ የነዚህም መውደም አስፈላጊ የማይሆኑበት ምክንያት የለም። እውነት ነው የናዚ ሥርዐትና ተግባር አድናቂዎች እንደነበሩለት ሁሉ፣ ኢሕአዴግም የራሱ እንደሚኖሩለት አይካድም። እንደነዚህ ዐይነቶቹ ሰዎች፣ የፋርሱ ባለቅኔ ሳኢዲ እንዳለው፣ ለሌላው ሰው ሥቃይ ደንታ የሌላቸው፣ ሰው የሚል መጠርያ ከቶም የማይገባቸው ግለሰቦች ናቸው ብሎ ጽሑፉን መዝጋቱ ይቀላል[18]

ቸር ይግጠመን።

[1] . አሁን ከኢጣሊያንኛ ቋንቋ በመበደር ባንዳንድ ዘንድ “ባንዲራ” በመባል የሚታወቀው በቋንቋችን “ሰንደቅ ዓላማ” ይባላል። ሰንደቅ ዓላማ ያንድ መንግሥት ሕዝብ የነፃነቱ፣ የአንድነቱና የእምነቱ እንዲሁም የመሬቱ ባለቤትነት ምልክት ነው። ቃሉ ሙሻዘር ሁኖ፣ “ሰንደቅ” ከነሐስ፣ ከብረት፣ ከብርና ከዕንጨት የሚሠራውን ዘንጉን ከነእንክብሉ ያመለክታል፤ “ዓላማ” ደግሞ ከላዩ ላይ ተንጠልጥሎ የሚውለበልበውን ሐር ያሳያል።

[2] . በኢትዮጵያ ምርመራ ከፍተኛ ዕውቅናና ስመጥሩነት ያተረፈው እንግሊዛዊው ሊቀጠበብት ኤድዋርድ ኡሌንዶርፍ ስለአፄ ምኒልክ ሲናገር፣ “በአፄ ምኒልክ ዘመነመንግሥት ኢትዮጵያ ክብሯ በጣም ከፍ አለ፤የዘመናዊ መንግሥት መሠረቶች ተጣሉ፤ ጠባያቸውም የሚታወቀው [አገሩን] በጥበብና በብልሃት በማስተዳደር ነው።” ይላል። [Edward Ullendorf, The Ethiopians: An Introduction to Country and People, 3rd ed., (Oxford: Oxford University Press, 1973): 90.]

[3] Stanislaw Chojnacki, “Third Note on the History of the Ethiopian National Flag: The Discovery of Its First Exemplar and the New Documents on the Early Attempts by Emperor Menilek to Introduce the Flag,” Rassegna di studi Etiopici, vol. 26 (1980-1981) ገ. 34-36.

[4] . C. H. Michel, Vers Fachoda à l’encontre de la Mission Marchand à travers l’Ethiopia (Mission de Bonchamps), (Paris, 1900) ገ. 247.

[5] . ኀይለማርያም ሠራቢዮን (አ. አ. 1863-1929)

[6] . ጸጋ ዘአብ፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ትርጒም

[7] . ነጋድራስ ደስታ ምትኬ፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ የተመሰለው ትርጓሜ

[8] ጸሐፌ ት እዛዝ ገብረሥላሴ፣ ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠነገሥት ዘኢትዮጵያ፣ (አዲስ አበባ፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት)፣ገ. ፻፵፮።

[9] . Šihab ad-Din Ahmad bin abd al-Qadr

[10] . Manoel Barradas (1572-1646)። መጽሐፉ በElizabeth Filleul ተርጓሚነት፣ በRichard Pankhurst አርታኢነት እንደ አ. አ. በሺ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ስድስት በእንግሊዝኛ ታትሟል። ሙሉ አርእስቱ Manoel Barradas, Tractatus Tres Historico-Geographici (1634): A Seventeenth Century Historical and Geographical Account of Tigray, Ethiopia (Wiesbaden: Harrassowitz, 1996)፡ 70-7፣ 84።

[11] . Abraham Ortelius (1527-1598).

[12] . Wllem Janszoon Blaeu (1571-1638).

[13] . Marcus Mosiah Garvey, 1887-1940.

[14] . ማርኩስ ጋርቬይ (Marcus Mosiah Garvey, 1887-1940) የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ቀለማት መስለውት፣የመላው ጥቊር ሕዝብና አገር የማንነት መለዮና መግለጫ እንዲሆኑ ያወጃቸው ቀለማት ጥቁር፣ አረንጓዴ፣ ቀይ ናቸው። በኢትዮጵያው ብጫ ቀለም ቦታ በስሕተት ጥቊር መጠቀሙን የተረዳው ቈይቶ ነው ይባላል።

[15] .Garrett Augustus Morgan, 1875-1963. ሞርጋን ብጫ ቀለም እንደማስጠንቀቂያ በመጨመሩ፣ ዘመናዊው ተሽከርካሪ ያደርስ የነበረው አደጋ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱ፣ የፍልሰፋውን መብት፣ ጀነራል ኤለክትሪክ ኩባንያ በአ. አ. በ፲፱፻፳፫ ዓ. ም. በአርባሺ የአሜሪቃ ብር ገዝቶት፣ ሦስቱ የኢትዮጵያ  ሰንደቅዓላማ ቀለማት  የመላው ዓለም  ዘመናዊ መጓጓዥ ዋና ተቈጣጣሪ ቀለማት ሁነዋል።

[16] . የፈለገ  “ከታሪክ መዝገብ – ለመሆኑ አማራ ማነው?” “ከታሪክ መድረክ – ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ትላንትናና ዛሬ።” የሚሉትን ንኡሳን ጽሑፎቼን ያንብብ።

[17] . የፈለገ የሚከተሉን ማንበብ ወይንም ማየት ይችላል። https://ethsat.com/2017/01/esat-special-ethiopians-prof-haile-larebo-10-jan-2017/; https://ethsat.com/2017/01/esat-special-ethiopians-prof-haile-larebo-part-two-21-jan-2017/ ; ምኒልክን ብትወቅሱ ማንነታችሁን ትረሱ www.ethiomedia.com/14news/emperor_menelik_ii_the_great.pdf

[18] . Human beings are member of a whole,

In creation of one essence and soul.

If one member is afflicted with pain,

Other members uneasy will remain.

If you have no sympathy for human pain,

The name of human you cannot retain.

(Persian poet Sa’adi, written in 1259)

 

ትርጒም፡

የሰው ልጅ ነው ያንድ አካል ክፍል

ሲፈጠር ካንድ ባሕርይ ነው ካንዲት ነፍስ

አንዱ ክፍል ቢደርስበት ሥቃይ

መጨነቅ አይቀረው የቀረው ክፍል

ለሰው ሥቃይ ኀዘን ካልተሰማህ

ሰው የሚል መጠርያ ከቶም አይገባህ።

5 COMMENTS

 1. ” The hired hand (mercenary) is not the shepherd… cares nothing for the sheep” (Jhon 10: 12)
  Dr Larebo, are you serious? At such a time when the whole nation is under siege, how do you get the gut to revive & insist such an existing controversy between Oromos & Amharas nationalists around the Ethiopian flag? Isn’t this the right time to organize a gofundme event to assist those displaced? Millions of homeless children & mothers are suffering due to lack of shelter, food, clean water, hygiene & clothing. Don’t you heard massive cholera and hepatitis outbreak among many communities who lost their home and are on the street? what you did for to meet their need? At least did you donate $20? Did you buy them a piece of bread? Did you at least send them your old clothes? Did you donate to the current Diaspora fundraising initiative by Dr. Abiy ($1/day)? Please be honest. What you did to advance the current democratization agenda by team Lemma? Even many Amhara elites who also love Ethiopia now moved to their nation and are supporting the change by whatever means they can. Hence, without any real contribution why you expect us to believe you loving Ethiopia for just hiding under your old pc and venting such a divisive issue? Why do you prioritize the flag issue over humanity? I know this is not the case either in Tigray or in Kambata where your family belongs. You are doing the exact copy of what TPLF elites have done in order to create enmity and instability among the nation based on the flag issue a few months ago. Even if you do not want to support the needy, you were supposed to get satisfied with the recent analysis of Dr. Abiy on the flag subject. A real and responsible intellectual knows when to say something unless he is mercenary and wants to profit from the suffering of others. The holy bible also says ” The hired hand (mercenary) is not the shepherd… cares nothing for the sheep”. What an insensitive, selfish and callous creature!

 2. በውነቱ የአንድን ጽሑፍ መነሻና መሰረት ተገንዝቦ ሂስ ማቅረብ የእውቀት ምልክት ነው። አቶ ፈቃደ ከላይ የተጻፈው ትንተና ስለምን እንደሆነ የተገነዘብከው አይመስልም። ያለፈውን 27ዓመታት በኢትዮጵያ ምደር ምን እንደተደረገና ተያይዞም ጠሚር አብይ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ ሰንደቅ ዓላማን በተመለከተ ምን አይነት በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ውይይት የተተነተነበት የያዘ ጸሁፍ ነው።
  ይሄንን በተመለከተ ምንም አይነት መረጃና ነጥብ ያዘለ ሃሳብ ሳይሆን ያቀረብከው፣ከአርእስት ውጭ ፣መነገርም ቢኖርበት እንኳን መድረኩን የሳተ ነው። አቶ ኃይሌ ላሬቦን ለመዝለፍ ካስፈለገ በጻፉት ላይ ማተኮሩ በተገባ ነበር፣ምን ሰጡ ምን በ diaspora ስም መፀወቱ ፣በኢትዮጵያ ያለውን የበሽታን አይነት መዘርዘሩ ፣የሳቸውን ጽሁፍ ስህተት አያደርገውም። ገንዘብ ሰጡ አልሰጡ ለማንም መግለፅም ፣በደረሰኝም ለሕዝብ ለምስክርነት ማሳየትም የለባቸውም። እሳቸው ፅሁፉን አሁን ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊትም ቀለል ባለ ይዞታው አቅርበውታል።ነገርግን የሰንደቅ ዓላማው ውይይት በተለያዪ ጊዜም አሁንም ስላላቋረጠ ፣ስር የያዘና ጥናታዊ ፅሑፍ በማቅረባቸው ምስጋና ሲገባቸው ፣ያልተገባ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አቅርቦ የተገዛና ሰርጎገብ ብሎ እረኛ ብሎ መስደብ ፣የራስን አለማወቅንና ትንሽነትን ያስመሰክራል። እሳቸው በኢትዮጵያዊ እምነታቸው ስለ ሰንደቅ ዓላማ ታሪካዊ ሂደት ሲያስረዱ፣የማይስማማ ደግሞ እንደሳቸው ተንትኖ መሟገት በተገባ ነበር። ግን ከየት ብሄረሰብ እንሚመነጩ መዘብዘብ በእርግጥም የህዋሃት የረጨውን መርዝ እንደምታስተናግድ በገሃድ አሳይተሃል።
  ስለ ሰንደቅ ዓላማ ብዙ ተብሏል፣ጠሚር አብይም በዝርዝር ሳይሆን በጨረፍታ አልፈውታል። እሳቸውም የተናገሩት ወይም የጠቀሱት ሁሉ ትክክል ነው ብሎ ለማስረጃነት ማቅረቡ ፣የሳቸውን ፍፁምነት ወይም ቃላቸውንእንደ መፅሐፍ ቅዱስ ቃል ማቅረብ ፣የመወያየትንና የዴሞክራሲን መንፈስ አለመገንዘብ ነው።
  አቶ ኃይሌ ላሬቦ ማንንም ለማጣላት ያቀረቡት ፅሑፍ አይደለም። የኦነግን ድርጊት መግለፅ የኦሮሞ ድርጊት ነው ብሎ የሚያምን ማንም ኢትዮጵያዊ አይገኝም።ህዋሃትና ኦነግ ያደረጉትን ታሪካዊ ኃጢአት ከዚህ በፊትም ተገልጿል ወደፊትም መነጋገሪያ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።አሁን በሙስናና የኢትን ንብረት በመዘበሩት ላይ ምርመራው ተጀምሯል። ብሔራዊ እርቅና መስማማት እንዲሰፍን የኦነግ ፣የህወሃት የኢሀዴግም ምንነታቸውና ድርጊታቸውም ተከታዩ ና አይቀሬው የምርመራ ሂደት ነው። ደባብሶ ማለፍ ኢትዮጵያችንን ለጀመርነው የታሪክ ምእራፍ አደናቃፊና እኩይ ሂደት ነው።
  አዲስ ስርአት ለመፍጠር ሀሳብን ማፈንና ዘለፋ ሳይሆን ውይይት አማራጭ የለሽ መሳሪያ ነው።

 3. እሺባህሉን ዘይቤውን ወደጎን አድርገን በጥቅሉ አማራነት ማለት ኢትዮጵያዊነት ማለት ነው፡፡ኢትዮጵያዊነትን በትክክል በተግባርም ስለሚያሳይ፣ ስለሚተበግረውም በጣም የተስማማኝ ገለጻ ነው፡፡በአፈታሪክ ወሬ ተደልለው አማራነትን ለማጥፋት የሚበላቀጡ ብዙ ስላሉ አምራነትንና ኢትዮጵያዊነትን ነጣጥለን ማየት የለብንም፡፡

  የወያኔ ክፋሽስትና ከናዚ በልጦ የሚገኘው የገዛ አገሩን ለጥቅም በመሸጡ ነው፣የገዛ ህዝቡን ለፓለቲካ ጥቅም አሳልፎ ኢሰብአዊ የውንጀል ድርጊት የፈጸመ ረካሽ ፣ወራዳ ማጅራት መቺ ነው፡፡ኢትዮጵያን አራቁተው ወና ያስቀሩ የጫካ ውንበዴ ጥርቅም ነው፡፡ ታሪክ ይፋረዳቸዋል፡፡

 4. This mentally slave guy is one of those who grew up and shaped with the self denial behaviors. The thesis of this guy cannot change historical facts. One of the hard dying Anti-Oromo individuals is the so called Larebo. Anti-unity and toxic are those like him and his mentors like Getachew Haile. They don’t believe in unity with diversity.

  One of his mentors Befekadu Degefe has mentioned last time in his statement at the conference of the Amhara elites in Bahir Dar about three months ago that some kids from southern Ethiopia go to school to become Amhara. Most probably his reference is Larebo and Efrem Madebo.

  Befakadu Degefe is an economist by training. But still he thinks with his Debteric mentality. He said shamefull Amaharaism is spirit. The main burden of Ethiopia is such poor individuals with backward and uncivilized mentalities

  No one knows better than Befekadu Degefe how the life hard is in his birth place for the ordinary families. In general, the people from Wallo, Gojam and Gonder were misused by the greedy Neftengas of Shewa during the eras of Menilik, Haile Selasien and Mengistu who promoted their objectives in the name of those innocent human beings. Thus, don’t forget that your families having been still suffering a lot as Walloye, Gojames and Gonderes under those inhuma systems of that empire state. From all these systems you have inherited only pseudo prides, bad mentality and cultures under which you are still in custody.
  Finally, I recommend those like Larebo to read the massages in the following links which may enlighten you:

  https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=572769853158534&id=100012765738803&refid=52&__tn__=H-R

  https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=1087054058122267&id=100004530481784&__tn__=H-R

  https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=10156797212449483&id=635689482&__tn__=H-R

  Besides that I recommend you all to read about the federal structures of the Switzerland, Belgium, Canada, Great Britain and South Africa which are all based on the ethnicities.

  I wish for all Ethiopian peoples mutual understanding and respect. Besides that I wish a democratic based and true unity, peace and prosperity for all of our peoples in our homeland Ethiopia.

 5. Gamadaa, Professor Larebo is challenging injustice with facts and figures fitting to intellectual discourse. Understandably, your response is with Facebook posts; that tells how miserably uninformed you are. Facebook posts are not historical facts nor intellectual references. There is no place for Mental Enslavement in our world. My two cent advice is, seek the truth – and truth will set you free. In a world running by knowledge and wisdom, hearsay and biased interpretation of facts are purely irrelevant. Most importantly, when it comes to a country of 100 + million people, it will be the apex of unparalleled ignorance. If you would like to challenge the good professor, ground your argument on scientific facts and figures. Or else go back to where you belong to; the teenagers forum called Facebook.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.